ከበቀለ ገሠሠ (ዶ/ር) –
፩ኛ/ መንደርደሪያ፤-
የአድዋ ጦርነት ድላችን ከፍተኛ ክብርና ኩራት ያጎናፀፈን ከመሆኑም በላይ ለዓለም ጭቁኖች በሙሉ የነፃነት ትግሎች ከፍተኛ ምሣሌ ጥሎ ያለፈ ተዓምራዊ ክንዋኔ ነበር። የማይጨዉም እልህ አስጨራሽ ትግልና ነፃነት እንደዚሁ። ጣሊያ እኮ በሁለቱም ጦርነቶች ወደአገራችን የዘመተችዉ የራሷን ጥቅም ለማስፋፋት ነበር። ይሄን ደግሞ የተማረችዉ ከርሷ በፊት የአፍሪቃን፤ የኢስያን፣ የፓሲፊክንና የአሜሪካን አገሮች ከተቀራመቱት እንግሊዞች፤ ጀርመኖች፤ እስፓኛዎችና ፖርቹጋሎች በመማር ነበር። የቤርሊን ጉባኤ በመባል በሚታወቀዉ ሴይጣናዊ ስምምነት ላይ የተደረሰ ዉሳኔ በመሆኑ ጣሊያም እንዳበደች ዉሻ እያለከለከች ወደ እኛ አገር ያቀናችዉ ድርሻዋን ልትቀራምት ነበር። በዓለም ላይ ይሄን ቅርምት ያልፈቀደች፤ ያልተበገረችና ነፃነቷን ጠብቃ እስካሁን የቆየችዋ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት።
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ነፃነትና ኩራት ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም የሦስተኛዉ ዓለም አገሮች የኢትዮጵያን ፈለግ በመከተል ለነፃነታቸዉ እንዲታገሉ ሞራል በመስጠት ሕያዉ ምሣሌ ሆኖ ለዘለዓለም የሚኖር ብቸኛ ታሪክ ነዉ። ኢትዮጵያ በነዚያ ጀግኖች አያቶቻችን ስትኮራ ለዘለዓለም ትኖራለች።
ዛሬ አልሞትንም እያልን እራሳችንን እያታለልን በደመ ነፍስ የምንንቀሳቀስ የቁም ማዉታን ግን በነዚያ አርበኞች አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ጀግንነት ደምና አጥንት በተገኙት ድሎች ከመኩራራት ባሻገር ዛሬ በአብዛኛዉ ተመሳሳይ አስተዋጽኦ ስናደርግ አንታይም። የቀደሙት አያቶቻችን በዘር፤ በጎሣ፤ በዕድሜና በጾታ ሳይከፋፈሉ በዐራቱም ማዕዘኖች በተባበረና በተቀናጀ መልክ የአገራቸዉን ነፃነትና የህዝባቸዉን ደህንነት ያስከብሩ ነበር፤ የአሁኖቹ ደግሞ የዉጪ ጠላቶቻችንን እየጋበዙ ድምበሮቻችንና መሬቶቻችንን ይቸበችቡላቸዋል፤ ይሰጧቸዋል። ህዝባችን ግን ዛሬ በገዛ አገሩም ሆነ በስደት ላይ እንደሁለተኛ ዜጋ እየተቆጠረ በምን ዓይነት ባርነት፤ መከራና ሰቆቃ ላይ እንደሚገኝ የማያዉቅ ዜጋ ይኖራል ብዬ አልገምትም። ዛሬ ካለፉት ታሪኮች መማር የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ነዉ፤ በጣም ያሳዝናል። ካለፉት ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችን መማር ካልቻልን ወይም ካልፈለግን ሰዎች አይደለንም፤ ከእንስሳትም በታች እንሆናለን። እንስሳት እንኳን ተመክሮአቸዉንና አካባቢያቸዉን ደህና አድርገዉ ይጠቀሙበታል፤ ለመኖር ያህል።
፪ኛ/ ከዐድዋ ጦርነትና ድል ምን እንማራለን?
ጣሊያን በፈረንጆች አቆጣጠር በ1885 ዓ/ም አካባቢ በምፅዋ ላይ መደራጀት ጀመረች። ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብ እየገፋች ባህር ነጋሲ በመባል የሚታወቀዉን ሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ይዛ ‘ኤርትራ’ የሚል ስም በመስጠት ሰፈረችበት። በዚያን ጊዜ የትግራይ ገዥ ራስ መንገሻ ነበሩ። ዐፄ ዮሃንስ በመተማ ጦርነት ላይ ከተገደሉ በኋላ የመንገሥ ፍላጎት ስለነበራቸዉና ለዚህም የጣሊያኖችን ድጋፍ ይሹ ስለነበር በመጀመሪያ ከዐፄ ምኒልክ ጋር ተባብረዉ ጣሊያንን ከሰሜኑ ክፍል ለማባረር ፍላጎት እንዳልነበራቸዉ ታሪክ ይናገራል። ደጃዝማች ባህታ ሃጎስ ከአከለጉዛይ ተነስተዉ ጣሊያኖችን ለመዉጋት ገጥመመዉ ሲገደሉ ከራስ መንገሻ በኩል ምንም ድጋፍ እንዳልነበራቸዉ ይነገራል። ከመጀመሪያዉ ተደጋግፈዉ አብረዉ ቢሰለፉ ኖሮ ጣሊያ በይበልጥ ተደራጅታ ወደ ደቡብ በቀላሉ ለመዝለቅ ባልቻለች ነበር።
ዳሩ ግን ጣሊያ በትግራይ በኩል እየገፋች ወደደቡብ የመጣችበቱ ዓላማ ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ለመያዝ እንደሆነ ሲረዱ ራስ መንገሻ ገስግሰዉ ሄደዉ ድንጋይ ተሸክመዉ ዐፄ መኒልክ ፊት በመቅረብ ይቅርታ ጠይቀዉ እጎናቸዉ ተሰለፍ።
በዐፄ መኒልክና በጣሊያ ምንግሥት መካከል ዉጫሌ በመባል የሚታወቀዉ ‘የወዳጅነት’ ስምምነት በፈረንጆች አቆጣጠር በ1889 ዓ/ም ተፈርሞ ነበር። የዚህ ስምምነት አንቀጽ 17 እንነደሚለዉ ንጉሠ ነገሥቱ (ማለት ዐፄ መኒልክ) ከፈለጉ ከዉጪ አገሮች ጋር ስለሚኖራቸዉ ግንኙነት በጣሊያን መሥሪያ ቤቶች ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ነበር። ጣሊያኖቹ ግን ሁን ብለዉ ይሄን ስምምነት በማጣመም ኢትዮጵያ የዉጪ ግንኙነቶችን በሙሉ በጣሊያ ባለሥልጣኖች በኩል እንድታደረግ ትገደዳለች ብለዉ ቁጭ አሉ። በዚህ መልክ ነበር እንግዲህ የአድዋ ጦርነት የተጀመረዉ።
የዐፄ ምኒልክ አዋጅ ተነገረ፤ ልብ የሚነካ ነበር። መልእክታቸዉ አጭር ነበር፤ አገር የሚያጠፋና ሃይማኖት የሚለዉጥ ጠላት ስለመምጣቱና በእግዚአብሔር ረዳትነት አገራቸዉን አሳልፈዉ እንደማይሰጡ በመግለፅ ጉልበት ያለዉ በጉልበቱ፤ ጉልበት የሌለዉ ደግሞ በሃዘንና በፀሎት እንዲረዳቸዉ ተማፀኑ።
በዚህም ጥሪ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዐራቱም ማዕዘናት ተንቀሳቀሰ። የመሃል አገሩ ሕዝብ በርሳቸዉ ሥር ተሰለፈ። የስሜን ጦር በእቴጌ ጣይቱ ሥር፤ የጎጃም ጦር በንጉሥ ተክለ ኃይማኖት ሥር፤ የሃረር ጦር በራስ መኮንን ወ/ሚካዔል ጉዲሣ (የ/ቀ/ ኃይለ ሥላሴ አባት) ሥር፤ የትግራይና የሃማሴን ጦር በራስ መንገሻና (የዐፄ ዮሃንስ ወንድም ልጅ) በራስ አሉላ ሥር ሲሰለፍ የወሎ ጦር በራስ ሚካኤል ሥር ነበር። ጣሊያን ዘመናዊ መሣሪያ ይዛ ስትመጣ የእኛዎቹ ግን ታቦት ይዘዉ በፊሉቤር፤ በጥቂት ጠብመንጃዎች፤ በእጅ ጦርና ጋሻ ብቻ ነበር የገጠሙት። ፈረስ የነበረዉ በፈረሱ፤ የሌለዉ ደግሞ በእግሩ ነበር የዘመተዉ።
ቸሩ እግዚአብሔር ይመስገን ድሉ ለአርበኞቻችን ሆነ። ሶላቶዎች ቅስማቸዉ ተሰበረ። የነጫጭባዉ ዓለም በሙሉ በከባድ ትካዜ ዉስጥ ወደቀ። በአዎሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩት ነጮች የጣሊያንን ክፉኛ መቸነፍ ማመንም ሲያቅታቸዉ ጊዜ ኢትዮጵያኖች እኮ ጥቁሮች አይደሉም፤ ከኛ ርቀዉ የሚኖሩ ነጮች ናቸዉ እስከማለት ደርሰዉ ነበር። ጣሊያን በአፍሪቃ ጥቁር አገር መቸነፏን ላለመቀበል።
፫ና/ ከማይጨዉ ጦርነትና ድል ምን እንማራለን?
የላይኛዉን ጦርነት ታሪኮች የሰማሁት ከትምህርት ቤቶችና ከጽሑፎች ሲሆን ስለማይጨዉ ጦርነት ግን ከአርበኛዉ አባቴ አፍ ጭምር ነበር፤ በወጣትነቱ ጦርነቱ ዉስጥ የገባ አርበኛና የዐይን ምስክር ነበርና።
ጣሊያ በአድዋ ከተቸነፈች ቀን ጀምሮ አርፋ አልተኛችም፤ ወራሪ ጓደኞችዋም ጭምር። ስለዚህ ለ40 ዓመታት ሙሉ ዝግጅት አድርጋ ልትወርረንና ቂሟን ልትበቀል ተመልሳ መጣች። ወገኖቻችን እንደገና በተለመደዉ ህብረታቸዉ ዘመቱ። ጀግናዉና አርበኛዉ አባቴ እንዳስተማረኝ፤ አሁንስ ዓላማቸዉ አቸንፈዉ ከአገር ማባረር ብቻ ሳይሆን እስከ ሮማ ድረስ ተከትሎ በመሄድ ጥሩ ትምህርት ለመስጠት ጭምር እንደነበረ ነዉ። በእዉነትም ወደ መጀመሪያዉ ላይ ጥልቅ ጉዳት አድርሰን ነበር። የአድዋ ሽንፈቷ እንዳይደገም ክፉኛ ተጨነቀች። የደረሰባትን ከባድ ጉዳት ለፋሺስቱ መሪ ለሙሶሎኒ አስታወቀች። ከቫቲካን ጭምር የሮማ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የገንዘብ መዋጮ አደረገ፤ ሴቶቹ እስከጋብቻ ቀለበታቸዉ ድረስ።
ከአንደኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ የተከለከለዉን የመርዝ ጪስ ከጦር አይሮፕላኖች ላይ ረጨችብን። ቤቶች ተቃጠሉ፤ ከብቶች አለቁ፤ የአርበኞቻችን ዐይኖች ተቃጠሉ። ጉዳዩን ለማመንም አስቸጋሪ ነበር። ለጊዜዉ ማፈግፈጉ የግድ ሆነ።
ታሪኩ ረዥምና እልህ አስጨራሽ በመሆኑ አሳጥረዋለሁ። ንጉሣችን (ቀ/ኃ/ሥ) ለሊግ ኦፍ ኔሽን ሊያመለክቱ ወደ ዠኔቫ ሄዱ። አፍንጫ ሲመታ ዐይን ያለቅሳል እንዲሉ የአዉሮፓ መሪዎች በሙሉ ለጣሊያን አዳሉ፤ በኛ ላይ አፌዙ። ንጉሣችን ተስፋ ቆርጠዉ በዚያዉ ወደ እንግሊዝ አገር አቀኑ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን እንደገና በጦር መሪዎችና በጎበዝ አለቆች ሥር እተደራጀ ለ5 ዓመታት ያላሰለሰ ትግል በማካሄድ ጣሊያኖችን ዕረፍት አሳጣቸዉ። አርበኞቻችን ለነፃነታችንና ለክብራችን ደማቸዉን ሲያፈሱና አጥንታቸዉን ሲከሰክሱ ባንዳዎች ግን ለሆዳቸዉ በማደር ጣሊያኖችን እያገለገሉ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸዉ የሚረሳ ታሪክ አይደለም። ያ ሁሉ አለፈና ጣሊያም እንደገና ተደመሰሰች፤ አገራችንን በቅኝ ሳትይዝ እንደባነነች መጥታ እንደባነነች በሃፍረትና በቅሌት ወደ አገሯ ተመለሰች። እግዚአብሔር ይመስገን።
፬ኛ/ ጥፋቶቻችንን አምነን ንሥሐ ገብተን ወደፊት ልንራመድ እንችላለን?
ሁል ጊዜ ዉድ አገራችንን በይበልጥ የሚያሰቃዩት የዉጪ ጠላቶች ሳይሆኑ የዉስጥ ባንዳዎች ናቸዉ። ይሄም በጣሊያን ወረራዎች ዘመናት ታይተዋል፤ በደርግ አስተዳደር ዘመን ዐይተናል፤ ዛሬም በወያኔ/ኢሕአደግ ሥር እየተመለከትን ነዉ። ‘ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ’ የተባለዉ ለዚህ ነበር። ሞት ላይቀር ነገር ብኩኖች ይስገበገባሉ። በልተዉ የሚጠግቡ አይመስላቸዉም፤ ለሺህ ዓመታት የሚኖሩ ይመስላቸዋል፤ ግብዞች።
ዛሬ ዉድ አገራችን በከባድ ጣጣ ዉስጥ ትገኛለች። ሕዝባችን ይፈናቀላል፤ ይገደላል፤ በገፍ ይሰደዳል። የወያኔ/ኢሕአደግ አንቀጽ 39 ሥራዉን እየሠራ ነዉ። በአንድነት ምትክ ክፍፍሉ እየሰፋ ይታያል። ቻርተሩ ሲረቀቅ ሆነ የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ሲረቀቅ ከወያኔ ጎን በመሆን ድጋፍ የሰጡ ተለጣፊዎች ነበሩ። አሥራ አምስት ተቃዋሚ ድርጅቶችን ያቀፈዉን ታላቁን ህብረት አፈረሱ። ድርጅቶች ፈለፈሉ። ገለልተኛ ታዛቢዎችና ነፃ የምርጫ ቦርድ ሳይኖር ምርጫ ዉስጥ መግባቱን እንዳታስቡት እያለ ሕዝቡ በነቂስ እያስጠነቀቃቸዉ ዘልለዉ ምርጫ ዉስጥ ገቡ። ከዚያ ምን ሆነ? ሁሉም የሚያቀዉ መሳቂያ ሆነዉ ቀሩ። ዛሬ በፓርላማ ተብዬዉ ዉስጥ አንድም ተቃዋሚ ድርጅት የለም። ይሄ ነዉ ዲሞክራሲ? ይሄ ነዉ ሰላም? ይሄ ነዉ እድገት?
ካለፉት ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችን መማር ከፈለግን አሁንም የዉድ አገራችንን ህልዉናና የመላዉን ሕዝባችንን ደህንነት ልናስጠብቅ እንችላለን። ዛሬም እንደገና አዳዲስ ፋሺስቶች እያንጃበቡብን ናቸዉ፤ አንዳንዶቹም ጠልቀዉ ገብተዋል፤ መሪታችንን ሊቀራመቱ፤ ህዝባችንን ሊከፋፍሉ፤ ኦርቶዶክስን ሊሰብሩ፤ ሙስሊሞችን ሊረግጡና ዉድ አገራችንን ሊያፈርሱ። የኢትዮጵያ መሬት የኢትዮጵያዉያን እንጂ የሱዳንም፤ የግብፅም፤ የቻይናም፤ የህንድም፤ የፓኪስታንም፤ የሳዑዲም ሆነ የቱርክ አይደለም፤ መሆንም የለበትም።
መፍትሔዉ ቀላል ነዉ። ከቀደሙት ጀግኖች፤ ቅዱሳንና ሰማዕታት እንማር። ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርብን እንሞክር። ራስ ወዳድነትንና ሆድ አደርነትን እንቀንስ። ለአገር አንድነትና ነፃነት በህብረት እንፀለይ፤ እንታገል፤ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን ያቺን የተረከብናትን ቆንጆ አገር እናዉርስ። አንዳንድ የዉስጥ ልዩነቶች እንኳን ቢኖሩን መጀመሪያ አገራችንን ከዉድቀት ካወጣናት በኋላ ዲሞክራሲያዊና ስልጡን በሆነ መልክ ተወያይተን መፍትሔ ልናገኝ የማንችልበት ምክንያት አይኖርም። በተለይ ባለፉት 40 ዓመታት ብዙ መቶ ሺህ ሕዝባችን (በተለይ ለጋ ወጣቶች) ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ሲሉ ተቀጥቅጠዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ተገድለዋል፤ ተሰደናል። እስቲ አሁንም ለዲሞክራሲ ግንባታ አንድ ላይ ሆነን እንታገል። በዲሞክራሲ ጎዳና የሕዝባችን እኩልነት ከተጠበቀ፤ ሰላምና እርጋታ ከሰፈነ፤ የኢኮኖሚ እድገት ከታየና የአገሪቷ መዋዕለ ንዋይ ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ከተከፋፈለ ዋናዉ ችግራችን ተወገደ ማለት ነዉ። ከዚያ በላይ ያለዉ ቅንጦት ወይም ህልም ይመስለኛል።
ስማኝ ተዉ ስማኝ ሀገሬ፤ አንድነት ይበጀናል ዛሬ።
ቸሩ ፈጣሪያችን የአገራችንን አንድነትና የሕዝባችንን ደህንነት ለዘለዓለሙ ይጠብቅልን፤ አሜን።