አቶ ኃይሉ ወንዴ (ዋሴ) በአደረበት ህመም ኬምብሪጅ ማሳቹሰትስ በሚገኘው ማውንት አውበርን ሆስፒታል ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም (January 26, 2021) ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል::
አቶ ኃይሉ ከአባቱ ከደጃዝማች ወንዴ (ዋሴ) እና ከእናቱ ወይዘሮ መልካነሽ አየለ መስከረም 9 ቀን 1938 ዓ.ም (September 19,1945) አዲስ አበባ ተወለደ:: ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ከዚያም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትሏል:: ኃይሉ ለተበደለው የኢትዮጵያ ሕዝብ መታገል የጀመረው ገና በወጣትነት ጊዜው ነበር:: ዓለም ማያ ኮሌጅ በነበረበት ወቅት ይካሄዱ በነበሩ የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያውን Bachelors of Science Degree እንዳገኘ በ1960 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ሲመጣም ትግሉን አላቋረጠም ነበር::
ኃይሉ ማሳቹሰትስ በሚገኘው በዚያን ጊዜ ቦስተን ስቴት ኮሌጅ ከሚባለው ተቋም የማስተርስ ዲግሪውን እንደጨረሰ ትምህርቱን እንዲቀጥል ዕድል አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በ1969 ዓ.ም ኢሕአፓን ተቀላቅሎ ወደ አገር ቤት ገብቶ ትግሉን ቀጥሏል:: አዲስ አበባ በሚገኘው የመምህራን ኮሌጅ አስተማሪ ሆኖም ሙያዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ እያለ በ1970 እና 1971 ዓ.ም በደርግና በተባባሪወቹ ሲካሄድ የነበረው ቀይ ሽብር እየተጧጧፈ ሲመጣ ኃይሉ በደርግ አፋኞች በቁጥጥር ስር ውሎ ከፍተኛ እስር እና እንግልት ስለደረሰበት ሕይወቱን ለማትረፍና ትግሉን ለመቀጠል ወደ ሱዳን ተሰደደ:: በሱዳን ቆይታው በአንድ በኩል በአዕፋድ ኮሌጅ በሙያው በመምህርነት እያገለገለ በሌላ በኩል በዚያ የሚካሄደውን የኢሕአፖ መዋቅር ተቀላቅሎ ለትግሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል::
ጥቅምት 1976 ዓ.ም (October 1983) በስደት ወደ ቦስተን መጥቶ ከባለቤቱ ወይዘሮ ሂሩት ግርማ ጋር ኑሮአቸውን መስርተው ወንድ ልጅ ከመውለዳቸውም በተጨማሪ በዕውቁ ኮርኔል ዩኒቨርስቲ ሌላ ማስተርስ ዲግሪ (Masters Degree in CityPlanning) አግኝቷል:: ኃይሉ ለረጅም ዓመታት በኖረበት ማሳቹሰትስ በመምህርነት እና በሆቴል አስተዳደር ለብዙ ዓመታት ከመስራቱም በተጨማሪ በቦስተን የኢሕአፖ ኮሚቴ ውስጥም ለረጅም ዘመናት አስተዋፅኦ አድርጎል:: በጣም የተረጋጋ ባህሪ የነበረው ኃይሉ ለዓመነበት ዓላማ በፅናት እየታገለ፤ ኑሮውንና ህይወቱን ለኢትዮጲያ ጭቁን ሕዝብ መስዋዕት ያደረገ ሰው ወዳጅና አክባሪ፣ ለሰው ችግር ተጨናቂና ግምባር ቀደም ደራሽ በመሆኑ በሚወዱት ቤተሰቡ በጎደኞቹና በሕብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅነትን ያፈራ ድንቅ ሰው
ነበር::
የአቶ ኃይሉ ወንዴ (ዋሴ) የቀብር ሥነ ስርዓት ጥር 26 ቀን 2013 ዓ,ም (February 3, 2021) በ11AM at Forest Hill Cemetery, 95 Forest Hill Avenue, Jamaica Plain, MA ይፈፀማል።
ከደብተራው ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ማስታወሻ: በሀገር አንድነት እና በህዝብ የመብት ጥያቄ ላይ የጸና አቋም የነበረው ጓድ ኃይሉ ሥራችንን ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ድጋፉ ያልተለየን “በርቱ!” ባያችን ነበር። በህልፈቱ የተሰማንን ከፍተኛ ሃዘን እየገለጽን ለመላው ቤተሰቦቹ፣ ዘመድ ወዳጆቹ እና የትግል ጓዶቹ መጽናናትን እንመኛለን። ትግሉም ይቀጥላል።