የተካኑ ሰይጣኖች፤ የመድረክ መዥገሮችና የኮረፌ ፈላስፎች

ከሀማ ቱማ – በጎጃም ሞኝ አንግሴ ይሉታል። አጠናባዡን ዳግም አረቄን መሆኑ ነው። በሲኒ ቢጠጣም ከበዛና ከተዘወተረ ምላስን ያጠቁራል። በትንሹ። በዋናው መልኩ ግን ሞኝን የነገሰ ያስመስለዋል–ንጉሶች ደግሞ እንዳየነው ለሥልጣናቸው ቀናኢ በመሆናቸው ፉክክሩ መዘዝ ያመጣል። በጸለምት ስሜን ኮረፌም ከብርድ መከላከል አልፎ በብዛት ከተጠጣ ያፈላስፋል ሲባል ሰምቻለሁ። የቋራው ደጋ እንዲህ ሲባልለት ግን አልሰማሁም። የአድዋ ፊልተር ከስብሓት ነጋ መነሁለል ጋርም ጥብቅ ግንኙነት አለው የሚሉ አሉ። ኮረፌ ሲበዛና ሲያፈላስፍ ማነኝ? እግዜር ነው እውነት የፈጠረኝ? ለምን ጉዳይና ተልዕኮ? ሥላሴዎች እንዴት አንድም ሶስትም ሆኑ? ሞት የሕይወት ቅጣይ ይሆን? ዘውድ የአንጥረኛ ቆርቆሮ አይደለምን? ለገዢዎች ማን ሥልጣን ሰጣቸው? ኢየሱስና ነቢዩ መሃመድ ጥቁር ነበሩ? ለምንስ እኔ አልነግስም? ዓይነት መዘዘኛ ጥያቄዎችን ያስጠይቃል ተብሏል። ዳግም አረቄና ኮረፌም  ዋጋቸው ተወደደ ወይም የትግሬ መጠጥ ተባሉ እንጂ (ጸለምት ራሱ የትግራይ አካል ተብሎ የለ?) በሀገራችን ሞልተዋል። ለማንኛውም መጠጥ ለጨዋታ በሚል በልክ መጠጣቱ ሳይሻል አይቀርም እላለሁ። ግን አልሆነምና ኳ ባደረጉ ቁጥር የነገሱ ሞኞች፤ የኮረፌ ፈላስፎች በርክተውብናል። ቀደም ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ  አይተውም ይባል የነበረው ተቀይሮ ወያኔን ያደቆነው ሰይጣን ተፈልጎ በመጥፋቱ አዋቂዎች ወያኔ ራሱ ገና በናቅፋ የተካነ ሰይጣን ነው ሲሉም ደምድመዋል። አንደምታውን 27 ዓመታት ከስቃይና መከራ ጋር አይተናል ማለትም እንችላለን።

ቢመከሩ ቢመከሩ ከቶም መሻሻል — መመከር – እምቢኝ የሚላቸው ብዙዎች አሉ። የታሸገ የቆርቆሮ ምግብ እንኳን የጊዜ ገደብ አለው ብንልም አልሰማንም ብለዋል።  በርግጥ ያልተመቸው ዓመት ያለፈውንም ቆርቆሮ ከፍቶ የመጣ ይምጣ ብሎ መብላት ብቻ ሳይሆን ለፈረንጅ ውሾች ድመቶች የታሸገውንም ሲሰለቅጥ አይተናል፤ አውቀናል። ታዲያ ለምግብ ሳይሆን ለወሬም ማለቂያ ማቆሚያ ጊዜ አለው–በተለይ ለአሉባልታና ሀሰት ወሬ። የጠነዛን ሀሰት አድሶ ማራገቡ አኖሌ ሐውልትን ያሰራ እንደሆነ እንጂ ሀቅን አይላበስም። ደርግ በኢሕአፓ ላይ የፈለገውን ሁሉ ሐሰትና ክስ ሲያሰራጭ ከርሞ ምንም የበጀው አልነበረም። የደርግ ውሸት  ከተነገረ 27 አመታት አልፎት ዛሬም ግን የግዜው ገደብ ካለፈም በኋላ ሲያላዝኑት መስማት ተገደናል። የኢሕአፓ ጠላቶች የሆኑትን ወዳጅ አድርጎ በማቅረብ ድርጅቱን የሲአዬ ቅጥረኛና የአረብ ፔትሮ ዶላር ምንደኛ ብሎ ሲዘልፍ መክረሙ ይታወሳል። ለኢሕአፓ ዶላር የለገሰ አረብን የበላው ጅብ እስከዛሬ አልጮህ እንዳለ ግን ሁላችንም የምናውቀው ነው። ከርዕዮቱም የተነሳ ሆነ ኢትዮጵያ በማለቱ በአረብ ሀገሮች ድርጅቱ ያልተደገፈ ሆኖ መቆየቱን ታሪክ መዝግቧል። ዛሬም የተቀየረ የለም። ባለን ተመክሮና ችሎታ፤ ኢሕአሠ ይቆጣጠረው በነበረው ጉባ አካባቢ ሊሰራ ታቀደ የተባለውን ግድብ ስራ ለማቆም ከሚመለከታቸው እርዳታ ለመቀበል ዝግጁ ብንሆን ምናልባትም ችግራችንን ቀርፈን እንደረጅ ነበር። ሶማሊያም ምዕራብ ሶማሊያ ያለውን የኢትዮጵያ አንድ ሲሶ እውነትም የሶማሊያ ነው ብለን ብንፈርም ሰፊ እርዳታ ሊሰጠን ቃል ገብቶልን እኛ አሌ ስንለው ወያኔ ግን ተቀብሎ በሞቃዲሾም ቢሮ ከፍቶ በአረቦች ሊረዳ ባልቻለ ነበር። ሻዕቢያን በተመለከተም ተመሳሳይ ማለት እንችላለን። በመሆኑም የሚሰለቁት ሀሰቶች እጅ እጅ ያሉና ጊዜም ያለፈባቸው ናቸው ማለት ይገባል። አዲስ ሀሰቶች ብቅ ካሉ ለምላሽ አንቦዝንም። ላደረ ለሻገተ — ገሞራው ለቀመለ ላለው – ወሬ ግን ጊዜም ምላሽም የለንም ብለናል።

በጣም የሰለቸና አሰቃቂ እንደምታ ሊኖረው የሚችል ሌላ የሻገተ ልፈፋ ደግሞ ትግሬዎችን የሚመለከተው ነው። በአጼው ጊዜ የተማሪውን እንቅስቃሴ ለመከፋፈልና ለማስጠላት ከኤርትራ “አጋሚዶዎች” ይባሉ ከነበሩት  ጋር የተያያዘ ነው ይሉ ነበር። ደርግም ኢሕአፓን ከሁሉም ጸረ ኢትዮጵያ ሰይጣን ሊያዛምድ ሞክሯል። ከወያኔ ጋር አብረው ቆሙ ብሎ ግን በሰፊው ሲቀላምድ አልተሰማም። ከኤርትራ ገንጣዮች ጋር መስራት ብቻ ሳይሆን የተፈጠረውም በነሱው ነው ሲል ግን ብዙ ጊዜ ተደምጧል።  ከላይ ልል እንደሞከርኩት ይህን ሲነገር የሞተን ቁርበት ይዘው ሚንኳኩ ግን እስካሁን አሉ። ኢትዮጵያን ከገንጣዮች፤ ጠባቦች፤ ከባዕድ ጠላቶች ስንከላከል ብዙ ጉዳትን የተቀበልነው ኢሕአፓዎች ግን ገና ከጠዋቱ ስምሪታችን በጎጥ፣ በጎሳ፤ በሀይማኖት በብሄረሰብ ደረጃ ከቶም ባለመሆኑ በዚህ ክስ አቅጣጫ የምንለው ብዙም አይኖር።  ለነገሩ ብዙ ጊዜ ነግረናቸው አውቀው የደነቆሩትን መምከሩ ከንቱ መሆኑን ደምድመናል ማለት ይቻላል። የፖለቲካ ድርጅት እንመሰርታለን ስንል ከኤርትራ ድርጅቶች ጋር ተገናኝተን በሚልም አልነበረም። በአልጄሪያ በስደት በነበርንበት ጊዜ ከአያሌ አለም አቀፍ ድርጅቶችና ሀገሮችም ጋር ግንኙነት የመሰረትን ሲሆን ከፍልስጤም ድርጅቶች ጋር የነበረን ቅርበት ከጀብሃ በአልጄሪያ ከነበረን ግንኙነት (የመጀመሪያ ግንኙነታችን ከሻቢያም አልነበረምና ) ይበልጥ የተቀራረበ ነበር። በውጭ ሀገር ካሉ ተራማጆች ጋር ተጣምረን፤ ድርጅት መስርተን፤ ጦርም አቋቁመን በባሌ /በጫካ/ በኩል ዘልቀን በመግባት ትጥቅ ትግል በጫካ እንጀምራለን የሚል አጠቃላይ ዕቅድ ነበረን። የሱዳኑም አስችጋሪ ሲሆን፤ የባሌውም በዚያድ ባሬ ጣልቃ ገብነት የሚሳካ እንደማይሆን ሲታወቅ ወደ ኤርትራ ግንባሮች መዞር ተገደን በዚያ በኩል ያለውን ግንኙነት ልናተኩርበት ልንገደድ ችለናል።  ከያሲር አራፋትም፤ እስራኤሎች ቱኒስ ሄደው ከገደሉት ከአቡ ጂሃድም፤ ከጆርጅ ሀበሽም፤ ከናይፍ ሀዋትሜም ወዘተ ጋር ግንኝነት የመሰረትነው ራሳችን ኢትዮጵያውያን እንጂ በኤርትራ ግንባሮች ድጋፍም አልነበረም። ለነሱም ለወያኔም ያልሰሩትን ሰሩ ብሎ የሚቀርበው ሸንዳራ-ሸውራራ አስተያየት ከመሆኑ ባሻገር ምንም የሀቅ መነሺያ የሌለው ነው።  በሻዕቢያ በኩል ፍዳ ከፍለን ሠራዊት ባናስገባ ኖሮ ይሻል ነበር እስከ ማለትም ዛሬ የደረስነው እኮ አልጋ በአልጋ ጉዞና ግንኙነት ሳይሆን ጎጂ ሆኖ በመገኘቱም ነው። በኤርትራ ሜዳ ጀብሃ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር መሪዎችን /ቲኤልኤፍ/ እንደሰበሰበው ሁሉ ሻዕቢያ የወያኔ መሪዎችን መሰብሰብ ሲጀምር እነዚህንም በሜዳ የነበሩት ሟቹ አቶ አሰፋ ሐብቱ (የድርጅታችን አባል የሟቹ መስፍን ሀብቱ ታላቅ ወንድምና የብንያም አዳነ ቅርብ ዘመድን) እንዲመሩ ጠይቆ በትግራይ ስም ለተደራጀ ቡድን አባልም መሪም ሊሆኑ እንደማይችሉ ገልጸውለት ነበር።  የትግራይ ትግሪኚ አባወራው ወልደ አብ ወልደ ማርያም ሆኑ ኢሳያስ አፈወርቂም ብርሃነ መስቀል ረዳን የትግራይ ቡድን መሪ እንዲሆን ላቀረቡለት ጥያቄም በደፈራችሁኝ የሚገባቸውን ምላሽ ሰጥቶ እምቢ አለ እንጂ ከእነሱ ጋር አልሰመረም።  ሻዕቢያ መንክዓ ብሎ ከአዲስ አበባ የመጡ የዪኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሊያጠቃ ሲነሳ ወደ ደቡብ የመን ለህክምና ወጥታ የነበረችውን የህክምና ኮሌጅ ተማሪ የነበረችውን ደሃብን ለመርዳት-ለማስመለጥ ተሞከረ እንጂ ለሻዕቢያ ድጋፍ አለተሰጠም።  በፖለቲካ ጉዳይ ከብርሃነ መስቀል ጋር ብንጋጭም በኢትዮጵያዊነቱ ግን ዛሬ ለሚከሰሰው ለእሱም፤ ለዘሩም፤ ለሌሎቹም ጥብቅና ለመቆም በበኩሌ ዝግጁ ነኝ። ኢትዮጵያዊ ተራማጆች፤ ጀግኖች፤ ጸረ ጠባቦችም የትግራይ ተወላጆች ነበሩና። ጀግናው ተስፋዬ ደበሳይንማ ከቶም ማንሳት የሚችሉ አይደሉም የዛሬ ቡከኖች!

በዚህ ተባለ በዚያ ማዘንም ንዴትም ከራቀን ዘመን አልፏል።  ፋይዳ ቢስ ነው — ከንቱዎችና ልፈፋቸውን ዘግተን ቀጥለናል።  ውሎ አድሮም አስከፊ የሆነውን የክህደትና የባንዳነትንም መዘዝ አይተነዋል። በመቆጨትና በመናደድ ሳይሆን ግን በመታዘብ የምናነሳቸው ትችቶች ምናልባትም ለአዲሱና መጪው ትውልድ ይጠቅሙ ይሆን በሚልም ነው።   ከዚህ በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ –በተለይም ወያኔያዊ ቃና ያላቸው ጽንፈኞች ብቅ ካሉ በኋላ – የትግራይ ተወላጅ በሆኑት ከላይ በተጠቀሱት ጓዶችና በነጸሎተ ሕዝቅያስ ወዘተም ላይ ክስና ውንጀላ ሲቀርብ ለመታዘብ ተገደናል።   ለብዙዎቹ ማፈሪያ ጽንፈኞች መልስ መስጠት ከቶም ፍላጎታችን አይደለም ስንል ቆይተናል።  ተያይዞ ግን ወደ ሜዳ ለመግባት የሠራዊቱ እርሾ በበረሃ ሲጓዝ ሕይወታቸ ያለፈው ብንያም አዳነና መሀመድ ማህፉዝ ትዝ ይሉኛል። መሃመድ ማህፉዝ ከወደ ጂማ አባ ጅፋር ቤተሰብ የተዛመደ ሲሆን ብንያም አዳነ ደግሞ ዘር ከተቆጠረ በውልደት ከትግራይ ነበር — እስከማስታውሰው እሱም ሆነ መስፍን፤እንዲሁም በደርግ የተደለው አንጋፋ ኢሕአፓው ዮሴፍ አዳነ የተወለዱት አዲስ አበባ ቢሆንም። በኢሕአፓ ምስረታ ከፍተኛ ሚና የነበረው መስፍን ሀብቱ የቅርብ ዘመዱ ሲሆን የሁለቱም ኢትዮጵያዊነት (የአጼው ሚኒስቴር የአበበ ረታ ዘመዶች ነበሩ) መቸም ቢሆን በጥያቄ ገብቶ የሚያውቅ አልነበረም።

የባለጌዎቹን ክስ ስሰማ ሌላ ትዝ የሚለኝ  ከአሜሪካ ተመልሶ በደርግ የተገደለው በውልደቱ ኤርትራዊ የነበረው ሙሉጊታ ሱልጣንም ነው። ያኔ በዚያ ጊዜ ውልደትና ዘር ጎሳ አንጠያይቅም ነበርና ሙሉጌታ ሱልጣንን ውልደቱን ያወቅኩትም ከተሰዋ በኋላ ነበር።  ብንያም አዳነ ከአልጄሪያ ወደ ሞስኮ ሄዶ እህቱንም (በኋላ መኢሶን የሆነችውን )ና ሊሎችንም ውደ ድርጅቱ የመለመለው እሱ ነው።  ወደ እነ ጸሎተ ልመለስና ጸሎተ ሰፈሩ (ጣሊያን ሰፈር) ከእኔም ሰፈር ጋር (ዮሐንስ) ስለሚቀራረብ እንተዋወቅ ነበር። በዩኒቨርስቲም በፖለቲካውም ተገኛኝተን የቅርብ ጓደኞች ሆንን። የጸሎተም ሆነ በወያኔ ደብዛው የጠፋው ይስሓቅ ደብረጽዮን (የመርካቶው ልጅ) ውልደታቸው ከትግራይና ኤርትራ መሆኑ ያወቅኩት ከተዋወቅን ብዙ ጊዜ በኋላ በአጋጣሚ እንደነበርም ትዝ ይለኛል። ለማንኛውም ጸሎተና ወንድሙን ያሳደጉት እናቱ የተቸገሩና ፍዳ የተቀበሉ ቢሆኑም አንድም ጊዜ ልጆቻቸውን ፖለቲካ ተዉ ወዘተ በሚል ሲጨቅጭቁ ያልተደመጡ ነበሩ።  ጸሎተ ከርቸሌ ታስሮ ሳለ እኚህ እናቱ ሊጠይቁት ሲሄዱ ከእሱ ጋር ጥቂት ጊዜ አጥፍተው በሰፊው የሚጠይቁት አለም በቃኝ ይባል በነበረው የነበሩትን ጠና ያሉ እስረኞች እንደነበር አስታውሳለሁ። ጸሎተ ጋ ብዙ አልቆዩም ስንላቸውም እሷ ምን ጎደላት ጎረምሳ ናት፤ ጓደኞቿ ጋር ናት ብለው ያስቁንም ነበር።  የጸሎተ እናት እንደ ደብተራው እናት ልጃቸውን አንቺ ብለው ነበር የሚጠሩት። አኩሪ እናት።  የጸሎተ ታናሽ ወንድምን ይትባረክን በጣም ባላውቀውም ያው አሜሪካ ለትምህርት ሄዶ፤ ኢሕአፓ ሆኖ፤ ከዚያም አቋርጦ እንደ ሰማዕት ሙሉጌታ ዜናና ክፍሉ ከበደ ወዘተ ለትግል ተመልሶ፤ በኢሕአፓነት በቆራጥነት ሲንቀሳቀስ ቆይቶ፤ በባንዳው ፍቅሬ መርዕድ ግድያ ላይ ተካፍለሃል በሚል ተይዞ፤ በሰናይ ልኬ ሳይቀር አሰቃቂ ግብረ ስየል ደርሶበት በደርግ 23 ኢሕአፓዎች (እነ ዘርዓ ብሩክ አበበ፤ ውብሸት፤ ወዘተ) ሲረሸኑ የተገደለ ነው።  ጸሎተም ወደ አሲምባ ዘልቆ በዚያው ህይወቱ አልፎ እናቱ አለወንድ ልጆቻቸውና ጧሪ ቀርተዋል።   እነዚህ ጀግና የኢሕአፓ ልጆችና ድሃ እናታቸው ናቸው ታዲያ ትግሬ በሚል ሰበብ የሚወገዙት? ለማን ተሰቃዩ፤ለማን ተሰዉ? ለትግራይ? ለጨቋኝ ? ለመሆኑስ የትግራይ ወንድም እህቶቻችንን – በኢትዮጵያዊነት የተሰዉትን የታገሉትን- ባልሆነ የሚከሱት እነማን ናቸው ብለን ብንጠይቅ መልሱ ድብቅ አይደለም። የውዥንብር ዶክተሮች በርግጥኑ ዛሬ ፈልተዋል፤ ወያኔም በለስ ቀንቶትሥልጣን ከመያዙም በላይ ገንዘብ አለውና መሃይምነቱን ሳይቀርፍ ዶክተር ተብሎ ይደንስብናል። ጅሎች በዚህም በዚያም ነግሰውብናል–በዚህም ዘመናዊው ዳግም–ውስኪና ኮኛክ–በቃኘው ጎጂ ሚናቸው ያደረሱት ጉዳት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ወደዚህ ርዕስ የገባሁት በአሁኑ ጊዜ ወያኔ ሀገራችንን ወደ አስከፊ አዘቅት ሊወረውር  ተነስቷልና አንደምታውን እንድንመዝንም ነው። የስብሰባ መዥገሮች -ሳልሚዎች- ያልኳቸው ክፍሎች–ስብሰባ ከተጠራ ጠቀመም አልረባም ሳይሉ ሁሌም ተገኝተው ሚዘባርቁ፤ ይህን  ወልፋቸውን ለማርካት ነጋ ጠባ ዋጋ ቢስ፤ ጉንጫ አልፋ ስምሪት ላይ ሚውሉ ሁኔታውን በበቂ አንደፋርሰው ሊመጣ የሚችለውን ችግር ለማስወገድ አስፈላጊው የጥንቃቄ እርምጃ እንዳይወሰድ ቢያግዱም  አደጋው ግን አፍጦ መጥቶብናል።  በውጭ ሃገሮች ባለፈው ሰሞን ይህን ዓይነት ርባና ቢስ ስብሰባዎች ሲካሄዱ ታዝበናል። ወያኔ በእሱ ብሶ ብሄር ተኮር ጥቃት ተስፋፋ በሚል የኢትዮጵያ ሕዝብ ጸረ ትግሬ ዘመቻ ላይ እንደተሰማራ አድርጎ ማቅረቡን መርጧል።  ይጠቅመዋል–የትግራይ ተወላጆችን አስፈራርቶ ከጎኑ ለማሰለፍ። ይህን የወያኔ ቅጥፈት ያጀቡት መኖራቸውም አሳዛኝ መሆኑ ሊሰረዝ የሚችል አይደለም።  ጸረ ትግሬ ቁጣ ሊነሳ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ግን የሚካድ ሊሆን አይችልም። ወያኔ ከተሳካለት የትግራይን ሕዝብ ከመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ አጣልቶ–እስራኤል አይሁዶችን አሰባስባ በአረቦች ላይ ጠንክራ እንደቆመችው ሁሉ፤ ከጎኑ አሰልፎ የስልጣን ዕድሜውን ሊያራዝም ዕቅድ አለው። አሊያም የትግራይን የመገንጠል ዕቅድ እስካሁንም እንዳልተወና የወሎ ጎንደር ለም መሬት ዝርፊያውም ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። የትግራይን ሕዝብ ወያኔ ለአደጋ ሲያጋልጠው ይህንን ሕዝብ ደግሞ በጣም የጎዳው ክፍል የትግራይ ምሁሩና የተማረው፤ ማለትም ከተሜው ንዑስ ከበርቴው ነው። ከወያኔ ጎን በመቆምና ዘረኝነትን አቅፎ በሕዝብ ላይ በመፈንጨት የትግራይ ተወላጅ በጅምላ ይጠላ ዘንድ ሆዳሞቹ ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል። ዛሬ ብዙዎች እሳት ካየው ምን ለየው፤ ትግሬ ሁሉ ያው ወያኔ ነው ብለው ቢደመድሙ ምክንያት አላቸው የሚያሰኘውም ይህ ነው። ከኢትዮጵያና ከሕዝቧ ጋር የቆሙ የትግራይ ከተሜዎችና ምሁሮች በርግጥም ጥቂቶች መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው። ወያኔ ለ 27 አመት በስልጣን፤ 17 ዓመት ትግል በሚለው ሲፈትለው የቆየው የዳሞትራ ድር ነው።  መርዘኛ።

በመሆኑም እየተካሄደ ያለው የሕዝብ ትግል ወደ ዲሞክራሲ ሳይሆን ወደ ብጥብጥና ፍጅት እንዲያመራ ወያኔ ባለው አቅም ሁሉ እየጣረ ነው። ይህንን ጥረቱን በየፊናቸው የሚደግፉት እንዳሉም እናውቃለን። በጎራዴያችን የአማራና የክርስቲያንን አንገት-ራስ ቀልተን ደም እናፍስ የሚሉት ጠባብ ምሁሮችን ጸረ ኢትዮጵያ  ውርጋጦች ምሳሌ ናችው። ካመቸን እንገነጠላለን ብለው ሚያጓሩት ደግሞ በዚሁ ሕዝብን ወደ ስጋት ጥለው ለወያኔ ከወደቅኩ ኢትዮጵያ ትጠፋለች ልፈፋ ተዓማኒነት ይሰጣሉ። ወያኔ ትግሬዎችን በየከተማው አስታጥቋልም ሲባል የቆየ ነው። እነዚህ ዘመሚቶች ደግሞ ግንጠላን ተዉ፤ ማንነታችሁ አትካዱ፤ ከሕዝብ ጋር  ሆናችሁ በኢትዮጵያ አንድነት ስር ችግር ለሚባለው ሁሉ መፍትሔ ፈልጉ ቢባል ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ለትግላችን ጋሬጣ ከመሆን አልተቆጠቡም። ይህም በተለይ የሚመለከተው አስመራ የመሸጉትን የኦጋዴን ግንባርና ኦነግን ነው። የግንጠላ አቀንቃኞችን በአስመራ አቅፎ ያለው ሻዕቢያም ለሀገራችን አንድነት ያሰጋል፤ ፈንጂ አጥምዷል የሚሉ ክፍሎችም ስጋታቸው ለትግላችን ያላቸውን አመለካከት ሊቃኘው ይችላል ብንል ስህተት አይሆንም። ወጣ ወረደ ወያኔ ባቀደው ተስካቶለት አንድም በስጋት ትግሉ ከቆመለት (የማይሆን ነገር ነው በአሁኑ ጊዜ) ወይም ሕዝብን እርስ በርስ ካፋጀና በትግራይ ሕዝብ ላይም ፍጅትን ከጋበዘ (በዕቅድ የተያዘ ነው) የሀገራችን ታሪክ  ላይ የሚያኮማትርና የሚያሳዝን ምዕራፍ ይጽፍብናል።  ነጋ ጠባ በዘረኝነት የሚቧርቀውና ንጹህ ዜጎችን የሚገድለው፤ የሕዝብን መደበኛ የበቀል ስሜት የሚያራግበው ለስልጣኑ መቀጠል የትግራይን ሕዝብ በነቂስ ከጎኑ ማሰለፍ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ነው።  ይህንን በመረዳት ከዚህ በቀጣይነት ሊመጣ ከሚችለው ከጥፋት ጉዞና ስምሪት ለመቆጠብ ሕዝብ ሙሉ ጥረት ማድረግ አለበት እያልን፣ ይህን ጥረት በቅድሚያ ሲሞክር መታየት ያለበትም በትግራይ ሕዝብ ነው እንላለን።   ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚል ዕምነታችን ጽኑ እንደሆነ ሁሉ በአንጻሩ ውቃቢ የራቃቸውና ጅላጅል የፖለቲካ መሪዎች ሀገርን ሊያጠፉ እንደሚችሉ በሶቭየት ህብረትም በዩጎዝላቪያም ያየነው ነው።  የኢትዮጵያን ጥፋት የሚፈልጉ የውጭ ጠላቶች ደግሞ አላጣንም።

ጠላትና ወዳጅን ለይቶ ማወቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ማወቅም አለብን ሲባል ቆይቷል። “ሞኝ ልጅ የአባቱን ገዳይ አባባ ይላል” የተባለው አለምክንያት አይደለም። የቻይናው የጦርነት ስልት ጸሓፊ ሱን ዙ ጠላትክን እወቅ፤ ከዚህም በላይ ራስክን እወቅ፤ መቶ ጦርነት ብትገጥም ሁሉንም ታቸንፋለህ ብሎ ነበር። በእኛ በኩል ማን ነው የሀገራችን ጠላት በሚለው ላይ ብዥታ ያሳየን የያዝን አይመስለኝም። ትግል ግድ የሚለውን ድጋፍ እዚህም እዚያም ለማግኘት ብንሞክርም በረጂዎቹ (ያውም ከተገኙ )ማንነት ላይ አልተደናገርንም ማለት እንችላለን። በአልጄርስ ከተማ የተገናኘናቸው ቬትናም፤ ኩባ፤ ቻይና ወዘተ ሊረዱን ጭራሽኑም ፍላጎት አላሳዩንም።  ሰሜን ኮሪያ ለኪም ኢል ሱንግ መልካም ልደት ምኞት ጻፉለት ማለት እንጂ ሌላ አቅዋም አልነበራቸውም።  የሰውየው ተክለሰውነት ደግም ጸረ ሶሻሊስትና አቅለሽላሽ ነው በማለታችን ራቅናቸው እንጂ የፈየዱልን የለም። ከሶማሊያ እርዳታ ብንጠይቅም ሶማሊያ የድርጅት ተወካያችንን አስራና በትግላችንም ላይ ሻጥር ለመፈጸም መዝመቷን አልሳትነውም። በደቡብ የመን ኤደን የከፈትነው ቢሮም በራሳችን ሲሆን ከደርግ ካልተስማማችሁ ብለው ሊጫኑን ሲሞክሩ ዘግተነው ወጥተናል። በደርግ የመጀመሪያ ሰሞንም ቻይና ራሷ ከመንግስቱና ሀይሌ ፊዳ ጋር ተቀራርባ፤ ለደርግ ጦር ክላሺንና ሲሜኖቭ ጠመንጃ አስታጥቃ ደርጉን ደግፉ ስትለን ጆር አልሰጠናትም። በአጭሩ ለማንም ያጎበደድንበት የሀርን ጥቅም አሳልፈን የሰጠንበት ሁኔታ የለም። ሻዕቢያም ሆነ ጀብሃ ሊያዙንና የሀገራችንን ጥቅም ማስቀደም እንድንተው ሊያደርጉን፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ሊያሰኙን አልቻሉም።  የጣሊያን ዜጎችን በጣና በለስ ስንጠልፍ የሱዳን አል ሳዲቅ አል ማህዲ አገዛዝ ልቀቋቸው ሲለን  እሱን ተወው አያገባህም አልነው እንጂ ማንንም በዚህ የተነሳ አለቀቅንም። ፋሺስቱ ኮለኔል የሶማሌን ወረራ ሰበብ አድርጎ ኢሕአፓን በአፍቅሮ ሶማሌ ሲከስና ሀሰቱንም በአዞ እንባ ሲያጅብ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር በጸረ ድርጅት ቅኝት ሊነዳ ጣረ እንጂ ሶማሊያን በመቃወም ሆነ በሶማሌ በመገደል ኢሕአፓ ስሙ ይነሳል እንጂ በሶማሌ ወረራ ደጋፊነት አይጠቀስም። ዛሬ በቶሮንቶ በስደት ላይ ያለው ኮለኔል አባስና መሰሎቹ በሸለምቦትና ሌሎች ቦታዎች በጓዶቻችን ላይ የፈጸሙትን ግድያና ግብረ ስየል ጠንቅቀን እናውቃለን። የደርግን ውሸት በማዳበር በታጠቅ ጦር ሰፈር ጠርሙስ ፈጭቶ በምግብ ከቶ ሚሊሺያውን ገደለ፤ በሀገር ጦር ላይ ከጀርባ ተኮሰ፤በሐረር ሶማሌን ደግፉ ብሎ ለተከታዮቹ መመሪያ አስተላላፈ ወዘተ የተባሉት ሁሉ –የኮለኔሎቹና ሻለቆቹ–ቀጣይና የቀመሉ ውሸቶች–ልብ ወለዶች- መሆናቸው ግልጽ ነው። ግን ከዚህ በፊት እንዳሰፈርኩት ውሸት ሲደጋገም የተባለ የናዚ-ፋሺስት ፈሊጥን ይዘዋልና የጅል ለቅሶ ዓይነት ይደግጋሙታል። ታሪክ ይፈተሽ ከተባለም ለሚነዛው ውሸት ማጠየቂያ የጽሁፍም የሀቅም ምንም መረጃ የለም። ወያኔ ግን የዚያድ ባሬ ወዳጅና ተባባሪ ሆኖ ከርሞ ዛሬ ዓይኑን በጨው አጥቦ በኦጋዴን ጦርነት ልንሳተፍና ሶማሊያንም ልንወጋ ጠይቀን ነበር ሲል ቀጥፏል። ከመቶ ውሸት አንድ እውነት ይሻላል የሚለውን በትግሪኛ አልተጻፈም መሰል እነ ስብሃት ነጋ ጨርሶ አያውቁትም ያሰኛል። አልሰማ አሉት እንጂ ወገናችን የትግራይ ሕዝብ ሓቂ ሚዛን ወርቂ ብሏቸው ነበር።

ወያኔ በዘረኛነት የተካነ ቡድን ነው ቢባል ስህተት ወይም ማጋነን አይሆንም። ትግራይን መገንጠል የሚል መርሃ ግብር አውጥቶ ይህ አላስኬድ ሲለውና የትግራይ ህዝብም ታሪክ ገደፍክ ሲለው የትግራይ ሰፊ ሕዝብ በሸዋ አማራ ተጨቁኖ መገንጠል ስለፈለገ ልናስተወው በሚል ድምጹን አስተጋባን እንጂ ልንገነጠል አይደለም ሲል ቀጥፏል። መገንጠል የሚለውንም የኤርትራ ግንባሮች የሚጠይቁትን ነጻነት ያቀልብናል በሚል የትግራይ መገንጠል ለሚለው ብዙም ፊት ሳይሰጡት ቀርተዋል። ይህን የመገንጠል ፍላጎት ወደ ትግራይ የበላይነት አቅዋም ለመለወጥ ወያኔ ሲነሳም በጠላትነት አውቆ የፈረጀውና ሊያጠፋም የተነሳው ኢትዮጵያዊነትን ነው። ዘጠኝ ጊዜ ድርድር ብናደርግም ወያኔ አማሮች ናችሁ አባይ ኢትዮጵያ ከትግራይ ውጡ ብሎን ያው ወደ ውጊያው አምርተውብናል። በመሆኑም በኢሕአፓና ኢዲኅ ላይ ጦርነቶችን ወያኔ ከፈተ። ከጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ጋር አብሮ ሀገራችንን አጠቃ። ወያኔ የሀገራችንን ደንና መሬት ለሱዳን ሊሰጥ የተነሳው ገና ጫካ እያለና በከሀዲዎች ድጋፍ ወደ ወልቃይትና አርማጨሆ መዝለቅ ከቻለ ጊዜ ጀምሮ ነበር።  የደቡብ ሱዳን ስደተኞችንም መንገድ  እያፈነ ለሱዳን ወታደር በማስረከብ በየሱዳኑ እርሻ (መሽሩዕ) አስገድሏል፤ ኢሕአፓም የደቡብ ሱዳኖች ሰፈር በነፍሶ ገበያ ተራራ /ቋራ/ ላይ መስርቷል በሚል ክስም ከሱዳን ጥቃት አስደርሶብናል። ምጸት እንበለው ትራጀዲ-ድራማ የደቡብ ሱዳን መሪ ሊሆኑ የቻሉት እነ ሳልቫ ኪርና ሪያክ ማሻር የወያኔ ወዳጅ ለመሆን ሲሰግዱ ልናያቸውም በቅተናል። ወያኔ በሰይጣናዊ ጽናት ኢትዮጵያ ሊያጠፋ ሲጥር፤ የውስጥ አርበኞቹ እነ ገብረ ህይወት፤ ደስታ፤ኮለኔል ፍስሃ ወዘተ  እየረዱት ና ኋላም ምዕራባውያንና አረብ ሀገሮች በረሃብ ሽፋን በሰጡት ሰፊ ድጋፍ ሲጠናከር ይህን ሁሉ በጽናት ሲታገል የነበረው ኢሕአፓ ለመሆኑ ማንም ዛሬ አሌ ሊል ሊነሳ አይችልም። ወያኔ ዳባት ደርሶ የጎንደር የያኔው አስተዳዳሪ ገዛኸኝ ወርቄ በኢሕአፓ ላይ ዘመቻ ያስተባብር እንደነብር እናስታውሳለን።  በባዕድ ሀገር–በተለይም በሰሜን አሜሪካ–በርካታ ዜጎች ወያኔ ኢሕአዴግ ነኝ ብሏል በሚል ድጋፊ ሲሰጡት እንደነበርና ድርጅታችንንም በአክራሪነት ሲከሱ መቆየታቸውን አልረሳንም። ከነዚህ ብዙዎቹ አሁንም የመድረክ መዥገር ሆነው አላናግር አላስተነፍስ ያሉ የወያኔ የውስጥ አርበኞችና ምስጦች ሆነውም እናያለን። ወያኔን ስንታገልና በገንጣይ ሀይሎች በሞላ ስንጠቃ አብሮን ተሰልፈው መስዋዕትነትን ከከፈሉ አባሎቻችንና ሕዝብ ውጪ ሌላው ከጎን ቆሞ ወይም ከሩቅ ተመልካች ሆኖ አሊያም የወያኔ ተማጓችና ደጋፊ ነበር ብንል ሀቅን ማቅረብ እንጂ በማንም ላይ ጣት ለመቀሰር እንዳልሆነም ግልጽ ሊሆን ይገባዋል።

ለድክመታችን በቅድሚያ ተጠያቂ ራሳችን ነን። ለፈጸምናቸው ስህተቶች በአራተኛው ጠቅላላ ጉባኤያችን–በ1972 ዓ.ም.–በጭልጋ ባደረግነው ስብሰባ በሰፊው ተወያይተንበታል። የዚህ ውጤቱ በአንድ በኩል አሉታዊ እንደነበርም የጠቀስን ቢሆንም (ለእውነትም ጊዜ አለው እንዲሉ) ለጥቃት የተጋለጥነው በራሳችን ድክመትም መሆኑን ግን ለመሸፈን ምንም ፍላጎት ኖሮን አያውቅምና ዝርዝሩ በተመለከተ ሀሰተኞችን ማሳረፍ ደግም ግዴታችን ሆኖ ይገኛል። ድርጅታችንን በከፍተኛ ደረጃ ከመጉዳት አንጻር አንጃ ያልናቸው የውስጥ አጥፊ የፖለቲካ ባዙቆች በቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው። በአሲምባ ተከሰተ ከተባለው አንጃ ውጪ ሌሎቹ አንጃዎች በሞላ ውልደታቸው ለጠላት እንመች እንገብር ከሚል አቅዋም የጀመረ ነው።
የመጀመሪያው አንጃ ብቅ ያለብን በአዲስ አበባ በብርሃነ መስቀልና በጌታቸው ማሩ መሪነት ሲሆን በዚህ ሂደት ዋናው ተዋናይ ብርሃነ መስቀል ነበር። ለምን እንዲህ ሆነ የሚለውን በበቂ ለማስረዳት በቅርብ አውቀው የነበረውን ብርሃነን ማንነት በተወሰነ ደረጃ ማቅረብ ይኖርብኛል። እሱ ክሊክ ብሎ ሊከሳቸው ከተነሳው ከነተስፋዬ ደበሳይ፤ ዘሩ ክህሸንና ሌሎቹ ይበልጥ እሱን የማውቀው ስለነበርም ሀቁን ማቅረብ ግዴታየ ነው። ብርሃነ መስቀል የአይሮጵላን ጠለፋ ሀሳብ ሲሰረጽ በከርቸሌ የነበር ቢሆኑም ተፈቶ ሲነገረው ግን ዋና ተስማሚ ሆኖ የድርጊቱና የተከተለው ሂደት ዋና አካል ሆኗል። ብርሃነ መስቀል የነቃና በተማሪው ማህበር በንግግርም በጽሑፍም ብዙ አስተዋጾ ያደረገ ሲሆን ታዋቂ የተማሪዎች መሪ ነበር።  በሀገር ቤት በቅርበት ባላውቀውም–በዕድሜም ታላቅችን ነበርና– ያው አስከፊ ስደት ጓዶች እንድንሆን አድርጎናል። ብርሃነ መስቀል በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩና ከፍተኛ ቦታ አለኝ ብሎ የሚያምንና ይህንንም ታሪኩን ለመጻፍ የሚያስችሉ በርካታ ሰነዶችን በቦርሳ ይዞ አይሮጵላን ላይ የወጣና በገቢር መሪ ለመሆን ብቁ ነኝ ብሎ ያመነና የተሰናዳ ነበር።  ብዙዎች ያደንቁት ስለነበርም ምናልባትም ስለራሱ የነበረው ግምት ትንሽ የተዛባ ሊሆን ሳይችል አልቀረም ማለትም እችላለሁ። እኔ ስለ ግለሰቦች ሀቀኛ ታሪካቸው በዚህ ዝርዝር ልገባ ቅንጣትም ፍላጎት የሌለኝ ቢሆንም የማነሳው ከተከሰተው ሁኔታ አንጻር ንክኪ ያለውና ሀሰቶችን በተመለከተ መሆኑ እንዲያዝልኝም እጠይቃለሁ። ብርሃነ መስቀል ለብዙዎች ንቀት ስለነበረውም ብንያምና እኔ ወደ ሜዳ እንድናጅበው የተወሰነው ምናልባትም  ሊቆጣጠሩት ሊያረግቡት ይችሉ ይሆናል በሚል ነው። በአልጄርስና በድርጅት ምስረታው ሂደት ብርሃነ የሚጠበቅበትን ያከናወነ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የነበሩት አሉታዊ ጠባዮቹ ችግር ፈጣሪ ሊሆኑ እንደሚችሉም ግልጽ ነበር። በአልጄርስ ሳለን የተወሰኑትና የተጻፉት ሁሉ በጋራ ቢሆንም እነ ሀይሌ ፊዳ ሳይቀሩ ሁሉንም አድራጊና ሰሪ ብርሃነ ብቻ መስሏቸው ቆይቷል። በምስረታ ጉባኤው ላይ ዋና ጸሃፊ ሲባልም ይህንን እንደ ስታሊን በፈላጭ ቆራጭ ደረጃ በመውሰዱ በሜዳም በአዲስ አበባም ከጓዶች ጋር ሰምሮ ሊሰራ የማይችልበት ሁኔታ ላይ አድርሶታል። ውጤቱም እንደታየው አስከፊ ነበር።

የሰፈር ልጆች ብንሆንም በቅርበት የማላውቀው ጌታቸው ማሩ ላይ ይህ ነው ብዬ የምናገረው የለኝም። የተማርኩት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከታላቅ እህቱ ከውድነሽ ማሩ ጋር ነው።  ወንድሞቹን የማውቀው በሩቁ ነው። ጌታችው ሳውቀው በመጀመሪያ ፖለቲካ ውስጥ አልነበረም።  ወደ 1968 ዓ.ም.  (እ/ኤ/አ) ወደ ፖለቲካ መግባት መጀመሩን በአራት ኪሎ በተደረገ የተማሪዎች ስብሰባ አይቻለሁ። ከዚያም ስለሱ የሰማሁት በዩኒቨርስቲ ከነጸጋዬ ጋር አለመግባባት ተፈጠረ ሲባል ሲሆን የችግሩም መንስኤ የእኛ ጓዶች (እነ ጸጋዬ ወደ ድርጅት ስራ ለማተኮር ራሳቸውን ከይፋ እንቅስቃሴ እንዲርቁ በተነገራቸው መሰረት)  ደብዘዝ ሲሉ፣ እነ ጌታቸው ደግሞ ሊመረቁ ሲሉ እነ ጸጋዬ የመሸሽ ዝንባሌ ያዙ በሚል የያዙት አቅዋም ነበር። ኋላም እነ ጌታቸው አብዮት የሚል ቡድን ሲያቋቁሙና መራራቁ አይጠቅምም ሲባል ሳሙኤል ዓለማየሁ ሀላፊነት ተሰጥቶት ከአሜሪካ ሲመለስ እነ ጌታቸውንም እነ ጸጋዬንም በማግኘትና በመተባበር አንድ ሊሆኑ የሚችሉበት ሂደት እውን ሊሆን ችሏል። ጌታቸው የድርጅታችን ፖሊት ቢሮ/ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ/ አባል ሆኖ ሲመደብ ጸጋዬም እኔም የዚህ ኮሚቴ አባል እንዳልነበርንም መጥቀስ እፈልጋለሁ። ጸጋዬ ወደ ሜዳ ስለሄደና እኔም በውጭ ስለቆየሁ በሀገር ከጌታቸው ጋር በስራ አንተዋወቅም። ብርሃነና ጌታቸው በኋላ አብረው መቆማቸውን ብርሃነ ራሱ ገልጾታል። ቢሆንም ግን ከደርግ ጋር አብሮ የመስራቱ ውሳኔ አቀንቃኝ ብርሃነ ለመሆኑ በበኩሌ ጥርጥር የለኝም።  በኤርትራ ሜዳ ሳሉ ጀምሮ የሠራዊቱ እርሾዎችና ብርሃነ መስቀል ስምምነት አልነበራቸውም።  በአሠራሩ ላይም ብዙ ሂስ አቅርበዋል። ወደ ደርግ የከዱት ስምንቱ (በመሰረቱ የየራሳቸውም የፖለቲካ ድክመቶች ነበሯቸው) በእሱ ላይ ብዙ ክስ አቅርበውም ነበር።

ድርጅቱ ከተመሰረተ በኋላ በአዲስ አበባና ሀገር ቤት በህቡዕ ተንቀሳቅሶ፤ የመርሃ ግብርም እርምት ተደርጎ፤ በመዲናይቱ በምስጢር በ1967 ዓ.ም. በተደረገው መለስተኛ ጠቅላላ ስብሰባ /ኮንፈረንስ/ ላይም የዋና ጸሃፊ ቦታ ሊሰረዝ በመወሰኑና ብርሃነ መስቀልም ከቦታው በመነሳቱ ከፍተኛ ተቃውሞን አሰምቷል። በመስራች ጉባኤ የተመደብኩትን ኮንፈረንስ ሊያነሳኝ አይችልም፤ አይገባውም በሚልም ለእኔም ሳይቀር ተቃውሞውን ጽፎ አስታውቆኝ ነበር። ወደ ሜዳ አትመልሱብን የሚል ጥያቄም ስለነበር በአዲስ አበባ በህቡዕ እንዲሰራ ተደረገ። ብርሃነ ተቀይሞ የቆየ ሲሆን የመኢሶኖች ብቅ ብቅ ማለትና በሥልጣኑም መድረክ መግነን እንዲሁ አስቆጥቶት ነበር። እኛ መያዝ ያለብንን ቦታ እንዲይዙ ለቀቅንላቸው ነው ያለው በላከልኝ ከ 30 ገጽ በላይ ደብዳቤ። ደርግ ተራማጅ እንጂ ፋሺስት አይደለም በሚልም ክርክሩን በሰፊው አቅርቦ አብረን ከደርግ መስራት አለብን የሚለውን መልዕክትም ሊያስተላልፍልኝ ሞክሮ ነበር። ከዚህ በተያያዘም በሶስት የድርጅቱ መሪዎች ላይ አሉታዊ ትችቶችን ሰንዝሮ እንደነበር አስታውሳለሁ። ብርሃነ ከደርግ እንስመር ብቻ ማለት ሳይሆን በውስጥ ውስጥ–ለምሳሌ ከመኢሶን ቅርብ ከነበረው ከብርሃኑ ዘርይሁን ጋርም በመነጋገር– ህብረት ተጠራ ለማሰኘትም በምስጢር ያደረገውን ጥረት ድርጅቱ ደርሶበታል። የጌታቸው ወንድም መለሰ ማሩም የተፈሪ በንቲ ረዳት ስለነበር በዚያም በኩል ሙከራ አድርጓል የሚልም ጥቆማ ነበር። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ለደርግ ጥቃት አጸፋ ለመስጠት መነሳት አይገባም ስህተት ነው የሚለውን ሀሳብ ጌታቸውም ስለተካፈለው ሁለቱም ይህ ሃሳባችን ወደ አባላት ይውረድልን ባሉት መሰረት ለአባላት ወርዶ በአብዛኛው ተቀባይነትን አላገኘም። አወራረዱም የአቀንቃኞቹ ስም ሳይጠቀስ “ሀ” ና “ለ” በሚል ይሁን መባሉን ብርሃነ በአሉታዊ በመውሰዱ–ስሜ ከተጠቀሰ አባላት ግልብጥ ብለው ስለሚደግፉኝ እነ ተስፋዬ ፈርተው ነው በሚል–፤ልቡ ሸፍቷልና፤ የፈለገውን ይፋ መድረክ (ብርሃነ የመድረክ ሰው ነበርና) አላገኘምና፤ በራሱ ላይ በነበረው መመካት ዴሞክራሲና የብዙሃኑን ውሳኔ መጻረሩ ምንም አልመሰለውምና ወደ ጎንዮሽ ሄዶ በአንጃነት ተሰማራ። በድርጅት ውስጥ ወይም ተጻሮ ድርጅት መመስረት የሚያስቀጣ ነበርና በህገ ፓርቲው ህገ ወጥ ተባለና እሱም አንዳንድ የድርጅቱን ዕቅዶች ወስዶና ህገወጥ እርምጃ ወስዶ የተወሰኑ ተከታዮቹን ይዞ ተሰወረ። አብረው ከተሰወሩትም ሁለቱ የጸኑ የኢሕአፓ አባላት ነበሩ።  በደርግ መያዙ ግን የእራሱና ምናልባትም የጓደኛው ጥፋት መሆኑም ይታወቃል።

ወደ 36 ገጽ የሚሆን ደብዳቤውን በተመለከተ በበኩሌ የመለስኩለት የብዙሃኑን ውሳኔ ተቀበል፤ ቅሬታ ካለህ በመዋቅር ለአቅዋምህ ታገል፤ ይህ መብትህ ከታገደ እኛም አብረንህ እንቆማለን፤ ለምን ባልተገኘሁበት ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወጣሁ ብለህ ተቃወም ብሎኝ ስለነበረም፣  እኔ በታሪክ አጋጣሚ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆንኩ እንጂ በዚህም ደረጃ ለመቀጠል ምንም ፍላጎት እንደሌለኝና ከሀገር ርቆ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ትርጉም እንደሌለው፤ ከደርግ ጋር አብረን እንስራ የሚለውን አቅዋም እንዳማልጋራውና በስነ ስርዕት በድርጅታችን ስብሰባ በተባሉት ጓዶችም ላይ ቅሬታውን እንዲያቀርብ መልሼለት ነበር። ጠባዩንም አውቅ ስለነበር በራሱ የድርጅትን ህግና ስነስርዓትም በጣሰ ጎዳና እንዳይሄድም አደራ ብዬው ነበር። ከዚህ ጊዜ በኋላም ከእሱ ጋር ግንኙነት አልነበረኝም። ከዚህ ከአንጃ ሁኔታ በተያያዘ ሆነ፣ ከመኢሶን ልዩነታችን በቅራኔ አያያዝ ድክመት ሳይሆን በመሰረታዊ ጉዳይ–የሀገራችንን የነገ ዕጣን– በተመለከተ መሆኑን አንዳንዶች ሊያድበስብሱ ቢሞክሩም ሀቅ አይደለም። የነበረው አማራጭ በአንጃዎቹ ሀሳብ ተስማምቶ ከደርግ ጋር ማበር (ይህን ደግሞ አባላት በአብዛኛው አልተቀበሉም) ወይም አንጃ የሆኑት የማፈንገጥ አቅዋማቸውን ትተው፤ የብዙሃኑን ውሳኔ አክብረው መቀጠል ነበር። ሌላ መንገድ አልነበረም። አንጃነት ክህደትን አቅፎ መጣና (ሁሌም ይመጣልና) አባላትን ለደርግ አውሬዎች በማጋለጥ፤ መዋቅር በማስመታት ወዘተ ያደረሱብን ጉዳት አባላት ሁሉ የሚያውቁት ነው። የአንጃን ችግር ለመቋቋም የተወሰዱ እርምጃዎች ሁሉም ትክክል ነበሩ ማለት ባይቻልም አንጃን መቃወምና መቋቋማችን ግን ብሄራዊ ግዴታ ነበርና ልንወጣው መቻላችንም ትክክል ነበር። ከዚህ በተያያዘ ብዙውን ግዜ የሚነሳውና ድርጅቱን ለማውገዝ የመድረክ መዥገሮችና የቀይ ሽብርም ወንጀለኞች የሚጠቀሙበት የጌታቸው ማሩን አሟሟት ይመለከታል። የጌታቸው ጓደኛ ወይም ፍቅረኛ ነበርኩ የምትል ሴት የራሷን ትረካም በመጽሃፍ መልክ ማቅረቧና ወያኔም ይህንን በሀገር ሙሉ እንዲናፈስ ማድረጉን አውቀናል። በከርቸሌ መደቧ አንጃ ከተባሉት ጋርም መሆኑን እናውቃለን። ለእሷ መልስ ለመስጠት ምንም ፍላጎት የለኝም–ታሪኳን መተረክ መብቷ ነው። እኔ በድርጅታችን ላይ ጻፍን የሚሉት ጋር ያለኝ ልዩነት ልብወለድ ሲጽፉ የህይወት ታሪካችን-ሀቅ- ሳይሉ እንደ ሀማ ቱማ ልብወለድ ሲሆን ልብወለድ ብለው እንዲያቀርቡ ነው። ወደ ጉዳዩ ልመለስና ጌታቸው ለምን ተያዘ፤ እንዴትና ለምንስ ተገደለ ለሚለው  ድርጅታችን ማብራሪያ የሰጠበት ጉዳይ አይደለም። ለነገሩ ህግና ደምብ ያለው ድርጅትና ሠራዊት ውስጥ በራሳቸው ፍቃድ የሚገቡ፤ አባል የሚሆኑ የዚያ ህግ ተገዢ ናቸው።  ህገ ፓርቲያችን ካጸደቁት መሪዎች ደግሞ ብርሃነም ጌታቸውም ይገኙበታልና ለህጉ ተገዢዎች ናቸው። በህጉ መሰረት በሞት የሚያስቀጣ ህግን ጥሰው ከተገኙ የሞት ቅጣት ሊፈጸምባቸው የሚጠበቅ ነው ማለት ነው። በማንኛውም ሰራዊት ለምሳሌ ሽሽት ያስቀጣል–መለስ ዜናዊ ፈርጥጦ ለሞት የሚያስቀጣው ጥፋት ሆኖ ሳለ ምህረት የተደረገለት በዝምድና ምክንያት መሆኑን ወያኔዎቹ ራሳቸው ነግረውናል። በሠራዊታችን ውስጥም የምስጢር ሌላ ቡድን የፈጠሩና ጥፋታቸው የተረጋገጠባቸው የተወስኑ ሲቀጡ ሌሎች ደግሞ በምህረት ተለቀዋል። ማለትም ጌታቸው በአንጃነት ተሰማርቶ የሚያስቀጣ ጥፋት ላይ ከተገኘ መቀጣቱ የሚጠበቅ ነው ማለት ነው። ከዚህ ባሻገር ግን ጌታቸው እንዴት ተገደለ ለሚለው በቅድሚያ የኢሕአፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ግደሉት ወይም ይገደል በሚል ወስኖበት እንዳልሆነ እኔ አውቃለሁ። በወቅቱ በአሲምባ እኔም፤ ዘሩም፤ጸጋዬም፣ ካልዘነጋሁ ጸሎተም የነበርን ሲሆን በየትኛውም ጊዜ በዚህ ላይ ወስኑበት ብሎ አልተጠየቅንም። በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገቢ ነው፤ ነጻ ከሆነ ደርግ ጋር ተጠቃሎ ጉዳት ያደርስብናል (ምስጢር ያውቃልና) የሚለውን አቀራረብ ግን በአሉታዊ ያየነው እንዳልነበረም አስታውሳለሁ። በአሠራራችን ማንኛውም የአመራር ኮሚቴ አባል የሰራውን ስህተት የእሱ ነው ብለን በግለሰቡ ላይ ጭነን ዞር የምንል ሳንሆን በኮሚቴው ደረጃ ስህተቱን ስንቀበል የቆየን በመሆናችን ዝምታችንን በዚህ መልኩ አይተን አለፍነው እንጂ ዛሬ እንደሚሰማው ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሳይቀር ክሱን ወደ እኛ ሊሰዱ ሲነሡ አበዛችሁት በሚል ማሳሰብ እንገደዳለን።   በሜዳ አንጃ ዳኛም ፍርዱንም አጽዳቂ የሆኑ ግለሰቦች ለምሳሌ ዛሬ የወያኔ ድምቢጥነትን መርጠው በነጻ ይለቀቁ ያለውን ጸጋዬ ደብተራውን ና በቦታው ጭራሽ ያለነበርኩትን እኔን በጥፋተኛነት ሲከሱም ማዳመጥ ተገደናል።   ትግል የተማሪ ማህበር እሰጥ አገባ ወይም ብርሃነ ይወድ እንደነበረው ፈንጠር ፈንጠር ብሎ ድስኮራ አይደለም።   የሞትና የሕይወት ጉዳይ ነው።  የተማሪ ማህበርና ድርጅት ሠራዊት አንድ አይደለም። ፈርቶ ፈርጥጦ ጓዶችን ለአደጋ ማጋለጥ፤ የሠራዊት ንብረትን ጠመንጃን ወዘተ ይዞ መክዳት፤ መክዳት በአጠቃላይ ያስቀጣል። ይህን የማይቀበሉ በዚያው በሩቁ ቢሆኑ ይመረጣል ማለት ነው። ለነገሩ ከዳ፤ ሸሸ፤ አሴረ፤ ህግ ጣሰ ያልነውን ሁሉ እንደ ወያኔ ብንገድል ኖሮማ ዛሬ በውጭ ሀገሮች ተደላድለው የሚኖሩ ስንቶቹ በየበረሃውና ጫካው በቀሩ ነበር። ራሳቸውም ይህን ሀቅ ያውቁታል።  ከዓመታት ትግልና ስቃይ መከራ በኋላ ሌላ የተከሰተብን አንጃ ከወያኔ ጋር ሰምረን፤ ፈርሙ የሚለንን ፈርመን እጅ ሰጥተን እንስራ ያለው የመጨረሻው አንጃ ነው። በችሎታም ሆነ ተከታይ በማግኘት ይህ አንጃ ቅራሪ ቢሆንም፤ከመጀመሪያው የሚወዳደሩ መሪዎችና አባላት ባይኖሩትም ተከፋፈሉ በሚል ያደረሰው ጉዳት መኖሩን መካድ አይቻልም። ይህኛው አንጃ የድርጅቱን ስም የራሴ ብሎ ሊጠቀም መነሳቱና ከድርጅቱ ጸሮች ጋር ሁሉ ሊገጥምና ድርጅቱን ሊጎዳ መነሳቱ፤ አጠፋን በልና (በአቅዋሙ ሳይሆን ጉባዔ ረግጦ በመውጣቱ) ወደ ድርጅቱ ተመለስ ቢባልም አልሰማ ማለቱና በተለይም ዋናውን ድርጅት ይጠፋል ብሎ በመገመቱ እነሆ በፖለቲካ ምድረበዳ ቀርቷል። ሳይውል ሳያድር–ድሮም የደርቡሽ ስምምነት ነውና–ሊከፋፈል ችሏል። በአልሞት ባይ ተጋዳይ ዛሬም አለሁ ሊሉ የሚቃጡ ጥቂቶች ቢኖሩም አንድ ጓድ እንዳለው ሟቾቹ ብለናቸው ዶሴያቸውን/ፋይላቸውን ከዘጋን ዓመታት እነሆ አልፈዋል። ከወያኔ መስማማት የሚሉትን ወያኔ በበኩሉ ማን ሊስምሽ ብሎ ስለዘጋቸው አልሰራላቸውም–ዛሬም ግን ከወያኔ ለመጣመርና የይስሙላ ሽግግር በሚል ገብቶ ፍርፋሪ ከስልጣን ለማግኘት እነሱም መሰሎቻቸውም እየጣሩ ናቸው።

ትግል ሳይታገሉ የሚሰለቹ ጉዶች እንደበዙ ሁሉ ለፋን ደከምን በቃ ለማለትም ፍንጥር ፍንጥር የሚሉ አስመሳዮች እንዲሁ አሉ። ዛሬ የወያኔ ውድቀት ሊመጣ ጫፍ ላይ ሲደርስ ከዚህ በፊት ይህ ዓይነቱ ድል ላይ ደርሰን ለምን እንደተነጠቅን ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ሁሉን አቀፍ ህብረትና ሽግግር ስንልም በመሰረቱ ጸረ ወያኔና ኢትዮጵያዊ ህብረትና ሽግግር መሆኑን መዘንጋት የለብንም።  ይህ ላይ ብዥታ በያዝን ቁጥር ተሸንፈናልና ስህተት መድገሙ አይጠበቅብንም።   መለስተኛ ቅራኔዎችንም በአግባብ ይዘን በዋናው ጠላት ላይ ማተኮር መቻላችንም በጣም ወሳኝ ነው።   አንዳንድ አጉል ተቺዎች ኢሕአፓ ብዙ ዓመት ታግሎ ለስልጣን አልበቃምና ይጥፋ ብለውም ይተቻሉ፤ ያወግዛሉም።   ለነገሩ ለሕዝባዊ ዓላማ ጸንቶ የታገለ ድርጅት ይመሰገናል እንጂ አይወገዝም። የደቡብ አፍሪካ የነማንዴላ ድርጅት ለድል የበቃው ከ 70 በላይ ዓመት ትግል በኋላ ነው።  ሌሎችም እንዲሁ አሉ። የሀቀኛ የሕዝብ ድርጅት ዋና ዓላማ ደግሞ ራሱን ለስልጣን ማብቃት ሳይሆን ሕዝባዊ መንግስት ምስረታና ዴሞክራሲን ለማስፈን መቻሉ ነው። ከታገለ ድርጅት ትምህርትን ቀስሞ ተመሳሳይ ለመስራት ለሀገር ለማከናወን  ከተቻለም ለመተካት መጣር የሚመሰገን ነው። ከትግሉም ከተግባራዊ ስምሪትም ጦመው ግን በወሬ ፋኖ መሪ ሊኮን አይቻልም።   የረጅም የትግል ተመክሮ ከወሬው ቀነስ ከትግሉ ከረር የሚል ነው። በጽናት የተጀመረና አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ትግል ከግብ አድርሱ የሚለን ነው። ለኢትዮጵያ እንጂ ለጎጥ ለጎሳ መቸነፉ አሳፋሪም ነው ይለናል።  ከተካኑ ሰይጣኖች፤ ከሞኝ የአረቄ ንጉሶች፤ ከመድረክ መዥገሮችና ከኮረፌ ፈላስፎች ይገላግለን። በትግላችን ከዘረኞች፤ ከባንዳዎችና ጸረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ሁሉ እንላቀቅ።

pdf