ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ታኅሣሥ 16 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በተለያዩ ቦታዎች የሚካሄዱት ተቃውሞዎች ቀጥለዋል – ወያኔ እስረኞችን ለቀቀ፤ በደል እንደደረሰባቸው ተናገሩ – ስኳር ከገባያ ጠፋ፤ ዋጋውም በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው – የቱጃሩ አላሙዲ ድርጅቶች ችግሮች እየገጠማቸው ነው – የውጭ ንግድ ገቢ እያሽቆለቆለ መሆኑ ተነገረ – የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሁኔታ አስጊ እየሆነ መጥቷል።
ወያኔ የህፃንትን ሞት ማቆም መቻሉን እየወሻከተ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከሰሀራ በታች በበሽታ የተቀጩ ህጻናት ጎልቶ ከሚታይባቸው ሀገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ተገለጸ፡፡ ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በዚህ ጉዳይ ካደረገው ጥናት መረዳት የተቻለው በኢትዮጵያ በቀላል ህክምና ሊድኑ የሚችሉ ከአምስት መቶ ሠላሳ በላይ የሚሆኑ ታማሚ ህጻናት በየቀኑ ይሞታሉ፡፡ በየአመቱ ከሁለት መቶ ሺ በላይ ህጻናት በተለያዩ በሽታዎች እንዲሁም በጠኔና በረሀብ በሞት ይነጠቃሉ፡፡ እነዚህ ህፃናት አብዛኞቹ እድሜያቸው ከሃያ ስምንት ቀናት በታች መሆኑን የቀረበው ጥናት ያብራራል፡፡ ወያኔ የሕዝብን ቁጥር ለመቀነስ ድምፅ በሌለው መሳሪያ ሕፃናትን እየፈጀ መሆኑ ነው በማለት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች ይተቻሉ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ በላከው መግለጫ የእስር ቤቶችን ሁኔታና ይዞታ እንከታተላለን የሚሉ የባዕድ ተቋሞች ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው በየእስር ቤቶች ያለውን ሰቆቃና ስቃይ እንዲታዘቡ በሚል ያቀረባቸውን ጥሪ እስካሁን ያልተቀበሉ መሆናቸውን መግለጽ ተገደናል ብሏል። ድርጅቶቹ ጥሪውን ያልተቀበሉበት ምክንያት የፖለቲካ ሰልፍ ሊሆን እንደሚችል ኮሚቴው ጠቁሞ ተቋሞቹ የሚረዱት ወያኔን በሚረዱ ባዕዳን ኃይላት በመሆኑ እነሱም ከባዕዳን ቁጥጥር ነጻ አይደሉም በማለት ገልጿል።
ወያኔ የሀገራችንን ሀብት ለባዕዳን መሸጡን የቀጠለበት መሆኑን የሚያረጋግጠው በአንድ በኩል የኢትዮጵያ የባህር አገልግሎት (ሺፒንግ ላይንስ) ለቻይና ሊሸጥ መወሰኑ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ የባቡር ኮርፖሬሽንን ለግል ባለሀብቶች ለመስጠት መወሰኑና በዚህ መሰረት ቻይናና ቱርክ የዚህ ስራ ተቋራጭ እንዲሆኑ መደረጉ መሆኑ ነው። በቢሊዮን ዶላር ወጭ ይሰራል የተባለው ከመቀሌ እስከ ሃራ ገበያ ያለውን የባቡር መስመር ለቱርክ ኩባንያ መስጠቱን ወያኔ ምስጢር ቢያደርገውም ሊጋለጥ ችሏል። ወያኔ ከቱርክ ጋር ያለው ዝምድናና ግንኙነት ለኢትዮጵያ ቅንጣትም የማይበጅ መሆኑ ከተጋለጠ ዓመታት ያለፉ ቢሆኑም ጉቦ ወሳኝ ነውና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ቢሆንም ተግባራዊ ሆኗል። በተያያዘ ዜና፣ ቻይና ለባቡሮች የግንባታ ሥራ ወጭ ያደረገችውንና ከቻይና ኤክሲም ባንክ ተሰጠ የታባለውን የ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ብድር ወያኔ እንዲከፍል የተጠየቀ መሆኑ ሊታወቅ ተችሏል።
የሱዳን አገዛዝ ኤርትራውያን ስደተኞችን ገንዘብ እያስከፈለ ወደ ውጭ አገር ያስወጣል በሚል ወንጀል ከሶ ወደ ጣሊያን የላከው መድሃኔ ተስፋማርያም በርሄ ለተከሰሰበት ወንጀል ምንም ጥፋት ያልተገኘበት ሲሆን ዋናው ተፈላጊ የሆነው መድሓኔ ይህደጐ መርዕድ ግን ለሱዳን ባለሥልጣናት ጉቦ ሰጥቶ መለቀቁ ዳግም መጋለጡ ታወቀ። ስደተኞችን ወደ ውጭ በማስወጥት ንግድ ወያኔም፣ ሻዕቢያም እንዲሁም የሱዳን መኮንኖች ያሉበት መሆኑ የተጋለጠ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ጥፋት የሌለበትን መድህኔ ተስፋ ማርያምን በተጠያቂው በመድህኔ ይህደጎ ፈንታ ወደ ጣሊያን የሰደደው የሱዳን የጸጥታ ተቋም ከፍተኛ ውግዘት እየደረሰበት መሆኑም ተጋልጧል። በተያያዘ ዜና ወያኔ ወላጅ ያላቸውን ልጆችና እጓለ ምውታን የሆኑትን በስፋት በጉዲፈቻ መልክ እየሸጠ ብዙ ሚልዮን ድላር ማትረፉን ያወገዙ ክፍሎች ባለፈው ዓመት ብቻ ወያኔ በሺ የሚቆጠሩ ሕጻናትን ሸጦ ብዙ መቶ ሚሊዮን ድላሮችን አትርፏል ሲሉ ከሰዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ታቃውሞዎች መካዳሄቸው ታውቋል፡፡ በጎንደር በተለያዩ የገጠር ቦታዎች ሲካሄዱ የነበሩት የትጥቅ እንቅስቃሴዎች መቀጠላቸው ሲነገር በጎጃምና በጎንደር አንዳንድ ከተሞችም “የታሰሩት ይፈቱ!” የሚል መፈክር በማንገብ ተቃውሞ ሲያደርጉ መቆየታቸው ታውቋል፡፡ በአምቦ ለተከታታይ ቀናት የተቃውሞ አድማና አመጽ ያካሄዱት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ መሪ ዶ/ር መረራና ምክትላቸው አቶ በቀለና ሌሎች በአጠቃላይ ወያኔን በመቃወም የታሰሩ እስረኞች ሁሉ ይፈቱ የሚል ድምጽ ማሰማታቸው ታውቋል፡፡ ሕዝባዊ አመጹ ይበልጥ እየተጠናከረና ቅርጽ እየያዘ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡
በሳለፍነው ሳምንት ከሕዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ ወያኔ ካሰራቸው እስረኞች ውስጥ ቁጥራቸው ከአንድ አራተኛ በታች የሆነ እስረኞች መለቀቃቸው ተነግሯል፡፡ ከእስር የተለቀቁት እስረኞች የታሰሩት በወታደር ማሰልጠኛ ቅጥረ- ግቢዎች ውስጥ መሆኑም ተወስቷል፡፡ ከጎንደር፣ ከባህር ዳር፣ ከፍኖተ-ሰላም፣ ከደብረ-ታቦር፣ ከጋይንት፣ … ወዘተ የተያዙት፣ የታሰሩት ብር ሸለቆ ሲሆን ከደብረ-ዘይት፣ ከአዳማ፣ ከጂማ፣ ከአርሲ፣ ከሐረር፣ ከሻሸመኔ፣ ከአምቦ፣ ከወሊሶ፣ ከቡራዩ፣ ከሰበታ፣ ከነቀምት፣ ከደምቢ ዶሎ፣ …ወዘተ የተያዙት ታስረው የከረሙት ጦላይ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ እስረኞቹ ከተያዙበት አንስቶ ከአንድ ወር በላይ በተለያዩ የማሰቃያ ቅጣቶችና በዱላ ቁም ስቅላቸው እያዩ እንደከረሙ ከተለቀቁት እስረኞች የተገኘው ማስረጃ ያረጋግጣል፡፡ ከእስረኞቹ መሀል የተሰማሩ ጆሮ ጠቢዎች እስረኞቹን እየጎነተሉ የሆዳቸውን እንዲናገሩ በማድረግ ለተለያየ ቅጣት ይዳርጓቸው እንደነበር መረዳት ተችሏል፡፡ እነዚሁ የወያኔ ሰላዮች ባቀረቡት መረጃ መሰረት ከእስረኞቹ ተነጥለው በርካታ እስረኞች ላይ እጅግ አሰቃቂ ስየል እየተፈጸመባቸው እንደሆነ መረዳት ተችሏል፡፡ አስረኞቹ ሲፈቱ በግድ የለበሱት ካናቴራ ላይ የተጻፈው “አይደገምም” የሚለው መፈክር አስቂኝ እንደሆነ ብዙዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ከሀምሌ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም በድፍን ኢትዮጵያ የተካደው ሕዝባዊ አመጽ ወያኔን አሰናብቶ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥ ርዓት ለመመስረት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ሙያ በልብ ብሎ፣ የንብ ምስል ያለበትን የወያኔ ካናቴራ ለብሶ የነበረው ዜጋ፣ ድምጹን ለተቃዋሚዎች ሰጥቶ ወያኔን ዘጭ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ አሁንም ሕዝብን ለመደለል መሞከር ቅቤ አንጉቶ እንጀራ ለመሳብ መሞከር ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ወያኔ እስረኛ የመልቀቁን ዜና የሚያሰራጨው አሁንም ያሰራቸውን ከአርባ-አምሳ ሺህ በላይ እስረኞችን ለመደበቅ ሲሆን ዜናውን በማስታጋባት ላይ የሚገኙት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በተለይ ብዙ ሺ አማራዎችና ወጣቶች በአጠቃላይ ታጉረው መገኘታቸውን በዝምታ ያለፉት መሆኑ ይታያል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፊት በየማጎሪያው ከ45ሺህ በላይ የፖለቲካ እስረኞችን አግቶ እያሰቃየ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ቀደም በርካታ ኢሕአፓዎች–እነ አበራሽ በርታም ጭምር–ታስረው የነበረበትን የሆለታ ማጎሪያ ግን፤ ብዙ ጊዜ ባይነሳም በቅርቡ ከታሰሩ ሺዎች ውስጥ የተወሰኑት በዚህ ውስጥ መታጎራቸው ይወራል።
ስኳር ከገበያ እየጠፋ ዋጋው በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሻቀበ በመውጣት ላይ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ በአጠቃላይ ስኳር ከገበያ እየጠፋ ሲሆን በድብቅ የሚሸጠው ደግሞ ኪሎው ከሰላሳ ብር በላይ እንደሚያወጣ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ለስኳር እጥረት ዋነኛ ሰበብ ወያኔ በቀጥታ ለሰሜን ሶማሌ፣ ለደቡብ ሶማሌ፣ ለደቡብ ሱዳን፣ ለጅቡቲ፣ ስኳር የሚሸጥ መሆኑ፡፡ ከዓመት ዓመት ስኳር ከአንዳንድ የውጭ አገሮች በተለይም ከብራዚልና ከህንድ እንደሚሸመት ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ አገሮች ወደ አገር የሚገባው ስኳር ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ከላይ ለተጠቀሱት የጎረቤት አግሮች ይቸበቸባል፡፡ በህገ-ወጥ መንገድም የስኳር ምርትን ከአገር አውጥተው ወደ ተጠቀሱት አገሮች የሚያስገቡት የወያኔ አባላት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በግንባታ ላይ መሆናቸው የሚነገረውና ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው ወደ አስር የሚሆኑት የስኳር ፋብሪካዎች ሥራቸው ተጠናቅቆ ለማምረት መብቃታቸው እስካሁን ተስፋ የሚሰጥ ፍንጭ ሲያሳዩ አልታየም። እነዓባይ ፀሐየ፣ ሳሞራና ሌሎቹ የዘረፉትን ገንዘብ እስካልመለሱ ድረስ የፋብሪካዎቹ መጠናቀቅ ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ እንደሚባለው ያለ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
የወያኔ ሸሪክ የሆነው የቱጃሩ የአላሙዲ ድርጅት ችግሮች እየተፈጠሩበት መሆኑ እየታየ ነው፡፡ በሞሮኮ ብቸኛው የነዳጅ ማጣሪያ ሥራ ተሰማርቶ የነበረው የአላዲ ኮራል ፔትሮሊየም ሆልዱንግስ ስድሳ ሰባት ከመቶ ድርሻ የነበረው ሲሆን በ1.34 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የታክስ እዳ የሥራ ፍቃዱን መነጠቁ ታወቀ፡፡ የወያኔ አባል እንደሆነ የሚነገርለት ሼህ አላሙዲ በተለያዩ ወቅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከልማት ባንክ እንዲሁም ለሸራተን ሆቴል ማስፈጸሚያ የተበደረውን እዳ እስከ ዛሬ መክፈል እንዳልጀመረ የሚታወቅ ነው፡፡ ሞሮኮ ውስጥ የደረሰበት ኪሳራ ከበድ ያለ መሆኑን ብዙዎቹ ይናገራሉ።
ወያኔ የኤኮኖሚው የጀርባ አጥንት አድርጎ የሚያየው የውጭ ንግድ እያሽቆቆለ በመሆኑ ስጋት መፍጠሩ ታወቀ፡፡ የውጪ ምንዛሪ ከእጥረት ወደ ባዶነት እየተሸጋገረ ባለበት ሁኔታ የውጭ ንግድ ከዓመት ዓመት ማሽቆልቆሉ እየተነገረ ነው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ የተመሰረተው በግብርና ውጤት ላይ ሲሆን ከአለፈው ዓመት ጀምሮ የቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የጥራጥሬ ዋጋዎች ማሽቆልቆላቸው አስደንጋጭ ነው በማለት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከዋጋ ማሽቆልቆሉ ጋር በተያያዥነት የምርቶቹ ተፈላጊነት የቀነሰበት ሁኔታ መከሰቱም ታውቋል፡፡ ወያኔ ዘረ-መል (ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ) ዘርን ለገበሬዎች ማደሉና ይህም በአብዛኛዎቹ አገሮች ከጥርጣሬ አልፎ በተጨባጭ መታወቁ ለተፈላጊነቱ መቀነስ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ተብሏል። ጥጥ በይፋ ዘረ-መል መሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረቱ የቱርክ፣ የቻይና፣ የህንድ፣ …ወዘተ አልባሳት በአውሮፓና በአሜሪካ ገበያቸው ሊዘጋ እንደሚችል አያጠራጥርም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከውጭ ንግድ ገቢ መቀነስ በተጨማሪ ከሀገር ጎብኚዎች ይገኛል ተብሎ የነበረው አራት መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሳይገኝ መቅረቱ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል፡፡ በየአመቱ የገና በዓልን በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ተገኝተው ስርዐቱን ይጎበኙ የነበሩ፣ ዘንድሮ በጣት የሚቆጠሩ ብቻ መምጣታቸው የወያኔን ኤኮኖሚ አከርካሪውን እንደሚለምጠው የኤኮኖሚ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡
የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሁኔታ አስጊ እየሆነ መጥቷል ተባለ፡፡ የአካባቢያችን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስጊ እየሆነ መምጣቱ በተደጋጋሚ የተገለጠ ሲሆን አንዳንድ ወገኖች ሁኔታዎቹ እየተባባሱ መምጣታቸውን የሚገልጹ መረጃዎች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። በመጀመሪያ ደረጃ ሳውዲ አረቢያ ጥቅሟን ለማስጠበቅና ከግብጽ ጋር ያላትን ቅራኔ ለማስተናገድ ከወያኔ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመፍጠር መንቀሳቀሷ ተጠቁሟል። በርካታ የሳውዲ ሚኒስቴሮችና ባለሥልጣናት ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ ሲሆን የሳውዲ ልዑካንም ወደ አባይ ግድብ ሄደው ግድቡን እንዲጎበኙ ተደርጓል። ይህ ሥራው እንደ ኤሊ እየተንፏቀቀ ነው የሚባልልትን ግድብ ሳውዲዎች መጎብኘታቸው ግብጽን ለመተንኮስ ነው ተብሎ ተገምቷል ያሉ ክፍሎችም፤ የሳውዲ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ኢትዮጵያን መጠቀሚያ ለማድረግ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የወያኔ ወዳጅ ተብዬው የጅቡቲው ኦማር ገሌህ ለሳውዲ የጦር ሰፈር መስጠቱ እንዲሁ ከኢትዮጵያ አንጻር መዘዘኛ መባሉም ተጠቅሷል። ወያኔ በአፋር አማጽያን የሚጠቃውን ገሌህን ለመርዳት ወደ ባልሆ ጦር መላኳ የሚታወቅ ሲሆን የገሌህ ጦር 50 በመቶ የመጡት ባለፈው ታህሳስ ጥቃት ከደረሰባቸው ከኢሳው ዩኒስ ሙሳ ጎሳ በመሆናቸው አማጽያኑን ለመዋጋት የሞራል ድቀት ደርሶባቸዋል ተብሏል። ገሌህ የኢሳዎችን የሃይማኖት መሪ ሙስጠፋ መሀመድ ኢብራሂምን አነሳስቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ያስወገዘ ሲሆን፤ በቅርቡም በማርማርሳን እጁን ጣልቃ አገብቶ በጎሳ ደረጃ በወቅቱ ለነበረው ረብሻም ተጠያቂ ነው ተብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ በበርበራ ወደብ ጉዳይ ሳውዲና ካታር በአንድ በኩል ግብጽ በሌላ በኩል የበላይነት ሽኩቻ እያካሄዱ መሆናቸው ሲገለጽ ወያኔ ይህን በተመለከተ ለሀገር የሚበጅ አቅዋምና ትልም አለመያዙ ተጠቅሷል። ይባስ ብሎ የሶማሊላንድ መሪ ሲላንዮ ባደረገው ሹም ሽር አክራሪ እስላማውያን የበላይነትን ይዘዋል መባሉም ተዘግቧል። ወያኔ በአሜሪካ ትዕዛዝ የአሜሪካንን ጥቅም ለማስጠበቅ ወደ ሶማሊያ ገብቶ በርካታ ዜጋዎችን ያስጨረሰና በኢትዮጵያ ላይ ዘላቂ ችግርን የፈጠረ ሲሆን፣ ጸረ አልሸባብ ውጊያው ስላልተሳካለት በቅርቡ የሞቃዲሾውን መንግሥት ተብዬ ቡድን በውጊያ ዳተኛ ብሎ መክሰሱ ተሰምቷል። በሶማሊያ ስለሚሰጠው አገልግሎት መጪው የአሜሪካ አስተዳደር ድጋፍና ገንዘብ እንዲጨምር ወያኔ የሚጠይቅ መሆኑም ታውቋል። በዚህም ሆነ በዚያ ወያኔ ኢትዮጵያን ለቀውስ እያጋለጠ እየቀጠለ ሲሆን በኢርትራ ደግሞ የከፍተኛ መኮንኖች ማጉተምተም እየጨመረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። የደሞዝ ጭማሪ ሊሰጥ ቀርቶ ያለው ደሞዝ ተቆረጠብን ያሉ መኮንኖች ኢሳያስን በፊት ለፊት በዞን 4 በተባለው ጠይቀውት መቆረጡን አልሰማሁም አጣራለሁ በሚል ጊዜ ሊገዛ መሞከሩን ውስጠ አዋቂዎች አጋልጠዋል። የኢሳያስ ጤና አጠያያቂ ነው በሚል በተኪነት የተሰለፉት ጄኔራሎች መሃል ሹክቻው የተጧጧፈ ሲሆን የጦሩ ከፍተኛ ሀላፊ ጄኔራል ፊሊፖስ ወልደ ዮሓንስ ዘመዱ በርካታ ወርቅ ይዛ ልትወጣ ስትል በአስመራ አይሮፕላን ማረፊያ በመያዟ ኢሳያስን የመተካት ዕድሉ ተጎድቶበታል ተብሏል። የኤርትራው ፈላጭ ቆራጭ መሪ ከቦታው ከተወገደ በዚያ የሚከተለው ብጥብጥ ኢትዮጵያ ላይ አንደምታ ይኖረዋል ብለው የሚያሳስቡ ክፍሎች የትግራይ ትግሪኝ ቅዠቱ ያልለቀቀው ወያኔ ኢትዮጵያን ሊያስጠቃ ይችላል የሚል ግምት ይሰነዝራሉ። ከዚህ በተያያዘም ከነሳውዲና ካታር ጎን በመሰለፍ ከአሜሪካንም መጠጋጋት የጀመረው ሻዕቢያንም ለማቀፍ አሜሪካ መለሳለስ መጀመሯ ተጠቅሷል። የዚህ ሁሉ መልዕክቱ የኢትዮጵያ ሕዝብን ትግል የሚያሳስቡ ሁኔታዎችና ክስተቶች እንዳሉና ሀገር አድን ትግሉ ይህን ሁሉ አጢኖ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና እርምጃም መውሰድ ይገባዋል ያሉ ታዛቢዎች የኢትዮጵያ ሕዝብና ተቃዋሚ ኃይላት ግራ ቀኙን አማትረው በማየት የህብረትና የትግል ስልት ሊኖራቸው ያስፈልጋል ብለዋል።