ፍካሬ ዜና (መጋቢት 02 ቀን 2010 ዓ.ም.) ወያኔ በርካታ ሰዎችን እያሰሰ በብዛት ያሰረ መሆኑ ተነገረ – ወጣቶች በብዛት እየታሰሩ ነው – የሶማሌ ልዩ ኃይል በሞያሌ ግድያ አካሄደ – የሙት ከተማ አድማ በድጋሚ ይካሄዳል ተባለ – በአድዋ፣ የአድዋ በአል አከባበር ፍፁም ጎሰኝነትን የተላበሰ ነበር ተባለ – ለሦስት ቀናት የተካሄደው የሙት ከተማ አድማ ወያኔን ክፉኛ የጎዳ መሆኑ ታወቀ – ወያኔ የኢንተርኔት አገልግሎትን እያፈነ ነው – የውጪ ምንዛሪ ዜሮ መሆን ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ግዢዎችን ማስተጓጎሉ ተሰማ – አሜሪካ ወያኔን ለመጠገን እያደረገች ያለው ሴራ ተጋለጠ።
ወያኔ በርካታ ሰዎችን እያሰሰ በብዛት ያሰረ መሆኑ ተነገረ
ባሳለፍነው ሳምንት ለሦስት ቀናት በተግባር ወያኔን ያራደው የሙት ከተማ አድማን ተከትሎ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ እንደሆነ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደርሱን መረጃዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡ ወያኔ ባሳፍነው ሳምንት የበርካቶችን ደም አፍስሷል፡፡ የአስራ ሦስትና የእስራ አምስት አመት ህፃናትንና የሃምሳ አምስት አመት አዛውንትን ገድሏል፡፡ በወያኔ የተደገሉ ወጣቶች ቀብር ስነስርዐትን አውኳል፡፡ እንዲሁም ወያኔ በለገጣፎ፣ በአምቦ፣ በአርሲ፣ የኦሮሞ ፖሊሶችን ከሕዝብ ጋር ወግናችኋል በሚል እያሰረ መሆኑ ሲታወቅ ይህ የፖሊሶች እስራት በሰፊው እንደሚቀጥል ግምታቸውን በርካቶች ሲሰጡ አድምጠናል፡፡ ይህ በእዲህ እንዳለ የኦሮሚያ የፖሊስ አዛዥ በፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቃቸው በሰፊው እየተነገረ መሆኑን አውቀናል፡፡ በተመሳሳይም ታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ እና በሶሻል ሚዲያ ነፃ ሀሳቡን ለአንባቢያን የሚያካፍለውን በአምቦ ዩኒቭርሲቲ ስር በሚገኘው የወሊሶ ቅርጫፍ መምህር የሆነው አቶ ስዩም ተሸመ መኖሪያ ቤቱ በግፈኛው የአጋዚ ጦር ተከቦ ታስሮ መወሰዱ የታወቀ ሲሆን ይህ ዘገባ እስተጠናከረ ጊዜ ድረስ የታሰረበት መዳረሻው አለመታወቁ ይነገራል፡፡
በተለያዩ ከተሞች ወጣቶች በብዛት እየታሰሩ ነው
በወለጋ፣ በአርሲ፣ በአምቦ፣ በቡራዩ፣ በአዳማ፣ በወሊሶ፣ በጅማ፣ በጪሮ፣ በወልቂጤ፣ በሰበታ፣ በሱሉልታ፣ በለገጣፎ፣ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ ወዘተ. ወጣቶች በጅምላ እየታሰሩ፣ መኖሪያ ቤቶች በድንገት በቀንም በሌሊትም በአጋዚ ጦር እየተደፈሩ በፍተሻ ስም በኗሪዎች ላይ ድብደባና እንግልት እየተፈጸመ መሆኑን ከየአቅጣጫው ከሚደርሱን መረጃዎች ተረድተናል፡፡ ከአንድ ቤት ሁለትና ሦስት ልጆች እየታፈኑ መወሰዳቸውን የሚገልጹ ወገኖች እንደሚሉት የታፈኑት የት እንደ ታሰሩ ስለማይገለጽ ወላጆችና ዘመድ አዝማድ ስንቅና ልብስ እንኳን የማቀበል እድል እንደተነፈጋቸው በምሬት እያነቡ መናራቸውን ከእማኞች ተገንዝበናል፡፡
የሶማሌ ልዩ ኃይል በሞያሌ ግድያ አካሄደ
ዐርብና ቅዳሜ እለት እንደ ከዚህ ቀደሙ የሶማሌ ልዩ ኃይል የሚባል ጦር በያቤሎ ሕዝብ ላይ ጥቃት በማድረሱ ሕዝቡ የደረሰበትን ጥቃት ለመመከት ባለው ኃይል እንደተሰማራ የወያኔ ጦር ወደ አስር የሚደርሱ ሰዎችን እንደገደለና በርካቶችን እንዳቆሰለ መረዳት ተችሏል፡፡ በዛሬው እለት እሁድ ወያኔ ኮማንድ ፖስት ያቤሎን የወረረው ኃይል ድንበር ጥሶ የመጣ ምንነቱ ያልታወቀ ኃይል መሆኑን በመጥቀስ ለደረሰው ጥፋት ይቅርታ በመጠየቅ የያቤሎ ሕዝብን የጨፈጨፉትን ወታደሮች ትጥቅ ማስፈታቱንና በቀጥጥር ማዋሉን በመጥቀስ ለደረሰው ስህተት ሕዝቡን የለበጣ ይቅርታ መጠየቁ እየገደሉ ማልቀስ የአረመኔዎች ባህርይ ነው ተብሏል፡፡
የሙት ከተማ አድማ በድጋሚ ይካሄዳል ተባለ
ወያኔ በእቸኳይ አዋጅ ስም ወታደራዊ አገዛዙን በማስፈን ሕዝብን እየጨፈጨፈ፣ እየደበደበ፣ እያንገላታ፣ የጅምላ እስራት እየፈጸመ በመሆኑ ባሳለፍነው ሳምንት የተካሄደው የሙት ከተማ አድማ በድጋሚ ከነገ ሰኞ አንስቶ እንደሚካሄድ ጥሪ የተላለፈ መሆኑን ከተለያዩ ምንጮች መገንዘብ ተችሏል፡፡በዚህ መሰረት ከአዲስ አበባ የሚወጡ እና ወደ አዲስ አበባ ከተለያዩ አቅታጫዎች የሚገቡ ማንኛውም ዐይነት የመጓጓዣ መኪናዎች እንቅስቃሴ እደሚስተጓጎል፣ የገበያ፣ የምግብ ቤቶች፣ መደብሮች፣ ትምህርት ቤቶች እና መስሪያ ቤቶች ሁሉ እንቅስቃሴ ጭጭ እንደሚል ይጠበቃል፡፡ በዛሬው እለት ወያኔ ጠቅላይ ሚንስትር ይሰይማል ተብሎ እየተወራ ቢሆንም የሕዝቡ ጥያቄ የጠገቡ ተባዮችን በተራቡና በተጠሙ ተባዮች ለመተካት ሳይሆን የተባዮች መፍያ የሆነውን የወያኔን ዘረኛ ስርዐት ከስሩ መንግሎ ለመጣል መሆኑን በርካቶች ያስረዳሉ፡፡ በነገው እለት የሚጀመረው ሕዝባዊ አድማ በበርካታ አካበባቢዎች እንደሚካሄድ ይገመታል ተብሏል፡፡
በአድዋ፣ የአድዋ በአል አከባበር ፍፁም ጎሰኝነትን የተላበሰ ነበር ተባለ
የወያኔ መሪዎች፣ ለዘመናት የአክሱም ታሪክ የትግራይ እንጂ የተቀረው ኢትዮጵያ እንዳልሆነ በእብሪት እየተናሩ ያሉትን በአድዋ ጦርነት ድልም እየደገሙት መሆኑን በአደባባይ የካቲት ሃያ ሦስት በአድዋ፣ በተከበረው የአድዋ ጦርነት የድል በአል በተከበረበት ወቅት አድዋ የዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊትን የመሩትና ለድሉ ከፍተኛውን አመራር የሰጡት አጼ ሚኒሊክ ስም እንዳይነሳ መደረጉን ወደ ስፍራው ከተጓዘ ቡድን መገንዘብ ተችሏል፡፡ እንዲህ ያለው ድርጊት ከወያኔ የሚጠበቅ እንደሆነ የሚጠቅሱ ወገኖች እንደሚሉት የአርበኞቹ ገድል በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ በሰፊው እየተነገረ በመሆኑ ወያኔ ታሪክን ለመበረዝና ለመከለስ እያደረገ ያለው ሴራ ይከሽፋል ብለዋል፡፡
ለሦስት ቀናት የተካሄደው የሙት ከተማ አድማ ወያኔን ክፉኛ የጎዳ መሆኑ ታወቀ
ካሳለፍነው ሰኞ እስከ እሮብ በተቀናጀ እና በተቀነባር ሁኔታ የተካሄደው ሥራ እና ገበያ፣ ማንኛውም ዐይነት የንግድ እንቅስቃሴ፣ የመጓጓዣ ካሚዮኖች እንቅስቃሴን ቀጥ ያደረገው ሕዝባዊ አመጽ በወያኔ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ቀውስ እና የፖለቲካ ኪሳራ ማድረሱን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ሕዝባዊ አመጹ ባስከተለው የኤኮኖሚ ቀውስ ወያኔ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ኪሳራ እንደደረሰበት መገመት የተቻለ ሲሆን በፖለቲካም በተመሳሳይ ሁኔታ ወያኔ ከአሁን በኋላ እየወሻከተና እየወሳለተ የአገዛዝ እድሜውን በስንዝር እንኳ ማራዘም እንደማይችል የሙት ከተማው አድማ አሳይቷል ተብሏል፡፡
ወያኔ የኢንተርኔት አገልግሎትን እያፈነ ነው
ወትሮውንም ቢሆን እየተቆራረጠ ያለው የኢንተርኔት አገልግት በርካታ የሥራ መስኮችን እየጎዳ መሆኑን ሥራቸው ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር የተቆራኘ ወገኖች ምሬታቸውን እየገለጹ መሆናቸው ታወቀ፡፡ ወያኔ ሲያሰኘው የኢንተርኔት አገልግሎትን እንደሚዘጋው የሚታወቅ ሲሆን አንዳንዴ የኢንተርኔቱን የማገናኘት ኃይል በእጅጉ ይቀንሰውና ግንኙነት እንዲታወክ እያደረገ መሆኑ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን፣ የህክምና ግንኙነቶችን፣ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ግብይቶችን፣ የኢንተርኔት አገልግሎት በመስጠት የተሰማሩትን፣ ወዘተ. እንቅስቃሴ እያሽመደመደው መሆኑን በመጥቀስ በርካቶች ምሬታቸውን ሲጠቅሱ ይሰማል፡፡ ወያኔ የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚያፍነው ከሀገር ቤት ወደ ውጪ እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የሶሻል ሚዲያ ግንኙነቶችን ለማፈን እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ይህን የወያኔን አፈና ፒሲፎን እና ቪፒኤን በተባሉ እና በመሰል አፕሊኬሽኖች ማፍረስ መቻሉ እየተስተዋለ መሆኑን በርካቶች ያስረዳሉ፡፡
የውጪ ምንዛሪ ዜሮ መሆን ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ግዢዎችን ማስተጓጎሉ ተሰማ
ለተለያዩ ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ከውጪ የሚገቡ ቁሳቁሶችን ለማስገባት የውጪ ምንዛሪ ባለመኖሩ እስከዚህ ወር ድረስ ግዢዎች ሳይፈጸሙ መክረማቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ወገኖች መገንዘብ ተችሏል፡፡ ለቢሮ ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ባለመገዛታቸው ሳቢያ ሥራ ለመስራት እንቅፋት መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለህይወት በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑ መድሀኒቶች ከገበያ እየተሟጠጡ በመሄዳቸው ህሙማን እየተሰቃዩ እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ ወያኔን ለመጠገን እያደረገች ያለው ሴራ ተጋለጠ
አሜሪካ የወያኔን አገዛዝ ለማራዘም የጥገና ለውጥ ለማምጣት በስልት ውስጥ ውስጡን እየሠራች መሆኗ ተጋለጠ፡፡ ከዚህ ቀደም በህወሀት ፊት-አውራሪነት በኢትዮጵያ የዘር ፖለቲካ እንዲነግስ በአሜሪካው ሲአይኤ በሚባለው የስለላ ድርጅት መሀንዲስነት ወያኔ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት እንደገባ የሚታወስ ነው፡፡ ይህ ድርጊት አሜሪካ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ከፈጸመቻቸው እኩይ ድርጊቶች አንዱ እንደሆነ የሚዘነጋ አለመሆኑን በአንክሮ የሚያነሱ የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት በዚህ ወቅትም በኸርማን ኮኸን የሚመራ ብድን በድጋሚ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታን እያተራመሰ መሆኑን ሆምጨጭ ብለው ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ኸርማን ኮኸን በቅርቡ ለቪኦኤ የሰጠውን ቃለ-ምልልስ በማንሳት ሲአይኤ አሁንም ሌላ የዘር ፖለቲካ እንዲቀጥል እያሴረ መሆኑን ለመገንዛብ እንዳስቻለ ያነሳሉ፡፡ ይህ ኮኸን የተባለ ሰው አሁን ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄው የጠቅላይ ሚንስትርነቱ ስልጣን በኦሮሞ መያዙን በመንሳት፣ እሱ ለቦታው ብቁ የሚለው ዶ/ዐብይ የተባለ በቅር የአወያኔ-ኦህዴድ ሊቀ-መንር የተደረገና የኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነቱን እንዲያዝ የተደረገ፣ እንደ ሆነና ለዚህ ሰው ድጋፉን እንደሚሰጥም ይፋ አድርጎልናል፡፡ በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄና እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ አመጽ ጥያቄ ወያኔ የፖለቲካ ሌባ እና የኤኮኖሚ ማጅራ መቺ በመሆኑ ወያኔ ይወገድ የሚል ነውና የእነኮኸን ሴራ ተንሳፎ የሚቀር ነው ተብሏል፡፡ በተያያዘም ሊታወቅ የሚገባው የወያኔ ቁንጮዎች በአጠቃላይ እየፈሰሰ በሚገኘው የሕዝብ ደም ተጠያቂዎች በመሆናቸው ወንጀለኛን በወንጀለኛ በመቀየር ግፍ ይበረክታል፣ ይስፋፋል እንጂ ቅንጣት ሕዝባዊ ለውጥ አያስከትልም በማለት የእነ ኮኸን ደባ በሕዝባዊ አመጽ ድባቅ ይመታል ተብሏል፡፡
ወያኔ አንድ እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ አባረረ
በኢትዮጵያ ብሉምበርግ የተሰኘው የዜና ተቋም ወኪል የነበረው እንግሊዛዊው ዊሊያም ዳቪሰን በወያኔ የኢሚገሬሽን ባለስልጣናት ከሀገር መባረሩ ተሰማ፡፡ ጋዜጠኛ ዳቪሰን ከብሉምበርግ በተጨማሪ የታዋቂ ግራ-ዘመም የእንግሊዝ ጋዜጣ ለሆነው ለጋርዲያንም የኢትዮጵያ ወኪል በመሆን እየሠራ እንደነበር የታወቀ ሲሆን ጋዜጠኛው በሚዘግባቸው ተጨባጭ መረጃዎች የወያኔን ገበና እያጋለጠ ነው በሚል ከሀገር እንዲባረር ተደርጓል ተብሏል፡፡ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ምንም ዐይነት የነፃ ጋዜጣ እንቅቃሴ አለመኖሩን ያጋለጠ ሲሆን በኢትዮጵያ በነፃ ጋዜጣና መጽሔት ስም በገበያ ካሉት አንድም የነፃ ጋዜጣና መጽሔት እንደማይገኝም በርካቶች ይናራሉ፡፡