ፍኖተ ዴሞክራሲ – በሆለታ የሚገኘው የአበባ እርሻ የሥራ መሪዎች የነበሩ 4 የኢኳደር ዜጎች ታሰሩ – የዳንጎቴ ፋብሪካ ሥራውን አቋረጠ – ዳንኤል ሽበሽ በዋስ ሲፈታ የአቶ በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄ ለሌላ ጊዜ ተቀጠረ።
የኢኳደር ዜጎች ንብረት የሆነውና በሆለታ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ አፍሮ ፍላወርስ ኩባንያ የሥራ መሪዎች የነበሩ አራት የኢኳደር ዜጎች ከሐምሌ 16 ቀን ጀምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን አዲስ አበባ የሚገኘው የኢኳደር ኤምባሲ አረጋግጧል። ሰዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉበት ምክንያት አበባው እንዳይጠወልግ የሚያደርግ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ኬሚካል በጥቅም ላይ እንዲውል በማድረጋቸው ነው ተብሏል። በኬሚካሉ መብዛት ምክንያት በርካታ ሠራተኞች ራሳቸውን ስተው የወደቁ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ሰራተኞች ወደ ተለያዩ ሆስፒታሎች ተወስደው ህክምና የተደረገላቸው መሆኑ ተነግሯል። ኩባንያው ሥራ የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን አስፈላጊውን መመዘኛ አሟልቶ መሆኑ አለመሆኑ አይታወቅም። የአበባ እርሻ በአካባቢው የአየር ብክለት ላይ እና በሰራተኞች ጤንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ተብሎ የተነገረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የወያኔ አገዛዝ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወሰነውን የቁጥጥር ደረጃ ሳይጠብቅ በዘፈቀደና በብዛት እንዲስፋፉ ያደረጋቸው የአበባ እርሻዎች ወደፊት መዘዛቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይናገራሉ።
የኦሮሞ አካባቢ ባለስልጣኖች ኢዚኢ ኤንጂኔሪንግ (EZE Engineering) የሚባል የቀጣሪና አስቀጣሪ ድርጅትን ተቋም የሥራ ፈቃድ በመንጠቃቸው የዳንጎቴ የሲምንቶ ፋብሪካ የተወሰኑ የምርት ስራዎች የተቋረጡ መሆናቸውን የዜና ምንጮች ገልጸዋል። የቀጣሪና አስቀጣሪ ተቋሙ በዳንጎቴ የሲሚንቶ ፋብሪካ የማዕድንና የማሸግ ስራ ላይ የተሰማሩ 400 ሰራተኞችን አስቀጥሮ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ፈቃድ ስለተከለከለ የፋብሪካው የማዕድን ምርትና የእሽግ ምርቶች መቋረጣቸው ተነግሯል። ፈቃዱ በባልስልጣኖች የተቀማው ሰራተኞች በዳንጎቴ ፋብሪካ ስር በቀጥታ ተቀጥረው ለመስራት የሚፈልጉ መሆናቸውን በመግለጽ የሰራተኞቹ ማህበር አቤቱታ በማቅረቡ ነው ተብሏል። ኩባንያው ምርቱን ለመቀጠል ሰራተኞችን የሚያገኝበትን የተለያዩ አማራጮች እየተመለከተ ነው ተብሏል።
የሰነድ ዝግጅቶች አልተሟሉም በሚል ምክንያት ሳይፈታ ቆይቶ የነበረው ዳንኤል ሽበሽ አርብ ሐምሌ 28 ቀን በ 50000 ብር ዋስ ተለቋል። በተያያዘ ዜና የአቶ በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄ አርብ ሐምሌ 28 ቀን ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በዚህ ቀን የዋለው ችሎት ውሳኔውን ለሌላ ቀን ያስተላለፈው መሆኑ ታውቋል። የዋስትና ጥያቄ አከራካሪ ሆኖ ብዙ ጊዜ የሚወስድ ሳይሆን በአርባ ስምንታ ሰዓት ውስጥ ውሳኔ ሊሰጠው የሚገባ ነው ያሉ ክፍሎች የወያኔ ፍርድ ቤት በእስረኞች ላይ በሚፈጽመው በተለመደው የማዘግየት ቅጣት ለነሐሴ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ መሆኑ ታውቋል።