ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ሚያዚያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የድርቁ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ደርሰው የተመለሱ የርዳታ ድርጅቶች ሰራተኞች እየገለጹ ነው – የወያኔና የግብጽ ባለስልጣኖች ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሁለቱ መካከል ያለው ችግር መፈታቱን አያሳይም ተባለ – የወያኔው ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተቋም ያቀረበውን ዘገባ ፓርላማው አጸደቀው – በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙ የካናዳ ባለስልጣን የወያኔ አገዛዝ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ለውጥ እንዲያደርግ አሳሰቡ።
በደቡብ፤ በደቡብ ምስራቅና በምስራቅ ኢትዮጵያ የገባው ድርቅ መጠኑ በጣም ከፍተኛ መሆኑን እየተገለጸ ሲሆን በተለይ የኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢን ጎብኝተው የተመለሱ የተባበሩት መንግሥታት ሰራተኞች ስለሁኔታው አሳሳቢነት ዘግበዋል። አብዛኞቹ ነዋሪዎች በእድሚያቸው ይህን ዓይነት ድርቅና ረሃብ ያላዩ መሆናቸውን ገልጸው ከከብቶቻቸው በሙሉ ማለቃቸውንና የያዙትን ቅርስ የጨረሱ መሆናቸውን ተናግረዋል ተብሏል። በአካባቢ ድርቁ ከገባ ጀምሮ ያለቁት ከብቶች የዋጋ ግምት ከ200 ሚሊዮን ዶላር የደረሰ መሆኑ ተገልጿል። ንብረታቸውን ሙሉ በሙሉ ያጡ ዜጎች በእርዳታ እህል ራስን ለማቆየት ወደ መጠለያ የሚሄዱ መሆናቸው ቢነገርም መጠለያ ጣቢያዎቹ እየጨናነቁ በመሆናቸው እርዳታው በተገቢው መንገድ አይደርስም ተብሏል። ባለፈው ዓመት በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ለነበሩ የድርቅ ተረጅዎች ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የተሰበሰበ 1.8 ሚሊዮን ዶላር
የሚገመት እርዳታ የተሰጠ መሆኑ ሲገለጽ በዚህ ዓመት መጠለያ ውስጥ ያሉና በተረጅነት የተመዘገቡ ዜጎችን ለመርዳት 945 ሚሊዮን ዶላር ወጭ እንደሚያስፈልግ ቢገመትም እስካሁን ድረስ የተገኘው ከ23.7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ተብሏል፡፤ በአሁኑ ወቅት በ58 መጠለያ ጣቢያዎች እርዳታ የሚሰጥ ቢሆንም 400000 ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው 222 ትናንንሽ መንደሮች የተሟላ እርዳታ እንደማይደርሳቸው ታውቋል ። ከእነዚሁ መካከል 42 ከመቶ ምንም ዓይነት የእህል እርዳታ የማያገኙ ሲሆኑ የመጠጥ ውሃ ሊያገኙ የሚችሉት ደግሞ 31 ከመቶ ብቻ ነው ተብሏል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ እልቂት ሊከተል እንደሚችል ብዙዎች ይገምታሉ።
በግብጽ ካይሮ ከተማ ውይይት ሲያካሂዱ የነበሩት የወያኔና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከውውይቱ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ መሆናቸው ታውቋል። የወያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተብየው ኢትዮጵያ የግብጽን ሕዝብ ለመጉዳት ፍላጎት የላትም ካለ በኋላ ኢትዮጵያና ግብጽ በፖለቲካ በሶሻልና በኢኮኖሚ ግንኙነት ያላቸው አገሮች እንደመሆናቸው መጠን ይህ ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር አለበት በማለት ተናግሯል። የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ በውይይቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል ባይሉም ግልጽና ቀጥተኛ ውይይት የተደረገ መሆኑን ገልጸው በየሁለት ወሩ ግንኙነቱ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል። ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ በጀርባ ያለውን ሁኔታ አይገልጽም የሚሉ ወገኖች ውጥረቱ ገና ያልረገበ መሆኑን ይገልጻሉ። የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ በኩል የግንኙነት ማሻሻያ ደብዳቤ ወርቅነህ ገብየሁን አስይዞ ሲልክ በሌላ በኩል ግብጽ በኢትዮጵያ ያሉትን ጸረ ሰላም ኃይሎች ላለመርዳታ ቃል ገብታለች በማለት ለአገር ውስጥ የዜና ተቋሞች መግለጫ በመስጠት የተመጻደቀ መሆኑ ተነግሯል። የአባይ ግድብ ስለሚያስከትለው ቀውስ ጥናት እንዲያደርግ ኃላፊነት የተሰጠው ኩባንያ የጥናቱን ውጤት ይፋ እንዲያደርግ በሁሉም በኩል ግፊት መደረግ ይኖርበታል የሚል አቋም በግብጽ ፕሬዚዳንት በኩል እንደተገፋም ለማወቅ ተችሏል። የአባይ ግድብ የግብጽ መንግስትን ክፉኛ እንዳስፈራው ሁሉ የግብጽ በተለይ ከደቡብ ሱዳንና ከሻዕቢያ ጋር ያደረገችው መቃራርብና ስምምነት የወያኔን አገዛዝ አስግቶታል የሚሉ ወገኖች የተድረገው ግንኙነት ለይስሙላ እና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እንጅ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም ይላሉ።
የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተባለው የወያኔ ፍጡር ስለ ሕዝባዊ አመጽ ጉዳይ የቀረበው ዘገባ ዛሬ በወያኔ ፓርላማ ተብየው በሙሉ ድምጽ ጸድቋል። የወያኔ አግአዚ ወታደሮችና የፌድራል የጸጥታ ኃይሎች ያካሄዱትን የጅምላና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ነጻ የሚያወጣው ዘገባ ለይስሙላ አንዳንድ ባለስልጣናትን ቢወነጅልም ወንጀሉን በተቃዋሚ ኃይሎችና በሰላማዊ ሰዎች ላይ መለደፉ ይታወቃል። እንደተጠበቀው ዘገባውን ያጸደቀው የወያኔ ፓርላማ የተቃዋሚ ድርጅቶች አባሎችናሰላማዊ ሰዎች በወንጀል እንዲከሰሱ ወስኗል።
በቅርቡ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ከወያኔ ከፍተኛ ባለስልጣኖች ጋር የተነጋገሩት የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፓርላማ ጸሐፊ ሚስተር ኦማር አልጋርባ የወያኔ አገዛዝ የዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ለውጥ እንዲያደርግ ያሳሳቡ መሆናቸው ተነግሯል። ባለፈው ዓመት በህዳር ወር ላይ መጥተው የነበሩት ሌላው የካናዳ ባለስልጣን እንዳነሱት ሁሉ እኝህም ባለልስልጣን በአገሪቱ ውስጥ ስላለው ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ፤ ስለ ብዙሃን ፓርቲዎች ተሳትፎ እና ስለ መሰራታዊ የሰው ልጅ መብት ጉዳይ አንሰተው መወያየታቸውን አፍሪካ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ ገልጿል።