በኢትዮጵያ የሚያካሂደው የዘር ፍጅት በጽኑ ሊወገዝና ዘረኛው አገዛዝም ሊወገድ ይገባል

(የኢሕአፓ መግለጫ፣ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም) በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ ላይ፣ በረዥሙ የሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታውቅ መርገም ሆኖ የተከሰተው ወያኔ ለ27 ዓመታት በቋንቋ ላይ ተመሥርቶ በዘውግ ሸንሽኖ ባመሰቃቀላትና አማራውን ጠላት አድርጎ በተንቀሳቀሰባት ኢትዮጵያ፣ ይባስ ብሎ የአማራውን ደም ካላፈሰሰ መሽቶ የማይነጋለት የኦነግና ኦህዴድ ጥምር ዘረኛ አገዛዝ ተተክቶ፣ እነሆ ለአራት ዓመታት ሳያባራ ባካሄደው የዘር ፍጅት ሀገሪቱን የዜጎቿ ጅምላ መቃብር አድርጓታል፡፡ ይህን መሠል አረመኔ ድርጊቱንም ሕዝብ ማንቁርቱን ይዞ ተጠያቂ ባለማድረጉና ተገቢ ቁጣውን ባለማሳየቱ ግብዙ ኮሎኔል አይዞህ እንደተባለ ሁሉ ፍጅቱን አባዝቶ አማራውን ማሳረድ ቀጥሎበታል፡፡

እነሆ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ያካሄደውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ “ኢመደበኛ በሆኑ ኃይላት ጥቃት ተፈጽሟል” በማለት በፈሰሰው የንፁሃን ደም ጭራሽ ተሳለቀበት፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ያለውን ንቀት በዕብሪቱ ግልፅ አደረገበት፡፡ አንድ የኦሮሞ ዘፋኝ ሞተ ብሎ የሀዘን ቀን ያወጀው ኮሎኔል፣ አካላቸው ተቆራርጦና በእሳት ጋይተው በአሰቃቂ ሁኔታ ላለቁት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ዓላማን ዝቅ
በማድረግ ሀዘንን መግለፅ ቀርቶ፣ የጠፋው ነብስ የሰብዓዊ ፍጡር መሆኑንም ላለመቀበሉ እንኳ በችግኝ ተከላ የፎቶ ፕሮግራሙን አሳይቶናል፡፡

ቀደም ሲልም በዚሁ አካባቢ በደረሰ የብዙ መቶ ንፁሃን አማራዎች ጭፍጨፋ፣ ያልጠበቀው ቁጣ ሲቀሰቀስበት፣ በወያኔ ጦርነት ሽፋን አለባብሶ አንዳለፈው ሁሉ፣ ዛሬም በወለጋ ያካሄደውን ጭፍጨፋ ለማለባበስ እየሞከረ ነው። አልፎም ሕግ ማስከበር በሚል ሽፋን፣ በፋኖ ላይ እና እንዲሁም ደጋፊ ናቸው በሚላቸው ወጣቶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ሀገር ወዳድ ዜጎች ላይ እያካሄደ ያለውን ፋሽስታዊ አፈና እና የሁለቱን (የወያኔና የኦነግ) ፀረኢትዮጵያ
ኃይላት የአማራን የማጥፋት ዕቅድ (ጀኖሳይድ) ተግባራዊ ለማድረግ፣ ዘረኛው ኮሎኔሉ ወያኔ መጣብህ በሚል ሕዝብን ለማዘናጋትና ፋኖን ለማጥመድ እሞከረ እንዳለ፣ ሕዝብ ያልነቃበት ቢመስለውም፣ የአደባባይ ምስጢር መሆኑ ግልፅ ነው፡፡

ኢ ሕ አ ፓ ይህን ዛሬ ሀገራችንን የደም መሬት ያደረጋት ኮሎኔል፣ የለውጥ ኃይል መስሎ ገና ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ ወዲያውኑ ጭምብሉን ገፎ፣ ያንኑ የገማ የገለማውን የወያኔ ሥርዓት ለማስቀጠል፣ በሸፍጥ ተፀንሶ፣ በሸፍጥ የተወለደ፣ አፈ ጮሌ የወያኔ ምልምል መሆኑን በማጋለጥ፣ ሕዝብም በዚህ አስመሳይ ድራማ እንዳይዘናጋ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ በሚቻለው ሁሉ አጋልጦታል፡፡ ታግሎታልም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በዚህ
አረመኔ ዘረኛ አገዛዝ እጅ ወድቃ፣ በወገኖቻችን ላይ ሳያበራ የቀጠለው መከራና ሰሞኑን በወለጋ የተካሄደውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እጅግ በመረረ ቋንቋ ያወግዛል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህን አረመኔ የዘር ፍጅት እንዲያወግዝና ወንጀለኛው አገዛዝ ለፍርድ ይቀርብ ዘንድ እንዲተባበር ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

ኢሕአፓ ከዚህ የአገዛዙ ጭፍጨፋ በህይወት ለተረፉት የሟች ቤተሰቦች ያለውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ መፅናናቱን እየተመኘ፣ ይህን በምድራችን ፅልመት ሆኖ የተከሰተ ዘረኛ፤ ወያኔ የተከለው የኦነግ/ኦህዴድ/ብአዴን የባንዳን አገዛዝ ከሕዝብ ጎን ሆኖ እንደሚዋጋውና በሃምሳ ዓመታት የትግል ጉዞው ያዳበረውን ተመክሮ በመጠቀም፣ ዛሬም የሚከፈለውን ማንኛውንም መስዋዕት ሁሉ በመክፈል ከከርሰ ምድሪቱ እንዲጠፋ ይታገላል፡፡

በኢትዮጵያ የተወሰኑ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ፍጅት (ጀኖሳይድ) አያካሄደ ያለውን ዘረኛ አገዛዝ በተባበረ ትግላችን እናስወግድ!!!
የዘር ፍጅት ወንጀለኛው ኮሎኔልና ግብረአበሮቹ ለፍርድ ይቅረቡ!!
እናቸንፋለን!!

(መግለጫውን በpdf ከድርጅቱ ድረ ገጽ ያንብቡ)