ዜና ፍኖተ

ነሐሴ 25 ቀን 2008 ዓም. ዜና (August 31, 2016 NEWS):

የወያኔ የጸጥታ ጦር በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ጎንደርና ወደ ጎጃም ለመገባት ሙከራ እያደረገ መሆኑ ከየአካባቢ የሚሰሙ ዜናዎች ይጠቁማሉ። ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰባስቡ በጠቅላላ 25 ሺ የሚገመቱ ወታደሮች በከባድ መሳሪውያዎች በመታጀብና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ወደ ክፍለ ሀገሮቹ በሚወስዱ በሁሉም አቅጣጫዎች እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተሰምቷል። በተጨማሪም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ልዩ ኃይል ተብየው የሚለብሰውን ዩኒፎርም የለበሰ ወታደር ከትግራይ ወታደር እያስገባ መሆኑም ተነግሯል። በአንዳንድ አካባቢዎችም ሕዝቡ ባካሄደው መከላከል የወያኔ ጦር ጉዞ የተሰናከለ መሆኑ ይሰማል። ከወሎ ወደ ጎንደር ይጓዝ የነበረው የአግአዚ ጦር ጋይንት ላይ ሕዝቡ ጦርነት ገጥሞ አላስኬድም ስላለው ወደ ኋላ ያፈገፈገ መሆኑ ይነገራል። በደባርቅ ከተማ በተነሳ ግጭት አራት ሰዎች መሞታቸውና በርካታ መቁሰላቸው ተነግሯል።

በደብረማርቆስ ለሶስት ቀን የሚቆይ የቤት ውስጥ አመጽ እየተካሄደ መሆኑ የተገኘው መረጃ ይገልጻል። ሕዝባዊ አመጹ ወደ ወሎና ወደ ሰሜን ሸዋ ይቀጣጠላል በሚልም እየተጠበቀ ነው። ትናንት ከምሽቱ ጀምሮ የወልድያ ከተማ ነዋሪ ለአመጽ ይነሳል ከሚል ስጋት በከተማው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር ተሰማርቶ እየጠበቀ መሆኑ ከማህበራዊ መገናኛዎች የተገኘው ዜና ይገልጻል።

በምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ግዛት በአካባቢው ባሉ ኦሮሞዎችና በአማራው መካከል ጠብ በመጫር ሁለቱን ብሔረሰቦች ሊያጣላ የነበረው የወያኔ አግአዚ ጦር ሴራው የከሸፈበት ከመሆኑም በላይ ከሕዝቡ ጋር በተድረገ ግጭት አራት የአገአዚ ጦር ተገድለው 13 የቆሰሉ መሆናቸው ሲታወቅ ከከብት አርቢዎች በኩል ሶስት መሞታቸውና ስድስት መቁሰላችው ታውቋል።

#ስድስት የሚሆኑ የሲቪክ ማህበረሰብና የሰብአዊ መብት ጠበቂ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በወያኔ አገዛዝ እየተካሄደ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣና ጭፍጨፋን አስመልክቶ ገለልተኛ የሆነ የዓለም አቀፍ ተቋም እንዲመረምረውና አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብ የጋር ጥሪ አስተላልፈዋል። ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓም የጋራ መልክቱን ያስተላለፉት ድርጅቶች – ኢስት ኤንድ ሆርን ኦፍ አፍሪካ ሂውማን ራይትስ ዲፌንደርስ ፕሮጀክት፤ ዘ አሶስሺየን ኦፍ ሂውማን ራይትስ ኢን ኢትዮጵያ፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ዘ ኢትዮጵያ ሂውማን ራይትስ ፕሮጀክት፤ ፍሮንት ላይን ዲፌንደርስ እና ዘ ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ፎር ሂውማን ራይትስ የተባሉት ድርጅቶች ሲሆኑ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በሚያሰሙ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ህገ ወጥ ግድያና እስራት እንዲሁም በሰብአዊ መብት ተንከባካቢ ድርጅቶች አባላት ላይ እየተወሰደ ያለው የእስራት እርምጃዎች አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል። ስድስቱም ድርጅቶች ባለፉት ሁለት ወራት በዜጎች እና በሰብአዊ መብት ተንከባካቢ ድርጅቶች አባላት ላይ የወያኔ አገዛዝ የጸጥታ ኃይሎች የፈጸሙትን ዝርዝር ድርጊቶች ገልጸው አገዛዙ ያለ አግባብ ያሰራችውን በሙሉ ባስቸኳይ እንዲፈታና ገለልተኛ የሆኑ የዓለም አቀፍ መርማሪዎችና ታዛቢዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ እንዲመቻች ጠየቀዋል።

በአሻንጉሊት ደረጃ ተቀምጦ ተናገር የተባለውን ብቻ ሲለፈልፍ የነበረው ኃይለማርያም ደሳለኝ ማክሰኞ ዕለት የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ውዥንብር የተሞላበት ነበር ተባለ። በጎንደር በጎጃም እና በሌሎች አካብቢዎች እየተካሄዱ ላሉት ሕዝባዊ አመጾች ዋናውና መሰረታዊ ምክንያት የወያኔ ቡድን የ25 ዓመታት ግፈኛ አረመኔያዊ አገዛዝ ሆኖ ሳለ ይህንን በመካድ የተለያዩ ምክንያቶች የደረደረ መሆኑ ታውቋል። በተለያዩ ቦታዎች ለተከሰቱት ችግሮች ከእድገቱ ያልተቋደሱ 20 ሚሊዮን ዜጎች ደሃ ስለሆኑ፤ የባለስልጣኖች የአስተዳድር ጉድለት እና በውጭ ኃይል የሚደገፉ ኃይሎች የሚጎነጎን ሴራ በማለት ምክንያት ለመስጠት ሞክሯል። የተፈጠረውንም ችግር ለመፍታት በአንድ በኩል ከሕዝቡ ጋር መክረን እንፈታለን በሌላ በኩል በኃይል እርምጃ የሕግ የበላይነትን እናስጥብቃለን በማለት እርስ በርሱ የተምታታ መግለጫ በመስጠት ሕዝብን ለመጨፍጨፍ የቆረጡ መሆናቸውን ገልጿል። በድህነት ደረጃ ከዓለም 188 አገሮች ውስጥ የመጨረሻውን 174ኛውን ቦታ በመያዝ የምትታወቀው ደሃ አገር ተሻሽላለች በማለት መመጻደቁ ብዙዎችን አስገርሟል። በድርቅና በረሃብ ቤት ንብረታቸውን አጥተው በውጭ እርዳታ ብቻ ህይወታችውን ያቆዩ ሰዎች በአንድ ወቅት 20 ሚሊዮን የደረሱ መሆናችው በሚታወቅበትና እንዲሁም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ስቃይ ኑሮውን እየገፋ ባለበት ሁኔታ በሚኖርበት ሁኔታ 20 ሚሊዮን ዜጎች ብቻ ደሃ ናቸው ብሎ መናገሩ ራሱንና መሰሎቹን እንጅ ማንንም ሊያታልል አይችልም በማለት በርከት ያሉ ወገኖች እየተናገሩ ነው። ከስላቅ ውጭ ምንም በሕዝብ ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ የሕዝቡን ብሶትና እልህ ጨምሮ ቁርጠኛነቱን ያጠናክረዋል ያሉ ወገኖች ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው የወያኔ አምባገነነት ተወግዶ ሕዝብ ባለመብትና ባለስልጣን ሲሆን ብቻ ነው በማለት ተችተዋል።

አንድ የእስራኤል ፖሊስ ኮሚሽነር እስራኤላውያን የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ ስለሆነ በከፍተኛ ደረጃ ይጠረጠራሉ ብሎ ዘረኛ የሆኑ ንግግር በማድረጉ ከፍተኛ የሆነ ወገዛ እየደረሰበት መሆኑ ከእስራዔል አካባቢ የሚደርሰው ዜና ይገልጻል። የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት የፖሊስ ኮሚሽነሩ ስራውን እንዲለቅና ኃላፊነቱን እንዲያስረክብ ሲጠይቁ የእስራኤል ፓርላማ አባል የሆኑት አቶ አብራሃም ንጉሴ የፖሊስ ኮሚሽነሩ የኢትዮጵያውያኑን ማህበረሰብ ይቅርታ መጠየቅ አለበት በማለት በማህበረስባዊ መገናኚያ መልክት አስተላልፈዋል። የእስራኤል ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከእስራኤል ፖሊስና የጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ በድልና የዘር ልዩነት ሲደርስባቸው መቆየቱና በዚህም ምክንያት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ለበርካታ ጊዜያት ግብ ግብ መግጠማችው ይታወሳል።

ዝርዝር ዜና ለማንበብ ከታች ይጫኑ:

http://www.finote.org/news.pdf

ለማዳመጥ  ደግሞ የሚቀጥለውን ይጫኑ: