ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 18, 2009 ዓ.ም.) – የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በንግድ ድርጅቶች ላይ ችግር እየፈጠረ ነው ተባለ፤ ስራቸውን ወደ ኬኒያ አሻገሩ – በደቡብ ወሎ በአንድ ትምህርት ቤት የፈነዳ የእጅ ቦምብ ጉዳት አደረሰ – ወያኔ ደራሲዎችንና የሰብአዊ መብት ታጋዮችን እያሰረ ነው – በሕዝባዊ አመጽ ንብረታቸው የወደመባቸው ኩባንያዎች ከመንግስት ካዝና ካሳ ሊከፈል ነው።
በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት በመዘጋቱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የንግድ ድርጅቶች ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው መሆኑ ታውቋል። ሥራቸውን ላለማስተጓጎል ሠራተኞቻቸውን ወደ ኬኒያ አዛውረው ስራውን እያካሄዱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። ባለፈው ዓመት ሐምሌ እና ነሐሴ ወር ውስጥ ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎች ስራዎችን ያስተጓለ መሆኑን የሚገልጹት እነዚሁ የንግድ ድርጅቶች በአሁኑ ወቅት የተወሰደው እርምጃ ጥልቀቱና ስፋቱ ከፍተኛ በመሆኑ ስራቸው የተደናቀፈ መሆኑ በምሬት ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት የቴክኖሎጂ ስደተኞች በሚል ስም መጠራት የጀመሩትን ሰራተኞች ወደ ኬኒያ አዛውረው ስራውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ እንቅስቃሴው ኬኒያ የበለጠ ገቢ በማግኘት እየተጠቀመች መሆኑ ለመረዳት ተችሏል። በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገግልግሎትን የሚቆጣጠረው የወያኔ የቴሌኮሙኒኬሽን ድርጅት ሲሆን በሌሎች ቦታዎች ኬኒያንም ጨምሮ አገልግሎቱ የሚሰጠው በግል ኩባንያዎች ነው። የኢንተርኔት እና የሶሻል ሚዲያ አገልግሎቶችን ለዜጎች በመስጠት በኩል ኢትዮጵያ ከዓለም የመጨረሻ ከሆኑት አገሮች አንዷ ናት። የኢንተነርኔት አገልግሎት ባልታገደበት ጊዜ እንኳ አገልግሎቱን የሚያገኘው ሕዝብ ከመቶ 3.5 ብቻ ሲሆን በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው የደቡብ ሱዳን እንኳ ከመቶ 15.9 የሆነው ሕዝብ የኢንተርኔት አገግሎት እንዳለው ይነገራል።
በደቡብ ወሎ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ የእጅ ቦምብ ፈንድቶ 22 ሰዎችን የጎዳ መሆኑ ከአካባብው የተገኙ መረጃዎች ይገልጻሉ። የእጅ ቦምቡን ወደ ትምህርት ቤት ውስጥ ያመጣው አንድ ተማሪ ሲሆን ከየት እንዳገኘው ማን እንደሰጠው እንዲሁም በምን ዓይነት ሁኔታ እንደፈነዳ መረጃው አያብራራም።
የወያኔ አገዛዝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምርኩዝ አድርጎ በየቦታው የጅምላ እስራት እያካሄደ መሆኑ የተገለጸ እስራቱ የጅምላ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ናቸው ተብለው በሚጠረጠሩ ታዋቂ ሰዎች ላይም ያነጣጠረ መሆኑ እየታየ ነው። ከዚህ በፊት በርከት ያሉ ጋዜጠኞች፤ የሰብአዊ መብት ታጋዮችና የፖሊቲካ መሪዎችና አባሎች ተለቅመው እንደታሰሩ በየጊዜው ዘገባ የቀረበ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ደግሞ የታወቀውን ደራሲና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ስለሞን ስዩም አገዛዙ ያሰረው መሆኑ ታውቋል። ሰለሞን ስዩም በርካታ የወያኔ አገዛዝን የሚነቅፉ በርካታ መጽሐፎች ጽፏል።
በሕዝባዊ አመጹ ንብረታቸው ለወደመባቸው ክፍሎች ከመንግስት ካዝና ካሳ እንዲከፈል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካይነት ካሳው ሕዝብ በታክስ መልክ ከሚከፍለው የመንግስት በጀት ላይ ተቀንሶ እንዲከፈል የሚል ሀሳብ የቀረበ መሆኑ የታወቀ ሲሆን በወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች ጸድቆ በስራ ላይ እንዲውል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው የሚለው ዜናም እየተስፋፋ ነው። የግል ባለሀብቶች የደረሰባቸውን ጉዳት በራሳቸው መወጣት ሲገባቸው የአገዛዙ ደጋፊዎችንና የጥቅም ተጋሪዎችን እንዲሁም የአንድ ጎሳ አባላትን ለመጥቀም የታቀድው ካሳ ሕዝቡ ላቡን አንጠፍጥፎ በታክስ መልክ ያስገባውን ገንዘብ ለግል ባለሃብቶች መደጎሚያ ማባከን አግባብ አይደለም የሚሉ ወገኖች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።