ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ኅዳር 28 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የዓለም ባንክ የብር ዋጋን እንዲያስተካከል ለወያኔ አገዛዝ ሀሳብ አቀረበ – የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ዜጎቹ ድጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጠ – ሳዑዲ አረቢያ በጂቡቲ የጦር ሰፈር ልትመሰርት ማቀዷ ግብጽን አሳስቧል።
የዓለም ባንክ በቅርቡ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባዘጋጀውና ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ዘገባ የወያኔ አገዛዝ የብርን ዋጋ እንዲያስተካከል ጠይቋል። በአዲስ አበባ በአንድ ሆቴል ውስጥ በተደረገ ስብሰባ የባንኩ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው የንግድ ዕቃዎች እያሽቆለቆለ መሄዱንና ይህም የውጭ ንግድ ገቢን እንዲቀንስ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ለማስተካከል የውጭ ምንዛሬን ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል። የብር ዋጋ ከዶላር እና ከሌሎች የውጭ ምንዛሬ ገንዘቦች ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ስለሆነ ዋጋው መቀነስ አለበት ብለዋል። በስብሰባው ላይ የተገኙ የወያኔ ባለስልጣኖች የብር ዋጋ መቀነስ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዋዎችን ስለሚያስወድድ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የሚፈጥር በመሆኑ ሊሲው አይመረጥም ብለዋል። የዛሬ ስድስት ዓመት የአንድ ዶላር ምንዛሬ በብር ከ13.80 ወደ አ16.85 ከፍ ማለቱ ከፍ ያለ የዋጋ ግሽበት ፈጥሮ እንደነበር በማንሳት ለመከራከር ሞክረዋል። የዓለም ባንክ ባለሙያዎች ቀደም ብሎ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት ከዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር የተያያዘ እንጅ ከብር ምንዛሬ ማስተካካያ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ጠቅሰው የብር ዋጋ አሁንም ከሚገባው በላይ የተተመነ መሆኑ ጠቅሰዋል። በባለሙያዎች አባባል የብሩ የምንዛሬ ለውጥ ከተስተካከለ በኢንዱስትሪ በአገርልግሎትና በውጭ ንግድ ዘርፍ ተጨማሪ ገቢዎች ሊገኙ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማክሰኞ ኅዳር 27 ቀን ባወጣው መግለጫ ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ዜጎቹ ቀደም ብሎ የሰጠውን የምክርና የማስጠንቀቂያ መግለጫ የሚያጠናክር መልእክት አስተላለፏል። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በተለይም ሕዝባዊ የሆነው የአመጽ አንቅስቃሴና አገዛዙ የሚወስዳቸው የአጸፋ መልሶች ምን ሊሆን እንደሚችሉ በአስተማማኝ መልኩ መተንበይ ስለማይቻልና ውጥረቱ ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን በመግለጽ መስሪያ ቤቱ ለአሜሪካ ዜጎች ሲያስተላልፍ የነበረውን ምክርና ማስጠንቀቂያ መስጠት መቀጠሉን ገልጿል። የወያኔ አገዛዝ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስታውሶ በዚህ ህግ መሰረት የዜጎች መሰብሰብ፤ ግንኙነት ማድረግ፤ የተቃዋሚ የቴሌቪዥንና የራዲዩ ጣቢያዎችን ማዳመጥ፤ በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ከውጭ ሰዎች ጋር መገናኘት የተከለልከለ መሆኑንና ይህንን የተላለፉ ዜጎች አለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደሚታሰሩ ገልጿል። የወያኔ አገዛዝ የያዛቸውን የአሜሪካ ዜጎች ለኤምባሲው በወቅቱ እንደማያሳውቅም ጨምሮ ገልጿል። በኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር ምክንያት የኢምባሲው የኮንሱላር አገግልግሎት ውስን መሆኑን አስታውሶ ወደኢትዮጵያ የሚሄዱ ዜጎቹ ከፍተኛ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክሩን አስተላልፏል።
ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ