ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም.) : የወያኔ ኮማንድ ፖስት አፋኝ ስራውን ለመቀጠል ወሰነ – የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በበጀት እጥረትና በዕዳ ጫና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል – ህገ ወጡን ፓትርያርክ በመስደብ ተከሶ የነበረው ጋዜጠኛ በነጻ ተለቀቀ – ሞጋዲሾ በሚገኘው ዲያን ሆቴል ላይ የፈነዱት ተከታታይ ፈንጅዎች ጉዳት አደረሱ – በምርጫው ያሸነፉት የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው – የብሩንዲ መንግስት በእስር አግቶ ያቆያቸውን የአገሪቱን ዜጎች መፍታት መጀመሩ ተገለጸ።
አምባገነናዊ ስልጣን የተሰጠው የወያኔው ኮማንድ ፖስት ባለፉት ሶስት ወራት ያከናወናችውን ተግባራት ገምግሞ ለሚቀጥሉት ወራት የሚያከናውናችውን ተግባሮች አቅዷል። የቁረጠው ፍለጠው ስልጣን የተሰጠው ይህ አስከፊ አካል ባለፉት ሶስት ወራት በወሰዳቸው እርምጃዎች ሰላማዊ ሁኔታን በማስፈን በኩል የተሻለ ውጤት ያስመሰገበ መሆኑን ገልጾ ህብረተሰቡ ድጋፍ ከመስጠቱም በላይ እርካታና ድጋፍ ያገኘ መሆኑን ገልጿል። በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ችግሮችንም ለመቅረፍ የኮማንዱ ፖስቱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ወስኗል። ከ 40 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን በጅምላ በማገትና በምርመራ ወቅት ኢሰብአዊ የሆኑ ድርጊቶችን በመፈጸም ዜጎችን በማሰቃየት የሚታወቀው ይህ ኮማንድ ፖስት ተግባሩ በምን ዓይነት መለከያ የሕዝቡን ድጋፍን እርካታ አገኘ መባሉ አስገራሚ ነው የሚሉ ወገኖች ኮማንዱ ይህን መሰል ዜና ለሕዝብ በማቅረብ ለማታለል የሚችለው ራሱንና የአገዛዙን ባለስልጣኖች እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም ይላሉ። በተለያዩ ቦታዎች የዜጎች ምሬትና ብሶት ከመቸውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ በሆነበትና በአንዳንድ ቦታዎች በተለይም በጎንደር በህዝቡ የሚካሄዱ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴዎች እየተጠናከሩ በሄዱበት ሁኔታ ጸጥታ ሰፍኗል የሚባለው ከእውነት የራቀ መሁኑን ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች እየገለጹ ይገኛሉ። በሚቀጥሉት ወራት ኮማንድ ፖስቱ በርካታ ዜጎችን በጅምላ ለማገትና እንደተለመደው ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ በምርመራ ለማሰቃየት እቅድ ያለው መሆኑም ታውቋል።
የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተባለው ድርጅት በበጀት እጥረትና በዕዳ ጫና ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን የኮርፖሬሽኑ አመራር ለወያኔ ፓርላማ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ዘገባ ዋቢ በማድረግ አፍቃሪ ወያኔ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ በዛሬው እትሙ ላይ ዘግቧል። ድርጅቱ በያዝነው የበጀት ዓመት ሥራዎችን ለማስኬድ 60.276 ቢሊዮን ብር ገንዘብ እንደሚያስፈልገው አቅዶ የነበረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 43 ከመቶ ከአገሩ ውስጥ ቀሪውን 57 ከመቶ ከአገር ውጭ ለመሰብስበ ታስቦ የነበረ መሆኑ ተነግሯል። እስካሁን ድረስ ከውጭ ይገኛል የተባለው ብድር ከየት ሊገኝ እንደሚችል አልታወቀም ተብሏል። በ2008 ዓም 95.97 ቢሊዮን ብር የነበረው የኮርፖሬሽኑ ዕዳ ወደ 102.52 ቢሊዮን ብር ያደገ መሆኑ ተጠቅሶ የወለድና የግድታ ክፍያ በየአመቱ ለውጭ ባንኮች እየከፈለ እንደሚገኝ ተጠቅሷል። ኮርፖሬሽኑ በጥር ወር መክፈል የሚገባው የብድርና የዋና ወለድ ክፍያ 2.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን የዚህ ክፍያ ምንጩ ምን እንደሆን ባለመታወቁ ስጋት ፈጥሯል ተብሏል። ዕዳውን ለመክፈል ምናልባት የተወነውን የኩባንያውን ድርሻ ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥ ሊገደድ እንደሚችልም ተነግሯል።
የህገ ወጡን ፓትርያርክ ስም አጥፍቷል ተብሎ የተከሰሰው የሰንደቅ ጋዜጣ አዘጋጅ ፍሬው አበበ ፍርድ ቤቱ በነጻ የለቀቀው መሆኑ ተነገረ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የአባ ማትያስን ብልሹ አስራር ያጋለጠውን የዲያቆን ዳንኤልን ጽሁፍ በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በማውጣቱ ፍሬው አበበ በአባ ማትያስ ተከሶ የነበረ ሲሆን ጋዜጠኛው አባ ማትያስን በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠይቆ መልስ ሳያገኝ መቅረቱ ይታወቃል። ለአንድ የቤት ክርስቲያን አባት ለተባሉ ሰው ይቅርታ መስጠት የመጀመሪያ የሞራልና የእምነት ግዴታ ሆኖ ሳለ ጋዜጠኛው የጠየቀው ይቅርታ መልስ ሳይገኝ መቅረቱ ብዙዎችን ሲያስገርምም ሲያሳዝንም ቆይቷል። በዛሬው ቀን ጋዜጠኛው መከላከያውን በሚገባ በማቅረቡ ፍርድ ቤት በነጻ ለቆታል።
ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም.በሶማሊያ ዋና ከተማ በሞጋዲሹ ዳያን በሚባለው ሆቴል ደጃፍ ላይ በተከታታይ በተቀናጀ መንገድ በፈነዱት ቦምቦች ቢያንስ 15 ሰዎች ሲገደሉ ከ50 በላይ ሰዎች መቁሰላችው ታውቋል። በመጀመሪያ በዳያን ሆቴል መፈተሻ ቦታ መኪና ላይ የተጫነ ቦምብ ፈንድቶ የተወሰነ ሰዎች ሲገድል የአልሸባብ ታጣቂዎች ወደ ሆቴሉ ገብተው ተኩስ ከፍተው ተጨማሪ ሰዎች ገድለዋል ተብሏል። ሁለተኛው መኪና ላይ የተጫነው ፈንጅ የፈነዳው የአምቡላንስ ሰራተኞችና ጋዜጠኞች ወደ ቦታው ከደረሱ በኋላ ሲሆን በዚህም አደጋ ቢያንስ አራት ጋዜ ጠኞች መቁሰላቸው ታውቋል። ከተገደሉት 15 ሰዎች መካከል አራቱ ወታደሮች ሲሆኑ ሌሎቹ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸው ተነግሯል።