ከኢያሱ ዓለማየሁ:
ውሸት ሲደጋገም እውነትን ይመስላል።
ጎብልስ (ናዚ)
ይመስላል እንጂ ውሸት ምን ቢደጋገም እውነት አይሆንም።
ጸገየወይን ገ. መ. (ጸጋዬ ደብተራው)
ኢሕአፓ ስሙ ሲወጣለት ዳቦ ያልተቆረሰ ሆኖ መከራ በዛበት ብሎ የሚቀልደው ጸጋዬ ገብረ መድህን (ደብተራው) የብዙ ውሸትና ሀሰት ሰለባ ሆኖ ሕይወቱም በወያኔ እጅ አልፏል። በዚህ ድርጅት ላይ ያልተደጋገመ ክስና ሀሰት የለም ብንል ትክክል ነው። ግን ሀቁ እየዋለ እያደረ መጋለጡ መታወቁ አልቀረም።
ደርግ ያስጨበጣቸውን ሀሰት እስኪያቅለሸልሸን ሲደግሙብን የቆዩ ጥቂቶች አይደሉም። ኢሕአፓ ኤርትራን አስገነጠለ፤ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ደገፈ ወዘተ ሲሉ በዚያው ልክ ደግሞ ድርጅቱ ሀቁን ሲነግራቸው ዓመታት አልፈዋል። ዛሬ ራሳቸው የሻዕቢያ መሪዎችና በቅርቡ መጽሃፍ የጻፉ ምሁሮቻቸው ሳይቀሩ የኤርትራ ድርጅቶችና የኢሕአፓ ጠብ ድርጅቱ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት መሆንና በቀጥታ ነጻነት የሚገባት መሆኑን አልቀበል በማለቱ የተነሳ ነው ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል። ኢሕአፓን ይወዳል ተብሎ የማይታማው ገብሩ አስራትም ቢሆን በመጽሃፉ ኢሕአፓ የነ ሻዕቢያንና የዚያድ ባሬን አቅዋም ባለመቀበሉ ተጠቃ (“በጥርሳችው ገባ”) ብሎ ሲያቀርበው ወያኔ ግን የሻዕቢያንና የሶማሊያን አቅዋም ደግፎ 3ሺ ክላሺን ከሶማሊያ እንደተላከለት ገልጿል። ዛሬም ግን ይህንን አስገነጠለና ወረራ ደገፈ ውሸት የሚደጋግሙት አሉ። ኢሕአፓ ከመመስረቱ በፊት ጀብሃ የተባለው ድርጅት ኤርትራ ነጻ አደርጋታለሁ ብሎ በ1960 ዓ. ም. የተመሰረተ ሲሆን፤ የችግሩ መንሰኤ ከነበረው መንግስት ስህተት ጋር የተገናኘ ሆኖ ሳለ ለፖለቲካ ስልጣን ያልበቃውን ኢሕአፓን አስገነጠለ ብሎ መክሰሱ የወያኔን ርኩስ ሚና ለመደበቅ መሆኑን ብዙዎች አይስቱትም። ደርጎች የፈጸሙትን ጸረ ሕዝብ ሽብርና ወንጀል ማጠየቂያ ለመስጠት ኢሕአፓን በአስገንጣይነትና ወረራ ደጋፊነት ችክ ብሎ ማቅረቡ ያዋጣናል ብለው የተያያዙት ናቸው። ሀቁ ግን ውሎ አድሮ ሊታወቅ ሊረጋገጥ ችሏል። አሁንም የሀሰት ክሱን ለማስተጋባት የሚጥሩ ካሉ አውቆ የደነቆረውን መድፍም አያነቃው ብለናቸው የምናልፈው ነው።
በወያኔ የቀጥታ ወይም የእጅ አዙር ድጋፍ በዓመት ቢያንስ እስከ ሶስት ጸረ ኢሕአፓ መጽሀፍ ነን የሚሉ ለህትመት ይበቃሉ። ዓይነታ ኢሕአፓ ነበርን ብለው ከሚቧርቁትም ውስጥ ለወያኔ ያደሩ እንዳሉ ለእኛ ምስጢር አይደለም። የነሻምበል፤ ሻለቃና ኮለኔሎች ቆሻሻ ብዕር ውጤት የሆኑት ብልግና ቢገባንም የራሳችን ጠማማ እንዲሉ አባል ነበርን የሚሉት ውሸትና መርዝ ግን የባሰና እግዚኦ የሚያሰኝ ሆኗል። በቅርቡ አንዱ እንደሰማሁት በሚል ደረጃ ደርቶና ደራርቶ በጻፈው ውስጥ ለምሳሌ ራሱን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አድርጎ በማቅረብ ውሸቱን ሌላ ደረጃ አድርሶታል። የመጽሃፉ ዋና እንቆቅልሽ ይህ ነጭ ውሸት ነው። ቢያንስ የእኛን በሕይወት መኖር የረሳ ይመስላል። በዚሁ ልክ መስራች ነበርን የሚሉም እንደ አሸን መፍላታቸው አልቀረም። የጸጋዬ፤ የዋለልኝ፤ የተስፋዬ ደበሳይ ቅርብ ወዳጅ ነን ብለው የሚዋሹም በርክተዋል። ለአኔው ለራሴ “ኢያሱን አወቀዋለሁ፣ ተጠንቀቀው!” ያለኝ ግለሰብ በአሜሪካ ይኖራል። የድርጅት ምስረታ ሂደቱ ውስጥ ሚናቸው ተመልማይ የሆነ ግን በምስረታው ጉባኤ የተገኙም አሉ። አንዳንዶች ስለ ኢሕአፓ የሚናገሩት ውሸታቸው ሊታመን ባለመቻሉና ይህንንም ስለሚያውቁ ያሳምንላቸው ይመስል ውሸትን በባሰ ውሸት ያጅባሉ። ይህ ጻፍኩ ባይ ግለሰብም ገለባ ተሳትፎውን (በኢሕአሠ ሕዝብ አደራጅ ክፍል) በውሸት አዳብሮና ራሱን ሊደርስበት ያልቻለውን የአመራር ኮሚቴ አባል አድርጎ ቀርቧል። እግረ መንገዱንም የኔን ኤርትራዊነት በማጋለጥ መልክ አቅርቧል። ከሐማሴንም ሐማሴን ያውም የከርነሽን ተወላጅ ነው ሲሉ የነበሩትን አስታውሳለሁ። ረዳት ፕሮፌሰር ዓለም እሸቴ ታላቅ ወንድሜ ሳሙኤል ደምቢዶሎ ተወለደን ሰምቶ አይ ኢያሱም ኦነግ ሊሆን ይችላል ያለውን አስታውሳለሁ። የእንቆቅልሹ ግለስብ ኢያሱ መልምሎ ወደ ሜዳ ላከኝ ላለው ከዚህ ቀደም ለዚሁ ድርጊቴ ድርጅቱን ይቅርታ ጠይቂያለሁና በዚሁ የማልፈው ጉዳይ ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ወደ ድርጅቱ የመለምልኳቸው ጥቂቶች ሲሆኑ ውሎ አድሮ ሲበላሹም “ሶሪ ኢሕአፓ” በሚል ጥፋቴን አምኛለሁ።
ኤርትራዊነትን በተመለከተ በውልደት ጥፋትና ወንጀል እስካልመጣ ድረስ በኢሕአፓ አያሌ ኢርትራውያን (ማለትም ኢትዮጵያውያን ) ታግለው ተሰውተዋል። ስመ ጥር አርበኞችም እኮ ከኤርትራ የመጡ ነበሩ። አይደለሁም እንጂ፣ ኤርትራዊ ብሆን ኖር እንኳን፤ እዛ ብውለድ ኖሮ እንኳን ልጆች ታዲያ ምን ይጠበስ የሚሉት ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ማንም ግለሰብ የሚገመተው በሚይዘው አቅዋምና በሚያካሂደው ትግል ነው። ገብረ እግዚአብሄር (ጋይም) ላይ በአዲስ አበባ የጠቆመው በውልደቱ አማራ ነው። እነ ደብተራው ላይ የወያኔን ጦር መርቶ ያመጣው ከሀዲም የጸለምት ተወላጅ ነበር። የነገሮች ሂደት በዘር ቆጠራ በጅምላ የሚወሰን አይደለም። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው ብንል ቦታው ነው። ስንቱ የትግራይ ተወላጅ ኢሕአፓ ሆኖ ሲሰዋ ቀሪው ደግሞ ለደርግም ለወያኔም አድሯል። ዛሬ የወያኔ ታማኝ አሽከሮች የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ብቻ አይደሉም። እኔና መሰል ኢሕአፓዎች ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብለን ብቻ የታገልንና የምንታገል እንጂ በተለምዶ አነጋገር ዘር ቆጠራ ውስጥ ያ ጀግና ትውልድ አልገባም። ይህን በሽታ ያመጡት እነሻዕቢያ፤ ወያኔና ኦነግ ናቸው። ኢሕአፓ ሲመሰረትም ከየቦታውና ብሄረሰቡ የመጡ አብዮተኞች ናቸው አባሎቹ መሪዎቹ የነበሩት። በሻዕቢያ በኩል ወደ አሲምባ በሚደረገው ጉዞ ላይ ሕይወታቸው ያለፈው ብንያም አዳነ (ውልደት ትግራይ የአዲስ አበባ ልጅ)፤ መሃመድ ማህፉዝ (ጅማ ኦሮሞ ፤ የአባ ጅፋር ዘመድ፤ ከአሚሪካ ወደ ትግል ሜዳ የመጣ) ምሳሌ ናቸው ለኢትዮጵያዊነት። ዘራብሩክ አበበ “ኤርትራዊ ነውና አናሳልፈውም (ከተዋጋ ለኤርትራ ይዋጋ)” ብሎ ክርችም ያለው ሻዕቢያ ነው። (ጓዱም በሌላ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶና ኢሕአሠን ተቀላቅሎ በወሎ ሲዋጋ ተይዞ በአዲስ አበባ ስየል ተቀብሎ በይፋ ከነ ውብሸት፤ ሙሉጌታ ሱልጣንና ይትባረክ ሕዝቅያስ ጋር በደርግ ተገድሏል)። በወያኔ የተገደለው የመርካቶው ይስሓቅ ደብረ ጽዮን በውልደቱ ኤርትራዊ ነበር። ወያኔን ሲፋለሙ የተሰዉት እነ ጃብርና ገለብ ዳፍላም በውልደት ኤርትራዊ ነበሩ። በወያኔ ተይዘው ተገደሉ የተባሉት እነሐጎስ በዛብህና ተክላይም በውልደታቸው ትግራዊ ናቸው። ኢትዮጵያዊ መቶ በመቶ። ልክ እንደ ዋሲሁን፤ ግርማ ጎልጃ፤ ደረጀ፤ አምበርበርና ሊሎች በውልደታቸው አማራ እንደነበሩት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ። በሮማ ከተማ (ጣሊያን) የሻዕቢያ ፊልም (ያውም የውሸት ጦርነት ያለበት) በይፋ ለህዝብ ሊታይ ቀርቦ እኔና አንድ ሌላ ጓድ (ያውም የአዲ ኢሮብ ተወላጅ) በአማራነት ተፈርጀን ካልወጣችሁ ሲኒማው አይጀምርም መባላችንን አስታውሳለሁ። ዘር ቆጠራ ከመጣ ኢሳያስም ሆነ የቅርብ አማካሪዎቹ ወደ አድዋ መወርወራቸው የሚደመጥ ነው። ግን ሻዕቢያ ናቸው ትላንትም ዛሬም። የእኔ ኤርትራዊነት ሳይሆን ጥያቄው ዋናው ጉዳይ የእኔ አቅዋምና ትግል ይዘት ነው። በዚህ ላይ ማንም እኔን ሆነ ድርጅቴን በ ጸረ ኢትዮጵያነት ሊፈርጅ ቢነሳ ውርደት ለራሱ ይሆናል። ማ ለኢትዮጵያ ታግሎና ተሰውቶ ከኢሕአፓ በላይ?
የራስ ጠማማ ባልኩት መሰመር ስገፋበት ድርጅቱ ላይ ጉዳት ያደረሱና አሁንም ስሙን ለማጥፋትና ትግሉን ለማደናቀፍ ግንባር ቀደም ሆነው የሚራወጡት ቀደም በድርጅቱ ነበርን የሚሉ በተለይም አንጃ ሆነው የሚወገዝ ታሪክ ያላቸው የክህደትም አባወራዎች ናቸው። የድርጅቱን ታሪክ ውስጠ አዋቂ ነን ብለው ይነሱና አወቅን ያሉት ከቅዱስ መጽሃፍ አጣቢዋ የማያልፍ ሆኖ ይገኛል። ልብ ወለድ ሊባል ሲገባው እውነተኛ ታሪክ የሚል ታፔላ ይሰጠዋልና ያው ትችቱ በዚህ ደረጃ ሲመጣ የጠነከረ መሆኑ የግድ ይሆናል። በበኩላችን ለብዙዎቹ መልስም የማንሰጠው በጽሁፋቸው ኢሕአፓ የሚለው ስም እውነት ሲሆን ሌላው ሁሉ ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑም ነው። እነ በረከትና ሕላዌ፤ መለስና ስዩም፤ መሰል ጠላቶች ስለ ኢሕአፓ ሲጽፉ ሀቁን ያቀርባሉ ብለን አንጠብቅም:: ወደ ኢየሱስ ተመለስኩ ባዩ ሳይቀር ቢጽፍ አማትቦ ውሸቱን መልቀቁ የሚጠበቅ ነው። ሌላኛዋ ወጣት ኢሕአፓዎችን አጋልጣ አስገድላ የለየላት አንጃ ሆና ዛሬ መጽሃር ጻፍኩ ብላ የወያኔ ተወዳጅ ጸሐፊ ብትሆን በበኩሌ እምባዛም አልገረምም። ሌሎችም ቢሆኑ ሚናቸውን (በተለይ ሊደብቁት የሚፈልጉትን የፍርሓት፤ የክህደት፤ የሙስና ታሪካቸውን) እናውቃለንና ከወዲሁ መከላከያ ምሽግ ያዘጋጃሉ። እኛ የምናውቀውን ሁሉ ልናጋልጥ ብንነሳ ምድር ቀውጢ ትሆንባቸው ነበር። እኛ ሀቁን አንለፍፍም–ይጎዳል እያልን። እነሱ ሊጎዱ ውሸትን ይፈጥራሉ። ምስጢር መዘክዘክና ማጥቃት የእኛ መስመር ባለመሆኑ ገበናቸውን አንጃ ሆኑ ወይም ከዱን በሚል ሜዳ ላይ አላስጣንባቸውም። ካበዙት ግን ሊቀየር ይችላልና ያኔም በሀቁ ላይ መከራከር የሚቻል ይሆናል። በድርጅት ደረጃ የተነሱብንን የአንጃ ስብስቦች በሞላ የተቃወምናቸው በፖለቲካ አቅዋማቸውና በወሰዱትም አፍራሽ እርምጃ ነው። አያያዛችን የተወሰነው ምን ግብ ሊደርሱ፣ ህግና ደምብን ጥሰው ቡድን ፈጥረው ተንቀሳቀሱ በሚል ነው። የመጀመሪያው አንጃ ከፋሺስቱ ደርግ ጋር እናብር በማለቱ ልዩነቱ ተከሰተ። የብዙሃኑን ውሳኔ ረግጦ አንጃ መስርቶ ጸረ ኢሕአፓ አሉታዊ እንቃስቃሴ በማድረጉና–በተጨባጭም ጉዳት በማድረሱ–በወዳጅ ጎራ ሊካተት ወይም ሊፈረጅ አልቻለም። የሜዳው አንጃም የተለየ ፖለቲካ ባያቀርብም ውስጥ ለውስጥ ቡድን መስርቶ ህጋዊ አመራሩን በሀይል ሊያስወግድ በማሴሩና ህግ በመጣሱ ነው ለፍርድ የቀረበው። የቅርቡ አንጃ ከወያኔ ጫማ ስር እንውደቅ ብሎ በመነሳቱና አባላት አይሆንም ሲሉት በህቡዕ ተደራጅቶ ድርጅቱን ሊቆጣጠር በህገወጥ መንገድ በመጣሩና ከህጋዊ ጉባኤም ፈርጥጦ ወጥቶ የድርጅቱን ስም በመስረቁ ነው ችግሩ የመጣው፡፡ አንጃ ስድብ ሳይሆን አቅዋምና ድርጊትን ገላጭ ነው። በሌሎች ድርጅቶችም የተከሰተ የሽንፈተኛነትና የክህደት ተውሳክ ነው። የሀቅ መረጃ ሳይኖረን በባዶ ክስን እንደማንደረድር መታወቅ ያለበትና መረሳት የሌለበትም ነው።
ድርጅቶች ባይታበዩ ከኢሕአፓ ሰፊ ተመክሮ፤ ከድሉም ከጠቃሚውም ሆነ ከአሉታዊው ብዙ መማርን በቻሉ ነበር። ያለፉ ስህተቶችን ሲደግሙ ታዝበናል። ማን ጠይቆን በሚል ዝምታንም መርጠናል ብዙዉን ጊዜ። ደም የተከፈለበትን ተመክሮ ለቀጣይ የሕዝብ ትግል ጥቅም መዋሉን ኢሕአፓ ሊቃወም የሚችለው አይደለም። በአንጻሩ ግን ኢሕአፓን ጥለውት ከሄዱ ከ30 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ መለስ ብለው ስለማያውቁት ኢሕአፓ ሊናገሩ ቢነሱ አደብ ግዙ ማለታችን የሚጠበቅ ነው ። በስመ ኢሕአፓና በነበርን ፈረስ እነ በረከትም፤ አዲሱም፤ ገነት ዘውዴም፤ ግርማ ብሩም፤ ሕላዌም፤ ሌሎችም እኛም ኢሕአፓ ነን ብለው አብረው ሊተረማመሱ የሚችሉበት መንገድ ከቶም የለም። ለጸረ ሕዝቦች፤ ወያኔዎች፤ ለደርግ ገራፊዎች ወዘተ በነበርን ከለላ ከሀቀኛ የኢሕአፓ ልጆች ጋር የጋራ መድረክ ሊሰጥ የሚነሳ ሂደትና ሙከራም መቃወማችን ሰማዕትንና ድርጅታችንን ማክበር ነው። በሆደ ሰፊነትና ማሰባሰብ በሚል ቀና አስተሳሰብም የተወሰደ እርምጃ ለአንዳንዶቹ የዓመሌን ብተው ይግደለኝ ሆኖባቸው በከፋው ጥፋታቸው ዳግም ሲዘፈቁ ታይተዋል። ድርጅትን መበተን፤ መከፋፈል፤ ለማፍረስ መጣር። መንጋቱ ላይቀር ጎህ ሲቀድ ውሸቱ እርቃኑን መቅረቱ እየታወቀ ዓይንን በጨው አጥቦ ሀሰትን በአደባባይ መለፈፍ ያዋርዳል። የኮልኔል ጎሹና የሟቹን ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ “ጦር” ወሬ ያስታውሷል! ኢሕአፓ አንድ ሆነ ተብሎ የቀረበው የነጭ ውሸት በዚህ ደረጃ የሚጠቀስ ነው ብለን አሳፋሪ ቧልቱን ግን በትችት ሳናከብረው እናልፈዋለን። በውሸት አጃቢነት ደግሞ ኢሕአፓ ሊሰለፍ አይጠበቅም፡፡ ውሸት ማለቱ ማጋለጡን ሁኔታው ካልፈቀደ በዝምታ ማለፉን ይመርጣል።
በኢሕአፓ ላይ የሚዘምቱ–በሽፋን ስም ጻፉ ወይም ከሰሱ–ማንነታቸውን ማወቁ እስካሁን ከባድ አልሆነም። ለሁሉም ድክመና ውድቀት (ለራሳችውም ወኔ ቢስነትና ከርስ አምላኩ መሆን) ኢሕአፓን ይከሳሉ። ድርጅቱ ስንት ደክሞ ለግንባር ምስረታ ያደረገውን ጥረት የሚያፈርሱ ሊሎች ሆነው ሳለ የለም ኢሕአፓ ነው ብለው ይደርቃሉ:: እስቲ እናንተው በናንተው ተደራጁ ብለን ስንተዋቸው፤ ስንርቃቸው ደግሞ እንኳን ሊተባበሩ እርስ በርስ ሲነካካሱና ተፈራቀው ሲወራጩ እያየን ነው። ኢሕአፓ በሚታገል ይቀናል ይላሉ– በፌዝ መልክ ይህ ብዙ ሊጻፍበት ይችላል። ታግሎና ደምቶ ሕዝባችንን ከወያኔ ነጻ የሚያወጣ ተገኝቶ ነው? የምናዝነው ትግል መነገጃ ሆኖ የዋሁ ዜጋን ለፍቶ ካገኛት ብር ሲለዩትና ውሎ አድሮ ኩም ሲያደርጉት ነው። ኢዴፓ ከምስረታው ወያኔ ወያኔ ስለሚሸት ብቻ ሳይሆን በነበረን ውስጣዊ መረጃ መሰረት ተቃውመነዋል–ጸረ ወሎዬም ተብለንበታል። የሌላ ድርጅት መሪም የወያኔ ድህንነት ክፍያ በየወሩ የሚደርሳቸው ቢሆንም ይህን በአደባባይ ለመንገር ሁኔታው ሳይፈቅድ ቆይቷል። ቅንጅት ሆነ አንድነት የሚለው መፍረሳቸውም በተመለክተ ወደ መሪዎቹና ወያኔ ማተኮር ሲገባ ኢሕአፓን ሊከሱ የሚነሱ አሁንም አሉ። በሀገር ቤት ከነበሩ ድርጅቶች ጋር ኢሕአፓ ተብብሮ ሰራ እንጂ አላጠቃቸውም፡፡ አንድነትን በተነ፤ ሰማያዊ ፓርቲ ላይ መፈንቅለ አመራር ሞከረ፤ ዝናብ አደረቀ፤ ምስር አስወደደ፤ ጎርፍ አመጣ፤ ለሲአዬና ለአረብ የቤንዚን ዶላር አደረ፤ ትምክህተኛ አማራ ነው፤ ኤርትራዊ ነው — ጊዜ ቢኖር በሬ ወለደን ጨምረን ብዙ በተቸነው ነበር። ብላሽ ልፈፋ!
ወያኔና የደርግ ርዝራዦች፤ የልደቱ ሎሌዎች (አሁንም ጥቂቶች አሉ መሰል!) የሚያቦኩት ውሸትን ነው። በነገራችን ላይ ኢሕአፓ ይህን ሁሉ ማድረግ ከቻለ፤ ሁሉን ማፍረስ ከቻለ ጠንካራ ድርጅት ነው ማለት ነው። ታዲያ ይህን ማለቱ ያዋጣቸዋል? ድክመትና ውድቀትን ማመን፤ ከውሸት መራቅ ነው ከድርጅቶች የሚጠበቀው። በኢሕአፓ ላይ የራስን ውድቀት ማላከክ የትም አያደርስም ማለት ነው። የአጼው ስርዓት ወደቀ በሚል ወጣቱን፤ ተራማጁንና ኢሕአፓን የሚወነጅሉና የሚጠሉ አሁንም አሉ። ለደርግ አድረውና ቅጥረኛ ሆነው የሰሩ፤ ወንጀሉን ቀለም እየቀቡ ሊያሳምሩ ሲጥሩ የነበሩ፤ የፋሺስቱ ኮለኔል የብዕር ቅጥረኞች፤ ገራፊዎችና ስየል ፈጻሚዎች፤ በባዕድ ሀገሮች ያሉ የቀይ ሽብር ወንጀለኞች ሁሉ የዚሁ ዓይነት ዘመቻ አቀንቃኞችና አሰራጮች ናቸው። ሌላ አንጠብቅም። የአጼው አገዛዝ አስከፊነትን በተመለከተ እንኳን ለ 77ኛው የደም ልደትዎ አደረስዎ ብለን በበተነው በራሪ ጽሁፍም ያኔም ያቀረብነው ነው። አረመኔውን ደርግ መታገላችንም ያኮራናል እንጂ አይቆጨንም። የልደቱን ወያኔነት በጊዜ ያጋለጡ ዶክተር ታየ ወልደ ሰማያትና ኢሕአፓ ጊዜ ራሱ ትክክል እንደነበሩ አረጋግጧል። ዋናው ጥያቄ ግን ይህን ሁሉ ኢሕአፓ ማድረግ ከቻለ የለም ተኗል ማለት ሳይሆን ገዝፏል ማለቱ የሚሻል አይሆንም? አንዲት የኦነግ ደጋፊ ግለሰብ የቅንጅትና ኦነግ ትብብር ለዴሞክራሲ (ኤ ኤፍ ዲ) የሚል ብቅ ብሎ የተነነ ህብረት ሲመጣ ኦነግን 80 በመቶ ኦሮሞ፤ ቅንጅትን ሰማንያ በመቶ አማራ ይደግፋቸዋል ብላ ከነገረችን በኋላ ታዲያ ምንድነው ጭንቀትሽ ስላት እናንተ አልደገፋችሁትምና ታፈርሱታላቸሁ ያለቸው ትዝ ይለኛል። ከብዙሃኑ ሕዝብ በላይ አቅም ካለን ምንድነን ማለት ነው? ቅንጅትንና ሁሉንም ህብረት ያውም አንድ ድምጽ ይዘን ለማደናቀፍ ከቻልን ስለእኛ ችሎታና አቅም ምን ይላል? ሕብረት እንዲመሰረት ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘብ አፍሰን ሳይውል ሳያድር ለማፍረስስ ለምን እንነሳለን? ይህን ከመቀበጣጠር ይልቅ እያንዳንዱ የህብረትና የመቀናጀት ጥረት ምን ጠቀመ ለምንስ ደከመ ፈረሰ ብሎ መመርመር ተገቢና ለቀጣዩም ትግል ትጥቅ የሚሆን ነው። ሌላ ሌላው፤ ክስ ድርደራው ጉንጭ አልፋ ነው — መሰረተ ቢስ ወሬ ወይም ሱዳኖች ከለም ፋዲ የሚሉት ነው።
ኢሕአፓ ትግል ሲጀምር ያነሳቸው የሕዝብ ጥያቄዎች ዛሬም ምላሽ እንዳላገኙ በገሃድ የሚታይ ነው:: ባሰ እንጂ አልተሻሻለም የሕዝብ ሁኔታ። ለነኦባማ የሚታያቸው የኢኮኖሚ ዕድገት ለሕዝብ አልታይ ካለ 24 ዓመታት አልፈዋል። የጤና ጉዳይ የተሻሻለ ባይሆንም ሕዝብ በሞላ አልታወረም። ያለውን አስከፊ ሁኔታ ያያል፤ ያውቃል፤ በስቃይም ይኖረዋል ያለው። ይህን ያልተለወጠ ሁኔታ ለሕዝብና ለሀገር በሚበጅ መልኩ እውን ለማድረግ አሁንም ትግል ያስፈልጋልና ትግሉ ቢቀጥል ድርጅቱ የሚወቀስበት ሳይሆን በቃኝ ብሎ ባለማረፉ ባለመተዉ የሚመሰገንበት ሊሆን በተገባ ማለትም ይቻላል። የሞት ወልፍ ያለበት ማንም የለም። ይህ ቢባልም ግን ድርጅቱ ባለው አቅም ሁሉ ወያኔን ለማውደም–አዎ ለማውደም- በመጣር ላይ ነው። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ደርግ ወደ መጨረሻው እንደሞከረው ሁሉ ወያኔም ኢሕአፓ የለም የሚል የሰጎን ፖለቲካን መከተልን መርጦ እየዳከረ ነው። ድርጅቱ ከሌለ ይህ ሁሉ ጭንቀትና ጫጫታ፤ ስጋትና የስም ማጥፋት ዘመቻ ለምንስ አስፈለገ? በየጊዜው ኢሕአፓ ጠፍቷል፤ ተኗል፤ የለም ብለው መርዶ የሚያረዱን አልጠፉም። ቢሆንማ ኖሮ እኛም አርፈን ነበር ብለን ልንመልስላቸው ይዳዳናል። በትግል ለዓመታት ድርጅትን አቆይቶ ባለ አቅም ትግልን መቀጠል ቀልድና ቀላል የሚመስላቸው መሐይሞች እንዳሉ እናውቃለን። ይባስ ብለውም ትግልን አቅልለው በገቢ ምንጭነት ደረጃ ሊያዩትም የሚከጅሉም አሉ። ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል የድርጅቱን መኖር መቀጠል የሚጠይቅ ነው። የትግሉን ግዳጅ ሌሎች ተቀብለው ትግሉ ተፋፍሞ ወያኔ ቢወገድ የመጀመሪያ ደስተኛ ኢሕአፓ ነው የሚሆነው። እኔ ካልሞትኩ ካልደማሁ የሚል ፉክክር ውስጥ ለመግባት ምንም ፍላጎት የለውምና። ለሀገራችን በቂ መስዋዕትነትን ከፍሏልና። ይህ በዚህ እንዳለ ግን ያለን ድርጅት የለም ብሎ መካዱ ራስን ማታለል ወይም ወያኔ እንዳቀደው ዓለምን ለማደናገር መጣር ነው። ድርጅት ከደከመ ከተጨባጩ ሁኔታ በተጨማሪ የውስጥ ከፋፋዮች የሚጠየቁበት ነውና ይህንን ድክመት ማስወገድ ይገባል። በዚህ ወቅት የአባላትም ሚና ድርጅቱን ለማጠናከር መጣር እንጂ ደከመ ብሎ (ያውም ራሳቸው ጥለው የወጡ ከሆኑ) መራቅና ትግል ማቆም ሊሆን አይችልም አማራጩ። ኢሕአፓ ባይኖርስ ትግል ይቆማል ማለት ነው?
ድርጅት የመሪዎች ወይም የአንድ ሁለት ሰው የግል ንብረት አይደለም። አንድ ጸሃፊ በቅርቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግለሰብን እንጂ ድርጅትን ተከትሎ አያውቅም ብሏል። ስህተት ነው። መሪዎችና የጎበዝ አለቆች፤ ሹመኞችና አጼዎች የነበራቸው ቦታ ባይካድም ሕዝብ ድርጅትን ተከትሎ ታግሏል። ኢሕአፓ ራሱ አንድ ምሳሌ ነው። ልምድና ባህል ወደተባለው መሪ ፍለጋ ቢገፋፋም። ያም ሆነ ይህ ግን ኢሕአፓ በጋራ አመራር የሚያምንና የሰራ ነው። ይህ አቅዋሙ የመጣው ከመርሃ ግብሩ ብቻ ሳይሆን ከተጨባጭ ተመክሮም ነበር። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ተብሎ የተመረጠው ብርሃነ መስቀል ረዳ እንደ ስታሊን ኮሚቴውንም ፓርቲውንም ሊተካ በመነሳቱና የአባላትንም መብት በመድፈሩ አመራሩ ተነጋግሮ ይህን ቦታና ስልጣን ሰርዞ የጋራ አመራር መርሆን አስረግጧል። ለብርሃነ መስቀል አንጃዊ ጉዞ ከስልጣኔ አላግባብ ተነሳሁ የሚለው ይህ ቅሬታው ከፍ ያለ ሚና ነበረው። ወደ አልሆነ አቅጣጫ እየተጓዘ ሳለ ባለሁበት ቦታ እንዲደርሰኝ የላከልኝ የ36 ገጽ ደብዳቤ ከ ዋና ጸሐፊ ቦታው መነሳቱን አማሮ እና በስፋት ማንሳቱን አስታውሳለሁ። በልምዳችን አንድ ግለሰብ ድርጅቱን ንብረቱ ሊያደርግ ሲጥር ወይም ሲዳዳው መርህ ተጻረረ ብለን የምናርመውና የምናስቆመው ነው። አንዳንዶቹ ድርጅቱን ሊጋልቡ ሞክረው ሲከሽፍባቸው ክሳቸውን ደርድረው ከድርጅቱ ይወጡና የሚፈጥሯት አንጃ ሊቀመንበር ለመሆን ሲሮጡም አይተናል። ኢሕአፓን ወደ ግለሰብ ንብረትነት ደረጃ ሊያወርዱ የሚነሱና የሚጥሩ ሁሉ (የእገሌ ኢሕአፓ የሚሉት ከንቱዎች) የአባላትን መብትና ሚና የሚጻረሩና የሚክዱ መሆናቸው አከራካሪ አይደለም። ኢሕአፓ አንድና አንድ ብቻ ሲሆን ንብረትነቱም እየታገሉ ላሉት አባሎቹ በሞላ ነው። ለከዱትና ከዓመታት በፊት ለተለዩት ባለቤትነን አይሰጥም። አንድ መሪ ብቻ ገኖ ወጥቶ ድርጅቱ ለመሆኑ ሌሎች መሪዎች አሉት ተብሎ ውርርድ የሚገባበትን ክስተት ከፈለግን በሀገር ቤትም በውጭም ምሳሌዎች ሞልተዋል። ድርጅቶቹ ጫጩ እንጂ አልጠነከሩም። የጓድ ሊቀመንበርን አይቀሬ ተክለ ሰውነት ጉዳቱን በኢሠፓም ያየነው ነውና ኢሕአፓ በዚህ ዓይነቱ ማጥ ገብቶ መንደፋደፍን አልፈለገም። የኢሕአፓ ስነ ምግባር ትሁትነትን፤ እዩኝ እዩኝ ባይነትንና ልታወቅ ባይነትን መተውን ይጠይቃል። ያሉትም መሪዎቹ ትሁት እንጂ የታበዩ አይደሉም። ሁሉን ከሃሊ ነኝ፤ ምርጣ ነኝ ባዮችን በየጊዜው ሸኝቷል። ይህ ነው ሌላው ሀቅ። ይህን የኢሕአፓ አቅዋም አንቀበልም ብለው ጌታ መሳይ አንድ መሪ የሚሰይሙ ድርጅቶች ይህን ለማድረግ መብታቸ የተጠበቀ ነው። ለእኛ ግን አልበጀንም።
የጋራ አመራር መርህ የዲሞክራሲያዊ አሰራር ዋና አካል ነው። ኢሕአፓ ዴሞክራሲያዊ አልነበረም/አይደለም ብለው የሚከሱት ራሳቸው ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በሕይወት መቆየታቸውና አሁንም የመተቸትን ዕድል ማግኘታቸው አሌ የሚላቸው ምስክር ነው። ሌሎች ድርጅቶች የተቃወማቸውን የት እንዳደረሱ ሲታወስ ኢሕአፓ ግን አሰናበተ እንጂ ሊበትኑት የተነሱትንም ሊያጠፋ አልጣረም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ውይይት አይታቀብም። የቡዝሃኑንን ውሳሌ መቃወም ሲመጣ ነው ችግር የሚከሰተው። ለአንጃነት የበቁት ራሳቸው በአመራር ኮሚቴው ጥቂት የነበሩ ቢሆንም አፊዳቪት ፈርመን ወደ ወያኔ እንለጠፍ ሲሉና ሀሳባችን ለአባላት ይውረድልን ሲሉ ስምንት ገጻቸውን አውርዶላችዋል:: በኢሕአፓ ውሳኔ የሚሰጠው በድምጽና የብዙሃኑን ውሳኔ በማክበርና ተግባራዊ በማድረግ ነው። የብዙሃኑን ውሳኔ ረግጠው እኛ ያልነው ካልሆነ በሚል የሚገተሩትን ግን የሚያስተናግድ ሊሆን አይችልም። በህቡዕ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ሊኖረው የሚችለው ዴሞክራሲ ስፋት ጥበት የሚወሰነው በተጨባጩ ሁኔታ ነው። ሀቁ ሲነገር ኢሕአፓ ውስጥ ዴምክራሲ የሚለው ተለጥጦ መገኘቱ ብዙ ጉዳትን አስከትሏል። በተለይም በተወሰነ ወቅት በሰራዊቱ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት በሚል የተወሰደው ውሳኔ ዴሞክራሲን በተመለከተ ጫን ብሎ ሲገፋ የወታደራዊ ዲሲፕሊንና አሰራር ጉዳይ ላይ አሉታዊ ተጸዕኖ አድርጓል። ለዚህም በበኩሌ ተጠያቂነቴን የምክድ አይደለሁም። ኢሕአፓን በዴሞክራሲ ማፈን መክሰስ ግን ወያኔያዊ ስላቅ ከመሆን አያልፍም።
ስለ ኢሕአፓ ከምስረታው እስከ መራራ ትግሉና ከፍተኛ መስዋዕትነቱ ብዙ ተዋሽቷል። አንድ የደርግ ሻምበል ድርጅቱ የተመሰረተው በ ምዕራብ ጀርመንና አልጄሪያ ድጋፍ ነው ብሏል፡፡ ለሌሎች ደግሞ ድርጅቱን ሻዕቢያ ወይም ኦስማን ሳቤ መሰረቱት ይላሉ። ኢሕአፓ የተመሰረተው በለውጥ ፈላጊ ተራማጅ ኢትዮጵያውያን ነው። ሌላ ወሬ ጉንጭ አልፋ ነው። መስራች ነን የሚሉም ሳይቀሩ የየራሳቸውን ቀበጣጥረዋል። ስለ ኢሕአፓ መናገር የሚችሉት በድርጅቱ ያሉት ናቸው ሲባልም እኛስ ነበርን አይደል ብለው ብስጭት የሚያሰሙ አሉ። የድርጅት ብተና ከተከሰተ ሰላሳ ወዘተ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በአሲምባ ና ከዚያም በኋላ ከተደረጉት ጦርነቶች ይበልጥ ከብተና በኋላ፤ ራሱን መልሶ ባቁቋመው ኢሕአሠ ተካሂዷል። የሰራዊቱም ቁጥር ከመቸውም ጊዜ የበለጠና የዳበረ ነበር። ከሱዳን ድንበር እስከ ጣና፤መተከልና የጎጃም ክፍሎች በሰራዊቱ ቁጥጥር ነበሩ። አምስት ጣሊያኖች የተጠለፉበት ሁኔታ ነበር። ይህ ሁሉ በድርጅትም በሰራዊት ደረጃ ያልነበሩትን የሚመለከት አልነበረም፤ አይደለም። በቅጡ የሚያውቁት አልነበረምና። ከዕለታት አንድ ቀን ኢሕአፓ ነበርን የሚሉ ሊተቹበት የሚችሉበትም አይደለም። ማን ያውራ የነበረን ከተቀበልን እንደሰማነውና እንደምንገምተው ልፈፋ ከንቱ ሆኖ ይገኛል። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበርኩ ዛሬ ግን ኢሕአፓ የለም እንዳለው ጅል፤ ሠራዊቱ ባርካ ገብቶ አብዛኛው በወባ አለቀ እንዳለው ዋሾ፤ እንደ ሀሰት መስካሪዎቹ ሁሉ ከንቱና መሳለቂያ ነው። ደም ገብረን፤ ለፍተን፤ መከራን ችለን ያቆየነውን ድርጅት ጥለውትና ጎድተውትም የሄዱት ባለቤት ነን ብለው ሊሰየሙበት አንፈቅድም። ነበርና ነን የተለያዩ ናቸው። ነበርን ለሚሉ መልሱ ምነዋ ድርጅታችሁን ተዋችሁት የሚል ነው። ነን ለሚሉ ደግሞ ለጽናታችሁ ምስጋና ከሰማዕትም ታገኛላችሁ፤ በርቱ ቀጥሉ ይባላሉ። የነንን ቅርስና ቦታ ነበርን ሊወስድ የሚችል አይደለም። “ሲያምራችሁ ይቅር” ይላል የሀገራችን ሰው!
ኢሕአፓ በድርጅት ደረጃ ታሪኩን ሊጽፍ የጀመረው ጥረት እንዳለ ተነግሯል። ከባድና ሰፊ ጉዳይ ነው። ሀቅንና ሀቅን ብቻ የሚያካትት መሆን ስላለበትም እየተካሄደ ካለው ትግል አንጻር ቀላልም ስራ አይደለም። ለማንኛውም ግን ታሪካችችን የምንጽፈው እኛ በትግሉ የቀጠልነውና ዛሬም ኢሕአፓ ነን የምንለው እንጂ በስብስቴ ዘመን ጥሎን የጠፋው አይደለም። የኢሕአፓ ታሪክ እንቆቅልሽ አይደለም–አባላቱ ያውቁታል፤ መንገደኞች ባያውቁትም። ጠለቅ ወጣ ያሉት ባይገነዘቡትም። ለወያኔ ያደሩ ወይም አንጃዊ አቅዋም የያዙ ብዕራቸውን ጥላቻና ታሪክ ብረዛ ስለሚተፋ የሚጽፉትን ብልሹ ያደርገዋል። የኢሕአፓን ውድቀት የሚመኙት ኢሕአፓ ነን ሊሉ ቢቃጡም ወዲያውኑ ራሳቸውን ያጋልጣሉ። ድርጅቱን በጅምላ ከመ ደርግ ወያኔ ሲያወግዙ፤ የለም ሲሉት፤ ኢዴሞክራሲያዊ ነው ብለው ሲከሱት፤ አፍርሰነው ሌላ ድርጅት እንመስርት ሲሉ፤ ወያኔን ትተው በጸረ ኢሕአፓነት ሲሰማሩና በድርጅቱ ላይ ሀሰትን ሲያሰራጩ ጥላቻቸውንና ማንነታቸውን ግልጽ ያደርጋሉ። ወደዱም ጠሉም። እንደ ደርግ ሹመት ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ራስን አምባሳደር ወይም ነን ማለቱ በኢሕአፓ አይሰራም። ማነህ ባለሳምንት ሲባል እኔ ብሎ መቅረብን ጠያቂ ነው። ያኔ በዘውዲቱ ነበርኩ አያዋጣም። ዛሬም አለሁን ይጠይቃል። በአሁኑ ጊዜ ግርግር ወያኔ የዘወራቸው/የሞላቸው ሁለት ግለሰቦች ታሪክ እንጻፍ ብለው ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ላይ ናቸው። የሁለቱም ታሪክ ምስጢር አይደለም። አስፈላጊም ሲሆን በዝርዝር ይጋለጡበታል። በረከት ጽፎላቸው አሳትሙ እንዳይልም ታሟል/ሞቷል ዜናው አለ። ለማንኛውም ድርጅቱን እናውቃለን ብለው የሚጽፉ ሐሳዊ መሲሆችን መጠበቁ አይከፋም፡፡ ውጤታቸው ግን ገለባ፤ ኢምንትና ከንቱ መሆኑ አያጠራጥርም።
እንጻፍ ካልንማ የምንጽፈው ሀቁን ነው። ሀቁ በእጃችን አለና ሀቁን የሚፈሩ መጥፋታችንን ይመኛሉ። ለደርግም ለወያኔም ለአሳፋሪ አንጃም አንተኛላቸውም። ሽማግሌዎች ከድርጅት አመራር ይወገዱ ብለው የሚጮሁት ለውጥን ፈልገው ሳይሆን ገበናቸውን የሚያውቁ ግለሰቦችን ጥግ ለማስያዝ ነው። ይህን ምክር ለእኛ ሁሉ ታላቅ ለሆኑትና ሚናቸውም ከተበላሸ ዓመታት ላለፉት አያቀርቡም። ኢላማቸው ኢሕአፓ ነው። የኢሕአፓን አመራር መራጭ ና ሰያሚ የኢሕአፓ አባላት ብቻ ናቸው፡፡ ማንም ሌላ ሀይል ይህ መብት የለውም። የተወሰኑ ግለሰቦችን በጫና ጫጫታ ብናስወግድ የአፍራሽ ዘመቻችን ይሳካል ብለው የሚያስቡ በቅዠት ላይ ናቸው። የኢሕአፓ ምሰሶ አባላቱ ናቸውና። እገሌዎች ከአመራር ወጡ አልወጡ ኢሕአፓ በያዘው መስመር ቀጣይ ነው፡፡ የአንድ ሁለቶች ወይም የአመራሩ መሳሪያ አይደለምና ነው፡፡ እኔ ከድርጅቱ የአመራር አባልነት ለ 13 ዓመታት ወጥቼ ቆይቻለሁ–ድርጅቱ ስራውን በሚገባ ቀጠለ እንጂ ለስኮንድም አልተንገዳገደም። ለድርጅቱ ቁልፍና ተኪ አልባ ግለሰቦች ነን ብለው የቃዡትና ወደ አንጃዊ ስምሪት የገቡት ያፈሩበት ክስተት በየጊዜው ተጋፍጧቸዋል እንጂ ሌላ አለተከሰተም።
ቂም የሚጠበቅ ነው። ጓዶቻችንን በሺዎች ደረጃ በፈጀው ደርግ ላይ ቂም ሲያንስ ነው። ሀገርና ወገንን በጎዳው ወያኔ ላይ ቂም ሲያንስ ነው። ቂም የትግል ቤንዚን ሊሆን የሚችል ነው። በደሉን የሚያውቀው የተበደለው ነው–ሊተርፍ ከቻለ። ኃይሌ፤ መንጌ፤ ወዩ መሌ የሚሉት ሰቆቃችንን የሚረዱ አይደሉም:: ከታሪክ አንጻር ውድቆች ናቸው፤ ማፈሪያዎች፡፡ ይህን የምለው መነገር ያለበት ሲሰማ ቢያናድድም መነገሩ ይጠቅማል በሚል ነው። ወደ ወያኔ መለስ ቀለስ እያሉና እየተሞዳሞዱ ገልበጥ ብለው ጸረ ወያኔ ለመምሰል እየቃጡ በኢሕአፓ ላይ የሚዘምቱትን እናውቃቸዋለን። ሁሉም ግን ሊነገር አይችልም። ድርጅት ስራው ይፋንም ምስጢራዊንም ያቀፈ ነው። ሁሉም በይፋ የሚነገር አለመሆኑንም መገንዘብ ተገቢ ነው። ከቀደም ተመክሮ ራሱ ምን መደረግ አለበትን፤ ስለ ጥንቃቄ፤ ስለ ሙያተኛ አሰራር ሰፊ ትምህርትን እንቅሰም። መጠየቅም መፈራት የለበትም። ኢሕአፓ ጉራ ሳይሆን የተመክሮ ባንክ ነው። ካፒታሊስት ስላልሆነም በነጻ መበደርም ይቻላል፤ ስህተትን ላለመድገም።
እየነገርናቸው ጠዋትና ማታ
ምክራችንን ሁሉ አድርገውት ዋዛ
ተጠበሱ አሉ በተራ በተራ።
እንዳይባልብን በጋራ እንጣር ።
ጸረ ወያኔው ትግል ይፋፋም!
ይቀጥላል……………….