ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 24 ቀን 2009 ዓ. ም. ) – ሕዝቡ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞውን እየገለጸ ነው – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመሪያ አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ስብስብ ለወያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ ላከ – 40 ሺ ዓመት የሚገመት ዕድሜ ያላቸውና የጥንት ሰዓሊዎች የሚጠቀሙባቸው አለቶች ድሬደዋ አካባቢ ከሚገኝ ዋሻ ውስጥ ተገኙ – በዴንማርክና በስዊዝ በኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ስልፎች ተደረጉ – 239 ስደተኞች ባህር ውስጥ ሰጥመው ሞቱ #የኤኳቶሪያል ጊኒ ፕርዚዳንት ልጅ ንብረት የሆኑት 11 የቅንጦት እና የስፖርት መኪናዎች በጄኔቫ ከተማ ባለስልጣኖች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ወያኔ የአስቸኳዩ ጊዜ አዋጁ የጸጥታውን ሁኔታው እንደ ቀድሞ መልሷል፤ መረጋጋት ፈጥሯል የሚሉ ፕሮፓጋንዳዎች በየቀኑ እየነዛ ባለበት ውቅት ሕዝቡ በተለያዩ ዘዴዎች በአገዛዙ ላይ ያለውን ተቃውሞ እያሳየ መሆኑ እየተነገረ ነው። ሕዝቡ በየቦታው በግልጽ አገዛዙን በማውገዝ ስሜቱን ከመግለጽ ጀምሮ ሥራ በማቀዝቀዝና በመሳሰሉት ተግባሮች ተቃውሞውን እየገለጸ ይገኛል። ህዝቡ ተቃውሞውን ከሚገልጽባቸው መካከል የወያኔ ንብረት የሆኑ ድርጅቶች የሚያመርቷቸውን አለመሸመት እንዲሁም የትራንስፖርት ሆነ ሌሎች አገልግሎቶችን ያለመጠቀምን ይካትታሉ። በባህር ዳር የዳሽንን ቢራ የሚጠጣው ሰው የሌለ ከመሆኑም በላይ ኩባንያው በነጻ ለማደል ጥሪ እስከማደርግ ደርሷል፡፡ በሰላም አውቶቡስ የሚጓጓዙ ተሳፋሪዎች፣ ወታደሮች የወያኔ አገልጋዮችና የጸጥታ ሰዎች ብቻ ሆነዋል የሚሉ መረጃዎች እየደረሱ ነው።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት እርዳታ ድርጅቶች የእርዳታ ተግባራችውን ለማከናወን እንቅፋት የገጠማቸውና ሥራቸው የተሰናከለ መሆኑን በመግለጽ ዘገባ ማስተላለፋቸው አይዘናጋም። Ethiopian Humanitarian Country team የሚባለውና የተመድ የእርዳታ ድርጅቶችን፤ ቀይ መስቀልንና ሌሎች የዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችን የሚያቅፈው ስብስብ ለወያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመሪያ አስመልክቶ ማብራሪያ የሚጠይቅ ደብዳቤ የጻፈ መሆኑ ተነግሯል። የእርዳታ ሰጭ ድርጅቹ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በአብዛኛው ጊዜ ተረጅውን በመሰብሰብ በመሆኑ ለእርዳታ የሚደረገው ስብሰባ በህገ ወጥነት የሚያስጠይቃቸው መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ጥያቄውን አቅርበዋል። በኢትዮጵያ በገባው ድርቅና ረሃብ ምክንያት 9.7% የሚሆን ወገን የምግብ ዕርዳታ የሚደረግለት መሆኑና እንዲሁም ከ700 ሺ በላይ የሆኑ በተለያዩ ካምፖች የሰፈሩ የውጭ ስደተኞችም ተረጅዎች መሆናቸው ይታወቃል።
በድንጋይ ዘመን የጥንት ሰዓሊዎች በአለት ላይ የሰውና የእንስሳት ስዕሎችን ለመሳል የሚጠቀሙበት ዕድሜያቸው ከ40 ሺ ዓመት በላይ የሆኑ የድንጋይ አለቶች በድሬ ደዋ አካባቢ የተገኙ መሆናቸውን ተመራማሪዎች ገለጹ። የጥንት ሰዓሊዎች የተለያዩ ቀለማት ያላቸውን አለቶች ፈጭተው ከዛፍ ላይ ከሚገኝ ፈሳሽ ጋር በማቀለቃል የተለያዩ ስዕሎችን ለመሳል ይጠቀሙባቸው እንደነበር ግምት ተወስዷል። ከቦርዶ ዩኒቨርሲት በመጡ ተመራማሪዎች አማካይነት የተገኙት 21 የተለያዩ አለቶች ድሬደዋ ውስጥ በሚገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ መገኘታቸው ታውቋል።
በዛሬው ቀን በዴንማርክ ዋና ከተማ በኮፐንሃገን ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ስልፍ አድርገዋል። ኢትዮጵያውያን የወያኔን አገዛዝ የሚያወግዙ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን ስርዓቱ በሕዝቡ ላይ የሚፈጽመው ግፍ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል። የታሰሩት ይፈቱ፤ ወያኔ ከሥልጣን ይወገድ፤ ነጻነትና መብት ለሕዝብ ይሰጥ የሚሉ ድምጾች አሰምተዋል። ከትናንት ወዲያ ማክሰኞ ዕለትም በስዊስ ጄኔቫ የተመድ ዋና መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ኢትዮጵያውያን ሰልፎች አካሂደው ቴዎድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት መታጨቱን በመቃውም ድምጻቸውን አሰምተዋል። ግለሰቡ ለቦታው ብቁ አይደለም ከሚለው በተጨማሪ ተመድ በኢትዮጵያ ለሚካሄደው ጭፍጨፋ ጆሮውን ይስጥ፤ በሕዝብ ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ ይቁም፤ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ይፈቱ፤ ሕዝብን የሚጨፈጭፈውን መንግስት በገንዘብ መደጎሙ ይቁም፤ ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ የሚሉ እና ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል። ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የመጡ ኢትዮጵያውያን በሰልፉ ላይ ተሳትፈዋል።
ሐሙስ ጥቅምት 14 ቀን 2009 ዓ.ም ከሊቢያ የወደብ ዳርቻ ወደ አውሮፓ በሁለት ጀልባዎች ይጓዙ የነበሩ ከ239 በላይ የሆኑ ስደተኞች ውሃ ውስጥ ሰጥመው የሞቱ መሆናቸውን የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ገልጸዋል። ድርጅቱ ይህንን ያወቀው ሁለት ህይወታቸው በጣሊያን የጠረፍ ጠባቂዎች የተረፈ ሰዎች ላምፓዱሳ ላይ ከተናገሩት መሆኑን ገልጿል። አብዛኞቹ የሞቱት ስደተኞች ከምዕራብ አፍሪካ የመጡ መሆናችው ይነገራል። ባለፉት 10 ወራት 330 ሺ የሚሆኑ ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ወደ አውሮፓ የተሻገሩ መሆናቸው ሲታወቅ ከእነዚሁ ውስጥ 4200 የሚሆኑት እንደሞቱ ይነገራል።
የጄኔቫ ከተማ አስተዳደር የኤኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዚዳንት ልጅ ንብረት ናቸው የተባሉትን 11 የቅንጦትና የስፖርት መኪናዎች በቁጥጥር ስር ያደረጉ መሆኑን ባለሥልጣኖቹ አስታወቁ። የባለሥልጣኖቹ እርምጃ የፕሬዚዳንቱ ልጅ የሕዝብ ንብረት በማባከን በኩል ከቀረበባቸው ክስ ጋር የተያያዘ መሆኑ ታውቋል። የመኪናዎቹ ዋጋ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር እንደሆን ተገምቷል።