- ክፍል ስድስት – ከሃማ ቱማ –
እንጻፍ ካልንማ እንጻፍ ቁም ነገር
ሀገርን አድኖ ዘረኛን የሚቀብር
እንጻፍ እንበላቸው ለኢትዮጵያ ዘለዓለም
ልጆቿ እስካለን የሚነካት የለም፡፡
ታሪክ የሀገር ቅርስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፡፡ ዛሬ የታሪክ ላፒሶች ሊክዱት ቢነሱም ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ሲኖራት አያሌ ዘመን ያለፈ በመሆኑ ታሪካችን፤ ቅርሳችን፤ ባህላችን በጽሁፍም ሰፎር ይገኛል፡፡ መንጎል ከብራና ተገናኝቶ፤ ቀርክሃም ተቀርጾ ከቀለሙ ተጠቅሶ ታሪክ የላትም የሚሏትንም ማፈሪያዎች ወላጆች ታሪክ ጽፋላቸዋለች፡፡ ወያኔና ሻዕቢያ፤ ከነሱም ሁሉን የቀዱት ኦነጋውያን እንደሚሉት ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ብቻ ያላት ሀገር አልነበረችም፤ አይደለችም ፡፡ ለማንኛውም ዛሬ መሃይሙም፤ ጥራዝ ነጠቁምም፤ ገና ፊደል የቆጠረውም፤ ቀጣፊውም ሁሉ መጽሃፍ ከታቢ ሆኗልና ጸጋ እንበለው መርገም ግልጽ ሳይሆን ይዳክራል፡፡ በኢህአፓ ላይ ለምሳሌ ከ22 በላይ መጽሃፍት ተጽፈው 24ኡ ሀሰት የተሞሉ ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ ትውስታ ተባሉ ትረካ፤ ትውልድ ይወቅ አሉ ምስክርነት፤ የደም ዘመን አሉ ከናይሮቢ ሰንጋ ተራ እስከ ቤተ መንግስት፤ ትግላችን አሉ ሌላ አብዛኞቹ ብዙ ገጾችን የሞሉትና እንቆቅልሽ በሚልም ወረቀት ያባከኑት በቅጥፈት ምዝገባ ነው፡፡ በየጊዜው ልንመልስላቸው ልናስተካክላቸው ሞክረናል፤ ከዋናው የትግል ትኩረታችንም ዕይታችንን ወደ ሌላ ሳብ አድርገውብናል፡፡ ሲተቹ ይበሳጫሉ፤ አትጻፉ አሉን ብለውም የምንቲታ ተቆጢታም ሲሆኑ ታዝበናል፡፡ መጻፉ ባይከፋም መሠረታዊ መንስዔው ሀቅ ሲሆን ጠቀሜታው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ መለስን፤ ስዩም መስፍንን ወዘተ በማወደስና የወያኔን ርኩስ ተልዕኮ ደብቆ ለማሳለፍ የተጻፉ መጽሃፍት ሁሉ ቋቅ የሚሉና የሀቅን ተራራ በሀሰት ሊንዱ የቃጡ ናቸው፡፡ የመንግስቱ፤ ፍቅረሥላሴና ፍስሃ ደስታ መጽሃፍት ባይጻፉ ቢቀሩ ምን ይጎድልብን ነበር ? እንጻፍ ከተባለ መጻፍ ያለበት ሀቅ ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ ትርጉምና ግምገማ ሌላ ነው፤ ውሸትን ሀቅ ብሎ ማስፈሩ ግን ወንጀልም ሊባል ይገባዋል፤ የወገንን ደም መርገጥ ነውና፡፡ የሻዕቢያው ባለ ቡርቃ መጽሃፍት ዓይነቶቹ ለምሳሌ ህዝብን ለማጋጨት የተጻፉ ርኩስ መጽሀፍት ናቸው፡፡ ኢብሳ ጉተማ ጣሊያን ቢገዛን ይሻል ነበር ያለበት መጽሃፍ ገዢና አንባቢ ማጣቱ እሰይ ያሰኛል። በኢህአፓም ላይ አንጎለ ሸንካላዎችና ሀቅ ገዳዮች ሁሉ ብዙ መቶ ገጾችን ጥርሳቸውን ነክሰው ውርጅብኝ ሰደውበታል ፡፡ ከዓመታት በፊት ይድረስ ለባለታሪኩ ተብሎ የቀረበውን ተረትና መስል ጽሁፎችን አጋልጠን የተቸን ሲሆን በቅርቡም የቀረቡትን ኢህአፓ ነክ ሀሰት ሙሉ ጥራዞች አስፈላጊ ባልንበት በሚገባ ከመተቸት ወደኋላ አላልንም፡፡
ውሸት ስራ ሆኖ ቀን ማታ ሚያደክም
ሀቅን የሚፈልግ ስራ ፈት ጠፋብን ።
ኢህአፓን በተመለከተ ቅጥፈቱ የሚጀምረው ገና ምስረታውን በሚመለከት ነው፡፡ መጋቢት 24 የተመሰረተበትን 48ኛ ዓመት አክብሯል፡፡ በቅድሚያ መስራች ነን ባዮቹ መብዛታቸው ! ቀጥለውም በነእገሌ ተመሰረተ ብለው ቀጣፊዎቹ መበርከታቸው ! የኢህአፓ መሪ የሚባሉ ከየስርቻው ወጥተዋል ፤ ብዙዎቹን አናውቃቸውም እኛ ኢህአፓዎቹ ። ሊያውቁ የሚገባቸው ሳይቀሩ ሲደባለቅባቸው እያነበብን ነው፡፡ የወያኔና ደርግ አሽከሮች የአረብ የቤንዚን ዶላር መሰረታቸው ሲሉ ነበር፡፡ አሜሪካ ደግሞ ሶቭየት ህብረት ድርጅቱን መሰረተ ብላ በኮንግሬሷም በነስፔንሰር አማካኝነት ስታጮህ ነበር፡፡ የድርጅቱ መሪዎችም እንድርያስ እሸቴና እሸቱ ጮሌ ናቸው ብለውንም ነበር ፡፡ ቀጥለውም ድርጅቱን የመሰረተው ኦስማን ሳሌህ ሳቤና ሻዕቢያ ነው ብለው ማሉ ተገዘቱ ፡፡ በቅርቡ አንድ የኢህአፓ መስራች ነኝ ሊል ሚዳዳው መደዴ ምሁር ለምሳሌ ኢህአፓ የተመሰረተው በአዲስ አበባ በነበር ቡድንና አልጄርያ በነበሩት ውህደት ነው ሲልም ጽፏል ፡፡ በአዲስ አበባ የነበሩት እነ ጸጋዬ ገብረ መድህን በአልጄሪያ ከነበሩት ጋር አብረው ከመጀመሪያው የሰሩ እንጂ ሌላ ቡድን አልነበሩም ፡፡ ከኢህአፓ ምስረታ በኋላ ወደ ድርጅቱ የተደባለቀው አብዮት የተባለው ቡድን ደግሞ ሌላ ነው ከናካቴው ፡፡ ይህን ታሪክ ሰሪ የመጀመሪያ የፖለቲካ ድርጅት ኢትዮጵያውያን መሰረቱት ማለቱ የሚከብዳቸው በዝቅተኝነት ስሜት የተዋጡና በወያኔ ሻዕቢያ ተሸነፍን ብለው የተደፉ እንዳሉም እናውቃለን ፡፡ የተማሪውም እንቅስቃሴ ቢሆን በነዚሁ ጠባቦች የተመራ ነው ብለው የሌላውን ኢትዮጵያዊ ታጋይ ሁሉ ታሪክ ይደመስሳሉ፡፡ ወደዱም ጠሉም ግን ኢህአፓን የመሰረትነው የኢትዮጵያ ልጆቿ ነን ፡፡ በየካቲት የአድዋ ድል በዓል ስናከብር ድሮ የተሸነፉና ያፈሩ ቅኝ ገዥዎች ይሉት የነበሩት ንግግር እንደገና አንገቱን ቀና ማድረጉን መታዘብ ተገደናል ፡፡ የጣሊያን ቅኝ ገዢ ሀይል በጥቁሩ ሰውና ጥቁር አርበኞች ድባቅ ሲመታ እንዴት ጥቁር ነጭን አሸነፈ እንላለን ብለው ኢትዮጵያውያን አፍሪካውያን አይደሉም የሚል ትረካ አስፋፍተው ነበር፡፡ በዚህም ዓመት እንደገና በአውሮፓ ይህ ንግግር ተደምጧል ፡፡ በዚሁ መንፈስ ነው በተማሪው እንቅስቃሴም ሆነ በኢህአፓ ምስረታና ትግል የተካፈልነውን ነጋ ጠባ ከማናውቀው ኤርትራ ወስደው የዚያን ማንነት ሊሰጡንና ውልደተ ኤርትራ ሲሉን ሚደመጡት፡፡ ለነገሩ እንጂ በርካታ ትውልደ ኤርትራ ኢትዮጵያውያን ለውድ ሀገራችን ተሰውተዋል፤ ድሮም ዛሬም ከዚህ መጣን ከዚያ ለእኛ ጉዳያችን አይደለም፡፡ አብርሃም ደቦጭ፤ ዘርዓይ ደረስና ሊሎችንም ያስታውሷል፡፡ ለእኛ ውልደት ቋንቋ ነው የሆነው ለዚህ ነው ፤ ዘር ቆጠራንም ሳንማር ዩኒቨርስቲዎችንም ወደድንም ሆነ ሳንወድ ለቀናል ፡፡ ኢትዮጵያዊም ፤ አፍሪካዊም፤ ዓለም አቀፋዊም ነን፡፡ ትግላችንም የአድዋውን ድል ዜጋ ታሪክ ተቀብሎ በአንድነት በኢትዮጵያዊነት የታገለ ስለሆነ መታፈርና ማፈር ካለበት ዛሬ በደም ጥራት ምርመራና ዘር ቆጠራ እርስ በርሱ የተሸነሸነው ነው ፡፡ በታሪካችን ማፈር ከተባለ ማፈር ያለባቸው ትላንትም ዛሬም ባንዳ የሆኑት ብቻ ናቸው ፡፡ በኢትዮጵያዊነት መኩራት፤ሀገርን ለማሻሻል መጣር ስንል ኢህአፓን መጥቀስ ግድ ይሆንብናል ፡፡ በኢትዮጵያ እንጂ በጎጥና ብሄረሰብ አንገለጽም በሚል ከመነሻውም ስንሰየም የኢትዮጵያ ነን ያልነውም ለዚህ ነው ፡፡ ኢትዮጵያዊነት እስካዛሬ መለያችን ሆኖ ቆይቷል ፡፡ ኢትዮጵያ በማለታችና የሀገርን ጥቅም ለግልና ጊዜያዊ ጥቅም አሳልፈን ባለመስጠታችን ወይም ወደ ጎጥ ባለመዝቀጣችን የኢትዮጵያ ጠላቶች ይኸው እስከዛሬ በጋራም በተናጠልም ጠላት ብለው ያጠቁናል፡፡ በበሬ ወለደም የራሳቸውን ባንዳነት በእኛ ሊያልክኩ በመጣር ለባዕዳን ሰገደ ሊሉን ዛሬም እየጣሩ ናቸው ።
ትውልድማ ነበር ያውም ጀግና
እነጥላሁን ዋለልኝን ያፈራ
ትውልድማ ነበር የተማረ
በወገኑ ሥቃይ የተብከነከነ
በሀገር ፍቅር የነደደ
የእነ ገመቹ፤ የነድላይ የጸሎተ።
አህያን ለቻይና እንደሸጥነው ሁሉ ከርስ አደሮችን ፤ የሰው ባዶ የሆኑ መሃይም ምሁሮችን መሸጥ ብንችል ኖሮ ሀገራችን ትርፍ በትርፍ ባገኘች ነበር፡፡ ፈልተውብናል፤ ይርመሰመሱብናል፡፡ አደብ ከሚባል ነገር ሳይተዋወቁም እያረጁ ናቸው፡፡ ቆመንለታል፤ ዓይንና ጆሮ ሆነንለታል ብለው የተመጻደቁበትን ህዝብ እየከዱ ከህዝብ ጠላቶች ጎን ሲቆሙ ቅንጣትም አልሰቀጠጣቸውም፡፡ ይባስ ብለው እንዲያውም የሽግግር ሂደትና ህዝባዊ መንግሥት የሚሉትን በጠላትነትና ለውጥ አጋጅነት ዋነኛው ወንጃዮች ሆነዋል፡፡ ኢህአፓን በተመለክተ ደግሞ የጎዳን የራሳችን ጠማማ ነው ያሉትን ዛፎች የሚያስታውስ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በድርጅቱ የነበሩና የከዱ ወይም በአንጃነት የተሰማሩ ናቸው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱበት፡፡ ነበርን ባዮች ናቸው ሀሰት እያጠነጠኑ የዘመቱበት፡፡ ወጥተው ከቀሩ ዘመን ያለፋቸው ወጥተን አልወጣንም ብለው በማያውቁት ድርጅት ላይ ትችታቸውን መጫን አላቆሙም። የነዚህን ቀጣፊዎች ውሸት ማጋለጥ የተገደድነው አዲስ ትውልድ 17 ዓመት በደርግ ና 27 ዓመት በወያኔ ውሸት ሲዘንብበት ስለከረመ ሀቁን ለማስፈር ስንል ብቻ ነው። እንጂማ ትኩረታችን በዘንድሮዎቹ ሸረኞችና ከታሪክ ምን ትውልዱ ይማር በሚለው ላይ ቢሆን ደስተኞች በሆንን ነበር። ሁሌም ደግሞ ማናቸው ማለቱን ምንገደደው ማንነታቸው ሀሰታቸውን ገላጭ በመሆኑ ነው። ህዝብ እንዲያውቃቸው መደረጉ አስፈላጊ ስለሆነ እንጂ ለሰኮንድም ቁም ነገር ለኢምንቶቹ የምንሰጣቸው አይደሉም።
በቅርቡ አንድ ከአዜብ ጎላ ጋር ሆኖ የህክምና መሣሪያዎችና መድሃኒት ሲሸጥ ከርሞ መለስ ሲሞት በበረከት ተይዞ የተለቀቀ ግለሰብ የድርጅት መሪ ነኝ ሊል ከመከጀሉ ባሻገር ያልሆነን ነገር ሆነ ብሎ በለመደበት ክህደትና ቅጥፈት በአውሮፓ በፓርቲው ሳለሁ በአጼው ላይ አብዮት ይሻላል ወይስ ጥገና በሚል ተከፋፍለን ነበር፤ በሶማሊያም ጥያቄ እንዲሁ ሲል ቃለ መጠይቅ ሰጥቷል። አብዮት ወይስ ጥገና ለውጥ በሚል የነበረ ክፍፍል በእንዳልካቸው ጊዜ በመኢሶንና ኢህአፓ በሚሆኑት መሀል የተነሳ ሲሆን ይህ ዋሾ የደርግ የጦር አይሮጵላን አብራሪ በየትና የት በዚያን ጊዜ የድርጅቱም የክፍፍል የሚለውም አካል እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ስር ነቀል ለውጥና አብዮት ብሎ ኢህአፓ ወስኖ የተደራጀውና ትግል የጀመረው በ1964 ስለነበር ግለሰቡ ያኔ በድርጅቱም አልነበረም። በኢህአፓ ውስጥ ሶማሊያን እንደግፍ አንደግፍ የሚል ውይይት ወይም ክፍፍልም መቸም አልተመዘገበም፤አልነበረም። በዚህ እንተወው እንጂ የዚህን ቀጣፊ ዝርዝር ታሪክና የወያኔ ሎሌነት እንተች ካልን ብዙ ገጽ ይወስዳል። የሠራዊቱም መስራች እየተባሉ ያሉ ስላሉ (አልነበርንም ሲሉ አልተደመጡም )እንዲሁ እርምት ማስፈለጉ አልቀረም። ኢሕአሠ የተመሰረተው በኢሕአፓ ነው። በድርጅቱ ውሳኔ። በዚህ ተዋጊ ሆነው የሚገቡትን አባላት ከየቦታው መርጦ ለስልጠና የላከው ድርጅቱ ነው። በውሳኔውና ሂደቱ የነበርነው እኛ ነን እንጂ ነበርን ባዮቹ በቦታው አልነበሩም። በዚህም ከነበሩት አንዱ ራሱን እንደ ሠራዊት መስራች አቅርቧል። የመጀመሪያ የሠራዊት አባል አካል እንጂ መሥራች ግን አልነበረም። የሰራዊት እርሾ ሆነው ወደ አሲምባ ሲጓዙ በኤርትራ መሬት ከሻዕቢያ ጋር አግኝተው ይዘዋቸው ወደ አሲምባ የዘለቁት ደግሞ በሩቁም መሥራች ነን ሊሉ የሚችሉ አይደሉም። ኤርትራዊው በረከት ሀብተስላሤ ዲሞክራሲያ በምስጢር ሲሰራጭ በነበረበት ጊዜ ከተወዳጅነቱ ስም ለማትረፍ አንደኛው የዴሞክራሲ ጸሓፊ እኔ ነኝ ብሎ ለጓዶች ለራሳቸው በየመን እንደቀደደ አስታውሳለሁ። ውሸት ምን ያደርጋል ፤ በኢህአፓስ ከታገሉ መስራች ነኝ፤ መሪ ነበርኩ ብሎ ጉራው ምንስ ያደርጋል ? ሊቀመንበር ነበርኩ ነኝ ብሎ መዋሸቱ ? ኢህአፓ መሆን መታገል፤ ጸንቶም መቀጠል በራሱ እኮ የሚያኮራ ነው እላለሁ። በታሪክ አጋጣሚ መሥራች ሊኮን ይችላል። ታዲያ ምን ይሁን? ድርጅቱን ከለቀቁ ከሰላሳ ዓመት በላይ የሆናቸው እንዴትስ ዛሬ ስለ ኢህአፓ–ትግሉን በጽናት ቀጥሎ ዛሬን ያስተናገደውን እናውቀዋለን ብለውስ በድፍረት ይተቻሉ? እነዚህ በሞላ ሆነ በተናጠል በድርጅቱ ለብዙ ዓመት የታገሉም አይደሉም። ከእለታት አንድ ቀን ነበርን ማለቱ ምንም ባይፈይድም ማለት ግን ይችላሉ። ኢህአፓ የተባለው ጎርፍ እኛንም ጠርጎ ወስዶን ነበር ማለት ይችላሉ–በቃ! ሞክረው ያኔም ያልተሳካላቸውን የማፍረስ ስራ ዛሬም ለምንስ ይገፉበታል? እኩይ ስራን ትተው ወደ ቀና ስምሪት ቢሰማሩ ምንኛ ለራሳቸው የአንጎል ዕረፍት በሰጡ።
የሚሰማ ካለ
ታሪክ እኮ ይጮሃል
የሚማርም ካለ
ታሪክ ያስተምራል
ሀገር ካልጠበቁት ተነስቶም ይሄዳል።
በድርጅቱ ላይ ያልተነዛ የሀሰት ክስ አልነበረም፤ አሁንም ቀጥሏል። አንዳንዱ የሞኝ ለቅሶ ነው፤ መልሶ መልሶ ችክ ያለ። ኢህአፓ ዚያድ ባሬን ሶማሊያን ደገፈ የሚለውን የደርግ ቅጥፈት ዛሬም አምነው ወይም ድርጅቱን የጎዱ መስሏቸው ሚያነበንቡ አሉ። ቁንጮ ዋሾውና የሽማግሌ ቀላሉ ስብሐት ነጋም ይህን ሀሰት ሊሸጥ ሲሞክር ከአንዴም ሁለቴም ተደምጧል። ሌላው ደግም ድርጅቱ ኤርትራን አስገነጠለ የሚለው ነው ። ደግመን ደጋግመን ይህን ማለት ምን ያህል የፖለቲካና የታሪክ እውርነት መሆኑን ብናስረዳም ጆሮአቸውን ደፍነው ይህን ክስ እንደ ጸሎት መደጋገሙን የመረጡ አሉ ። የሥርዓቶቹን ጥፋት በድርጅቱና በኢትዮጵያዊው ታጋይ ዋለልኝ ላይ ለመለጠፍ አሁንም ይሞክራሉ ። እዚህም ላይ የሰሙትን በጭፍን ደጋሚዎች፤ ጭራሽ አላዋቂዎች፤ ወገበ ነጮች መድረኩን አጣበዋል።
ከዚህ በተያያዘ ኢህአፓ ቢትወደድ አዳነን ገደላቸው የሚል ክስም ሊጠቀስ የሚገባው ነው። ይህን ክስ ከሚደረድሩት ጥቂቶች ውስጥ አብዛኞቹ እሳቸውንም የሆነውንም አያውቁም። ይህን ክስ ደርድሮ መጽሀፍ የጻፈ አንድ የኢሕዴአ ድርጅት አባል ነኝ ብሎ ሱዳን የነበር ግለሰብ ወያኔ በንግድ አባብሎና ወደ ሜዳ አስገብቶ በጉድጓድ እስር ቤት እስኪገረጣና ጢሙ እምብርቱን እስኪያልፍ አቆይተው የለቀቁት ዛሬ በሳን ሆሴ አሜሪካ ነዋሪ የሆነ የሰው ከንቱ ነው። ስላሰቃየው ወያኔ ማጋለጡን ፈርቶ–ሲለቁት ትንፍሽ ትልና ብለው አስፈራርተውታል ይባላል– መጽሃፍ ከተብኩ ብሎ ተሽቀዳድሞ ኢህአፓን ከሷል። ይህን የሃሰት ክስ ያመኑ የቢትወደድ ዘመዶችም በድርጅቱ ላይ ቂም ይዘው እንደቆዩም የምናውቀው ነው። ቢትወደድ አዳነ ስመ ጥር ከተባሉት የኢትዮጵያ አርበኞች አንዱ ሲሆኑ ኢህአፓ ለምን እንደሚገድላቸው ማንም እስከዛሬ መልስ ሊሰጥ የቻለ የለም። በግሌ በገዳሪፍ አውቂያቸው ወዳጅም ሆነን ልጄ ይሉኝ እንደነበር ምስክር ሞልቷል። በዘጠና ዓመት ወደ ጠገዴ ገብቼ ልርዳችሁ ያሉትን በተመለከተ ይህን ግዳጅ ለእኛ ተዉት፤ እርሶ በበቂ ታግለዋል (ኢዲህ መሪ ሆነውም ደርግን በጎንደር ተፋልመዋልና )፤ ሀገር ሲረጋጋ ይመጣሉ ፤ የአሁኑን ትግል ለወጣቶች ይተዉት ብያቸው የተስማሙኝ መስሎኝ ነበር ። ነገር ግን ሜዳ እያለሁ ተከታዮች ይዘው ከሱዳን ወደ ጠገዴ ሊዘልቁ መጓዛቸውንም ያወቅነው ሞቱ ተገደሉ ሲባል ነው። ዘመነ በሪቅ በተባለው ቦታ ቢትወደድና ሌሎች ላይ ተኩስ ከፍተው የገደሏቸው በርግጥም ቀደም የኢህአሠ አባል የነበሩ የሰሜን ልጆች ሲሆኑ (የሰባቱንም ስም ወዲያውኑ አትመን አጋልጠናል ) ወደ ሱዳን ከድተው ሊወጡ ሲሉ እነ ቢትወድድን በድንገት አግኝተው ተኩስ ከፍተው ገድለዋቸዋል። ከሃዲዎቹ የፈረጠጡት ድርጅቱ ከኢዲህ ያደረገውን ግንባር ተቃውመው ይሁን በትግሉ ተስፋ ቆርጠው በሚገባ ግልጽ ባይሆንም ሱዳን ደርሰው አራቱ ወዲያውኑ ወያኔን መቀላቀላቸው ታውቋል። የአርማጨሆ ህዝብ ታጋይ ነን እያሉ ያስቸገሩትን አለሌዎች አሳርፉልን ባለን መሠረት ሥነስርዓት ልናስይዛቸው ተነስተን ነበርና የቢትወደድን መገደል ሲሰሙ በድርጅቱ ላይ አመቺ ጊዜ አገኝን ብለው ዘመቻን መረጡ። የተወሰኑ ጓዶች (ያውም ድርጊቱን ያልሰሙትን ጨምረው) አባላትን ገደሉብን ። ይህ ድርጊት ወደየት እንደሚያመራ በመገመት ለቢትወደድ ዘመዶችና ኢዲህ መሪዎች በደምብ አውቀው በነበረው በዋግ ሹም ነወጠ አማካኝነት ተገናኝተን እንወያይና ችግሩን በሰላም እንፍታ፤ድርጅቱ አዛውንቱን አልገደለም ከሀዲዎች አንጂ በሚል ጻፍንላቸው። በህዝብ ላይ ፏልለው የነበሩት እነ ሻለቃ ዘለቀና ሻለቃ በሪሁን ግን አሻፈረን አሉ። ለማንኛውም የውይይት ቀንና ቦታ ተወስኖ በቀኑ ወደ ቦታው የተወሰኑ አመራሮችና ሀይል ሲጓዝ በደፈጣ ተኩስ ተከፈተብን። በውጊያ ዋግ ሹም ነወጠም ሻለቃ ዘለቀም ተገደሉ፤ ከእኛ በኩልም እነ ጓድ ብርሃኑ ዴንጀር ተሰዉ ። ስለ ሂደቱ ባጠቃላይ የሚያውቁ ምስክሮች ዛሬም በአሜሪካም በሀገር ቤትም እያሉ ነው የሀሰት ክሱ የሚውጠነጠነው። በበኩላችን በትግል የተሰማራነው ክፋሺስት አገዛዝ ጋር ለመፋለም እንጂ ከመንደር ፏሉሎችና ከሀገሬው ጋር ለመዋጋት ባለመሆኑ ጦርነቱን ልንቀጥለው ትጥቁም ብዛቱም ቢኖረንም ግጭቱን ትተን ወደ ቋራ መሻገሩን መረጥን ። በዚህም ወቅት ነው ሁለት ብርክ የያዛቸው (ዛሬ የአንጃ መሪና ተባባሪ የሆኑ )ትግሉን እናቁም ጥሪም ለአመራሩ ያቀረቡት። ተቀባይ ቢያጡም ውሎ አድሮ አንዱ ወደ ሱዳን ወጥቶ በዚያው ሲሰናበት ሌላው ደግሞ ትግሉን ለመቀጠል ያመነ መስሎ አድብቶ የመጨረሻውን አንጃ አደጋ ድርጅቱ ላይ አድርሷል።
የጅብ መንጋ ሄዶ የቀበሮው መጣ
ከርሳም ደም የጠማው ሀገር የሚያጠፋ።
ትግላችን በህዝብና በሀገር ፍቅር የተነሳ የተጀመረ ነው። ግን ጭቆናን በመጥላት። ስለዚህም ፋሺስትና ባንዳን መጥላትና፤ ፍትህ ሲጠፋ መናደድ መቃወም ከነፍሳችን ከራቀማ ለምንስ ብለን ትግል ጀመርን? ጭቆናን ጥላቻ የትግላችን ቤንዚን ነው ። ዛሬም ያኔም ጠላትን አትጥሉ፤ በደፈናው ፍቅር ይስፈን፤ ብረት አታንሱ አታምጹ የሚሉን የህዝብ ነጻነት ጠር ናቸው ባይ ነኝ ። ወያኔ ሥልጣን ይዞ ሀገር ሲያጠፋ ብረት አታንሱበት ብለው የቧረቁብንን ሁሉ የተቃወምናቸው ለዚህ ነው ። የጃንሆይን ባለሥልጣኖች ከደርግ ጋር አብረው በእስር ላይ እያሉ በምርመራ ያሰቃዩአቸውና ግደሏቸው፤ ለሲቪል ሥልጣን አትልቀቁ ብለው የመከሯቸው ፕሮፌሰር መስፍን ለምሳሌ መለስ ዜናዊና ወያኔን ልጆቼ ብሎ ለእስር የተዳረጉትን እነ ጸጋዬን (ደብተራውን) አላውቃቸውም ከማለታቸው ባሻገር ኢሰመጉ ይባል በነበረ እንድርያስ እሸቴ ምክርና ግፊት በተመሰረተው ተቋም አንዴም ሳያነሱና ይፈቱ የት ደረሱ ሳይባል መቅረቱ (እስከ ዛሬም አያነሷቸውም) የሚጠቀስ ነው። ፐሮፌሰር መስፍን አስተማሪዬ ስለነበሩ አንቱ ብላቸውም የአንቱነትን ክብር ከነሳኋቸው ዓመታት አልፈውኛል ። ሚኒሶታ በተባለ የአሜሪካ ከተማ አግኝቼም ለምን ደብዛቸው ለጠፋው ለነ ጸጋዬ አልቆሙላቸውም ብዬ ብጠይቃቸው የክንፈ ገብረ መድህን ጥሩ ሰው መሆን ሊያስረዱኝ መሞከሩን መርጠው ላንዴም ለሁሌም ዓይኖትን ላፈር ልል አብቅተውኛል ። ከደርግ ጋር ሆነው በህዝብ ላይ ትንሽም ግዙፍም ወንጀል የፈጸሙት ዛሬም በዚያው በከፋው አቅዋምና ጎዳና ላይ መገኘታቸው በጣም የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ጉዳይ ነው ። የኢህአፓ ታጋዮች ስንቱ ጀግና ለመስዋዕትነት ተዳርገው፤የት
እንደተቀበሩ እንኳን ወላጅ ዘመድ የማያውቅበት ሁኔታ ሰፍኖ፤ፋሺስቶችና ሽብርተኞች ግን በነጻ በገራችን ሲፏልሉ፤እነ ፍስሃ ደስታና ፍቅረስላሤ ይባስ ብለው ወንጀላቸውን ደግፈው አሁንም ሲለፍፉ፤ ሲንደላቀቁ ማየቱ የምጸትም ምጸት መሆኑ አልቀረም ። የደርግ ቡችሎች–ተስፋዬ ርስቴ ተባለ ተክሌ የሻው–መጽሃፍ ጽፈው ኢህ አፓና መኢሶን ተጨራረሱ ብለው ደርግን የዳር ተመልካች ሊያደርጉ እንደ ጣሩት ሁሉ አንድ የዘመኑ ጋዜጠኛ በሉኝ አሳቻ ሰው ደግሞ በቅርቡ ይህንኑ ደግሞታል ። ኢህአፓ የተጋጨው ካገዛዙ ዋና ከደርጉ/ከመንግሥቱና ጭፍሮቹ ሲሆን የመኢሶን ሚና ደግሞ የደርግ ደጋፊና ባንዳ በመሆን በግፉና ግድያው ተሳታፊ መሆኑ ነው ። ደርጉ ድርጅቶቹ በነጻ ቦክስ ሲፋለሙ የሚያይ አርቢትሮ ነው ሊሉ የሚጥሩት ሁሉ ሀሰተኞች ናቸው ። ተክሌ የሻው የተባለው ባንዳ የደርግ አመራር አባል ሆኖ፤የጋዜጣቸው ሠርቶ አደር ዋና አዘጋጅ ሆኖ ከመነከሩ ሌላ በትግራይ ተመድቦ ሳለ ወያኔ ተጫውቶበት ስንቱን ለኢትዮጵያ የቆመን የትግራይ ተወላጅ የወያኔ ሰላይና ካድሬ እያለ የረሸነ ጅል ነፍሰ ገዳይ ነው። በአማራው ላይ አሁን ሆን ብሎ የመጣ መርገምና አላዋቂ ሳሚ ። ስደት ከወጣም በኋላ ሞረሽ የሚል ተቋም መሰረትኩ ብሎ ዋና ስምሪቱ ወያኔ ላይ ሳይሆን ኢህአፓ ላይ መሆኑን ሁሉም ታዝቦታል። ዛሬም ወደ አዲሱ ኮለኔል ተጎንብሶ ሀገር ውስጥ እንዳለና ዘመቻውም ያው መሆኑን፤ ለአማራው ህዝቤ ለሚለው ለቅንጣትም ጠበቃ ሆኖ ሊቆም አለመቻሉን ታዝቢያለሁ። ጓደኛውና የቀድሞው መኢሶን–ደምሴ በለጠ– ከላስ ቬጋስ ተመልሶ በተድበሰበሰ ሁኔታ አዲስ አበባ በኮለኔሉ ጊዜ ሲገደል ትንፈሽ ማለትም አልደፈረም። የኢሕአፓን የፖለቲካ አቅዋም ለመተቸት ችሎታውም ብስለቱም ባይኖረውም የፈረደበትን ዋለልኝ በመወንጀል ግን ዋና ሆኖ የኤርትራን መገንጠል ከቦታው ያደረሰው ጥፋት የእሱና አለቆቹ አገዛዝና ወያኔ መሆናቸውን ይሸፋፍናል። ባለ አምስት ስድስት መቶ ገጾች መጽሃፍትን የቸከቸኩብን ብዙዎቹ (መንግሥቱ፤ ፍቅረሥላሴ፤ የዕንቆቅልሹ መቶ አለቃ፤ ብርሃኑ ነጋና ጓደኛው፤ ወዘተ) ይህ ሁሉ ውሸት እንዴትስ መጣላቸው እንዳንል የተካኑ ቀጣፊዎች በመሆናቸው አግዚኦ ብለን ትተናቸዋል ። እንጂ ብዙ ልንላቸው ልንተርክ መረጃውም ችሎታውም አለን።
“ደርግ ሚባል ጉድ አይቼ
ኮለኔል ጠላሁኝ ለይቼ
ይሻለኝ ነበረ ምሁሩ
ህይወት ስለሰጠ ለሀገሩ
ዘንድሮ ግን
ሁለቱንም ጠልቻልሁ
ዶክተር ኮለኔል ሲሉ ሰምቻለሁ።”
ፍስሀ ደስታ በደርግ ውስጥ ሆኖ ለወያኔ ሲረዳ የቆየ ቆሻሻ ሰው ለመሆኑ መረጃ የሚጠይቅ ካለም መረጃው ሞልቷል። ከወያኔም ከደርግ አካባቢም ያገኘነው መረጃና የምናውቀው ብዙ ነው። ወደ ትግራይ እየዘለቀ ወያኔን ትታችሁ (“የመንደር አይጥ!” ) በኢህአፓ ላይ አተኩሩ ይልም ነበር። ድርጅቱን ለማጥፋትና ወያኔ ላይ ትኩረት እንዳይደረግ ያቅሙን ሁሉ አድርጓል። አንድ የወያኔ ተቃዋሚ ግለሰብ በለንደን ከተማ አግኝቶት ከደርግ ሊተባበር መፈለጉን ሲገልጽለት ይህንን ዜና ለወያኔ አሹልኮ ከማቅረቡና ከመሻጠሩ ሌላ ዘንዶም ሠራዊት ተብሎ በነ ኮለኔል ቃለክርስቶስ አባይ የተቁቋመውን ሀይል መንግሥቱ እንዲያፈርሰው እንዳይረዳው ያደረገም ፍስሃ ደስታ ነው። ፋሺስቱንና ቡከኑን ኮለኔል “ነገ በእኛስ ላይ ቢነሱ?” በሚል በማስፈራት። በዚሁም መንፈስ ከኤርትራው ጀብሃ ወጥተው ጀብሃን ሊወጉት በተደራጁት ፋሉል ላይ የሀሰት ዘመቻ ለመንግሥት አድርሶ ጀብሃን አንቀጥቅጠው የነበሩት እንዳይረዱና እንዲከስሙ አድርጓል ። ወያኔ አዲስ አበባን ሊይዝ ሲደርስም ከሀገር እናውጣህ ላሉት የሰጠው መልስ ወያኔ እኔን አይነካኝም የሚል ሲሆን ወያኔ ለእሱም ለተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በአሜሪካ በኩል የሰጠውን ቃል አፍርሶ ለእስር ሲዳርጋቸው ከርቸሌ ሆኖ በደርግ ጓደኞቹ ላይ ስለላ እያካሄደ መረጃ ለወያኔ ሲያቀርብ መክረሙም የሚታወቅ ነው ። ሲለቀቅም ስብሃት ነጋ አቅፎ ደግፎ ትግራይ የወሰደውና መጽሃፉንም ያሳተሙለት አለምክንያት አይደለም ። የወያኔ አጋርና ዘረኛ ትግሬ ሆኖ ይኸው እነ ጸጋዬን፤ መምህር አግማሴና ስንቶቹ ደብዛቸው በጠፋበት ሀገር ነጻ ሆኖ እየተንደላቀቀ አለ ። በቀይ ሽብር ጊዜ እርምጃ ይወሠድ ብሎ የፈረመባቸው አያሌ ሰነዶች የእሱ መሆናቸውም የሚካድ አይደለም ። በጻፈው መጽሃፍ ግን ኢህአፓን አጥፊ ብሎ ሊከስ ከመነሳቱ አልፎ ሽብርተኞችና ባንዳዎች፤ እንዲሁም አንዱ የአንጅ ግሳንግስ መጽሃፉን አቅድነቅውለት ሲቸከችኩ ለመታዘብም ደርሰናል ። አንዳድን የፖለቲካ መሃይሞችም ይባስ ብለው ጓዱ ጓዱ ሲሉት ለጻፈው ሀሰት ሁሉ ኢህአፓ ማስተባበያ እንዲያቀርብ ሊያስገድዱን ሲሞክሩም ለመታዘብ በቅተናል ። መበደል ወታደር በድሏል ግን ባለገር ይካስ ወይም ይቅርታ ይጠይቅ ዓይነት አጓጉል ፈሊጥ። ታሪክን ከመቅጽበት መርሳትና የማይሆን ይሆናል ብሎ ቅዠት ። ከዚህ በፊት በመድረክ ድንገት ብቅ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ያለን አንድ ግለሰብ-ማለትም ኦባንግ ሜቶ የሚባልን– ገበና አስጠተን ወገን ጠንቀቅ ብለን ነበር ። ብዙ ሰሚም አልነበረም። የጋምቤላው ጀግና ብሎ አድናቆት ለፋፊዎች በዝተውብን አስቸገሩ ። ያን የአፋሩን አጭበርባሪ መኢሶን ማህሙዳ ጋስን ሲያዳንቁ እንደነበሩት ማለት ነው። ኦባንግ አመጣጡም ሆነ ስራውም ከፈረንጆቹ ፤ ከወንጌለኞች ጋር ነው፤ ንዋይ አፍቃሪ ነው፤ ሀቀኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን ልክ እንደ ዶክተር መስፍን ጥግ ሊያስይዝ የተላከ ነው ብንል ማን ሊሰማ? ከውሁዳን ቢወለዱም እኮ ከሀዲ ባንዳዎችን ማውገዝ ምንም ጥፋት የለውም ኢትዮጵያዊ እስከሆንን ድረስ ! አሜሪካ ኮለኔሉን አምጥታ የህዝብ አመጽ ልታከሽፍ ስትመከርና ስታሴር አማካሪ የነበሯት ውስጥ ሁለቱ ዋናዎቹ ካሳ ከበደና ኦባንግ ሜቶ መሆናቸውን ቀደምም ገልጸን አጋልጠን ነበር ። ይኸው የለመደች ጦጣ ነውና ኦባንግ አዲስ አበባ ሄዶ ሊሰግድ ሲዝለፈለፍ ስለናቁትና ስለዘጉት ማምረር ሲገባው ገልበጥ ብሎና በሀፍረት ጎዳናው ቀጥሎ ደርግ ኢትዮጵያን ሊጎዳ የመጣ ሀይል ወይም አገዛዝ አልነበረም ሲል በይፋ ለፍፎ በወገን ደምና መስዋዕትነት ላይ ተሳልቋል፤ ቀልዷል። የራሳችንን የመወናበድ ዝንባሌ በሚገባ ሳይወድ አጋልጧል። ሰዎቹ ግን ያው ናቸው ። ምንም አልተማሩም፤ ምንም አልተቀየሩም ። ደርጎቹ የከፉ ደርጎች ናቸው ዛሬም፤ ወያኔዎቹም ቆሌ ቢስ ዘረኛ ዛሮች ናቸው ምንም እንኳን ዛሬ ግደይ ሳይሆን መገርሳ ቢባሉም።
ዛሬን ዛሬ ጠልቼ፤ የነገውን ማሰብ ፈርቼ
የጊዜን ኋላ መብራት አበራሁ
ባለፈው በሞተው ተቀብሮ ባበቃው
ልጨፍር ተነሳሁ።
ቀደም የህዝብን ትግል በወያኔ ጊዜ በ1997 ዓ.ም. አፈር ያበሉትን ከሀዲዎች ዛሬ ሀገር ወዳድ ሀገር አድን ብሎ ለመቀበል መቅበዝበዝ ይታያል። የወያኔ መጋዣዎችን ዳግም ለማቀፍ ክጀላ ። በአሁኑ ጊዜ የሽግግር ሂደትን ደጋፊ መስለው ብቅ ብለዋል አንዳንዶቹ ። የለየላቸው ለምሳሌ እንደ ግንቦት 7 ዓይነቶቹ ኮለኔሉን ደግፈው ሽግግር ማለት ጸረ ለውጥ መሆን ነው ብለው ይፋ ወጥተዋል ቢያንስ። አስመሳዮቹና ግን ከወያኔ ሲያሴሩ ቆይተው የሽግግር ሂደት ደጋፊ መስለው ብቅ ሲሉ ትላንትን የረሱ ደግሞ ጥሩ አቅዋም ያዙ ብለው ክህደቱዎችን ሊደግፉ ደፋ ቀና ሲሉ መታዘብ ተገደናል ። ገና ከጥዋቱ አነሳሱም ሂደቱም የወያኔ ነው ብለን ያጋለጥነው ኢዴፓ የተባለ ቡድን መሪ ዛሬ ሀገር ወዳድ ከቶም ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅ ሲገባ ያደረሰውን ጉዳትና ጥፋት ዘንግተው አንድ መፈክር ሰርቆ ስላስታጋባ ደህና ሆነ፤ አቅዋሙ ተሻሻለ ማለት ብቻ ሳይሆን ሽግግር ሂደት ሲል ኢህአፓ ምን ማለቱ እንደነበር እንደሆነ ዳግም ያስረዳ በሚል የተባለውን ሁሉ ረስተው ክህደቱን ደጋፊ ቅብጥርጥር ሲያሰሙ ማድመጥ ተገደናል ። ይህ ጉዳይ የተጠናወተንን አሳሳቢ ድክመት ጠቋሚ ከመሆን አልፎ ምንኛ የሀገራችንን ሁኔታ እንደማንከታተል፤ በብልጭታ እንደምንደናበር፤ የፖለቲካ ብስለት እንደጎደለን ፤ የአልጫ ፍቅር ሰለባ መሆናችንንም የሚያጋልጥ ሆኗል። ያ የሚተቹት ትውልድ ቢያንስ የነበረው የፖለቲካ ንቃት ሩቡን ባገኙት የሚያሰኝ ነው ። ይህን ቡድንና መሪዎቹን ያኔ ከጅምራቸው ስናጋልጥ መረጃችን መቶ በመቶ ጠንካራና ከወያኔ ራሱ ጉያ የተገኘ ነበር። በመረጃችን አቅዋም ላይ በእራሱ ምክንያት ያጀበን ዶክተር ታዬ ወልደ ሰማያት ብቻ ነበር። በየጊዜው ለሚደርሰው ሀገር ጎጂ ውዥንብር ተጠያቂ ራሳችን መሆናችንን መካድ አንችልም። ችግሩ ከፖለቲካው ጦመኛ፤ ከወሬውና ሁካታው ፈሳኪ በመሆናችን መሆኑንም መቀበል አለብን ። ዘመን ሲያልፍ በዓለም ደረጃ የፖለቲካ ንቃትና ብስለት ውድቅ ሆኗል። ቀደም በዚያ ትውልድ እንደነበረው ርዕዮታዊ ግንዛቤን ለማጠናከር ማንበብ ማጥናትን ማንም ዛሬ ጠያቂ የለም፤ ቢያንስ ግን ተጨባጩን ሁኔታ ማወቅ መከታተልን ዛሬም መጠየቁ አልቀረም ። ታዲያ ህሊናውም ግንዛቤውም ላይ ተኝቶ በባዶ ሚንጣጣ በበዛበት ሁኔታ ንቃት ቢጠፋ አስገራሚ አልሆነም። ትላንት ተረስቶ፤ ዛሬን ማወቅ ተስኖ ነገን እንዴት ልንረዳው? እንዴትስ ልናወቀውና ልንዘጋጅለት? ሽግግር ስንል ሸግግር ሲሉ በሚል ከዓመታት በፊት ያወጣነው ጽሁፍ በዚህ በሽግግር ርዕስ መባል ያለበትን የጨረሰው ስለሆነ የምጨምርበት የለም።
ካለም በዚህ ጉዳይ ዕንቅፋት የሆኑትን መጥቀስ ብቻ አስፈላጊ ይሆንብኛል ። ደርግ ለጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት የተቃወመው ሥልጣኑን የሚቃረነው በመሆኑ ነበር ። ወያኔ ሽግግር ሲል በራሱ ቁጥጥር ስር የፈለገውን መፈጸም በመሆኑ ስብሰባ ከመስሎቹ ጠርቶ ራሱን በሥልጣን በነሌንጮ ለታ አጨብጫቢነትና በሻዕቢያና አሜሪካ ድጋፍ እነ ኢዴኅቅን አግልሎ እውን አድርጓል ። ውሸት አይታክቴው ወያኔ (ጌታቸው ረዳ የተባለው የሰው ቃርዳ) ከደርግ በቀር ሁሉን ለሽግግር ጉባኤ ጋብዘን የሽግግር መንግሥት መሰረትን በሚል በሰሞኑም ሳይቀር ሲዋሽ ተደምጧል ። የዛሬው ዘረኛ ደግሞ ራሱን ኮለኔል አሻግሬ ብሎ ሰይሞ ከነአካቴው ሽግግር ማለት ለእኔ ኮሶ ነው ብሎ ተሰይሞ ይገኛል ። የደርግ አገዛዝ አክትሞ በሀገር ላይ አደጋ ሊመጣ ሲል በድርጅት ደረጃ ባደረግነው ጥረት የፈረንሳይና ጣሊያንን ድጋፍ አግኝተን የተሞከረውን ከዚህ በፊትም ገልጠነዋል ። የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒሲቴር አንድሮዮቲን አግኝተን በሀሳቡ ተስማምቶ መንግሥቱ ሀይለማርያምን ወደ ሮማ ጠርቶ (ካስፈለገም ለመንግሥቱ ጣሊያን ጥገኝነት ሰጥቶ ሊያግባባው ተስማምቶ) የሽግግር ሀሳብ ተቀበል ብሎ ካነጋገረው በኋላ ፋሺስቱ ኮለኔል ተስማማሁ ብሎ ወደ ሀገር ሲመለስ ክተት ማወጁንና ሸብረክ ማለቱንም ገልጸናል ። ፈረንሳይም የወያኔ ወደ አዲስ አበባ ግስጋሴ ቆሞ፤ ካስፈለገ ጅቡቲ ካለው የፈረንሳይ ጦር የተወሰነው በገላጋይነት አዲስ አበባ ገብቶ፤ ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀይሎች በፈረንሳይ ምድር ስብሰባ አድርገው የሽግግር ውሳኔ ላይ ይድረሱ ስትል ያቀረበችውን ሀሳብ አሜሪካ በክፉ ወስዳ ወያኔ ባስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲገሰግስ ከመግፋቷ በላይ በነተስፋዬ ወልደ ስላሴ፤ ካሳ ከበደ ወዘተ አማካይነትም ከደርግ በኩል ምንም ተቃውሞ እንዳይኖር ለማድረግ የመንግስቱንም ሽሽት ሳይቀር አዘጋጅታ ኢትዮጵያን ለወያኔና ሻዕቢያ አስረክባለች፤ የሽግግር ጥረታችንን አክሽፋለች ። ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በዘረጋው ኬላ ብዙዎች ሊያመልጡ የጣሩ ደርጎች ተይዘው ለወያኔም ተሰጥተዋል።
በዚህ ቀውጢ ግዜ ኢትዮጵያን ለመታደግ የወስድናቸው ልዩ ልዩ እርምጃዎች ጊዜ ሲፈቅድ የሚተረክ ይሆናል ። የወቅቱ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትም ሞስኮ ድረስ ሄዶ ጎርባቾቭ የተባለው ህዝብን ከሀዲ መንግሥቱን እንዳይረዳ አስማምቶታል ። ድርድር በሚል ለንደን የመጡትን የአገዛዙ ወኪሎች የተባሉ ቅጥረኞችዋን ከሞላ ጎደል ወዲያውኑ ጥገኝነት ሰጥታ እነ አሻግሬ ይግለጡን፤ ቢሊሊኝ ማንደፎን፤ ተስፋዬ ታደሰን አሜሪካ ማስገባቷን ልንረሳ አንችልም። ከለንደኑ ስብሰባ በፊት ኢዴኅቅ አግኝቶ ቢመክራቸውማ ያው ለአሜሪካ እጅ ሰጥተዋል ። የሽግግር ሂደት የኢትዮጵያን የቀውስና ግጭት ሁኔታ አስወግዶ ወደ ብሄራዊ መንግሥት መመስረት ዋነኛውና ብቸኛው መንገድ በመሆኑ እስከዛሬ ድረስ የሥልጣን ጥመኞችና በተለይም ባዕዳን ቢቃወሙት የሚያስገርም አይሆንም።
የቀልድ ቋት ኢትዮጵያ፤ ጉደኛ ታሪከኛ
ክብርሽ ያላት ያፈቀራት ዱር ወዳቂ ስደተኛ
ላጥፋሽ ያላት ልገንጥልሽ
ቤተኛ፤ ባለሥልጣን ሹመኛ።
በመሆኑም የነሱ ጥቅማቸውን ለመጠበቅ መዋደቀቻው የሚጠበቅ ቢሆንም የእኛ ግን የራሳችንን፤ የሀገራችንን ጥቅም ነጋ ጠባ አሳልፎ መስጠት ወይም ማስበላት በዝምታ ሊታለፍ የሚገባው ሊሆን አይችልም። በአጭሩና በእቅጩ ለሰፈነው ውዥንብር ተጠያቂው እኛም ራሳችን ነን ብዬ አምናለሁ። ባለሜንጫውና ገንጣዮች የክብር እንግዳ ሲባሉና እነ ቡርቃ ዝምታን ደራሲዎች ባለጌ ሻዕቢያዎች ቤተ መንግሥት ሲጋበዙ የኢትዮጵያ ሀቀኛ ልጆች ግን አሁንም የቂሊንጦ የጠዋት ማታ ታዳሚዎች መሆን ተገደዋል። ለኢትዮጵያ የደሙላት እስካዛሬ ህቡዕ ወይም ስደተኛ ናቸው ። ከወያኔ ጋር ሆነው የፈጁን፤ ከደርግም ጋር ሆነው የጨፈጨፉን፤ አሶሳ በደኖዎችን የቀፈቀፉት ጭራቆች፤ የባድሜ ደም አፍሳሾች፤ ሁሉም ጸረ ኢትዮጵያ ጭራቆች አልፎላቸዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ የሚያስተዛዝበው ግን እኛው ራሳችን ጠላቶቻችን ወዳጅ ብለን አቅፈን የሰማዕትን ደም ዳግም ስናረክስ ስናፈስ ነው ማለት ይቻላል። ታሪክ የሠራውን ትውልድ እያወገዝን ገዳዮቹን፤ ሀገር አጥፊዎችን እርሶና እሳቸው ስንል መሰማቱ ያሳዝናል ። የኢትዮጵያ ታሪካ የህዝብ ትግል ዋና አካል የሆነውን ኢህአፓን በተደረገበት አፈና ተባብሪ ሆነው የህዝብ ጠላቶችን የመድረክ አባወራ ማደርጋቸውን ሁሉም ሊታዘብ የሚችለው ሁኔታ ነው ። ድርጅቱን የሚመለከትን ጉዳይ እንኳን አብራሪ ብለው የሚያቀርቡት ድርጅቱን ከካዱ ዘመን ያለፈናቸውን ወይም ከታሪክ እውቀት አንጻር ግልቦችን ነው። በሰሞኑ ስዩም መስፍን የተባለውን የውሸት ቋት ቃል መጠይቅ አድርገውለት ቀደም በመጽሃፍ ሳይፍር እንደቀጠፈው ሁሉ በስፋት ሳያፍር ዋሽቷል ። የሚያስገርመው እንበልና ዓመታት አልፈው የረሳና የማያውቅ ትውልድ ብቻ ሀገራችንን ሳይሞላት ሁሉን የምናውቀው ባለንበት ሲዋሹ ነው።
በዚህ ጎን መነሳት ያለበት ሌላ ነጥብ ጋዜጠኛነትን ይመለከታል። በሀገራችን ዘንድሮ ጋዜጠኛ መሆን–ያው እንደ ፖለቲከኛ- ምንም ዕውቀትንና ስልጠናን የማይሻ መስክ ተደርጎ ተወስዷል ። የጦር ሠራዊት መድፈኛው፤ የደህንነቱ ሰላይ መኮንን፤ ነጋዴው፤ የደርግ እስክስታ መቺና ጮቤ ረጋጭ ሁሉ ጋዜጠኛ ነኝ ብሏል ። ቃለ መጠይቅ አቅራቢ፤ ሰበር ዜና ብሎ ቀጣፊ፤ የእውነትን ጭራ ይዞ በሀሰት ጋላቢ ሁሉም ጋዘጠኛ ሆኖብናል ። ቅጥረኛ ጋዜጠኛን እንኳን ድሮም የምናውቀው ነው ። እነኝህ ጋዜጠኞች ቃለ መጠይቅ ሲያቀርቡ ስለጉዳዩ ምንም አያውቁም፤ መጠየቅ ያለባቸውን አይጠይቁም፤ የጋዜጠኛ ስነ ምግባር ጋር ማንም አላስተዋወቃቸውምና ብዙ ጉዳት እያደረሱ ናቸው። ሀሰትን በማሰራጨቱ መስክ ማንም አይደርስባቸውም፤ የአሉባልታ ዋና አሰራጮችም ናቸው፤ ሀቁን ማቅረብ ሲገባቸው የራሳቸውን ጥላቻና ጎባጣ አቅዋም ማራገቡን ይመርጣሉ ። በዚህም መስክ ኢህአፓ ላይ በየፊናቸው ዘምተዋል። የሚያቀርቧቸው ከንቱዎች ኢህአፓን ሲዘልፉ ምላሽ ስጡ ብለው ድርጅቱን አይጋብዙም፤ አንጃ ግራንጃውን ኢህአፓ ሊቀመንበር መስራች ወዘተ ብለው በማቅረብ ለኮለኔሉና ገንጣዮች ይረዳሉ ። የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የተባለው ያው የአሜሪካ በመሆኑ ቢዘምትብንና ሊይለየን ቢሞክር ባንገረምም ሊሎቹ ደግሞ ጀርባቸውን ስንመረምር ወይም የደርጉ ርዝራዦችና ወንጀለኞች ሲሆኑ አሊያም የወያኔ ቅጥረኛና አገልጋይ ሆነው እናገኛቸዋለን ። ለቃለ መጠይቅ የሚያቀርቧቸው የደርግና የወያኔ ወንጀለኞች ናቸው ። ቀባብተው ያቀርቧቸዋል፤ አውሬዎቹን ሰው ሊያስመስሉ ደፋ ቀና ብለው መድረክም ሰጥተው ህዝብን ያደናግራሉ ። መንግሥቱ፤ ፍቅረ ሥላሴና ፍስሃ ደስታ በኢህአፓ ላይ እንዲዘምቱ መድረክ ሰጥተው የተከሰሰውንና ሰለባ የነበረውን ድርጅት መሪዎች ሆኑ አባሎች አንዴም ጋብዘው ሲጠይቁ አይታዩም። በተወሰነ ጊዜ በዜጎች ግፊት አንድ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛ ባልደረባ ቃለ መጠይቅ ላቅርብልህ ብሎ ስለ ኮለኔሉ አመጣጥና የአሜሪካ ሴራ የነገርኩትን ሆነ አንጃውን ያጋለጥኩትን ማሳለፍ አትችልም ብለው ከልክለውት ሊክደው የሞከረውን ሀቅ (ራዲዮው የአሜሪካ መንግሥት መሳሪያ መሆኑና ጸረ ኢህአፓዎች ሚርመሰመሱበት መሆኑን ) ግተውታል። 44 ዓመታት ይህ ራዲዮ በኢህአፓ ላይ ዘማቾችን ሲያቀርብ ኢህአፓን አምስቴም መጠየቁና ማቅረቡን አላስታውስም ። አንጃዎቹን ማነንታቸውን እያወቁ የኢህአፓ አመራር ብለው አቅራቢዎች የለየላቸው ብቻ ሳይሆኑ ከነሱም ተለይተናል ብለው ሚመጻደቁትም መሆናቸውን ታዝበናል።
ወደ ቁምነገሬ ለመመለስ ወያኔና ህብረት አፍራሾችን ጋባዥ የሆኑት የሚዲያ ሰዎች (በሀገርም በውጭም) በቅርቡ ስዩም መስፍን የተባለውን ቀጣፊ ከአንድ መሰሉ ጋር በቃለ መጠይቅ አርበው አይተናል፤ ሰምተናል። በቅድሚያ ስለ ውሸትና ውሸታሞች አንድ ልበል ። እኛ ገና ሲመሰረት ወያኔን የሟርተኛ ዋሾዎች ግንባር እንለው የነበር ነው ። የመጀመሪያ መርሃ ግብራቸው ራሱ ውሸት አዘል የግንጠላ ሰነድ ነበር ። ሀብታሟን ትግራይ ያደኸያት የምኒሊክ የሸዋ አማራ ጦር ነው የሚል ታሪክ ከመፈብረካቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ መኖር አይችልም፤ አማራው ጨቁኖታልና ብለው ከመጀመሪያው የቀጠፉ ናቸው ። መለስ ዜናዊ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብሎ ሲከራከር ከሶስት መቶ ገጽ በላይ የያዘ መጽሃፍን ጽፎ አሰራጭቷል ። 10 መጽሃፍ ከማነብ ከኢሳያስ ጋር መወያየቱ ይበልጥ ያስተምረኛል ያለም ጉድ መሆኑን መርሳት አይገባም ። ወያኔን የሻዕቢያ ልብ ወለድ ስንለው የቆየነውም ልብ ወለድ አጠንጣኝ ስለነበርም ነው ። ባጭሩ ወያኔ እንደ ድርጅት የወጣለት ዋሾና፤ ትግሉም በውሸት ላይ ማጠየቂያ የገነባ መሆኑ ይታወቃል ።ስለዚህ የሚገርመው ስዩም መስፍን ባይዋሽ ነበር ። ይህን ግለሰብ የማውቀው በሱዳን ሳለና ስዩም ሙሳ ይባል በነበረበት ጊዜ ነው ። አናግሬው አላውቅም፤ቢሆንም ስራ ነውና ማን መሆኑን አውቅ ነበር ። የውጭ ጉዳይ ስራቸውን የሚሰራ ነበር በሱዳን ። የሱዳን ባለስልጣኖች ስዩምን አህያ ማለት አህያን መስደብ ነው ይሉ እንደነበረው ችሎታ ቢስ ቀትረ ቀላል የሆነው ይህ ግለሰብ በመለስ ዜናዊ መመሪያና ትእዛዝ ስር ይሰራ የነበር ነው ። መለስ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሲያረገው ስራውን በሚገባ እንደማይሰራ ስላወቀ በፓትሪክ ጂልክስ የሚመራ የንግሊዝ ቡድን አማካሪ ተደርጎለት አብዛኛውን የወጭ ጉዳይ ስራ (መግለጫ እስከማርቀና ማሰራጨት ድረስ) ሲሰሩ የቆዩት እንግሊዞቹ ናቸው ። የስዩም ዝምታ መጨመትና የማዳመጥን ችሎታ የሚያሳይ ሳይሆን የመሀይምነቱን መሸፈኛ ሆኖ ነው የቆየው። ሞኝ ዝም ሲል አዋቂ ይመስላል ሚባለው በትግርኛም አለ። ስዩም ቢያንስ ጅል መሆኑን ያውቃል፤ ቢሆንም ግን ከወያኔያዊ ውሽትና ቅሌት ሊርቅ መቸም አልቻለም። ከዚህ ተያይዞ መታወቅ ያለበት ሀቅ ደግሞ ውሸት የለመደበት ሰው ሆነ ድርጅት ለቅጥፈቱ ምክንያት ወይም አስገዳጅ ሁኔታ ባልታየበትም ዝም ብሎ መሸምጠጡ የሚታይ ሊሆን መቻሉ ነው ። ኮለኔሉም ይኸ ተነቅቶበት እያለ ውሸት ያዘንብብን የለ? ስዩም ጨንባሳውን በጨው አጥቦ ሱዳንና ሶማሊያን በኢትዮጵያዊነት ተቃውመን ስንቆም ኢህአፓ ግን በብዙ መስክ እነሱን ይተባበርና የነሱንም እርዳታ ያገኝ ነበር ብሎ ሳያፍር ዋሽቷል። መንግሥቱ ኢህአፓን ለማስጠላት ዚያድ ባሬን ደገፈ ብሎ ምድረ ደርግ ሲያናፋ የቆየውን ሀሰት ስብሓት ነጋም አልፎ አልፎ ሊያጮኽው መሞከሩን ጠቅሰን ማውገዛችን ይታወሳል። ስዩም በልማድ ብቻ አይደለም መዋሸት የተገደደው። ከዚያድ ባሬ ጋር፤ ከአረቦች ሁሉ አብረው፤ ኢትዮጵያንም ክደው (አልፎም መለስ ለጋዳፊ አረብ ነን ብሎት) የፈጸሙትን ጸረ ኢትዮጵያ በደል ሰው የረሳ መስሏቸው ኢህአፓን በመክሰሰ ክልስ የተከለሰ ታሪክ ሊጽፉ መጣራቸው ብቻ ሳይሆን ዛሬም የህዝብ ትግል አኮሳምኗቸውና ጥግ ይዘው ሲያቃስቱ ቅጥረኞቻቸውን ን(እነ በቀለ ገርባ ወዘተ) ለመልስ ምት አሰማርተው ሀገር ወዳድ ሊመስሉ ሲጥሩ ማነታቸውን ወንጀላቸውን አልረሳ ብሎ ያስቸገራቸው ኢህአፓ በመሆኑ ድርጅቱ ላይ መዝመታቸው ነው።
ዚያድ ባሬን ማን ደገፈ? ወያኔ።
ከምዕራብ ሶማሊያ ጋር አንድ ሶስተኛ ኢትዮጵያ የሶማሌ ግዛት ነው ብሎ ማን ተፈራረመ? ወያኔ
ማን ሞቃዲሾ ቢሮ እንዲከፍት ተፈቅዶለት ሰራ? ወያኔ።
ማን የሶማሌ የዲፕሎማት ፓስፖርት ጭምር ተሰጠው? መለስና ስዩም፤ ወያኔ።
ማን በሶማሊያ የድጋፍ ወረቀት ተጽፎለት በአረቦች ተረዳ? ወያኔ።
ማን በሱዳን ግፊት ተከዜ ድልድይን ሊያፈርስ ሞከረ? ወያኔ።
ማን ሱዳንን ለመርዳት ደቡብ ሱዳኖችን ሊያጠቃ ወለጋ ጦር ላከ? ወያኔ።
ማን ለ ሱዳን መሪዎች ከፍተኛ ጉቦ ሰጥቶ የሱዳንን የመሳሪያ መግዣ ሰነድ አግኝቶ ደርግን መውጊያ በሚሊዮን ወጪ መሳሪያ ከቻይና ገዛ? ወያኔ።
ማን በጸረ ኢትዮጵያ ምዕራባውያን በረሃቡ ሽፋን ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሰጦት ጄዳህ ባለው ሳውዲ አሜሪካ ባንክ አስቀመጠ? ወያኔ።
ማን ወጣት ትግሬዎችን ለሻዕቢያ መሳሪያ ልዋጭ አድርጎ በናቅፋ አስጨረሰ? ወያኔ።
ሞኝ አያውቁብኝ ባይ እንዲሉ ነው። አልጄርስ ሄዶ የኢትዮጵያን መሬት ለሻዕቢያ ለቆ አሌ ብሎ ሲዋሽ በህዝብ የተጋለጠ ኢህአፓ ሳይሆን ስዩም መስፍን ራሱ ከነአለቃው ነው ። ስዩም መስፍን የኢትዮጵያ ዋና ጠላት፤ ዘረኛ፤ በሙስና የተጨማለቀ፤ በርግጥም ባለጌ ፍጡር ነው። ለነዚህ መድረክና ድምጽ ሰጥተው ዳግም ኢትዮጵያን ሊጎዱ ሊያስጎዱ የተነሱትን ማውገዝ ተገቢ ነው። ለሀገር ቆመናል እያሉ ከርሳቸውን ሊሞሉ ብቻ ቆርጠው የተነሱት ከወያኔም ከወንጀለኞች ሁሉ ጎን ቆመው ኢትዮጵያን እየጎዱ ነው። የኢህአፓ መርሁ ስልጣን በሆነው መንገድ፤ ማለትም ሀገርንም ሸጦ፤ የሚል ቢሆን ኖሮ የታሪክ ጎማ ሚሄድበት መንገድ ሌላ ሊሆን ይችል እንደነበር ግልጽ ነው ። የሥልጣን ጥምና ዘረኝነት ወያኔን ወደ ወንጀልና ውድቀት እንዳመራው ሁሉን ዛሬም ኮለኔሉ ተመሳሳይ በሽታና ደዌ ይታይበታልና መጨረሻውን ከወዲሁ መናገር እንችላለን። ዋሽተው ለስልጣን የበቁና የቀጠሉ ዋሽተው ከትቢያ ሊነሱ መፈቀድ የለበትም። ወያኔና ዘረኞች ሁሉ ይውደሙ።
ይሻልን ስንጠብቅ ይብስ እየመጣ
ጸረ ሕዝብ ያልነውን ጸረ ሀገር ሲተካ
ትላንት የደም እንባ ዛሬም ቀጣይ ጣጣ
ትኩሱ ሬሳ ደረቁን ሲያስረሳ
ግደይ ስብሀትን መገርሳ ሲተካ።
ይቀጥላል……