ኢያሱ ዓለማየሁ:
“ኩኩሉ ሲል ሰማን የእኛም አውራ ዶሮ፣
ምን ሊያሰማኝ ይሆን ጆሮዬ ዘንድሮ።”
የተጨቆኑና የተበደሉ ሕዝቦች የመከራ ኑሮአቸውን በቀልድና ስላቅ ያጅቡታል ነውና የአዲስ አበባ ተራቢዎች ‘’የዘንድሮ አውራ ዶሮ ኩኩሉ ቢልም በትግርኛ ነው’’ ብለው ችግራችንን ቁልጭ አድርገው አስቀምጠውታል። በአማርኛ የሚያሰማው ደግ መልዕክት የለውም። ምናልባት በቻይና ቋንቋ? እሱንም የሚሰሙት የገዢዎቹ የደላቸውና ለትምህርት ወደ ቻይና የተላኩት ልጆች ናቸው።
ምን ይሰማ ጆሮ? መላኩ ተፈራ ልቀቁኝ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስቲር ተብዬውን ሲማጸን? ፍቅረስላሴ ሀገር አዳንን ብሎ በኢሕአፓ ላይ ሁሉን ጥፋትና ወንጀል ሲጭን? የኢሕአፓን በመስዋዕት የታጀበ ትግል ወደ ፍቅሬ ነበረ ነበረች ሲያወርዱት? በረከት ስምዖንና ስብሓት ነጋ ስለ ጠላታቸው ኢሕአፓ መጽሃፍት ሲያጽፉ? ጠባብ ኦሮሞዎች አንዱን የሻዕቢያ ቅጥረኛ ስሙን ቀይረው ገዳ ሲሉት? የኢሕአፓን ታሪክ በርዘንና ከልሰን እንጻፍ ብለው ድርጅቱን ከከዱ 34 ዓመት ያለፋቸው ሲፍጨረጨሩ? የግንቦት 7 ረዳት ነው የተባለው ሻዕቢያ የድርጅቱን ዋና ጸሃፊ አሳልፎ ሰጠ ሲባል? ኦባማ ጸረ ሕዝቡን ወያኔ ሲያወድስ? ደግም ክፉም ይሰማል። የሚዘልን ከመሬት ሆነህ ጠብቀው ብለው ሶማሌዎች እንደሚተርቱት ከአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ጣቃ በፈጠነ የሚተረተሩት ከነ ደለበ ውሸታቸው መጋለጣቸው አይቀርም። ዝም ያለም ይናገራል፣ ይጽፋል፣ ተኛ የተባለውም ይነቃል፤ ተስፋ አስቆራጭ የሆነውም አበረታች ይሆናል። ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲሉ። ረጅም ጊዜ ሳንጠብቅም በያዝነው በዚሁ ጊዜና ወቅት ግን ሐሳዊ መሲሆችና የታሪክ ላፒሶች እየተጋለጡ መሆኑንም እያየን፣ እየታዘብን ነው። እሰየው ብንል አይፈረድብንም።
የታሪክ ሚዛን ያልገባቸው አንዳንዶች ለምን ያለፈን ታወራላችሁ ሲሉ ይደመጣሉ–ባለፈም በነበር ለምን እሰጥ አገባ ይበረክታል ብለውም ያማርራሉ። የሚገርመው ደግሞ እነዚሁ ሰዎች የሆነውን ሳያውቁ፤ ታሪክን ሳይረዱ ያለፈውን–በተለይ ታግሎ የተሰዋውን–ትውልድ ሊተቹና ሊያወግዙ መሬት አልበቃቸው ብለው ሲገኙ መታዘባችን ነው። በየጊዜው ህዝብ ለመራራና ስር ነቀል ለውጥ ሊሰዋ ተነስቶና የደም ዋጋም ከፍሎ አቸናፊ አልሆነም ብለው የሚተቹ ታሪኩን የረሳ ስህተቱን ይደግማል ነውና ዛሬም ከስህተት ሲዘፈቁ እንዲያውም በቅድሚያና በትኩረት ያለፈውን ታሪክ–ደጉንም ህጸጹንም–መመርመር እንዳለባቸው ማወቅ ይገባቸዋል። ታሪክ ከተረሳ ደግም የአባትህን ገዳይ አባባ የማለት ቅሌት ሊከተል መቻሉ ግልጽ ነው። ስንቱን ሕዝብ የደም እንባ ያስለቀሰውን አጼ የሚያወድሱና መቸም ቢሆን መቸም ሀገርን ሊረከቡና ሊጠብቁ የማይችሉ ጉዶች ፈልተው የለምን? ብዙ መቶ ሺዎችን የጨፈጨፈውና ሀገሪቷን ለገንጣይ መንጋ አሳልፎ የሰጠውን የደርግ አረመኔ ቡድንን ጸያፍ ታሪክ ለማደስ ላይ ታች የሚሉ አልተከሰቱምን? ይባስ ብለው ሀገሪቷንም ሕዝቧንም ላጠፋ ተነስቻለሁ ብሎ የቧረቀውንና ስንት ጉዳት ያደረሰውን ግብዝና ዘረኛ ግለሰብ ባለቀና ቅርስ አድርገው ሊያቀርቡ ስንት ገንዘብ የሚያፈሱትን እያየን አይደለንምን? የቀድሞይቷ ኢትዮጵያ መሪዎች ትልቅ ስህተት አርበኛውን፤ ለሀገር ቀና ያሰበውን አግልለው ባንዳውን ሲሾሙ ወይም በመሾማቸው ነው። ለበላይ ዘለቀ እየዘፈኑ ለገዳዩ አጼም ውዳሲ ማቅረቡ ዘግናኝ ነው። ቅጥ ያጣ መደናገር! ታሪክ ለምናውቀውና ለኖርነው ደግሞ ጨው በቁስል የሆነ ሁኔታ። ታሪኩን የረሳ ግን ዜጋን የገደለና ሀገርን ያጠፋ ሲዘፈንለት አብሮ ቼቼ ባይ ሆኖ ቆሽትን ያነዳል፤ ያቃጥላል።
አነሳሴ እንኳን ነበርንበትና ሀሰትን ይዛችሁ አትሞጀሩበት ለማለት ነው። ታሪክ ተራኪ ነን ብለው የተነሱ አንድም ነጋዴዎች፤ አንድም የብዕር ቅጥረኞች (ወይም በቀድሞ አነገጋር የብዕር ኩሊዎች) ሆነው ስለበዙ ቶሽ–ወግዱ ማለቱ የዜጋ ግዴታ ሆኗልና በሌላው እንኳን ባንሰማራ ታሪክንና ቅርስን በመንከባከብ መስክ ግዴታን መወጣት ይጠበቃል ነውና ታሪክ ሲበረዝ አይሆንም አይፈቀድም ማለቱ የግድ ይሆናል። እኔም የበኩሌን በዚሁ መስክ ማለት ደግሞ ሰማዕት የጣሉብኝ/የጣሉብን ግዴታ ነው። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በምስረታው ነበርኩና። ከእኔ በላይ ማን ሊናገር ሊጽፍ ማለቱ ባይቃጣኝም። በሬ በቶሮንቶ፤ ዋሽንግተንና ላዖስ ሲወልድ ባናይም — ቢያንስ በኢትዮጵያ– ሲወልድ ሳናይ ዓመታት አልፈዋልና ሀሰቱን ሀቅ ብሎ ለመቀበል አይሆንልንም።
እንጻፍ ካልንማ ስለ ፍቅር እንጽፋለን። እገሌን ወደድኩት፤ እገሊት ፍቅሬ ነበረች የሚለው ተራ ትረካ (ያውም ውሸት ወይም አጠያያቂ የሆነን) ሳይሆን በጓዳዊ ፍቅር የተደረጉ ገድሎችን ማለት ነው። የያዘውን የሳያናይድ መርዝ ሌሎች ስቃያቸው ሲበዛ ሰጥቶና ሁሉንም በእኔ አላኩብኝ ብሎ መክሮ ሊገመት የማይቻል ስቃይና ስየልን ተቀብሎ የሚሰዋ– የጓዳዊ ፍቅር ገድል። ጓዶችን ላለማጋለጥ ራሱን የሚያጠፋውን፤ የሕዝብ ፍቅር ሞልቶት መስዋዕትነትን በጸጋ የሚቀበለውን፤ የምትቀበለውን ማለት ነው። እንጻፍ ካልን ስለ ድላይም ሆነ ጽጌ፤ ስለ ቆንጂትም ሆነ ስለ ዘውዲቱ ዋሲሁን፤ ስለ ዳሮ ነጋሽም ሆነ መድፈሪያሽ ወርቅ (ጀሚላ)፤ ስለ ሕብስቱም ሆነ ዘውዱ፤ ስለ አንጋው ከበደና ሰለሞን ከበደ፤ ስለ ጉግሳ፤አባይ፤ ደበሳይ ካህሳይ፤ ጡመልሳንና እናቱ፤ በ1986 ዓ.ም. በቋራ ለተሰዉት ስለነ ጃብርና ግርማ ጎልጃ ፤ስለ ሃይሌ ዐባይ (አምባዬ)፤ ስለ የሺጥላ ውብሸትና ወንድሞቹ መሸሻና ሙሉሸዋ፤ ስለተሰዉት አንጋፋ አባሎች ዮሲፍና ብንያም አዳነ፤ ጸሎተና ይትባረክ ሕዝቅያስ ስለነ ውብሸትና መሀመድ ማህፉዝ፤ ሙሉጌታ ሱልጣን፤ ኢንጂነር ኦስማን፤ ተካልኝ ወልደ አማኑኤል፤ አልማዝ፤ ማርቆስ ሐጎስና ስንቶቹ ላባደሮችና መሪዎቻቸው ወዘተ የምንጽፈው ስለ ጀግንነታቸው ብቻ እንጂ ሌላ ትርኪ ምርኪ ብዕራችንን አያደርቀውም። ጀግናው ጀጃው ለምሳሌ ወያኔ ኢሕአፓ/ሠን ለማጥፋት የከፈተውን ዘመቻ ለመቋቋም ከተወሰኑ ጓዶች ጋር ሆኖ ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ በቋራ ሲንቀሳቀስ በ1984 ዓ.ም. ተከቦ ባለበት ሲታኮስና ጠላትን ሲገድል ቆይቶ በመጨረሻ ንብረቱን ሁሉ አቃጥሎ፤ ብረቱንም ሰብሮ እጅ የሚሰጥ መስሎም ሊይዙት የመጡትን ወያኔዎች ከራሱ ጋር በቦምብ ገድሎ ታሪክና ጀብዱ ሰርቶ አልፏል። በ1972 ሰራዊቱንና ኢሕአፓን ከድተው የፈረጠጡት (ድርጊታቸውን የሚገልጸው ይህ ብቻ ነውና) ዛሬ የሰራዊት ታሪክ አዋቂ ነን ብለው ልንጽፍ ነው በሚልም ሲውገረገሩ ከነሱ ክህደት በኋላና ወያኔም ስልጣን ከያዘ በኋላ ስለተደረገ ተጋድሎ የሚያውቁት ቅንጣትም የለም ። ያውም ለወያኔ የገደል ማሚቴ መሆኑን ትተው ያልነበራቸው የመጻፍ ችሎታ ድንገት ከተከሰተ ሊጽፉ ከተነሱ ማለት ነው። ቢከፍቱት ተልባ ነውና የምናውቀውና ሁሉ እናውቃለንና ድንገት ጉድ አጋላጮች ከተኙበት ነቁ ብለን ኢሕአፓዎች እንቅልፍ የምናጣ አይደለንም። እኛ ግን ለሕዝብና ለሀገር ፍቅር ሲሉ መስዋዕትነትን የተቀበሉትን እንዘክራለን እንጂ በሕይወት የሉም ብለን ሀሰት አንጠርቅም። ጽጋዬ ደብተራው የለም ብለን የራሳችንን ጥፋት ሁሉ በእሱ ላይ አናላክክም። ያልነበረንን የታሪክ ቦታ ለራሳችን አንሰጥም። በቀቢጸ ተስፋ አናላዝንም። እንጻፍ ካልን ብዕራችን ይህን የጀግንነት ታሪክ ይዘክራል ያወድሳል እንጂ በግል ስሜት ተነድተው ዋይ ዋይ የሚሉትን አይከተልም። ስህተት ይተች ስንልም ውንጀላ ሳይሆን ሂስ ነው፤ ሚዛኑን ያልሳተ። ከዳተኞች ውለው አድረው በወያኔ ኮርኳሪነት በድንገት ኢሕአፓን ሊያጠቁ ቢነሱም የሚገርመን ክስተት የማይሆነው ለዚህ ነው። ለመሆኑ የኢሕአፓን ታሪክ ጸሀፊ መሆን የሚከጅሉት አለምንም ስጋት ወደ አዲስ አበባ የሚመላለሱ ብቻ ሳይሆኑ ከእነ በረከት፤ አዲሱ ለገሰ፤ ህላዊ ዮሴፍ፤ ወዘተ ጋር እራት ተጋባዥ ናቸውና ቀላጅ የሰይጣን ወዳጅ እንላቸዋለን። ይህን ስንተወው ደግሞ ለእኛ ፍቅር ስንል ሀገርና ሕዝብን የሚመለከት ነው። የግለሰብ ስሜታዊ ጉዳዮች ለግለሰቦቹ ግዙፍ ቢመስሉም ከሀገርና ህዝብ አንጻር ግን ሚዛናቸው ዝቅ ያለ ወይም ገለባ ነው። ፍቅር ለሕዝብ፤ ፍቅር ለኢትዮጵያ –ይህ ነው ቅዱስና ክቡር ጉዳይ፤ ከመሬት ተንፏቆ ክጭቃ ተንከባሎ የማይገኘው።
እንጻፍ ካልንም ስለ ጥላቻና ጠላትነት መጻፍም ግዴታችን ነው። ያልተመታ ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል የሚባልብንም አይደለንም። ህዝብና ሀገርን ሊያጠፋ በተነሳ ከይሲ ድርጅት ላይ፤ ብርቅ ጓዶቻችንን እነ ጸጋዬና ይስሃቅ፤ በለጠ፤ ስጦታውን፤ አዛናው ፤ ደሳለኝን፤ ሐጎስና ተክላይን ወዘተ ከማጎሪያው እያወጣ በረሸነ አረመኔና ዘረኛ ቡድን ላይ ጥላቻ ቢኖረን እሰየው የምንባል ነን። በ አሲምባ የተገደሉትን እነ ገመቹንና ሌሎቹን ጓዶችንም አንረሳም። ያልቆሰሉ፤ ያልደሙና ምንም ስቃይ ያልደረሰባቸው ከወያኔ ዕርቅ ወሰላም ቢሰብኩም አንገረምም– ያልደረሰበት ግልግል ያውቃል ተብሎ የለ? ጥላቻና ቂም ይቅር ይላሉ አንዳንዶች–ለምንና እንዴት? ወንጀል የፈጸሙት አጠፋን ብለው ይቅርታ ጠየቁ? በፍጹም። ይባስ ብለው ደግ አደረግን ብለው መጽሃፍም እየጻፉ፤ ዳግም በደማችን ላይ ሊቀልዱ እየጣሩ ናቸው። ከወያኔ ተጣላን ቢሉም ከዓመታት በፊትም ሆነ ከስልጣን መያዛቸውም በኋላ የወያኔን ወንጀልና ገበና የራሳቸው አድርገው ሲደብቁ እንጂ (በአንጻራዊ ደረጃ ገብሩ አስራት ሲቀር) ሀቁን ተጸጽተው አውጥተው አጠፋን ሲሉ አልተደመጡም። ጨቋኝን፣ በዝባዥን፣ ግፈኛን ወራሪን መጥላት ግን የዜጋ ግዴታ ነው። ከጠላት ጋር መሞዳሞድ አይቻልም–ውጤቱ ክህደት ይሆናልና። ስለዚህም ታሪክ ስንጽፍ ለጠላት የነበረንና ያለን ጥላቻ ለብዕራችን የማይነጥፍ ቀለም ይሆናል። ጠላትን ጎርፍ ሲወስደው እንትፍ ብለህ ጨምርበት ያሉት አባት እናቶቻችን በከንቱ አይደለም ።
ቀደም እንደጻፍኩት ዛሬ ስለ ኢሕአፓ መጽሃፍ ጻፍኩ ማለቱ ከንግድም አንጻር የደራ ሁኔታን ፈጣሪ ሆኗል። ፈጠን ፈጠን ብሎ በ ስመ ኢሕአፓ ጸረ ኢሕአፓነትን መጻፍ በዘመኑ አነጋገር የሚያበላ ሆኗል። የዛሬ 35 አመት በየምክንያታቸው ድርጅቱን ጥለው የሄዱ ዛሬ ተመልሰው ስለ ድርጅቱ እንጻፍ ቢሉ ራሳቸውን ለትዝብት የሚዳርጉ ናቸው–ያልነበሩበትንና ያልኖሩትን ታሪክ ሊጽፉ የሚዳክሩ ናቸውና። ታሪክ ጸሃፊ የሚባሉትም ጥረታቸው ከንቱ መሆኑን በየጊዜው ጠቅሰን ልናጋልጥ የጣርነውና የተቸነው ነው። አንዱ ፕሮፊሰር ለምሳሌ የወያኔ የክልል አንድ ተወላጅ ነውና ቀይ ሽብርን ኢሕአፓ ቆሰቆሰው ሊለንም ሞክሯል። ሌላው የታሪክ ዶክተርም ተመሳሳይ ሊጽፍ ሞክሮ ታረም ብለነዋል። ለሀቅ የሚቆሙ ታሪክ ተንታኞች ጠፍተዋል፤ ትንተናዎቻቸውም ግልብ ሆነዋል ማለትም ይቻላል። ኢሕአፓ ለከተማ ትጥቅ ትግል የተዘጋጀ ወይም ይህን ምርጫ ሲመሰረት ጀምሮ ያደረገ አልነበረም። ብዙዎች መነሻና መድረሻ መንስኤና ውጤት እየተማቱባቸው ትንተናቸው ዋጋ ቢስ ሆኖ ቀጥሏል። በወያኔ አሁን ድጋፍ ተሰጥቷቸው ላይ ታች የሚሉና ድሮ አመራር ነበርን ብለው የሚለፍፉ ( የዛሪ 35 ዓመት) ያልተነገረ ታሪክ አለ በሚል በኢሕአፓ ላይ የተነሱ ሁሉም አንጃዎች ትክክል ነበሩ ለማለት እየጮሁ ናቸውና ምን ፈለጉ ስንል ባያስገርምም የተሰጣችው ተልዕኮ የድርጅቱን ታሪክ አክስሎና ያሉትንም አመራሮቹን ማውገዝና ማጥላላት መሆኑን መገንዘቡ አላቃተንምና በጌቶቻቸው አነጋገር ‘’እንታይ ጉዱ በዓል ዘመን ዘይብላ ዘበን ከይትሓልፍሲ፤ ኣንጭዋ ግምኦ ትቍነን’’ ማለት የግድ ይሆናል። ጊዜ የሰጠው ቅል የሚለውም ይሰራል። ጥራዝ ነጠቆቹ ለምሳሌ የመጀመሪያው አንጃ ልክ ነበር፤ የከተማውን ሁለገብ ትግል ሲቃወሙ ይላሉ። ከነ ብርሃነ መስቀል አንጃ ጋር ልዩነቱ የከተማ የትጥቅ ትግል ስልት ሳይሆን ደርግ ጋር መተባበር አለመተባበር የሚለው ነበር። ከመኢሶንም ቢሆን ልዩነቱ መነሻው ይህ ነበር። ከቀጣይ አንጃዎችም ጋር ልዩነቱ ተመሳሳይ ነበር። የቅርቡ አንጃም ለወያኔ ገብረን ፈርመን ሀገር እንግባ ሲል ልዩነት ተፈጠረ እንጂ የውስጣዊ ዲሞክራሲ ጉዳይ አልነበረም ልዩነት ያስነሳው። በወያኔ ቀስቃሽነት ያልተነገረ ታሪክ እንጻፍ ብለው የተነሱት የ1972 ፈርጣጮች እንዴት ስለ ኢሕአሠ እስከ 1986ና ኢሕአፓ በ2007 መጻፍስ ይችላሉ? ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ከሚባለው ሁሉ በላይ ነው። እንቀጥል ካልን ደግሞ ታሪኩን የምናውቀው የግድ ከሆነ ‘’ማን ማን ነው? ምን ነበር?’’ ብለን ልንጽፍ ልንገደድ ነው። እንጻፍ ካልንማ እስከዛሬ ሆድ ይፍጀው የነበረው ወጥቶ በአደባባይ ሊሰጣ፤ ሊነገር ነው ማለት ነው። ያዋጣል? በጥሞና ቢታሰብበት ደግ ይመስለኛል። ማስፈራራት ሳይሆን ቀና ማሳሰቢያ ነው። ከ1972 ጀምሮ ዝምታን አቅፈው የከረሙ በአሁኑ ጊዚ ፍየል ምላስ ሊሆኑ ምን አነሳሳቸው? ጸረ ኢሕአፓዎችንና የአንጃን መንጋ ደግፈው ሊራወጡ ማን ቀሰቀሳቸው? ራሳቸው ለብዙ ችግሮችና ድክመቶች ተጠያቂ ሆነው እያሉ ማለታችን አይቀር ይሆናል። ወደ ግለሰቦቹም ምነነትና ታሪካቸው መገፋፋታችንንም ማምለጥ አንችልም።
ኢሕአፓን በተመለከተ ያልተሰራጨ ሀሰት የለም። የሚጠበቅ ነው–ለሀገር አንድነትና ለዲሞክራሲ ሲል ታግሏልና ጠላቶቹ ብዙ ናቸው። ድርጅቱም ለምን ተተቸሁ የሚል ሳይሆን ለትችቶቹ ምላሽ እየሰጠ፤ ራሱን በየጊዜው እየገመገመና ለማረም እየጣረ የቆየ ነው። በቅርቡ መጽሃፍ ያሳተመው የወያኔ የቀድሞ አመራርም የኢሕአፓ መከራ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አላስረክብም በማለቱ ነው ሲል አረጋግጧል። ኢሕአፓ የኢትዮጵያ የቅርብና የሩቅ ጠላቶች ሁሉ ጥፋ ብለው አጥቅተውታል–ከአቅዋሙ ጋር የመጣ ጣጣ ነው። ለኢትዮጵያ የቆመ ሁሉ ላይ የቅርብም ሆነ የሩቅ ጠላቶች ይረባረባሉ። ኢሕአፓ ኢትዮጵያን ቢክድ ወዳጆቹ ብዙ ይሆናሉ–የትናንትም ዛሬም ሀቅ ይህ ነው። ኢሕአፓ ራሱን እንደ ወያኔ ለገበያ ቢያቀርብ፤ ሀገራዊ መርሆውን ቢሸጥ፤ ሀገራዊ ጥቅምን ለድርድር ቢያሰጣ፤ አረብ ነን ቢል፤ ሲሶ ኢትዮጵያን የሶማሊያ ግዛት ነው ብሎ ሞቃዲሾ ተጉዞ ቢፈርም፤ አሜሪካ ለወያኔ ስገድ ቢለው ቢሰግድ ወዘተ ምናልባትም ደጋፊና ደጓሚ ማግኘት ይችል ይሆናል። ምን ለመስራት? ምን ጥቅም ለማግኘት? ብዙውን ጊዜ ተድበስብሰው የሚያልፉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው። ወደ ታሪክ መለስ ስንልም አሉባልተኞቹ የሚሉትን-የሚለፍፉትን ወደ ጎን ስንተው– በሀገር ጉዳይ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው በሌጣው የሚወሰድ አይደለም። ዋና ፍላጎታችን ሀገርን ማዳን ከሆነ፤ ሀገርን ሸጠን ሀገርን ማዳን የሚለው ጎዳና ወስዶ ገደል ከታች ነው። ለዚህም ነው ዛሬም ከወያኔ ጋር ዕርቅ ሰባኪዎች ጋር ስምረት ስምምነት ሊደረግ የሚቻል ሆኖ የማይገኘው። ተኩላና በግ፤ ፍየልና ነብር በአንድ በረት አያድሩም። አንዳንድ የለመደባቸው አሳዛኝ ፍጡሮች ትላንት ስንቱን ሕዝብ ባልሆነ ቅስቀሳ አስፈጅተውና አሳስረው ከመለስ ዜናዊ መውጫ ፍቃድ አግኝተው ተሰደው ዛሬ ደግሞ ተመልሰው ለወያኔ ምርጫ አጃቢ የሚሆኑት ሕዝባችንን የሚያሳፍር ከመሆኑ ሌላ ምናልባትም በወያኒ ፓርላማ ተብዬ ግፋ ቢል ሁለት ወንበር ከማግኘት ውጪ የሚያተርፉት ጭራሽ የለም። የደቡብ አፍሪካ ዓይነት የዕርቅ ሂደት ይምጣልን የሚሉትንም በተመለከተ ቢሆንም የዚህን ሙከራ ሂደትና ክሽፈት መገንዘብ ያልቻሉ ከመሆናቸው ሊላ ወያኔ በዕርቅና ሰላም ተሞክሮ ያላገጠ፤ ያሰረና፤ ወግዱልኝ ያለ መሆኑንም የዘነጉ ናቸው ማለትም ይቻላል። በደቡብ አፍሪካም የዘረኞቹ ስልጣን ከተወገደ በኋላ ነው ይህ ጥረት የተደረገው። የጋንዲንስ የህንድ ነጻነት ጉዳይም ከሚባለው ውጪ እንደነበር ታሪክ ይመዘግባል። ታዲያ ዛሬስ ከወያኔ ጋር ዕርቅ ሰበካ ጊዜው አላለፈበትም? የሞኝ ነገር መልሶ መልሶ ያሰኝብናል።
ግማሽ አርበኛ ግማሽ ባንዳ መሆን የሚቻል አይደለም። ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ መላጣ። እንጻፍ ካልንማ ሀቁን ማስፈር ስላለብን ምናልባትም የሽፍንፍኑን ባታሊዮን የምናስቀይም ይሆናል። የሚገደን አይደለም። ታሪክና የሕዝብ ዕጣ ተደቅኖ ባለበት ማንን እናስቀይም ይሆን የሚለው ቦታ አይኖረውም። ኢሕአፓን የሚጠሉና ያ ትውልድ ይጥፋም የሚሉ እንዳሉ እናውቃለን–እነዚህ ግን ብዙዎች ወይ የዚያን ጊዜ ወንጀለኞች ወይም የወያኔ ቅጥረኞችና ሆዳሞች ናቸው– ማለትም በወያኔ የተገዙ። የዛሬን ውድቅ ሚናቸውን ለመሸፈን ግን ግልጋሎታችን ለወያኔ ሳይሆን ለሀገር ነው ማለት ይቀናቸዋል። ሀገር ማገልገል ከፈለጉ ለወያኔ መቸም አያድሩ ነው ሀቁ። መሰደድ ይቻላል–ሌላም ስራ መያዝ ይቻላል። የወያኔ ሰላይ፤ ገራፊ፤ ነፍሰ ገዳይ ከመሆን ይልቅ ማለት ነው። ያች አይቀሬ የፍርድ ቀን ስትመጣ ይህ ሁሉ ይጠየቃል–ብልጣ ብልጥ ሆዳምም ምሱን ያገኛል። በታሪክም መስክ ይህ ይኖራል። እንጻፍ ስንል ይህን ሁሉ በዝምታ የምናልፈው አይሆንም። በብሄረሰብ ጥያቄ ዙሪያ ተሸሽገው ግና ሰልፋቸው ለባዕዳንና ለራሳቸው ሆድና ጥቅም የሆነውንም ማጋለጥ አይታለፍ ግዴታ ሆኖ ያለን የሚሆንም ነው። ታሪክና ሀቅ ለስላሳ ወይም ጀርባ አካኪ አይዞህ ባይ አይደሉም–ያለውንና የነበረውን ይናገራሉና ሁሉም እንደሚናው መስቀሉን ይሽከማል፤ ፍርዱን ይቀበላል። የሚደበቅ የለም ማለት ነው። ለዚህም ነው ሀቁ ይነገር ሲባል የሚከፋው ጥቂት አለመሆኑን ማወቅ ያለብን። የሀሰት ታሪክ የሚጽፉትን ወይም ሊጽፉ የሚቃጡትን ስንቃወም በአንጻሩ በእኛ በኩል ደግሞ ሀቁን ማስፈሩ ይጠበቅብናል። የዛሬ ትግል ምናልባትም ጠላትን ላለመጥቀም ዝምታን የግድ የሚልበት ሁኔታ ቢመጣም ያለፈውን በተመለክተ ግን ሰፋ ያለ ሜዳ ቢኖርም ያም መጭ ማለትን የሚፈቅድ ላይሆን መቻሉን መገንዘብ የግድ ይሆናል። ምስጢሮች እንደ ይዘታቸውና አንደምታቸው የመነገርና የመገለጥ ሁኔታቸው ይወሰናል። ለምሳሌ ጠላትን ለማጥፋት የተወሰዱ እርምጃዎች ሁሉ መነገር አለባቸው ማለትም አይደል። ከድርጅት ታሪክ አንጻርም ምስጢር ብለን የምንጠብቃቸውና በጊዜ ገደብ የምንይዛቸው መኖራቸው ግልጽ ቢሆንም በማያውቁት የሚቀባጥሩ ሲመጡ ግን የተሰዉ ጓዶች ቅርስ፤ የድርጅቱ ስምና ዝክር ነውና መከላከል አስፈላጊ ይሆንብናል። በጥፋትም በስህተትም ተካፋይ ብቻ ሳይሆን ዋና ተጠያቂ ሆነው በግልባጩ ጊዚ አልፏልና የሚያስታውስ የለም በሚል ሚናቸውን ሊክዱና ሌሎችን ሊከሱ ሲነሱ ሀቁ ይህ ነው ማለቱ ግዴታችን ይሆናል፡፡ ይህ ቢባልም ግን ታሪካችንን የምንጽፈው ከድጡ ወደ ማጡ ለገቡት ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን በቅድሚያ ላለው ትውልድና ለመጪው የሰማዕትን ገድል ለማስረከብና ከፈሰሰው ደም ትምህርትን ቀስሞ ቅርሱን ያዳብርም ዘንድ ነው። የአርበኞች ሳይሆን የባንዶች ታሪክ ከሰፈነና ከተወደሰ ታሪኩን የረሳ አቅራሪና ትውልድ በላዬ በላዬ እያለ በዚያው ምንም ሳይጎረብጠው ሀይሎ ሀይሌ ብሎ ሲወዘወዝ ማየት እንገደዳለን።
እንጻፍ ካልንማ –መጻፍም ይኖርብናል–የዚያን የጀግና ትውልድ ሰፊ ተመክሮ–ጸጋውንም መርገሙንም፤ስህተቱንም ድሉንም ሁሉ በነበረው ሁኔታ አጥርና ክልል ውስጥ አስገብተን ማቅረብና ለገምጋሚም ሀቀኛውን ሁኔታ ማስጨበጥ መቻል አለብን ማለት ነው። ይህ ሆነ ይህ ተደረገ ሀቅን መደርደር ብቻ ሳይሆን ለምንና እንዴትንም ለማቅረብ፤ ለማስረዳት። የዛሬ የኋላ መብራት ከያኔው ተጨባጭ ሁኔታ ዕይታ ጋር እንዳይጋጭ። ለዚህም ነው ታሪክ ተብለው የተሞከሩት ከሀቀኛ ታሪክ ርቀው የግል ቁርሾን ወይ ወንጀልን ድበቃ፤ ሀላፊነትን ለመካድ ምክንያት ሲሆኑ አሌ ማለት ግዴታችን ሆኖ ያለው። ታሪክ ተረት ተረት የሆነው ለወያኔዎች እንጂ ለእኛ አይደለም። ውድ ጓዶቻችን በዘረኞች ሲገደሉና በዚያውም የቅርሳችን ትረካና ትዝታ ሙሉ የመሆኑ ዕድል ሲጠፋ ቁጭታችን ትንሽ ሊሆን አይጠበቅም። ጊዜ ተቻኮሉ፤ ሰማዕትን ተከላከሉ ይለናል። የህቡዕ ድርጅት ደግሞ ሽፍን ነው በሚል ሀቁን በሚደብቁና ሀሰትን ለሚያሻሽጡ ያመቻል። ብርሃነ መስቀል ለሞዛምቢክ ሲዋጋ፤ ሊቀመንበር ማኦን ሲገስፅ ሲመክርና ካስትሮን ሲያስጠነቅቅ ፤ በምስረታው ያልነበረ መስራች ሲሆን፤ በተወሰነ ተልዕኮ ጭራሽ ያልነበረው ዋናው ሲሆን፤ መስራች ያልነበረው መስራች ነኝ ሲል፤ ለሀገሩ የቆመው ለሶማሊያ ተሰለፈ ሲባል፤ ድርጅቱ ራሱ በምዕራብ ጀርመንና አልጂሪያ ተቋቋመ ሲባል፤ ኤርትራን ሲያስገነጥል ወዘተ ወዘተ–ያልሰማነውና ያላነበብነው ምን አለ? መጽሃፍ የተባሉትን 60 ገጽ አንበን ከ60 በላይ ውሸት እያገኘን መሰላቸታችንም ምስጢር አይደለም። ማን ያውራ ያልነበረ ማን ያርዳ ያልቀበረ የሆነ ይመስላል መርሆው። ምን ያስገርማል በዚህ ሁኔታ ውሸት ታሪክ ነኝ ሊል ቢሞሸርና ጥቅም ፈላጊና ዘረኛ ዋሾዎች ቢፈሉ!
ኢሕአፓና ታሪኩ ስንል የንብ ቀፎን የነካካን ሆኗል–እኛ ኢሕአፓዎች ያልጻፍነውን ታሪክ ለመሆኑ ማን ሊጽፈው ይጠበቃል? ኢሕአፓነት ማለት ከዕለታት አንድ ቀን የዛሬ አርባ ሰላሳ አምስት ዓመት በኢሕአፓ ሰፊ አዳራሽ ላስ ብሎ ማለፍና መውጣት ከሆነ በረከትም፤ አዲሱም፤ ጉዲትም፤ ተፈራም፤ ሕላዌም፤ ሀሰንም ፤ አባተም፤ ግርማና ስማቸውን ሳንጠራ የምናልፋቸውም “ኢሕአፓ ነበሩ”። ጎርፍ ያመጣቸውና ያው ጎርፍ እንደ አባይ አምባዛ አስክሮ የተፋቸው። መወለድ ቋንቋ ነው ይላል የሀገራችን ሰው — ነበርንም ከንቱ ነው! መሆንና ጸንቶ መቀጠል ነው ዋናው። የእኛ ጸጋ ይህ ነው–የምንኮራበትና የሚያኮራን። ደከም ሸብረክ ያለውንና ቃል ኪዳኑን ያረከሰውን እየሸኘንና የተወውን ችግር እየተቀበልን ድርጅቱን ጠብቀን ታግለናልና ከማንም–በተለይም ከድተውን ዓመታትን ካሳለፉ ወይም ከወያኔ ጋር ካበሩ ዲስኩር ለመስማት ፍላጎት ባይኖረን የሚያስገርም ሊሆን አይገባውም። እኛ ስንታገል በዱር በገደሉ/ እነማን ነበሩ በመላ ሀገሩ/ ብንል አግባብ አለው። ሁናቴው ሲጠጥር ላልተው የተፈቱ የሚያወሩት ታሪክ፤ የሚጽፉትስ ታሪክ ከየት የመጣ ይሆናል?
ፎክሮ ከሚሸሽ ታሪክ ከሚያበላሽ፣
ቃል ኪዳንን ክዶ ከሚሆን ርካሽ፣
ነፍሱንም ከሚጥል ከሚሆን ተልከስካሽ፣
ይሻለን ነበረ ባልነበረ ጭራሽ ።
ብንልስ ይፈረድብናል?
ያለን የነበረን ሁኔታ መካዱ ከንቱ ነውና ልንጽፍ ስንነሳ ና ሀቅን ቦታዋን ስናስይዛት ትላንትም ዛሬም መድረኩ አመቸ ብለው የዘበራረቁትን ከማሳፈር አልፎ እኒያ ውድና ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች ሞት ለፋሺስት! ሞት ለዘረኛ ገንጣይ ብለው በሞት አይፈሬነት ለምንስ እንደተሰው የምንዘክር ይሆናል። ውድ ሀገራችን ያሏትንም ጠላቶች ማንነት ይዘትና የዓመታት ሻጥርንም ዘርዝሮ ማቅረብ የግድ ይሆንብናል። ይህን ግዳጅ በጋራ ለመወጣት ደግሞ ጥረታችን ተጀምሯል። በዚህ ግጥም ይህን ክፍል ልደምድም፡
“ምን እንበላቸው?
ምን እንበላቸው ለ አዲሶቹ ሁሉ፣
ታሪክን ሀገርን እንረከብ ላሉ፣
እንበል መንግስቱ ነው የሀገር መለያ፣
ወይስ ያ መለስ ነው ሚሆን አርአያ?
ኢትዮጵያዊ ሲባል ጀግና ነው አርበኛ?
ሀሰት ነው ሀቅ ነው ይነገረን ለኛ?
ብለው ቢጠይቁን
ምን መልስ እንስጣቸው
ምን እንበላቸው?
እንበል ወይ እዩ የወያኔን መንጋ
ከርሳሙን ፈርጣጩን
ወይስ እንበላቸው ጀግና ሞልቷል ገና
ለሀገር ለወገን ቆርጦ የሚሰዋ?
ምነው ሆዳም በዛ የእኔ እኔ ባይ መንጋ
ወኔ ህሊና አልባ
ብለው ቢጠይቁ ምን መልስ እንስጣቸው
ምን እንበላቸው?
እንበላቸው ወኔ በደርጉ ተገድሏል
ጀግናም አርበኛውም ካለቀ ጊዜ አልፏል?
ወይስ እንበላቸው ዛሬም ጀግና ሞልቷል
ጠዋት ባይሆን እንኳን ማታ ላይ ያምጻል?
አሊያስ እንበላቸው
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ናት ታሪክም አልዋሸ
የከርሳሙ መንጋ መች ብዙሃን ሆነ?
ወኔ መቼ ሞቶ መቸ ተቀበረ?
የጀግኖቹ ትግል ከቶ መቼ ቆመ ?
ያገራችን ህዝብስ ሀራሬ መች ሸሸ?
የከሃዲስ መንጋ መቼ ህዝብ ተባለ? ”
የኢሕአፓ ሀቀኛና ሙሉ ታሪክ በድርጅቱ ይጻፋል !!
ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል !!
ማስታወሻ
የቃላት ጉዳይ፡
አንዳንድ ቃላት–ሁኔታውን ገላጭ ሆነው እያለ — አንዳድንድ ሰዎችን ያስቀይማሉ። አንዳንዴ ካለማወቅ ነው የሚተቹት። ለምሳሌ አድርባይ አቅዋምን ገላጭ ሳይሆን ስድብ ይመስላቸዋል። ሆዳም የሚለው ቃልም አሉታዊ ይዘት ያለውና የነቀፌታም ቢሆንም የተስወሰኑ ሰዎችን –ለሆዳቸው ያደሩትን– የሚገልጥ ነው። በትግሉ ጎራ ያለንና በሆዳሞች የተጎዳን ሆዳም ማለት ሲያንሰን ነው–ፕሮፌሰር አሥራት ሆዳም….እንዳሉት ሁሉ። ለባንዳና ቡከን፤ ለከሀዲና ሀገር ሺያጭ ወይም ለዘረኛ ደግሞ ለስለስ ያሉ ሌሎች ቃሎች ፍለጋ መግባት የሚያስፈልገን አይመስለኝም። አቅዋማቸው ከነይዘቱ ሲነገራቸው የሚያፍሩ የሚቀየሙ ካሉ በቃሉ ሳይሆን በራሳቸው አቅዋም ነው ማፈር ያለባቸው። ምግባረ ክፉን በስም መደገፉ ወይም ማሳመሩ የ እኛ ተልዕኮ አይደለም።
ኢ.ዓ.
ይቀጥላል………………………