ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕጽናት መርጃ ተቋም በኢትዮጵያ እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ዝርዝር መረጃ አቀረበ – የወያኔ አገዛዝ የመቀሌን የሰማዕታት ሐውልት በ700 ሚሊዮን ብር ሊያቆነጅ ነው – የወያኔ ጭምብል ኢሕአዴግ የሚካሄደው ድርድር ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ መሆኑ ተረጋገጠ – የካታሩ መሪ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት ግብጽን ለማስጨነቅ ነው ተባለ – በሰሜን ተራራ ካለው ሰሜን ፓርክ ከቀያቸው የተነሱ ዜጎች የወያኔን አገዛዝ እያማራሩ ነው – በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ የተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት ጉዳት አደረሰ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ተቋም ሰሞኑን በኢትዮጵያ ስለተከሰተው የድርቅ ሁኔታ በሰጠው ማጠቃላያ የተረጅዎችን ብዛት እንዲሁም የእርዳታው መጠንና ዓይነት ለይቶ በማወጣት ዓለም አቀፍ እርዳታ እንዲደረግ ተማጽኗል። መግለጫው በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙ 16 አውራጃዎች ድርቁ መስፋፋቱን ገልጾ ባጠቃላይ 5.6 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጿል። በምግብና በውሃ ማነስ የሚሰቃዩ ህጽናት ቁጥር 4 ሚሊዮን መድረሱና ከእነዚህም ውስጥ 300 ሺ የሚሆኑ ሕጻናት በከፍተኛ የአልሚ ምግብ እጥረት እንደሚሰቃዩ ዘርዝሯል። ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ ህጽናት መካከል በድርቁ ምክንያት የትምህርት አሰጣጡ የተሰናከለባቸው ሁለት ሚሊዮን ሕጽናት መኖራቸውንም ጠቁሟል። በአፋር አካባቢም ከፍተኛ የውሓ እጥረት መኖሩን ገልጾ በሁሉም አካባቢዎች የውሃ እጥረትና የመጻዳጃ አገልግሎት እጥረት የገጠማቸው ዜጎች 9.2 ሚሊዮን እንደሚገመት ተገልጿል። ከጎረቤት አገሮች በተለያም ከሶማሊያ እና ከደቡብ ሱዳን ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የገቡና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቁጥር 801 ሺ መድረሱም ተጠቅሷል። ለነዚህ ሁሉ ዜጎች እርዳታ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረትና ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ እርዳታ ሰጭዎች እጃቸውን እንዲሰነዝሩ ተማጽኗል።
በረሃብ እየተሰቃዩ ለሚገኙ ወገኖቻችን ከፍተኛ እርዳታ እየተጠየቀ ባለበት ሰዓት የወያኔ አገዛዝ በመቀሌ ከተማ ገንብቶት ለነበረው የሰማዕታት ሀውልት ማስዋቢያ በ 700 ሚሊዮን ብር ወጭ ግምባታ ለማካሄድ ያቀደ መሆኑ ተነግሯል። ወጭው የሚደረገው በሀውልቱ ዙሪያ ዘመናዊ ህንጻዎችንና ሌሎች የግንባታ ስራዎችን ለመስራት ነው ተብሏል። ገንዘቡ ከወያኔ አባላትና ደጋፊዎች የተገኘ ይባል እንጅ ከአገሪቱ ሀብት የተዘረፈ መሆኑን ብዙዎች ይነገራሉ። በ1976 ዓም. ወገኖች በረሃብ ሲያልቁ የ10 ኛውን የፓርቲ ምስረታ ለማክበር ሲሙነሸነሽ የነበረው ድርግ መጨረሻው ውድቀት መሆኑን ያስታወሱ ክፍሎች የወያኔም ቡድንም ዕጣ ፋንታ ከውድቀት አያመልጥም ይላሉ።
የወያኔው ጭምብል ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር እያካሄደ ነው በሚባለው ውይይት የተወሰኑት ከድርድሩ ወጥተው ሌሎቹ አለ ገለልተኛ አደራዳሪ ውይይቱን ለመቀጠል መስማማታቸው እንደታሰበውና እንደተገመተው ድርድር ተብየው ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የተደረገ ተንኮል መሆኑ ተረጋገጠ ተባለ። ቀደሞውኑም ቢሆን ድርድሩን ከመጀመር በፊት መሰረታዊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ ይገባ ነበር የሚሉ ክፍሎች አሁን ከድርድሩ የወጡ የተቃዋሚ ኃይሎች ወደፊት ምን አቋም እንደሚወስዱ ግልጽ ባይሆንም ወያኔ ጠፍጥፎ ከሰራቸው የስም ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሄዶ ወያኔ በተንኮል ተግባራዊ እንድሆኑ የፈለጋቸው ጉዳዮች ስምምነት ተደርሰባችው ተብሎ እንደሚገልጽ ይተነብያሉ። ባለፉት 25 ዓመታት የወያኔን ማንነትና አታልይነት በደንብ የተረዳው ሕዝብ ምንም ዓይነት ማጭበርበር የማይቀበል መሆኑን በሙሉ ልብነት መናገር ይቻላል በማለትም አስተያየታቸውን ጨምረው ይገልጻሉ።
የካታሩ መሪ ኤሚር ሼክ ታሚም በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ የሚመጡ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን በተለያዩ መስኮች የትብብር ስምምነቶች እንደሚፈረሙም ተገልጿል። የካታሩ መሪ ጉብኝት ዓላማ ግብጽን ለማበሳጨትና በግብጽ ለሚወስደው እርምጃ ከወያኔ ጎን መቆማቸውን ለማስየት ነው እንጅ ሌላ ፋይዳ ያለው ስራ ለመስራት አይደለም በማለት አንዳንድ ወገኞች አስተያየታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
በጎንደር ክፍለሀገር በሰሜን ተራራ በሚገኘው የሰሜን ፓርክ ውስጥ ዝርያቸው ልዩ የሆኑ ተኩላዎች በቁጥር እያነሱ መጥተው ባጠቃላይ 120 ብቻ መሆናቸው ተገለጸ። የወያኔ አገዛዝ በፓርኩ ዙሪያ የሚገኙትን 9 መንደሮች አፍርሶ ወደ 3000 የሚጠጉ ሰዎችን ወደ ሌሎች ቦታዎች እያሰፈረ ሲሆን ቀያቸውን እንዲለቁ ተደረገው ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ የተደረጉት ገበሬዎች የተሰጣቸው ካሳ አነስተኛ መሆኑን በመጥቀሰ እያማረሩ መሆናችውና ቀሪዎችም አንነሳም በማለት እያንገራገሩ መሆናቸው ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ወገኖች ገልጽዋል።
እሁድ ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ታንታ እና አሌክሳንድርያ በሚባሉ በግብጽ ከተሞች ውስጥ በሚኖሩ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ አይሲስ በወሰደው የቦምብ ጥቃት 44 ሰዎች የሞቱ መሆናቸውና በርካታ መቁሰላቸው ባለስልጣኖች ገልጸዋል። አንድ አጥፍቶ ጠፊ ታንታ ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦምብ በማፈንዳት 27 ሰዎች የገደለ ሲሆን ሌላው አጥፍቶ ጠፊ ደግሞ አሌክሳንድርያ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመግባት ሙከራ ሲያደርግ ከውጭ በፖሊሶች በመከልከሉ ከበቱ ክርሲያኑ ውጭ ያፈነዳው ቦምብ 17 ሰዎች ገድሏል። የአይሲሲ አስተዳድር ለጥበቃ የአገሪቱን ወታደሮች በተለዩ ቦታዎች ያሰማራ ሲሆን ለሶስት ወራት ያህል ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀም መሆኑ ተነግሯል። አይሲስ የተባለው አሸባሪ ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነትን ወስዷል። የግብጽ ኦርቶዶክስ ተከታዮች ቁጥር ከአገሪቱ ህዝብ መካከል አስር ከመቶ ሲሆን በእስላማውያን አክራሪዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽምባቸው ቆይቷል።