(ፍካሬ ዜና ጳጉሜ 05 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የአመት በዐሉ ገበያ እንደተለመደው ሰማይ መውጣቱ ታወቀ – አዲስ አበባ በቆሻሻነት የቀዳሚነትን ክብረ-ወሰን እየያዘች መሆኑ ታወቀ – ወያኔ የጠፈጠፋቸውና ለማዳ ተቃዋሚ የሚባሉት ግንባር መመስረታቸው ተነገረ – የእስራኤሉ ኩባንያ ወያኔን ሄግ በሚገኘው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መክሰሱ ተሰማ – ኢትዮጵያ በቀውስ ከሚናጡ ሀገራት አንዷ መሆኗ በጥናት መረጋገጡ ይፋ ሆነ – በከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ እየፈለሱ ከአገር መውጣታቸው ድንጋጤ ማስከተሉ ታወቀ – ኢትዮጵያ በቀውስ ከሚናጡ ሀገራት አንዷ መሆኗ በጥናት መረጋገጡ ይፋ ሆነ – በመጪው አመት የሥራ-አጥ ቁጥር በእጅጉ ይንራል ተባለ = ወያኔ የእርስ በእርስ ግጭቶችን መለኮሱን እንደቀጠለበት ከሚደርሱን ዘገባዎች መገንዘብ ተችሏል።
የአመት በዐሉ ገበያ እንደተለመደው ሰማይ መውጣቱ ታወቀ
የዘንድሮው የአዲስ አመት መሸጋገሪያ ገበያ ለሽያጭ የቀረቡ የበግና የበሬ ገበያ ብዛት ከአምናው ያን ያህልም የተለየ አለመሆኑ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚገኙ ገበያዎች የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ አምና በመላው ሀገሪቱ እንደ ሰደድ እሳት በተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ሳቢያ ወደ አዲስ አበባ ለሽያጭ ይገቡ የነበሩ የበግና የበሬ አቅርቦት መስተጓጎሉ የሚታወስ ነው፡፡ ዘንድሮም ወደ ገበያ የወጡት ብዛታቸው ከአምናው የማይበልጥ መሆኑን ገበያዎችን ከቃኙ ወገኖች መረዳት ችለናል፡፡ ዘንድሮ በተለያዩ የማህረሰብ መገናኛ ብዙሀን ወያኔን በመቃወም ለመስከረም አንድ የተላለፈው ጥቁር ልብስ የመልበስ ጥሪ የከብት ነጋዴዎችን ማሸማቀቁን ከገበያው ማስተዋል ይቻላል ተብሏል፡፡ የዶሮ ገበያውን በስፋት የሸፈኑት በዘመናዊ ሁኔታ የተራቡት ዶሮዎች ሲሆኑ ዋጋቸው ከሁለት መቶ ሃምሳ እስከ ሦስት መቶ ሃምሳ ሲሆን በባህላዊ ሁኔታ የተራቡ ዶሮዎች ዋጋ ከሦስት መቶ እስከ አምስት መቶ ብር መሸጣቸው ታውቋል፡፡ የበግ ዋጋ ከሁለት ሺ አምስት መቶ ብር እስከ ሰባት ሺ ብር ሲሸጥ ተስተውሏል፡፡ የአንድ በሬ ዋጋ ከአስራ አምስት ሺ ብር እስከ ሠላሳ ሺ ብር እየተሸጠ ነው ተብሏል፡፡ አንድ ኪሎ ቅቤ ከሁለት መቶ ሰማንያ እስከ ሦስት መቶ ሃያ ብር እየተሸጠ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለሁሉም የሀገር ውስጥ የምግብና የእህል ሸቀጣች ዋጋ መጨመር ነጋዴዎች ከሚሰጧቸው ምክንቶች አንዱ የዶላር መጨመር መሆኑ በጣም አነጋጋሪ ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አበባ በቆሻሻነት የቀዳሚነትን ክብረ-ወሰን እያያዘች መሆኑ ታወቀ
ወያኔ ከአመት አመት የአዲስ አበባን እያወረደና እያዋረደ እንደሚገኝ በተለያዩ ጊዜያት በስፋት የተገለጸ ጉዳይ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ የወያኔ ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የአዲስ አበባን ከመቆሸሽ ባለፈ መጠንባትን ሲዘግቡና ለዚህ ተጠያቂ የሆነውን ወያኔን ሲተቹ ተሰምተው አይታወቅም ተብሏል፡፡ በዚህ እያከተመ ባለው የክረምት ወቅት በበርካታ ቦታዎች የአዲስ አበባ የፍሳሽ መውረጃ ቱቦዎች በቆሻሻ በመደፈናቸው ዝናብ በጣለ ቁጥር አራት ኪሎ፣ ቦሌ ከሳይ ኬክ ቤት እሰከ ወሎ ሰፈር ድልድይ፣ መገናኛ አደባባዩ ዙሪያ፣ ከዊንጌት እስከ ፓስተር አውራ መንገዶቹ ወደ ግዙፍ ጅረትነት እየተለወጡ የእግረኛ ተጓጓዦችን ጉዞ እያተጓጎሉ ሲሆን በወያኔ በኩል አንዳች እርምጃ ሲወሰድ ባለመታየቱ ወያኔ ለአዲስ አበባ ጥፋት የቆመ ነው ተብሏል፡፡ ዘንድሮም በመሀል ፒያሳ አላ ሙዲ በተባለ የወያኔ ተላላኪ ግዙፍ ፎቅ ለመገንባት በወያኔ የተቸረው መሬት ላይ ቁፋሮ ጫር ጫር በማድረግ ብቻ ከአስራ አምስት አመታት በላይ ማስቆጠሩ ሰውየው ሆን ብሎ አዲስ አበባን ለማጥፋ የተሰለፈ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ተብሏል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በአዲስ አበባ የሲዳማ፣ የዶርዜ፣ የወላይታ፣ ወዘተ. ህፃናት በጫማ ጠራጊነት፣ በአነስተኛ ሱቅ በደሬተነት፣ ተማርተው በአውራ ጎዳዎች ላይ ከጠዋት እስከ ማታ ሲውሉ የሚጸዳዱት እዚያው በሚውሉባቸው ጎዳናዎች ላይ ነው ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቀድሞ አዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫ ይታዩ የነበሩ ከትግራይ ይመጡ የነበሩ በልመና የሚሰማሩ ወገኖች ዛሬ አይታዩም፡፡ ይህ የሆነው ወያኔ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እንደ የአሜሪካ ተራድኦ፣ ኦክስፋም፣ ሴቭ ዘ ችልድረን፣ ወዘተ. ድርጅቶች ዘጠና ከመቶ የሚሆነው የእርዳታ ሥራቸውን በትግራይ እንዲያደርጉ በማደረጉ ነው ተብሏል፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እንደ ጉድ በዝተው የሚታዩትን የወላይታ፣ የዶርዜ፣ የሲዳማ ህፃናትን መታደግና ወደ ትምህርት ቤት ማስገባት አንዱ የአዲስ አበባን ገጽ ማስተካከያ ነውና አገር ወዳዶች ያስቡበት ተብሏል፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ ዙሪያው መጸዳጃ ሆኗል፡፡ ሚኒሊክ አደባባ ዙሪያው ይከረፋል፡፡ አውራ ጎዳናዎቹ በአጠቃላይ በግማት የተበከሉ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ የወያኔን በቁሙ መጠንባትና መከርፋት የሚጠቁም እንደሆነ ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡
ወያኔ የጠፈጠፋቸውና ለማዳ ተቃዋሚ የሚባሉት ግንባር መመስረታቸው ተነገረ
በየጊዜው ከወያኔ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለዛ-ቢስ ሞዛዛ ድርድር የተባለ ቀልድ የሚቀልዱት ድርጅት ተብዬዎች ሁሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የወያኔ የእጅ ሥራዎች እንደሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ለወያኔ ማደራቸው ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞችንና ሀቀና ታጋዮችን እንዲከታተሉ ተመድበው እያሳሰሩ እንደሆነ የሚታወቅ ነው ተብሏል፡፡ ጋዜጠኛ እስክድር ነጋን ያሳሰረው ዘመኑ ሞላ የሚባል የወያኔ ጆሮ ጠቢ እንደሆነ በሰፊው ይነገራል፡፡ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት እንደተመሰረተ የሚነገርለት ግንባር መርሀ ግብሩ የተነደፈው በወያኔ መሆኑ ሊጋለጥ ይገባዋል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ህክምና የቁልቁል እየተፍገመገመ እንደሆነ ተገለጸ
በሀገር አቀፍ ደረጃ ህክምና ዘመናዊ ቅርጹንና ይዘቱን የያዘው በትግራይ ብቻ እንደ ሆነ ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በአዲስ አበባ እድሜ ጠገቦቹ ጥቁር አንበሳና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች እስከ ዛሬ የምርመራ መሳሪዎች የተሟሉ የሌላቸው በመሆኑ እንደ ኤም አር አይ እና ሲቲ ስካን የመሳሰሉ ምርመራዎችን ማግኘት የሚቻለው ከሆስፒታሎቹ ውጪ በሚገኙ ጥቂት እነዚህን የምርመራ መሳሪያዎች በሚያሟሉ ማዕከላት ብቻ በመሆኑ በሽተኞች ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጋቸውም በላይ ከቦታ ቦታ በሚያደርጉት ጉዞ ለስቃይ ይዳረጋሉ ተብሏል፡፡ በሀኪሞች ስህተት የበርካቶች ህይወት እያለፈ ሲሆን ይህን ለመቋቋም አግባብነት ያለው ህግ ሊደነገግ ሲገባው በዝምታ መታለፉ የወያኔን ደንታ ቢስነት የሚሳይ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ የኦክስጂን አገልግሎት የሚሰጥ አምቡላንስ እጥረት ስላለ፣ አለ ከሚባል ይልቅ የለም ማለቱ ይቀላል የሚሉ በርካቶች መሆናቸውን ተገንዝበናል፡፡
የእስራኤሉ ኩባንያ ወያኔን ሄግ በሚገኘው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት መክሰሱ ተሰማ
እስራኤል ኬሚካልስ ( አይ ሲ ኤል) የተሰኘ በኬሚካል አሰሳና ማቀነባበር ሥራ የሚሠራ ግዙፍ ኩባንያ ሄግ በሚገኘው በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በወያኔ ላይ ክስ ማቅረቡ ወያኔዎችን ማስደንጡ ሊታወቅ ተችሏል፡፡ ይህ አይ ሲ ኤል የተባለ ኩባንያ በዚህ አመት በጥቅምት ወር አለአግባብ በወያኔ ታክስ እንደ ተከመረበት በመጥቀስ በአፋር በዳሎል አካባቢ ፖታሽ የማውጣት ሥራውን አቋርጦ መውጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ኩባንያው አላና ፖታሽ ከተባለ ኩባንያ ጋር በጋራ ሥራውን እየሠራ ባለበት ለወያኔ ሹሞች እጅ መንሻ ገንዘብ ባለመስጠቱ ከተገቢው የሂሳብ አሠራር ውጪ ግብር እንዲከፍል እንዲጣልበት በመደረጉ ሥራውን መቀጠል እንደተሳነው አሳውቆ ለቆ መውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ኩባንያው በከፈተው ክስ ወያኔ ሥራውን በማሰናከሉ 198 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲከፍለው ኔዘርላንድ በሚገኘው በኩባንያው ቅርንጫፍ በኩል ክስ መመስረቱ ሊታወቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ በቀውስ ከሚናጡ ሀገራት አንዷ መሆኗ በጥናት መረጋገጡ ይፋ ሆነ
የወያኔ ዘረኛ አገዛዝን በመቃወም ሃያ ስድስት አመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ ላይ ያለውን ተቃውሞ ሲሰነዝር መክረሙን ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ሲሆን ወያኔ ሕዝባዊ አመጾችን ለማፈን በርካቶችን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በአልሞ ተኳሾችና በስየል እያሰቃዩ በሚገድሉ ገዳዮች እየገደለና በጅምላ መቃብር እየቀበረ መሆኑም ሊደበቅ ያልቻለ ሀቅ ነው ተብሏል፡፡ አንድ ተቀማጭነቱ አሜሪካ የሆነ የሀገራትን የቀውስ ደረጃ በየአመቱ የሚያወጣ ድርጅት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በአስራ ዘጠነኛ እንደሆነች መጥቀሱ የሚታወስ ሲሆን በቅርቡ ይፋ ባደረገው በአገሪቱ እየተስፋፋ በመሄድ ላይ የሚገኘው ሕዝባዊ አመጽና አመጹን ለመግታት ወያኔ የወሰደው የጅምላ ግድያ ቀውሱን እያባባሰው እንደሆነ በመጥቀስ ኢትዮጵያ አስራ አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚትገኝ ባደረገው ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ እየፈለሱ ከአገር መውጣታቸው ድንጋጤ ማስከተሉ ታወቀ
የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ የያዙ የተማሩ ሰዎች በየጊዜው እየተሰደዱ መውጣታቸው በወያኔዎች ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑ ታወቀ፡፡ እንዲህ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ሀኪሞች፣ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው መሀንዲሶች፣ አውሮፕላን አብራሪዎች፣ ወዘተ. ከሀገር እየፈለሱ መሄድ ወያኔ የሚጨነቅለትን የውሸት ኮስሞቲክ ግጽታውን በመግፈፍ ማንነቱን እንደሚያጋልጡበት ስጋት እንዳደረበት ይሰማል፡፡ አብዛኛዎቹ ሀገራቸውን ለቀው ስደትን የመረጡበት ሰበቡ የደሞዛቸው ዝቅተኛ መሆንን የሚያነሱ ሲሆን ዋናው በነፃነት የምርምር ሥራዎችን ማከናወን ባለመቻላቸው ነውም ተብሏል፡፡
በመጪው አመት የሥራ-አጥ ቁጥር በእጅጉ ይንራል ተባለ<
የዛሬ አምስትና አራት አመታት ከተለያዩ የዩኒቨርሲቲዎች ያጠናቀቁ ተማሪዎች ሥራ ማግኘት እንዳልቻሉ በስፋት የሚታወቅ ነው፡፡ ወያኔ ዘንድሮ አስር ቢሊዮን ብር የሥራ አጦችን ቁጥር ለመቀነስ መመደቡን ይፋ ባደረገ ማግስት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ገንዘቡ በወያኔዎች መበላቱ ታውቋል፡፡ በየአመቱ ከየዩኒቭርሲቲዎችና ከሙያ ማሰልጠኛ ጠቋማት ከሁለት መቶ ሺ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እያጠናቀቁ ቢወጡም ሥራ ግን የሚታሰብ አይደለም፡፡ የትግራይ ተወላጆች ከሌላው በተለየ ሁኔታ ሥራ እንዲያገኙ ያደረጋል ተብሏል፡፡ የሌላው ኢትዮጵያዊ ወጣት ሀገሩ ኢትዮጵያ ሆና ሳለች በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ሥራ ማግኘት የህልም እንጀራ ሆኗል ተብሏል፡፡ በመጪው አመት ወያኔ በለመደው ወጣቶችን መሸንገያው “አነስተኛና ጥቃቅን” በሚለው ሟርት መቀጠል አይቻለውም እየተባለ ነው፡፡ ወጣቶች በሀገራቸው ሠርቶ የመኖር መብታቸውን ለማስከበር የመረረ አመጽ ሊያካሄዱ እንደሚችሉ ከወዲሁ አመላካች ሁኔታዎች እያታዩ ነው ተብሏል፡፡
ወያኔ የእርስ በእርስ ግጭቶችን መለኮሱን እንደቀጠለበት ከሚደርሱን ዘገባዎች መገንዘብ ተችሏል
ማንኛውም አምባ-ገነን መንግስት ከቃሬዛ መቃብር ገብቶ አፈር እስካልለበሰ ድረስ እድሜውን ለማራዘም ሕዝብን ከህዝብ፣ ጎሳን ከጎሳ፣ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ፣ ሀይማኖትን ከሀይማኖት፣ ወዘተ. መባጋጨት ሕዝባዊ አመጹ ክንዱን አስተባብሮ በአንድነት እንዳይቆም ለማድረግ መማሰኑ እንደማይቀር የሚታወቅ በመሆኑ ወያኔ በዚህ እኩይ ድርጊት መጠመዱ እየታየ ነው ተብሏል፡፡ ጭናክሰን እና አወዳይ ኦሮሞዎችን ከሶማሌዎች ጋር፣ ጉጂዎችን ከሲዳማዎች ጋር፣ ወላይታን ከሲዳማ ጋር፣ ቅማንትን ከጎንደሮች ጋር፣ ወልቃይት ላይ ትግሬዎችን ከአማራዎች ጋር፣ ሰሜን ሸዋ ላይ አማሮችን ከአፋሮች ጋር፣ ወዘተ. በማጋጨት ፀረ-ወያኔው ሕዝባዊ አመጽ በወያኔ ላይ ተባብሮ መቆም አንዳይችል በከፋፍለህ ግዛ የጨቋኞች ይትበሀል ሕዝብን እርስ በእርስ እያጋጨና ደም እያቃባ ነው ተብሏል፡፡ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ገሪ የተባለ የሶማሌን ጎሳ እና ቦረናን በማጋጨት ከሠላሳ ሰዎች በላይ ህይወትን እንዳስጠፋ ለማወቅ ተችሏል፡፡