ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 22 ቀን 2009) – ወያኔ አዲስ የካቢኔ ሚኒስትሮች ሾመ፤ የጉልቻ መለዋወጥ ችግሮችን አይፈታም – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የሰብአዊ እርዳታ ተቋሞችን እንቅስቃሴ አዳክሟል – በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ምክንያት በርካታ ኩባንያዎች እንቅፋት እየገጠማቸው ነው።
የወያኔ አገዛዝ በትናንትናው ዕለት አዳዲስ የካቢኔ ሚኒስትሮች መሾሙ ተነግሯል። ከ30 የካቢኔ ሚኒስትሮች መካከል 9 ኙን ብቻ አስቀርቶ 21 ቀይሯል። ከሃይ አንዱ ውስጥ 15ቱ አዳዲሶች ሲሆኑ የተቀሩት ከቀድሞዎቹ ውስጥ ወደ ሌላ የሚኒስትር ቦታዎች የተዛወሩ ናቸው። የኢሕአዴግ አባል ያልሆኑ ሰዎችም ገብተውበታል ተብሏል። አገዛዙ ለወራት በውስጡ እድሳት እንደሚያደርግና በአመራር ቦታ ላይ ያሉትን ማሰናበት ብቻ ሳይሆን በፈጸሙት ወንጀል በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ሲዝት እንደነብር የሚታወቅ ነው። የህዝብን ቀልብ ለመሳብ በሚል አብዛኛዎቹ ተሿሚዎች የዩኒቭርሲቲ መምህራን የሆኑና በትምህርትም 3ኛ ዲግሪ የያዙ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ አብዛኛው የዩኒቭርሲቲ መምህራን የያዟቸው የትምህርት ደረጃ ማስረጃ የምስክር ወረቀቶች የይስሙላ መሆናቸውና በዚህም ሳቢያ ትውልድ ገዳይ የሆነውን የወያኔን የትምህርት ስርዐት ካለምንም ማቅማማት ሲያራምዱ የቆዩ በትውልድ ገዳይነት የሚጠየቁ መሆናቸውን ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ ከተሿሚዎች ውስጥ በወያኔው ዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት በየአመቱ በሚቀርበው የኦዲት ምርመራ ላይ በዋና ዘራፊት፣ በፊት አውራሪት የሚጠቀሱ ዩኒቨርስቲዎችን ሲመሩ የነበሩ ሰዎች አሉበት። እነዚህ ሰዎች በወንጀላቸው ሊጠየቁ ሲገባቸው አሁኑ በካቢኒ ሚኒስትርነት ደረጃ መሾማቸው የወያኔን ቢያጥቡት አይጠሬነት የሚያሳይ ነው በማለት አንዳንድ ወገኖች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ ይህ የወያኔ ሹመት ወደ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ አመጽ ለማሽመድመድና ህዝቡን ለማማለል የተወጠነ ቢሆንም ፤ የደብተራ ጋጋታ ቅዳሴ አያሳምርም እንደሚባለው ምንም ለውጥ ሊያመጣ እንደሚያችል ግልጽ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ሕዝቡ እያካሄደ ባለው አመጽ የጠየቀው የወያኔ አምባገነን አገዛዝ ከስሩ ተመንግሎ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲተካ በመሆኑ የሸክላ ጉልቻን በድንጋይ ጉልቻ የተካው ወጥ ለማጣፈጥ የሚጥረው የአሁኑ ሹም ሽር የሕዝቡን ጥይቄ አይመልስም። የሕዝቡ ጥያቄ ሊመለስ የሚችልው የወያኔ አገዛዝ ሲወገድ ብቻ በመሆኑ ሕዝባዊ አመጹ ተጋግሎና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሳይታለም የታየ ከመሆኑም በላይ በራሳችንም ታሪክ የታየ ነው ተብሏል።
ወያኔ በሕዝብ ላይ የጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የሰብአዊ እርዳታ ተቋሞችን እንቅስቃሴ እያዳካመው መሆኑ እየተነገረ ነው። ብዙዎች በእርዳታ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ጋዜጠኞች ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ከመፍራታቸውም በላይ የስራቸው እንቅስቃሴ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፤ ምን ችግር እንደገጠማቸውና ችግሮቹ በምን ዓይነት መንገድ ሊፈቱ እንደሚችሉ በይፋ መናገር እየከበዳቸው መጥቷል። የሚሰጡት ሃሳብ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ባልሆነ መንገድ ተተርጉሞ የሚያካሄዱትን ፕሮጀክት ሊከለከለሉ እንደሚችሉ እንዲሁም እስከናካቴው ከአገር ሊባረሩ እንደሚችሉ ፍርሃት ያለባቸው መሆኑ ታውቋል። የትራንስፖርት ችግርና የእንቅስቃሴ እገዳ በመኖሩ የሚካሄዷቸውን ፕሮጀክቶች ለመከታተል አዳጋች እንደሆነባችው አንዳንድ የውጭ አገር ኤምባሲዎች ይገልጻሉ።
ላለፉው አንድ አመት ሲካሄድ በነበረው ሕዝባዊ አመጽና ተከትሎ በመጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በአገር ውስጥ ስራ ለመጀመር አቅደው የነበሩ የውጭ ኩባንያዎች እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማደረግ እያመነቱ ከመሆናችው በላይ አገሩ ውስጥ ያሉትም ኩባንያውቸውን እየነቀሉ ለመውጣት ማቀዳቸውን በውጭ አገር የሚገኙ ኤክስፐርቶች እየገለጹ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት በአገዛዙ እንደመፍትሄ የሚቀርቡ ሁሉ ተቃዋሚዎችን የማያረካ በመሆኑ ችግሩ የሚቀጥል መሆኑንም ተንብየዋል። የአመጹ እንቅስቃሴ እስካልቆመ ድረስ በአገሪቱ ላይ የፖለቲካውን ቀውስ ተከትሎ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችልም ብዙዎች ይናገራሉ።