የፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ፍካሬ ዜና – የውጪ ምንዛሪ እጥረት ወያኔን እግር ተወርች እየያዘው መሆኑ ተሰማ – የዓባይ ግድብ ወያኔን ብርክ እያስያዘው መሆኑ ተነገረ – ከወደብ ያልተነሳ ማዳበሪያ ከጥቅም ውጪ መሆኑ አነጋጋሪ ነው ተባለ – ከወደብ ያልተነሳ ማዳበሪያ ከጥቅም ውጪ መሆኑ አነጋጋሪ ነው – ደቡብ ኦሞ በተከሰተ ግጭት በሰው ህይወት ላይ አደጋ መድረሱ ተነገረ – ወያኔ በሐረርጌና በያቤሎ የሕዝብ ደምን ማፋሰሱ እያነጋገረ ነው።
የውጪ ምንዛሪ እጥረት ወያኔን እግር ተወርች እየያዘው መሆኑ ተሰማ
ወያኔ የብር የውጪ ገንዘብ የመመንዘር አቅምን ከሰበረ ወዲህ ያንሰራራል ተብሎ የታሰበው የወጪና የገቢ ንግዶች ይብሱን እየተሽመደመዱ መሆናቸው እየተስተዋለ ነው ተባለ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንኮታኮተ በመሄድ ላይ በመሆኑ የዋጋ ግሽበት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጨመረ መሆኑ ተነገረ፡፡ በዚህ ሳቢያ ወያኔ ከውጪ ለማስገባት የተዋዋላቸውን እያፈረሰ መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡ በቅርቡ ወያኔ አብዝቶ እየለፈለፈለት ያለው ከግማሽ በላይ የቻይና ሀብት መሆኑ የሚታወቀው የብረታ ብረት ኢንጀነሪንግ ለከፍተኛ መኮንኖች ለሚሠራው የአፓርትመንት ህንጻ ለመገንቢያ የወጣው የፌሮ ብረት ግዢ ጨረታ ዋጋው በመጨመሩና የውጪ ምንዛሪ ገንዘብ ባለመኖሩ ጨረታው ሙሉ በሙሉ መሰረዙ ታውቋል፡፡ ይህ የብረት ግዢ ሆን ተብሎ ለዘረፋ እንዲያመች አገር ውስጥ የሚገኙ ብረት አምራቾችንና የብረት ነጋዴዎችን ያገለለ ነበር ተብሏል፡፡
የዓባይ ግድብ ወያኔን ብርክ እያስያዘው መሆኑ ተነገረ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግብጽ ባለስልጣናት እያሰሙት ያለው ፉከራ የወያኔ ቁንጮዎችን እያረደ መሆኑን ሾልከው ከሚወጡ መረጃዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡ ወያኔ ግድብ እያለ የፖለቲካ ቁማር ሲቆምር ግብፅ የባህረ-ሰላጤው ሀገራትን በአጠቃላይ ከጎኗ ማሰለፍ ብቻ ሳይሆን የግድቡ ጉዳይ የባህረ-ሰላጤው ሀገራት ጉዳይ እንዲሆን በስፋና በጥልቀት መሥራቷ የሚታወቅ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ በተረፈም አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራትን በተለይ ደግሞ እስራኤልን ግድቡን አስመልክታ ሰፊ ዘመቻ በመስራት አመለካከታቸው ከግብፅ አንጻር እንዲሆን ማድረጓ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡
ወያኔ የብዙሀን መገናኛዎችን ሊለጉም መሆኑ ታወቀ
ወያኔ የመገናኛ ብዙሀንን የሬድዮ፣ የጋዜጣና የመጽሔት፣ የቴሌቪዥን፣ ወዘተ. በአጠቃላይ በቁጥጥሩ ስር በማድረግ የሕዝብን የማወቅና የመረዳት መብት እየረገጠ በመሆኑ የተለያዩ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ወያኔን እያወገዙና እያጋለጡ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ በነጻ ጋዜጣና መጽሄት ማሳተም ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ጋዜጠኞች እየታፈኑ ታስረዋል፤ በወያኔ ነፈሰ-ገዳዮች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ በወያኔ ተይዘው ከመሰቃየት በሚል በርካታ ጋዜጠኞች ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየታተሙ ካሉት ጋዜጦችና መጽሄቶች ውስጥ ዘጠና ዘጠኝ በመቶው አፍቃሪ ወያኔና ወያኔ የእጅ ሥራዎች መሆናቸውን ውስጥ አወቆች ያስረዳሉ፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት ወያኔ ይህን ጥርዥ ብርዥ የሚለውን የነፃ የብዙሀን መገናኛ አውታሮችን በአጠቃላይ ጥርቅም አድርጎ ለመዝጋት በህግ ሊደነግግ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከወደብ ያልተነሳ ማዳበሪያ ከጥቅም ውጪ መሆኑ አነጋጋሪ ነው ተባለ
አንድ መቶ ዘጠና ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ ከሦስት አመታት በላይ በመቆየቱ ከጥቅም ውጪ መሆኑና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ኪሳራ ማድረሱ ታወቀ፡፡ የዚህ ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ የመቆየቱ ሰበቡ፣ ማዳበሪያውን የሚያቀርበው ያራ የተባለው የኖርዌይ ኩባንያ ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነና የመሬቱን የለምነት የተፈጥሮ አቅም የሚያዳክም በመሆኑ ትክክኛውን ማዳበሪያ እንዲያቀርብ ክርክር አየተደረገ በመሆኑ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ያራ የተባለው ድርጅት ከወያኔ ጋር ባለው ሽርክና የወያኔ ቁንጮዎች የሚዘርፉትን ገንዘብ ወደ ድብቅ ባንክ የማዘዋወር የውንብድና ተግባር ይፈጽማል የሚል ግምታቸውን የሚቸሩ በርካቶች መሆናው ታውቋል፡፡ይህን ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደብ ለማንሰት ለወደቡ ኪራይና የቅጣት ክፍያው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ገንዘብ የሚከፈለው በአሜሪካ ዶላር ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለመክፈል የሚታሰብ አይደለም ተብሏል፡፡ የሀገር ገንዘብ በየጊዜው በእንዲህ ባለው ሁኔታ እየተዘረፈና እየወደመ ለመሆኑ የታወቀ ነውም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
አፋር የተገደለው ጀርመናዊ አገዳደል እያነጋገረ ነው
ባሳለፍነው ሳምንት አንድ ጀርመናዊ አፋር ኤርት አሌ የተባለ የእሳተ-ገሞራ ሀይቅን እየጎበኙ በነበሩበት በጥይት ተመተው መገደላቸው በስፋት ሲነገር መሰንበቱ የሚታወስ ነው፡፡ እኚህ ሰው ከጀርመን አአለን ከተባለ አካባቢ የመጡ ሲሆን በሙያቸው የአፍንጫ፣ የጆሮና የጉሮሮ የህክምና ዶኮተር ሲሆኑ ዋልተር ሮፕርት የተባሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ወያኔ እንደ ተለመደው የድርጊቱ ፈጻሚ ሻዕቢያ ነው ሲል ጣቱን ቢቀስርም የሚያምነው ግን እንደሌለ እየታየ ነው ተብሏል፡፡ በአፋር፣ በሰመራ ወያኔ በየአመቱ የሚያካሄደው አፍዝ አደንግዝ የጭፈራ በዐል ላይ ሆን ተብሎ ጥቁጥ ድባብ ለመጣል የተደረገ መሆኑን የሚያስረዱ እንደሚሉት ድርጊቱ የተፈጸመው በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ወያኔን በሚቃወሙ ኃሎች የተፈጸመ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ የጀርመን መንግሰት ከአሁን ቀደም በደቡብ ኦሞ ማጎ ብሔራዊ ደን ውስጥ ዲርክ ዶናት የተባሉ የቅሪተ-አካል ተመራማሪ ደብዛቸው በመጥፋቱ ለማፈላለግ ሰው አልባ-ጀቶችንና ሁለት መቶ የጀርመን ወታደሮችን በማሰማራ ፍለጋውን እንደሚጀምር መወሰኑ የሚታወቅ ነው ተብሏል፡፡ ይህ በዚህ ባሳፍነው ሳምንት የተከሰተው ድርጊት ጀርመን ከወያኔ ጋር ያላትን ሽርክና ቆም ብላ እንትመረምር ይገፋፋታል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ደቡብ ኦሞ በተከሰተ ግጭት በሰው ህይወት ላይ አደጋ መድረሱ ተነገረ
ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ኦሞ በሙርሲ ቦዲ አስራ ሁለት ሰዎች በድንገት በተከሰተ ሁከት መገደላቸው ታወቀ፡፡ ድንገቱ ሊከሰት የቻለው አንድ የቦዲ ተወላጅ በመኪና ተገጭቶ በመገደሉ ሳቢያ በአካባቢው በሚተላለፉ መኪናዎች ላይ የአካባቢው ኗሪዎች በከፈቱት ተኩስ የአስራ ሁለት ሾፌሮች መገደላቸው ታውቋል፡፡ ሙርሲ ቦዲዎች በልማት ስም የኦሞ ወንዝ ተፋሰስ በወያኔ እንዲወረር በመደረጉ በየጊዜው የተለያዩ የአመጽ ድርጊቶችን በመፈጸም በወያኔ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን ቁርሿቸውን ለመወጣት አጋጣሚውን መጠቀማቸው እንደሆነ አካባቢውን የሚያውቁ ያስረዳሉ፡፡
ወያኔ በሐረርጌና በያቤሎ የሕዝብ ደምን ማፋሰሱ እያነጋገረ ነው
ሰሞኑን ወያኔ ልዩ ፖሊስ ብሎ ያደራጃቸውን በባቢሌ፣ በያቤሎና በተለያዩ አካባቢዎች በማዝመት በረካቶች ተገድለዋል፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ እየታፈኑ ተወስደዋል፤ በረካቶች እየተፈናቀሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ከወራት በፊት በምስራቅ ሐረርጌ ከስድስት መቶ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይኸው ድርጊት ሀርጌሳ ድረስ ዘልቆ የኦጋዴን ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን እየተደበደቡ ቤት ንብረታውን ጥለው እንዲወጡ መደረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡በአሁኑ ወቅትም እንደዚህ ቀደሙ ግድያ እየፈጸመ ያለው ወያኔ ያደራጀው ልዩ ፖሊስ የተባለው ኃይል መሆኑ የታወቀ ሲሆን የድርጊቱ ሰለባዎች ደግሞ ኦሮሞዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይህ ድርጊትን ወያኔ ሆን ብሎ እድሜ ለመግዛት የሚያደርገው እንደሆነ በርካቶች ደጋመው አበክረው ያስረዳሉ፡፡