ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም.)
በጎንደር የተለያዩ ክፍሎች በሕዝባዊ ኃይሎች እየተካሄደ ያለው ተጋድሎ ተጠናክሮ መቀጠሉ ከየቦታው ከሚደርሱን ዜናዎች ማወቅ ችለናል። በታችና ላይ አርማጭሆ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴና በወገራ የተለያዩ ቦታዎች እንቅስቃሴዎቹ መቀጠላቸው ሲነገር በተለያዩ ቦታዎች ከወያኔ ኃይሎች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች ሕዝባዊ ኃይሉ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል። በምስራቅ በበለሳ አካባቢው እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወደ ጃናሞራና ደረስጌ እንዲሁም ዲልይብዛ መዛመቱ ሲታወቅ በምዕራብ ጎንደርም በቋራ ቆላማው ክፍል በወያኔ ላይ ያመጸው ሕዝብ እንቅስቃሴውን እያጠናከረ መምጣቱ ይነገራል።
ከአስቸኳይ ጊዜ ወዲህ በወያኔ አገዛዝ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ከመሆናቸውም በላይ ለቤተሰቦች ሆነ ለዘመዶች ያሉበት ያልተገለጸ መሆኑ ይታወቃል። በአንዳንድ የማጎሪያ ጣቢያዎች ያሉ ወጣቶች ከፍተኛ ድበደባ የሚፈጸምባቸው መሆኑን የሚገልጹ መረጃዎች ከየአካባቢው ሾልከው ከሚወጡ ዜናዎች ማወቅ የተቻለ ሲሆን አገዛዙ ያሉበትን ቦታ ለዘመድ ወዳጅ የማያሳውቀው ባሰራቸው ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ ለመደበቅ ነው የሚሉ አሉ። ከየቦታው በጅምላ እየተለቀሙ በማጎሪያ ጣቢያዎች የታጎሩት ወጣቶች ለምን ያህል ጊዜ በእንዲህ ዓይነት ስቃይ እንደሚቆዩ ግልጽ አይደለም። በተያያዘ ዜና ቀደም ብለው በወያኔው የይስሙላ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ውሳኔ ታሰረው በዘመዶቻቸው ሲጎበኙ የነበሩ እስረኞች ከታሰሩበት ቦታ እየተነሱ መዳረሻቸው እየተጠፋ መሆኑ እየተነገረ ነው። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአሸባሪነት ተወንጅሎ በዝዋይ እስር ቤት ታስሮ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ሰሞኑን በዚህ እስር ቤት ውስጥ አለመኖሩ እንደተነገራቸው የቅርብ ዘመዶቹ ገልጸዋል። ወዴት እንደወሰዱት ወይም በህይወት ይኑር አይኑር የማያውቁ መሆናቸውንም ጨምረው ተናገረዋል።
የምሥራቅና የመካከለኛው አፍሪካን ከድርቅና ከረሃብ ለመከላከል የቅድሚያ እርምጃ ለመውሰድ የተቋቋመው ከተለያዩ ድርጅቶች የተውጣጣው ቡድን ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም ባሰራጨው ዘገባ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በተለይም በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ እና በኬኒያ በዚህ ዓመት ቢያንስ 15 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ የምግብ እርዳታ ሊያስፈልገው እንደሚችል ገለጿል። ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ኀዳር መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ በተጠቀሱት አካባቢዎች የነበረው የዝናም መጠን በአማካይ ከሚጥለው በጣም አነስተኛ በመሆኑ የሚቀጥለው የመኸር ወቅት ዝናም በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል የሚል ግምት ተወስዷል። ከስድስት ዓመት በፊት የደረሰውን ዓይነት የሕዝብ እልቂት እንዳይደርስ የምግብ እርዳታን በመሰብሰብ በኩል ከአሁኑ ጀምሮ ዝግጅት ያስፈልጋል ብሏል። በሶማሊያ 5 ሚሊዮን በኢትዮጵያ 5.7 ሚሊዮን ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾ እርዳታውን ለመሰበስብ ከአሁኑ እንቅስቃሴ መጀመር እንዳለበት አሳስቧል።