ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥር 18 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በባህር ዳር በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች እና በሕዝብ ወገኖች መካከል የተኩስ ልውውጥ ተደረገ – ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት ኢትዮጵያን ከፍተኛ ሙስና ከሚካሄድባቸው አገሮች መካከል መደባት – በኩዌት የሞት ቅጣት ከተፈጸባቸው መካከል አንደኛዋ ኢትዮጵያዊት መሆኗ ታወቀ – ሼኩን በመግደልና እስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ሴራ በመጠንሰስ በሚል የሀሰት ክስ የተወነጀሉ ዜጎች የእስራት ቅጣት ተፈረደባቸው – በወያኔ አገዛዝ ሶማሌያ ውስጥ የተሰማሩ ወታደሮች ባካሄዱት ግድያ ላይ የአፍሪካ ህብረት ያደረገውን ምርመራ ይፋ እንዲያደርግ ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ – የአልሸባብ አባላት የአሜሪካ የስለላ ድርጅት አባሎች ናቸው ያሏችውን ሶስት ግለስቦች ገደሉ – የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ላይ ያሉት የኬኒያ ዶክተሮችና ነርሶች እስከ አምስት ቀን ድረስ እንዲመለሱ ፍርድ ቤት አዘዘ።
ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 15 ማዘጋጃ ቤት አካባቢ ማንነታቸው ባልታወቀ የሕዝብ ወገኖችና በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ታውቋል። ከወያኔ በኩል ምን ያህል እንደሞተና እንደቆሰለ ባይታወቅም የህዝቡ ወገን በኩል ሁለት ሰዎች መጎዳታቸው ይነገራል። በአካባቢው የጸጥታ ውጥረት የፈጠረ ቢሆንም ብሶት ያለበትን ሕዝብ ተስፋ ከፍ አድርጎታል ተብሏል። ዝርዝሩን እንደደረሰን እናሰማለን።
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው አመታዊ ዘገባ በፈረንጆቹ 2016 ዓ.ም. በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ሙስና ከተካሄደባችው አገሮች ኢትዮጵያ አንዷ መሆኑን ዘግቧል። ጥናት ከተካሄደባችው 176 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ 108ኛ ሆና ስትመደብ ዴንማርክ፤ ኒውዚላንድ፤ ፊንላንድ፤ ስዊድንና ሲወዘርላንድ የሙስናው ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ከሚታይባቸው አገሮች መካከል በመጀመሪያው ተርታ የተመደቡ ናቸው። በኢትዮጵያውስጥ ሙስና በጣም ተስፋፍቶ የሚገኝ መሆኑን አገዛዙ ራሱ ያመነው ሲሆን ጥናቱ የወያኔ ቁንጮ አባላት በተለያየ ስልትና በድብቅ በየጊዜው ወደ ውጭ የሚያወጡትን የአገር ሀብት ቢያካትት ኑሮ ኢትዮጵያ ከመጨረሻዎቹ አገሮች መካከል ልትመደብ ትችል ነበር ተብሏል።
በዛሬው ቀን በኩዌት የሞት ቅጣት ከተፈጸባቸው ግልሰቦች መካከል አንደኛዋ ኢትዮጵያዊት መሆኗ ታውቋል። አማከል በሚል ስም የተጠቀሰችው ኢትዮጵያዊት በሞት የተቀጣችው በ2000 ዓ.ም. በአሰሪዋ ላይ የግድያ ወንጀል ፈጽማለች በሚል ክስ ነው። በወያኔ ባለስልጣኞች አሻሽጭነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ በባርነት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎች ከፍተኛ በደል የሚደርስባቸው መሆኑ በየገዜው የተዘገበ ሲሆን ከሚደርስባቸው ግፍና ስቃይ መብዛት የተነሳ አንዳንዶቹ በደም ፍላት ርምጃዎች ሲወስዱ መቆየታቸውም የሚታወቅ ነው።
ሼክ ኑሩ ይማምን በመግደልና፤ የእስላማዊ መንግስት ለማቋቋም ሙከራ በማድረግ በሚል ክስ ተወንጅለው የነበሩ 13 የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከ 6 እስከ 16 ዓመት በሚድርስ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት የወሰነባቸው መሆኑ ታውቋል። ግለሰቦቹ የሀሰት ክስ እንደተመሰረተባቸው በርካታ ወገኖች ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው። በተያያዘ ዜና የጋምቤላ መሬት ለባዕድ ከበርቴዎች መሸጡን በመቃወም የሚታወቁትና በሽብረተኛነት ክስ ተወንጅለው በእስር ላይ የሚገኙት አሞት አግዋ ጥር 10 ቀን 2009 ዓም. የወያኔው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ50 ሺ ብር ዋስትና ከእስር ተፈተው ጉዳያቸውን እንዲከራከሩ ቢወስንም የቅሊንጦ እስር ቤት እስካሁን ያልፈታቸው መሆኑ ታውቋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው የሰብአዊ መብት ተንከባካቢ ድርጅት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር የወያኔ አገዛዝ በሱማሊያ ያሰማራቸው ወታደሮች 14 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ሲያካሄደው የነበረውን የማጣራት ምርመራ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቋል። ባለፈው ዓመት ሐምሌ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በሱማሊያ ከባይደዋ ከተማ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዋርድንሌ በሚባለው መንደር ወታደሮቹ ምንም ዓይነት የተኩስ ጥቃት ሳይደርስባቸው በየቤታቸው የነበሩ 14 ነዋሪዎችን የገደሉ መሆናቸውንንና ብዛት ያላቸውን ማቁሰላቸውን የአይን እማኞች የመሰከሩ መሆናቸው ይታወቃል። ይህን መሰረት በማደረግ በሱማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ወዲያውኑ የማጣራት ሂደት መጀመሩ የሚታወቅ ቢሆንም ውጤቱን ግን እስካሁን ይፋ ሳያደርግ ቆይቷል።