ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ አልቀነሰም ተባለ – የወያኔ ጦር ከሶማሊያ የወጣው ሕዝባዊ አመጹን ለማፈን አይደለም በማለት የወያኔ መኮንኖች እያስተባበሉ ነው – የአለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፕሬዚዳንት አፍሪካ በድህነት በዓለም ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች አሉ።
ባለፉት ሁለት ወራት የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው ክፍያው ብዙም አለመቀነሱ በርካታ ዜጎችን ያስቆጣ መሆኑ ተነገረ። ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተዳከሙት የንግድም ሆነ የልማት ሥራዎች መጠነ ሰፊ የሆነ የገቢ መቀነስ ማስከተላቸው በየጊዘዜው የተዘገበ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም የወያኔ አገዛዝ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቀደም ብሎ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ክፍያ ያስከፈለው የደረሰበትን ኪሳራ ለመሸፈን ነው ተብሏል። በተያያዘ ዜናም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በአንዳንድ ቦታዎች የመንግሥት ሠራተኞች እና አስተማሪዎች ደሞዝ በጊዜው እንዳልተከፈላቸው ታውቋል። ላለፉት ሁለት ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው ዜጎች በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከፍተኛ ችግር መድረሱን በመግለጽ በምሬት ይናገራሉ።
የወያኔ አገዛዝ ሶማሊያ ውስጥ ያሰማራውን ጦር ቀንሶ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው ሕዝባዊ አመጹን ለማፈን አይደለም በማለት አንዳንድ የወያኔ የጦር አለቆች እርምጃውን እያስተባበሉ ይገኛሉ። የወያኔ ጦር ሶማሊያን ለቅቆ የወጣባቸው በርካታ አካባቢዎች በአልሸባብ ታጣቂዎች መያዛቸው የታወቀ ሆኖ ሳለ በሶማሊያ የሚገኝ አንድ ከፍተኛ የጦር አለቃ ሶማሊያ ውስጥ ያለው የወያኔ ጦር የአልሸባብን ርዝራዦች ለመቆጣጠር በቂ ነው ብሎ መናገሩ ብዙዎችን አስገርሟል። ብዛት ያለው የወያኔ ጦር ከሶማሊያ ወደ አገሩ የተመለሰው አስፈላጊ ባለመሆኑ እንጅ ሕዝባዊ አመጹን ለማፈን አይደለም በማለት ይኸው የወያኔ መኮንን ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ያቋቋሙት የተማሪ ማህበር፣ በዚህ ዓመት ሊደረግ የታሰበው የማህበሩ የሥራ አመራር ምርጫ በአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት እንደማይካሄድ ገልጿል። የወያኔ አገዛዝ የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስብሰባና ቅስቀሳ ለማድረግ የሚከለክል መሆኑን በመጠቆም ተማሪዎች ከምርጫው እንቅስቃሴ ራሳቸውን ቆጥበው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ መመሪያ ተሰጥቷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን ማህበር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚማሩ 3000 ተማሪዎችን በአባልነት ይዟል።
አይፋድ (IFAD)ተብሎ የሚጠራው የአለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት ዶክተር ካንዮ፣ አፍሪካ በችግርና በድህነት ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች በማለት ተናገሩ። ምንም እንኳ የአፍሪካ አህጉር በማዕድን በነዳጅ እና በጋዝ ሃብታም ቢሆንም በዓለም ላይ ደሃ ከተባሉ 25 አገሮች መካከል 23ኡ አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው 389 ሚሊዮን የሚሆነው የአፍሪካ ሕዝብ በዝቅተኛ ድህነት ደረጃ የሚኖር መሆኑን አስረድተዋል። የአፍሪካ ድህነትም ከ1982 ወዲህ እየተባበሰ መሄዱን ዘርዝረዋል። ከሳህራ በታች ያሉ አገሮች 25 ከመቶ የሆነውን የዓለምን ለም ቦታ ይዘው ከዓለም 10 ከመቶ የሚሆን ምርት ብቻ የሚያመርቱበት ምክንያት አስተዋይ መሪዎች ባለመኖራቸውና በሥልጣን ላይ ያሉትም በሙስና ስለተዘፈቁ ነው ብለዋል።