ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በባህር ዳር አካባቢ ትጥቅ ለማስፈታት የተሞከረው ዘመቻ ከሸፈ – በተለያዩ ቦታዎች በጅምላ እና በነጠላ የማሰሩ ተግባር በሰፊው ቀጥሏል – የቅሊንጦን እስር ቤት በእሳት አያይዛችኋል የተባሉ 38 እስረኞች ተከሰሱ – የውጭ ዜጎች የሆኑ የትናንሽ አውሮፕላን አብራሪዎች በወያኔ ባለስልጣኖች ታገቱ – የወያኔና የኬኒያ ባለስልጣኖች ስለድንበር ጸጥታ ለመነጋገር ተሰበሰቡ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በባህር ዳር ቀበሌ 14 እና አካባቢው ትጥቅ ለማስፈታት የተካሄደው ወረራ ሕዝቡ በእቢተኝነት እንደተቋቋመው ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡ የአማራ ፖሊስና ልዩ ኃይል በጋራ ባካሄዱት ወረራ ሕዝቡ ቤቱን ላለማስፈተሸ መንገድ ዘግቶ መቋቋም ማድረጉንና መሳሪያ ያላቸውም ቢሆኑ ህጋዊ ፍቃድ የተሰጣቸውና እየገበሩበት እንደሚገኝ በማስረዳት ወራሪውን የወያኔ ኃይል መመለስ እንደቻሉ ታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢው የወያኔ ደህንነቶች በየምሽቱ በተቃዋሚነት የሚጠረጥሯቸው የከተማዋ ኗሪዎች ቤቶችን እየፈተሹና ቤተሰቦቻቸውን እያንገላቱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከፍተሻ ጋር በተያያዘ ጥቂት ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡ እንዲህ ያለው የቤት ፍተሻ ዝርዝሩ ባይደርሰንም በጎንደርና በአካባቢው በሚገኙ ከተሞችም መካሄዱን ተረድተናል፡፡ በሁሉም ስፍራዎች የተፈተሹ ቤቶች ቀድሞ የኢሕአፓ ሠራዊት- የኢሕአሠ አባላት የነበሩ እንደሚበዙባቸው ተረጋግጧል፡፡
በምዕራብ ወለጋ በነጆ የተማሪዎች አመጽ ተቀስቅሶ በርካታ ተማሪዎች የታሰሩ መሆናችውን ከቦታው የደረሰን ዜና ይገልጻል። ክቅርብ ቀናት ወዲህ በተለያዩ ከተሞች በዩኒቨርስቲና በሌሎች ተቋሞች የሚማሩ ተማሪዎች የታሰሩ ጓደኞቻቸው ባስቸኳይ እንዲፈቱና የወያኔ አስከፊ አገዛዝ እንዲያበቃ በመጠየቅ የአመጽ እንቅስቃሴ በማደረግ ላይ ሲሆኑ በተለያዩ ቦታዎችም ተስፋፍቶ ይቀጥላል ተብሎ ተገምቷል። በሌላ በኩል የወያኔ አገዛዝ በጅምላም ሆነ በተናጠል የሚያካሄደውን እስራት በስፋት መቀጠሉ ታውቋል። የሰማያዊ ፓርቲ የምክር አባል የነበረችው ወይንሸት ሞላ በጸጥታ ኃይሎች ተይዛ የታሰርች መሆኑ ሲታወቅ በጎንደርም በተለያዩ ቀበሌዎች ያሉ የከተማው ነዋሪዎችና የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህራን ባለፉት ጥቂት ቀናት ተይዘው ታስረዋል። የከረዩ አባ ገዳም የሆኑትም ተይዘው ወደ አልታወቀ ቦታ ተወስደዋል የሚል ዜና አለ።
በቅሊንጦ እስር ቤት እሳት አያይዛችኋል የተባሉ 38 እስረኞች ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑ ተነግሯል። በክሳቸው ውስጥ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከል አመጽ ማስነሳት የአሸባሪ ድርጅቶች አባሎች በመሆን ሌሎች ሰዎችን መመልመሉ የሚሉት የተጠቀሱ ሲሆን እሳቱ ከመነሳቱ በፊትም ያልተግባቧቸውን ሰዎች ይደበድቡ እንደነበር ተጠቅሷል። በቅሊንጦ የተካሄደው የእሳት ቃጠሎ የወያኔ አገዛዝ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲካሄድ የነበረው ሕዝባዊ አመጽ መልቁን እንዲቀይር ያደረገው እኩይ ተግባር መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከእሳቱ በፊት የተኩስ ድምጽ እንደተሰማ የአይን እማኖኞች ከመመስከራቸውም በላይ በእሳት ቃጥሎ ምክንያት ከሞቱት ዜጎች መካከል የተወሰኑት በጥይት ተመተው እንደሞቱ የአስከሬናቸው ምርመራ አረጋግጧል።
የመጀሪያውን የአውሮፕላን በረራ ለማስታወስ ቪንቴጅ ኤር ራሌይ በሚል ስም የተወሰኑ ፈቃደኛ የሆኑ አብራሪዎች በትናንሽ አውሮፕላኖች በመሆን በአምስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከግሪክ እስከ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ እቅድ አውጥተው ጉዟቸውን መጀመራቸው ይታወቃል። ህዳር 3 ቀን 2009 ቀን ከክሬት ግሪስ በመነሳት በግብጽ በሱዳን ያለውን ጉዟቸውን ጨርሰው የተወሰኑት ጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያ ሲያርፉ በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች መታገታቸው ተነግሯል። አብራሪዎቹ ቀደም ብለው ፈቃድ ማግኘታቸውና ሆቴል መያዛቸው የሚታወቅ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት የወያኔ አገዛዝ ሰዎቹ ወደ ያዙት ሆቴል እንዳይሄዱ አግዶ በአውሮፕላን ጣቢያው ያሳረፋቸው መሆኑ ታውቋል። የሞባይል ስልካቸው ስለተወሰደባቸው ከስዎቹ ጋር ግንኙነት ማድረግ ያልተቻለ መሆኑም ተገልጿል።
ሰሞኑን የወያኔ የኬኒያ ባለስልጣኖች በድንበር ዙሪያ ሲመክሩ የነበረ ሲሆን በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የድንበር ጸጥታ ሁኔታ ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል። ከዚህ በፊት የነበረው ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ችግር የነበረበት መሆኑ ከመገለጹ በላይ ችግሮቹ ተወግደው ስምምነቶቹ በትክክል በስራ ላይ ሊያውሉ የሚችሉ ሀሳቦች ተጠቁመዋል ተብሏል። የአሁኑም ስምምነት ምን ያህል ስራ ላይ እንደሚውል ወደፊት ይታያል ተብሏል።
ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮን ያዳምጡ: