ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 30 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የወያኔ ባለስልጣኖች ስብሰባ ለወልቃይት የማንነት ጥያቄ መልስ ሳይመልስ ተበተነ – የኮንሶ ሕዝብ ተጠሪዎችን ለማፈን የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈ – በቀላፎ ከሚገኘው የወያኔ ጦር ወደ 300 የሚደርሱ ወታደሮች ኮበለሉ ተባለ – የስንዴ ምርትን የሚያመክን በሽታ በኢትዮጵያ መከሰቱ ተነገረ፤ ተመድ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አዲስ ድርቅ ይከሰታል አለ – የሱማሌ ግዛት የፍትህና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ የሚል ድርጅት ተቋቋመ።
የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች በቅርቡ ባካሄዱት ስብሰባ በጠባብነት ላይ የተመሰረተውንና የአንድን ዘር የበላይነት የሚያስቀድመውን የዘረኝነት ፖለቲካ ለማሰቀጠል መሀላ ፈጽመው መበተናቸው ተሰምቷል። ይህ የወያኔ ባለስልጣኖች ስብሰባ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ያንቀሳቀሰውና በተለይም የጎንደርና የጎጃም ሕዝብ ደሙን ያፈሰሰለትና ውድ ልጆቹን ለእስርና ለስየል የገበረ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄና እንዲሁም ከጎንደር ተቆርሶ በትግራ ስር እንዲካለል የተደረገው የመሬት ጥያቄን በተመለከተ ምንም ነገር ሳይለወጥ እንዳለ እንዲቀጥል ወስኖ መበተኑ የወያኔን ዘረኝነትንና አምባገነንነትን የሚሳይ መሆኑን የፖለቲካ አዋቂዎች ያስረዳሉ፡፡
የኮንሶ ሕዝብ ተጠሪዎችን ከሕዝብ ለመነጠል ሲካሄድ የነበረው ሴራ መክሸፉ ታወቀ፡፡ ለረጅም ዓመታት የኮንሶ ሕዝብ ባህላዊ ወኪሎች ከሕዝብ ጋር ቀጥተኛና ግልጽ ውይይት በማድረግ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለሚመለከታችው አካላት አቅርበው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ሲወተውቱ የቆዩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ለሕዝቡ ጥያቄ የተሰጠ ምላሽ አፈናና እስራት መሆኑም ይታወቃል፡፡ የወያኔ ባለስልጣኖች እነዚህን የሕዝብ ወኪሎች ከኮንሶ ሕዝብ ለመነጠልና ለማሰር ማቀዱን በቅርቡ ከሕዝብ ጋር ባደረገው ስብሰባ ቢገልጡም ስብሰባው በሕዝቡ ተቃውሞ መበተኑን ከስፍራው ከደረሰን መረጃ መረዳት ችለናል፡፡
ወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አውጆ የኢትዮጵያ ሕዝብን አርዶና አንቀጥቅጦ ለመግዛትና የግፍ ቀንበሩን በሕዝብ ላይ እንደጫነ ለመሰንበት እያደረገ ያለው መፍጨርጨር እየከሸፈበት መሆኑን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደርሱን ተጨባጭ መረጃዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡ ወያኔ በተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ባለሌላ ማዕረግና ተራ ወታደሮችን በብሔረሰብ መስመርና በተለያዩ ሁኔታዎች እንደሚከፋፍላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ መከፋፈል በወታደሩ ውስጥ የመተማመንና በአንድነት የመቆም ሁኔታ እንዳይፈጠር ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም አልፎ በተለያዩ ጊዜያት በየጦር ሰፈሩ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ በወታደሮች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ ደፍረው የተናገሩ ወታደሮች ለመቀጣጫ ተገድለዋል፡ ፡ ጥቂት የማይባሉም ታፍነው ስየል ከተፈጸመባቸው በኋላ በህይወት ይኑሩ ይገደሉ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በቅርቡ በጠረፍ አካባቢ የሚገኘው ወታደራዊ ኃይል በገፍ እየኮበለለ መሆኑ ከደረሰን ውስጣዊ መረጃ ተገንዝበናል፡፡ ከቀላፎ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ ወታደሮች ከነሙሉ ትጥቃቸው እንደተሰወሩ መረዳት ተችሏል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ወዴት እንደሄዱ ፍንጭ አልተገኘም፡፡ ከወያኔ ከፍተኛ ደህንነት ተቋም እንደሚሰማው እነዚህን ወታደሮች በገንዘብ የሚያስኮበልል የውጪ ኃይል ማለት ግብፅና ሸሪኮቿ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የሚሰማው፡፡ ወያኔ እራሱ በጫረው እሳት፣ ወታደሩ ላይ በፈጸመው ግፍ፣ መለብለብ ብቻ ሳይሆን መቃጠሉና አመድ መሆኑ የማይቀር እንደሆነ በርካቶች ይናገራሉ፡ ፡
የስንዴ ምርትን የሚያመክን በሽታ በኢትዮጵያ መስፋፋቱ ተገለጸ። ቀደም ብሎ በተወሰኑ የደቡብ አካባቢ ክልሎች ታይቶ የነበረው ይህ የእህል በሽታ ወደ ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ግዛቶች መስፋፋቱ ተጠቁሟል። በሽታው በአብዛኛው የስንዴ ምርትን በ50 ከመቶ ማበላሸቱ የታወቀ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎችም ሙሉ ለሙሉ ምርቱን ያመከነ መሆኑ ታውቋል። እስካሁን ድረስ በተደረገው ጥናት በሽታው በ2200 አካባቢዎች 300 ሺ ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ ቦታዎችን ያጠቃ መሆኑም ተደርሶበታል። የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የእህል በሽታዎችን በማስቆም ከፍተኛ ሚና የተጫወተ መሆኑ ሲታወቅ አሁንም ተመሳሳይ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2009 ዓም ባወጣው ዘገባ የመኽር ዝናም በመቀነሱ ምክንያት በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አዲስ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ገልጿል። ጥናት ከተካሄደባችው 212 ወረዳዎች መካከል 93 ወረዳዎች በድርቁ ምክንያት ምንም ምርት የማያገኙ መሆናችው ድርጅቱ ሲገልጽ 45 ወረዳዎች ደግሞ የምርታቸውን 50 ከመቶ እንደሚያገኙ ገልጿል።
የሱማሌ ግዛት የፍትህና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ የሚል ስም የያዘ ቡድን የተቋቋመ መሆኑን ጥቅምት 28 ስቶክሆልም ስዊድን ውስጥ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል። ማብራሪያውን የሰጡት የቡድኑ መሪ በኦጋዴን ውስጥ ሕዝቡ በወያኔ አገዛዝ የሚደርስበት ከፍተኛ ግፍና መከራን አንስተው አዲስ የተቋቋመው ድርጅት ዓላማ በአካባቢው የሕዝቡ መብትና ፍትሕ እንዲከበር ለመታገል ነው ብለዋል። ድርጅቱ የፖለቲካ ዓላማ የሌለውና የፖለቲካ ድርጅት አለመሆኑን ገልጸው በኦጋዴን ክልል የሚኖረው ሕዝብ በተለያዩ አስተሳሰቦች ቢከፋፈልም መብትና ፍትህን በማስጠበቅ በኩል አንድ እንዲሆን የሚጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።