(ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ) – ራስን በማስቀየርና ገለባን ምርት አስመስሎ ለመሸጥ ወያኔን የሚደርስበት የለም። ጮሌ፤ ዋሾ፤ ወንበዴና ዘረኛ ቡድን ነው። ሕዝባዊ መንግሥት ይመስረት፤ ሁሉን አቀፍ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይደረግ ሲባል ጠቅላይ ሚኒስቴር ልንቀይር ነው፤ የተወሰነ እስረኛ ልንፈታ ነው ወዘተ በሚል የሕዝብን ጥያቄ ወደ ጎን አሽቀንጥሮ ዋና ጥያቄ ያልሆነውን ዋና ጥያቄ ያደርጋል። በ 1997 የሆነውን ያስታውሷል። ዋናው ጥያቄ የሰረቀውን የህዝብ ድምጽ የሚመለከት ሆኖ ሳለ የያዛቸውን እስረኛ ይፈታ ዘንድ ዋና ጥያቄ አድርገው–ሁሌም ተወናባጅ ተቃዋሚዎች – በመጮህ ዋናውን መሰረታዊውን ጥያቄ ረሱለት፤አስረሳቸው።ለዚያውም የእኛን እስረኞች ብቻ ልቀቅልን ብለው ሊያሳፍሩን።
ዛሬም የተያዘው ይህ ነው። ወያኔ የወረደውን ስልጣን አልባ ጠቅላይ ሚኒስቴር በሌላ ቀየረ አልቀየረ በመሰረቱ ፋይዳ ቢስ ነው። በዚህ ሁኔታ ገበየሁ ቢሄድ ተተካ ባልቻ አይደለም፤ሊሆንም አይችልም። አንዳንዶች ለወያኔ ያደሩ ወያኔ እነ እገሌን ይሹምልን ብለው መለመንም ጀምረዋል። ሀፍረት! አንድ ተቃዋሚ ነኝ ባይ አይታክቴ ልፍስፍስ ደግሞ ወያኔ ስልጣን ያለው ጠቅላይ ሚኒስቴር ይመድብልን ሲልም ተደምጧል። ማፈሪያ! ወያኔ እርስ በርሱ ማን ለወያኔ ይመቻል ያመቻል በሚል የተወገደውን መጋዣ በሌላ ቢተካው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም የሚጠቅመው የለም። ዋናው ዓላማው ለውጥ ተደርጓልና ትግሉን አቁሙ ማለት ብቻ ነው። የወያኔ ወራጁ ጠላይ ሚኒስቴር እንደ ወያኔ ፕሬዚዳንቶች ጥላ የማይጥል ርባና ቢስ ስልጣን አልባ ሆኖ የተጫወቱበት፤ የዘወሩትና የሾፈሩት ግለሰብ ነው። የሕዝብ ፍላጎት በወያኔ ስር የወያኔ ጉድ አስፈጽሚ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲመድብለት አይደለም። የወያኔ ዘረኛና ኢዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያከትም ነው የሕዝብ ፍላጎት። የኑሮ ሁኔታው ዴምክራሲያዊ ለውጥ እንዲያገኝ ነው የሕዝብ ፍላጎት። ጉልቻ ቅየራ ሳይሆን ወጥ ቤቱና ቅመማ ቅመሙ ሁሉ ይቀየር ባይ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ። የወያኔ ስር ዓትና መንገድ ለኢትዮጵያ የማይበጅ ጸረ ሕዝብ አገዛዝ መሆኑ ለ27 ዓመታት ታይቷል። የሚጠገን፤ የሚሻሻል አይደለም። ስርዓቱ የበሰበሰው እንደ አሳ ከጭንቅላቱ ነው –በስባሹ ወያኔ ነው። ስለዚህም የገለማውን ቡድንና አገዛዝ ይዞ ምንም ለሕዝብ ሊበጅ የሚችል ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ላለፉት አምስት ዓመታት ሕዝብ በሰላም ለለውጥ ታገለ። ምን አገኘ? ሁለት የአስቸኳይ ጊዘ አዋጅ። ግድያና እስራት፤ ግብረ ስየልና ሕጻናትንም ያልማረ ፍጅት። የቀጠለ ከይሲ ዘረኝነት፤ የብዙሃኑ መታፈን፤የኮማንድ ፖስት ዴሞክራሲ፤በደም በሞት የታጀበ። ምንም ለውጥ አልተገኘም። ወያኔ ባዕዳንንም ተማጥኖ፤ቅጥረኞችና ጽንፈኞችንም አሰማርቶ አሁንም ቢሆን ነገ የያዘው ዘረኛና ጨቋኝ ፖለቲካ ሊቀጥል እንጂ ለለውጥ ጊዜው አልፎበታል።
በመሆኑም ማን ይመደብ ይሆን የሚለው ሕዝብን የማይመለከት ከመሆኑም በላይ ምንም ለውጥን የሚያመጣ አይደለም። የአማራ ወይም ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መመደቡ፤ ሴትም ሆነች እስላም ዜጋ በዚህ ቦታ መሰየሙ ማንንም ለውጥ መጣ በሚል ሊያደናግር አይገባውም። ወያኔ ጨንቆት በከፍተና ደረጃ ሊያደናግር ሲያሴር ቆይቷል። ወያኔ ቢዳከምም ቢከፋፈልም አሁንም የፍጹም ሥልጣን ባለቤት ነው። ይህ ነው መቀየር ያለበት፤ ወያኔ ስልጣን አልባ መሆን አለበት። የራሱን ተለጣፊዎችና እስከዛሬም ሆነ አሁንም አገልጋዮች በመሾሙ ስልጣን አጋራ ወይም ተወ ማለት አይደለምና የተጀመረው ትግል ሳይበርድና ሳይቋረጥ መቀጠሉ የግድ ነው። ወያኔና ጭፍሮቹ እገሌ ከእገሌ ይሻላል፤ እገሌ እኮ ወያኔን ይቃወማል፤ይጋፈጣል ወዘተ በሚል ሊቀልዱብን የሚጥሩት ሁሉ ውድቅ መሆን አለበት። የወያኔ ሰላይ የሕዝብ ድርጅት መሪ ተብሎ ሲሸጥ ቧልቱን ገዝተን ጉድ የሆነው ይበቃል። ከዚህ በፊት አሁን የወረደው መጋዣ ሲሾም ስልጣን ይዞ ለውጥ የሚያመጣ መስሏቸው እየጠበቅንህ ነው ብለው ሲመክሩት ሲማጸኑትና፤ ለውጥም ሊኖር ይችላል ብለው ሲደናበሩ የነበሩ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችና አዋቂ ተብዬዎች አይተናልና አሁንም ያ ሁኔታ እንዳይደገም ያሰጋል። አንዱ ተቃዋሚ ወያኔ የረባ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሹምልን ሲል ለውጭ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ መስጠቱ አያረጋጋንም። ሕዝብ ሲል የቆየው እኮ ወያኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሹምልን ሳይሆን መንግስታችንን ራሳችን በምርጫ በፍላጎት እንመስርት ነው። ሕዝብ ነው ባለስልጣን፤ሕዝብ ነው ጠቅላይ ሚኒስቴርም መንግስትም መራጭና መስራች መሆን ያለበት። ከዚህ ግብ ሳንደርስ ወያኔ ሾኬ ሊመታን (ቴስታ ሊመታን ማለትም እንችላለን) ሲጥር ይህን መደገፍና ከወዲሁ ምንም ይህ ነው የማይባል መስዋዕትነት ያልከፈሉት በተለይ ወደ ቀቢጸ ተስፋ ገብተው ወያኔ እንዳለ ሆኖ የተሻለ ሰው ይመድብልን፤ ተጨማሪ ስልጣን ያካፍለን፤ ከቅርጫው ድርሻችንን ይጨምርልን ብሎ መገኘቱ ማንም ሀገር ወዳድ ነኝ ለሚል አሳፋሪ አቅዋም ነው። ወያኔ ስልጣን ካልለቀቀ ከወያኔ የዘረኛ ዘራፊ ጎራ ማን የተሻለና ለሕዝብ የሚበጅ ሰው ሊመጣ? ሕዝባዊ መንግሥት ብለን እየተዋደቅን ከዚህ ግብ ለመድረስ አቅሙም ውሳኔውም እያለን ለምንስ በወያኔ ቡቱቶዎች ረክተን ትግል ልናቆም ይጠበቃል? ያረገውን አርጎ አበጀሁ ቢላችኹ/ ይህን ባለጊዜ ምን ትሉታላችሁ የሚባልበት ጊዜ አልፏል። ባለጊዜው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ ብቻ ነው። ማለትም የወያኔ እህል ውሃው አልቋልና በቃህ ነው መልዕክቱ እንጂ ከቶም ሌላ ሊሆን አይገባውም ።ከወያኔ ጋር ከርመውና ቆሽሸው፤ሀገራችንን በየአቅማቸው በድለው፤ ዛሬ ገልበጥ ብለው ሕዝባዊ ነን ሊሉ ሲሞክሩ ብንጠራጠራቸው ተገቢ ነው። የሚያዋጣውና መፍትሔው በሩቁ መያዝና ባልገውበት ከነበረበት የስልጣን መድረክ ማራቅ ብቻ ነው። አሊያም በሌሎች ሀገሮች እንዳየነው አልሸሹም ዞር አሉ ይሆንና የጠላነው ስርዓት በቀጥታም በቅጂም ይቀጥልብናል ።መስዋዕት በከንቱ መባላችንም አይቀርም።
በትግላችን ሂደት ላይ ገና ብዙ ዕንቅፋት እንደሚገጥመን ግልጽና የምንጠብቀውም ነው። ጠላት የሚወረውርብን ሁሉ መልሰን በራሱ ላይ ማፈንዳት መቻል አለብን። ጠቅላይ ሚኒስቴር ቀይርልን አላልንም ስልጣን ልቀቅ እንጂ ሊባል ይገባዋል። በዚህም ላይ በውስጥም በውጭም በተቃዋሚ ስም ጥሩን ባዮች ሁሉ አቅዋማቸው ከሕዝብ ጎን አድርገው፤የሚጠበቅባቸውን ድፍረትና ጽናት አንጸባርቀው፤ ለፍርፋሪ ሳይሆን ለሕዝባዊ መንግስትና ለአንድነትና ብልጽግና እንዲቆሙ ጥሪ እናደርግላቸዋለን። ሳይታገሉ ለደከማቸውን ግን ከሕዝብ ወኔ ተውሳችሁ ካልተቀየራችሁ ወደ ታሪክ ትቢያ እንጂ ወደ ቤተ መንግሥት መግባቱ ዘበት ነው የምንላቸው ይሆናል። ምሁሮች በሕዝብ ላይ የሚፏልሉበት ጊዜም አክትሟል ባይ ነን፤እንዲያከትምም ስንታገል ቆይተናልና እንቀጥልበታለን። ለሕዝብ አውቅልሃለሁ የሚሉትን ግብዞች ሕዝብ በትግሉ ወደ ጎን አሽቀንጥሮ የትግሉ ባለቤት ራሱ መሆኑን በደሙ በማረጋገጥ ላይ ነው። መራነው ቃኘነው ባዮቹ ከሞላ ጎደል የአፍ ጠላፊዎችና የትግል ገዝጋዦች መሆናቸውን ነቅቶባቸዋል። የትግሉ ባለቤት ህዝብ ነው ያልነው ሀቅ ነውናም የወያኔም ሆነ የደጋፊዎቹን ጋሬጣ አስወግደን ትግላችንን እስከ ተወሰነለት ግቡ ለማድረስ ሳንወላውል መታገል አለብን። ወያኔ እገሌን ጠቅላይ ሚኒሲቴር ሾምኩላችሁ በሚልና ምናልባትም ለአንዳንዶች መጨመቺያና አፍ ማዘጊያ ሹመት በመስጠት የሕዝብ ትግል እንዲቋረጥ ለማድረግ መምከሩን መናገር ነቢይነትን አይጠይቅም። መውጫ የለውምና ቅጥረኞችና አድርባዮችን አድኑኝ ተቀበሉኝ፤ ሕዝብ አደናግሩልኝ ብሎ መማጸኑ የታየም የሚጠበቅም ነው። ግን መቸም የማይሻረውና የማይለወጠው ሀቅ ማንም ሆነ ማን የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስቴር የሕዝብ ሳይሆን የወያኔ ነው። ቁምነገሩ የፖለቲካ ስልጣን በሁሉም መስክ በወያኔ እጅ ያለ መሆኑ ነው። የሰራዊቱ፤ የፖሊሱ፤የቢሮክራሲው፤ የኢኮኖሚው ወዘተ አዛዥ ናዛዥ ዘረኛው ወያኔ መሆኑ ነው። በምርጫ ለመሸነፍማ ወያኔ በ1997 በአፍጢሙ ሕዝብ ደፍቶት አልነበር። እንዴትስ ስልጣኑን እንደያዘ ቀጠለ? የዚህ ምላሹ ዛሬም ወቅታዊ ነው። መቀየር መወገድ ያለበት ወያኔ ከነስርዓቱ ነው። ሌላው ሁሉ ንግግር ጉንጭ አልፋ ነው።
ወያኔን ለማስወገድ ትግላችን ተፋፍምፕ ይቀጥል!!
ጸረ ወያኔ አንድነታችንም ይጠንክር!!