ከሀማ ቱማ –
” ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ምን አነሳሳኝ ለሚለው ምላሽ ለመስጠት እየሞከርኩ ነው፡፡ ጊዜው የሀሳዊ መሲሆች፤ የአስመሳይ ታጋዮች፤ የነበርን፣ መሠረትን፣ ዓይን አውጣ ቀጣፊዎች፤ የለየላቸው ባንዳዎችና ዘረኞች በመሆኑ ንትርኩ ጉንጭ አልፋ ሆኖ እንዲሁ በግፋቸው ሲወገዙ ህዝባችን ተሰደበ በሚል ሊለጉሙንም ይቸኩላሉ፡፡ ባንዳ፤ አንጃ፤ ከሃዲ መሆን የሚያሰድብ ቢሆንም ማነታቸውን ገላጭ እንጂ ተራ የታባክ ስድብ አይደለም፡፡ ወደ አነሳሣኝ ልመለስና ባለፈው ሰሞን ስለትግሉና ያ ትውልድ ሰማዕትና ስለ ቀይ ሽብር ሰለባዎች የሚዘግበው መኮንን ተስፋዬ፤ስለ ዋለልኝ መኮንንና ማርታ መብራቱ ታሪካቸውን ባቀረበበት ወቅት፤ቃሪያ ነገሮችና ርዝራዦችም ቢሆኑ የተነገሩትን ይዘው አሊያም አድሃሪ ስርዓታቸውን ደግፈው ተረባረቡበት፡፡ ከሁሉም የገረመኝ ግን እነዚህን ንጹህ ሰማዕት የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሻዕቢያና ጀብሃ ሎሌዎች/አባሎች ሊሉ መነሳታቸው ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ በዘመኑ ከነበሩት አንዱ የግራ ክንፍ ምሁር ጋ ወደ ሀገር ቤት ደውየለት ስንወያይ “ብዙም አይግረምህ ፤ የዘንድሮ ማፈሪያዎች ዕድልና መድረክ ቢያገኙ ዘርዓይ ደረስና አብርሃም ደቦጭን ሻዕቢያ ብለው ይከሳሉ፤ አይ ጊዜው አይገጥምም ብትላቸው ደግሞ”ቢሆንም”ብለውህ ነው የሚደርቁት”ሲለኝ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ተነሣሁ እንጂ ዋለልኝን ለቀቅ፤ ያን ትውልድ ለቀቅ ብዬ ክዚህ በፊት በዚህ ርዕስ የምለውን ብዬ ነበር፡፡ “
እንጻፍ እንጻፍ ይወገዝ ካልንማ፣
ዝምታ ሀጢያት ነው ህዝብ ሀገር ሚጎዳ፣
ለታሪክ በራዦች የሚለግስ ሜዳ፣
ለአስመሳይ ቡከኑ፤ ለባንዳና አንጃ፣
የሚሰጥ ቀዳዳ፣
እንጻፍ እንጩህ ሀገሩ ይንጫጫ፣
ታሪክ ሀቅ ይመዝገብ ሀሰት ይጣ መውጫ፡፡
በሚል ሀገራችንን ሊያጠፋ የሚቅበዘበዘውን መንጋና ሾፌሩን ዘረኛ አገዛዝ አምርረን መታገልና በስፋትም ማጋለጥ አለብን ፡፡ አገዛዙ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ የስማዕት ማምረቻ ፋብሪካ ሆኗል፡፡ ታሪክ የኢትዮጵያ ምሁራንን አኩሪ ገድል እንዳልመዘገበ ሁሉ ዛሬ መድረኩ የተጨናነቀው በፖለቲካ ሸማሻዎች፣ መሀይም ምሁሮች፣ ቀፎ ታፔላ ለጣፊዎችና ባንዳ_ አንጃዎች ነው፡፡ ያልታደለች ሀገር ጥራ ግራ፣ ደም ተፍታ፣ላብ አፍሳ ያስተማረቻቸው ሲመረቁ፤bድፍንቅል እየሆኑ አሳፍረዋታል፡፡ ሀቁ ሲነገር ጠነከረ አይገባም የሚሉትን ብንሰማ ኖሮ በጊዜ ሹሞቹንም የወያኔ ጉዲፈቻ ብለን ባላጋለጥና ድንብርብራቸንን አውጥተው ቀንበር በጫኑብን ነበር፡፡ መጻፍ፣ ማጋለጥ፤ መጮህ፣ መታገል ሲያንስ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ከሆንን፤ ያለችን ውድ ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ከሆነች፤ ያ ያ የምንለው የቅዠት ሀገር እስከሌለን ድረስ፤ ከሀገር በፊት ሆድን ካላስቀደምን፤ ታሪክም አልዋሸ፤ ትውልድም አልከሰመ ካልን ዘንዳ ቀደም የታየው ጀግንነት፤ ከጥቁር አንበሳ ወጣቶች እስከ ስድሳዎቹ ትንታጎች ዛሬም እውን ሊሆን በተገባው ነበር ፡፡
በደርግም፣ በወያኔም አገዛዞች ወንጀል ማመካኘት ይቻላል ግን አያዋጣም፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ ወደ መጪው ወይም ወዳለፈው ሀኬት መለጋቱን ትቶሀላፊነቱን መሸክም መቻል አለበት፡፡ ያለፈውማ ባመነበት በጸናበት ሀገሬ ብሎ በጀግንነት ተሰውቶላታል፡፡ ፋኖነቱ በምላስ ሳይሆንበጓንዴ በክላሺን ነበር፡፡ መትረየስ ምላሶች ሳይሆኑ ብሬንም፤ ጎርዩኖቭም ያንጣጡ ጀግኖች ነበሩ፡፡ ሞት ለፋሺስቶች ብሎ ያ ትውልድ ተጋፍጧቸዋል ፡፡ ዛሬስ? እዚህ ላይ ነው ትኩረታችን፤ ጥያቄያችን ሊሆን የሚገባው፡፡ እኛስ? ከትግሉ እንዴት ነን? ስለ ትግል እንቀባጥራለን ወይስ እንታገላለን? የታገለውን ትውልድ ታሪክ እናብጠለጥላለን ወይስ በተጨባጭ ትግል የበለጠና የደመቀ ታሪክን ልናስመዘግብ ቆርጠን ተነስተናል? ሰው ሆኖ መኖር፣መሞት፤ወይስ ከንቱ ሆኖ ከትቢያ መደባለቅ ነው ጥያቄው፡፡
ምሁር ነን ይሉናል ዶክተር ፕሮፌሰር፤
ሀገር ህዝብን ክደው ተብለው ከርስ አደር፡፡
ግም ለግም ተቃቅፎ
ሆዱን ሲያሽ በቁንጣን
ልትሞት ነው ኢትዮጵያ በዘረኛ መንጋ እያስፈጀች ህዝቧን ፡፡
ሀቀኛና ያወቅነውን ታሪክ በሚገባ ለማቅረብ ብዙ ጊዜ ብንጥርም አውቆ የተኛን ሰው ሆነው ያንኑ የገለማ ሀሰት የሚዘባርቁትን ማረም ባለመቻላችን እንደ ሞኝ ልቅሶ መልሶ መልሶ ሀቁን ለማስረዳት መጣሩ ግዴታችን ሆኖ ይገኛል፡፡
ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ምን አነሳሳኝ ለሚለው ምላሽ ለመስጠት እየሞከርኩ ነው፡፡ ጊዜው የሀሳዊ መሲሆች፤ የአስመሳይ ታጋዮች፤ የነበርን፣ መሠረትን፣ ዓይን አውጣ ቀጣፊዎች፤ የለየላቸው ባንዳዎችና ዘረኞች በመሆኑ ንትርኩ ጉንጭ አልፋ ሆኖ እንዲሁ በግፋቸው ሲወገዙ ህዝባችን ተሰደበ በሚል ሊለጉሙንም ይቸኩላሉ፡፡ ባንዳ፤ አንጃ፤ ከሃዲ መሆን የሚያሰድብ ቢሆንም ማነታቸውን ገላጭ እንጂ ተራ የታባክ ስድብ አይደለም፡፡ ወደ አነሳሣኝ ልመለስና ባለፈው ሰሞን ስለትግሉና ያ ትውልድ ሰማዕትና ስለ ቀይ ሽብር ሰለባዎች የሚዘግበው መኮንን ተስፋዬ፤ስለ ዋለልኝ መኮንንና ማርታ መብራቱ ታሪካቸውን ባቀረበበት ወቅት፤ቃሪያ ነገሮችና ርዝራዦችም ቢሆኑ የተነገሩትን ይዘው አሊያም አድሃሪ ስርዓታቸውን ደግፈው ተረባረቡበት፡፡ ከሁሉም የገረመኝ ግን እነዚህን ንጹህ ሰማዕት የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሻዕቢያና ጀብሃ ሎሌዎች/አባሎች ሊሉ መነሳታቸው ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ በዘመኑ ከነበሩት አንዱ የግራ ክንፍ ምሁር ጋ ወደ ሀገር ቤት ደውየለት ስንወያይ “ብዙም አይግረምህ ፤ የዘንድሮ ማፈሪያዎች ዕድልና መድረክ ቢያገኙ ዘርዓይ ደረስና አብርሃም ደቦጭን ሻዕቢያ ብለው ይከሳሉ፤ አይ ጊዜው አይገጥምም ብትላቸው ደግሞ”ቢሆንም”ብለውህ ነው የሚደርቁት”ሲለኝ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ተነሣሁ እንጂ ዋለልኝን ለቀቅ፤ ያን ትውልድ ለቀቅ ብዬ ክዚህ በፊት በዚህ ርዕስ የምለውን ብዬ ነበር፡፡ አለል ዘለል ባዮች በዘመነ መንጋ አልፎላቸዋል፡፡ ይሉኝታና ማፈር እርም ሆኗል፤ መቅደድ መቀደድ ነግሶባቸዋል ብዙዎች፡፡ ውሸት ላይ የተመሰረተ አገዛዝ የበላይነትን ሲያገኝ ዋሾው እንደሚፈላ በታሪክ የታየም ነው ፡፡ ከዓመታት በፊት ገጣሚውና ትንቢተኛው ሀይሉ ገብረ ዮሃንስ (ገሞራው) ሲገጥም፦
” እችላለሁ ብሎ ያሻጋሪ አታላይ
አርክሶ አጣላ፤ከኑሮ ሊለያይ” ብሎ ነበር፡፡
የሚያውቁ ዝም ሲሉ አላዋቂዎች ይጮሃሉ እንዳይባል ግን ከዝምታችን መለያየት የግድ ነው፡፡ እኔ ዋለልኝንም ሆነ ማርታን፤ ጌታቸውና አማኑኤልን አውቃቸዋለሁ ፡፡ ዋለልኝ የነበረውን የጭቆና ሀቅ ፍርጥርጥ አድርጎ በድፍረት ስለጻፈው የተነኩና የዚያን ግዜ ሁኔታ ሊክዱም የሚከጅሉና ምናልባትም ጸሁፉንአንብበው ያልገባቸው፤ አሊያም ሳያነቡ በስማ በለው የሚነዱ እሱን ጸረ ኢትዮጵያ ጸረ አማራ አድርገው ሊያቀርቡ ሲዳክሩ ዓመታት አልፈዋል ፡፡ ወያኔም ኢህአዴግ ብሎ ሊያውናብድ እንደቃጣው ሁሉ “ኦፐሬሽን ዋለልኝ”በሚል ሊያደናግር የጣረውን ውጠው በዋለልኝ ላይ ጥላቻቸው ሰማይ የነካ ጅሎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ዋለልኝም፤ ማርታም፤ ጌታቸውም ወዘተ ጥርት ያሉ ጽኑ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ጀግኖች፡፡ በወቅቱ ቀይ ዘብ እንባል ለነበርነውና ለጋልነው ግራ ክንፎች እንዲያውም ዋለልኝና ጥላሁን ግዛው ለስለስ ያሉ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ እንላቸው ነበር ፡፡ በፖለቲካ ብንለያያም ለምሳሌ የብርሃነ መስቀልን ኢትዮጵያዊነት ተጥራጥረንም አናውቅ፡፡ የአዲ እኢሮቡ ጀግና ተስፋዬ ደበሳይን በኢትዮጵያዊነቱ ሊጠይቀው ብቃት ያለው ማንም የለም_ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ነበርና፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያዊነት ሹሙ ይበልጥብናል ባዮችማ አፋቸውን መክፈትም ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ ዘር ያልቆጠረውን ትውልድ ባይረዝሩት ይሻላል እንላቸዋለን፡፡ ዋለልኝ የብሄር ጭቆና አለ ማለቱ ለሚያማቸው ይመማቸው እንጂ ሚሊዮኖች የሚያውቁት ሀቅ ነው፤ ስናድግም ያየነው ነው፤ ለትግል እንቅፋትም እየሆነ የተማሪውን እንቅቃሴ ሊያዳክም የሚችል በመሆኑ ልናስወግደውና አንድነትን ልናጠናክር በሚል የተጋተርነው ጥያቄ ነው ፡፡ የብሄር ጥያቄን ያመጡብን እንጂ ዋለልኝም፣ እኛም፣ የተማሪው እንስቃሴም፣ ኢህአፓም ያመጡት አልነበረም፤ አይደለም፡፡ አይነሴ ጉዳይ በመሆኑ ዋለልኝ ያበጠው ይፈንዳ በሚል ደፍሮት መጋረጃውን ከፍቶታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እነ ዋለልኝ ባመኑበት ተሰልፈው ውድ ህይወታቸውን የሰጡ በመሆናቸው ማንም ቡከንና አንጎለ ሸንካላ ሊተቻቸው የሞራል ብቃት መቸም አይኖረውም ፡፡ ዋለልኝ ከኢህአፓ መስራቾች አንዱ እንደመሆኑና በምስረታው ሂደት ተስፋዬ ደበሳይ ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ እሱንና ጸጋዬ ገብረመድህንን አማክሮ የተመለሰ በመሆኑ ዋለልኝ የኤርትራ ግንባሮችን፤ ንኡስ ከበርቴ ብሄርተኞችና ተገንጣዮች በሚል አሉታዊ ግምጋሜ እንደነበረው የምናውቅ ምስክሮች አለን፡፡ ማርታ አባቷ የኤርትራ ተወላጅ ቢሆኑም ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላ አልነበረችም፤ ወንድሟም ኢህአፓ ሆኖ በከተማም በገጠርም ታግሏል እንጂ ግንባሮቹ ጋ አልሄደም። አባቷም የአጼው ተሿሚ ሆነው በኢትዮጵያዊነታቸው ጸንተው ያረፉ ጄኔራል ናቸው፡፡ በሬ ወለደው ይሰቀጥጣል፡፡
ያልቀበረ ያርዳ የተባለ ይመስል
ያልነበረ ያውራ የተባለ ይመስል
የእነ ነበርን ወሬ ሀገሪቷን ሞላት
የነበረው ሳይሆን ያልነበረው በላት፡፡
የሀሰት ዘመቻ በተለይም የምሁር ተብዬዎች ዛር፤ አዶ ከብሬ እየሆነ የመጣው ቅጥፈት ያነጣጠረው፤ በኢሕአፓ ላይ መሆኑ አያስገርምም ፡፡ ይህ ድርጅት ለህዝብና ለኢትዮጵያ ቆሞ በሀቅ ለሃቅ ስለታገለ ጠላቶቹ መብዛታቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ትንሽ ትልቁ ድርጅቱን ይጠላሉ፡፡ ባንዳና አድርባዮች ሊወዱትም አይጠበቅ፡፡ ወያኔና ገንጣዮችን ከመጀመሪያው ስለታገላቸው ጠላት ያሉት ከያኔው ነው፡፡ አንዳንዶች ድርጅቱ ገንጣዮችን ደገፈ፤ የኢትዮጵያ አንድነትን አጠቃ ብለው ሲቀባጥሩ ብንሰማም የሚመለክታቸው ገንጣዮች ግን ከመጀመሪያቸው እንደጠመዱት፤ እንደተቃወሙት ይታወቃል፡፡ ኢሕአፓ ለሻዕቢያም፤ ለጀብሃም ለሶማሌም ሆነ ለአረቦች ሀገር አሳልፎ የሰጠበት ሰኮንድም የለም፡፡ ወያኔን፤ ገና መገንጠልና ህዝብ አብሮ መኖር አይችልም፣ አማራ ተራማጅ የለውም ሲል ጀምሮ ተቃውሞት ተገኘ እንጂ፤ የነአረጋዊ ግደይ፣ ስብሃትና አባይ ጸሀዬን ወያኔያዊ ጥቃት መቋቋም ተገደደ እንጂ በርከክ ብሎ አላበራቸውም፤ አልደገፋቸውም፡፡ በጸረ ወያኔው ትግልም ስንቶቹ የትግራይ ተወላጅ ኢሕአፓዎች መሰዋታቸው ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባይ ባይሆንማ ከነሱ ድጋፍና እርዳታን አግኝቶ ዛሬ የኢትዮጵያ አጥፊ ቡድን ማለትም የባዕዳን ቅጥረኛ አንዱ በሆነ ነበር፡፡ ይህን እኩይ ዘመቻቸውን በተለመለክተ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ የታሪክ ጸሃፊዎችና ምሁሮች ክህደት ነው፡፡ ብጣቂ የፈረንጅ ዲፕሎማ ያውም ወያኔ እየገዛ በሚንበሸበሽበት_ ለማግኘት ምርምርና ጥናት ሲያደርጉ ኢትዮጵያና ፖለቲካዋን በተመለከተ ጥራዝ ነጠቅነትን እውቀት ብለው መቀባጠሩን መርጠው ይገኛሉ፡፡ “በማያውቁት የሚዘባርቁ ቢወገዱ ኢትዮጵያ ባማረባት”ያለው ሰው እውነት አለው ፡፡ ስለ ኢህአፓ ታሪክ የማያውቁትን ሲዘባርቁና ምስክርነት ብለው ራሳቸውን ሲያዋርዱ የቆዩት የባጁት ታሪክ አዋቂ ነን ባዮች፤ ዛሬ ዘረኞቹ የኢትዮጵያን ታሪክ በአኖሌ ጭቃ ሲለውሱት ከቆላ አይጥ ይበልጥ ጉድጓድ ምሰው ተደብቀዋል፡፡ የሟቹ የነጋሶ ጊዳዳን ያህል እንኳን አሌ ሊሉ አልደፈሩም፡፡ ስለዚህም በአያሌው ስለ ኢሕአፓ የሚጽፉት ያውም ብዙ መቶ ገጾችን አጥፍተው ጭራሽ የፈጠራ ወይም የደርግ ወያኔ ድሪቶ ሀሰትን አድሰው ሆኖ ይገኛል፡፡ ሀሰታቸውን ብናጋልጥም ያደቆነን ሰይጣን ብለው ሙጭጭ ብለው ቀጥለውብታል ፡፡ አውቀው በጠላትነት በዚህ የተሰማሩትን መቸስ ማል ጎደኒ በሚል ስናልፍ ሳያውቁ ግን አውቀናል ብለው የሚሸናከሉትን ከማስረዳት ሌላ ምን ማድረግ እንዳለብን ግልጽ አይደለም፡፡
መስራች ነን ይሉናል ያውም ሊቀመንበር
ምሁር ነን ይሉናል ያውም ዶክተር ፕሮፌሰር
“ወ” ማለት ሳይችሉ ወኔ ጠፍቶባቸው
የጨቋኝ ጫማ መሳም ሆኖ መለያቸው፡፡
ከድርጅቱ የምስረታ ሂደት እስከ ታሪካዊ ትግሉና የዛሬ ይዘቱ ያልተዋሸ የለም፡፡ አንዱ የደርግ ወያኔ አሽከር ለምሳሌ ድርጅቱ የተመሰረተው በምዕራብ ጀመርንና አልጄሪያ ኢምባሲዎች እርዳታ በአዲስ አበባ ነው ብሎ ተፈጥሟል፡፡ ሁለቱ መንግሥታት ያኔ በጋራ የሚሰሩ ሳይሆኑ የተጻረሩ ቢሆኑም የሁለቱንም ኤምባሲዎች የምናውቅ አልነበረንም በጊዜው፡፡
አንድ የመኢሶን ዋሾ ደግሞ ክሀገር ሲወጡ መኢሶንን አስፈቅደው ነው ሲል ከትቧል፡፡ በጊዜው መኢሶን የሚባል ድርጅት ያልነበረም ከመሆኑ በላይ በአይሮጵላን ወደ ካርቱም ስንበር ማንንም አላስፈቀድንም ነበር፤ አየር መንገዱንም ጭምር ማለትም እንችላለን ፡፡ ብዙ ተዋሽቷል፤ ዛሬ ለዘረኞች ያደረው አንጃ መሪ በተማሪ ማህበር ሳለን ኢሕአፓን ለመመስረት ስንታገል ነበር ሲልም ቀጥፏል፡፡ በዚያን ጊዜ (እሱ በ 60 ዓም ወደ ሶማሊያ ሲሸሽ) እኛ ከሀገር የወጣነውና ወደ ድርጅት ምስረታ የተሰማራነው በ1961 ነሃሴ ነበር። እሱ የዋናው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር ተጻራሪ ነበር፡፡ ግለሰቡን እኔ ለምሳሌ አይቸውም አላውቅም፤ ንግግርም አልነበረን በአዲስ አበባ፤ የተማርነው በቅደም ተከተል ባንድ ህግ ኮሌጅ የነበረ ቢሆንም፡፡ ተማሪ ሆነን ኢሕአፓ የሚባል ድርጅት መመስረት የሚል ነገርም አናውቅም ነበር፡፡ ለነገሩ ኢሕአፓን ስንመሰረትም ስሙ ኢሕአፓ አልነበረም፡፡
ስንቱን የገደሉ
ስንቱን ሰው የፈጁ
ዛሬ ተዘክረው በክብር ሲቀበሩ፤
ለፍትህ ለሀገር የሞቱት ተረስተው
ዛሬም እንደ ትላንት በዝምታ ታልፈው
ይሉኝታ ባጡትም በሰፊው ተወግዘው፡፡
የኢሕአፓን የምስረታ ሂደት ከዚህ ቀደም ላቀርብ የሞከርኩ ቢሆንም ተሳሳቹና ተራኪው ስለበዛ እንደገና ማቅረብ እገደዳለሁ፡፡ ለአንዴም ለሁሌም ይሆናል የሚል ቀጭን ተስፋ አለኝ፡፡ በቅድሚያ ግን መስራች ማለት ምን ማለት ነው ? የድርጅቱን ሀሳብ ጠንስሰው ሂደቱን የጀመሩት ወይስ በጉባዔ የተገኙት? በሁለተኛውም ስሌት ቢሆን ዛሬ መሥራች ነን ብለው ሚወራጩት መስራች ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በዚህ በዚያም በሂደቱ አልነበሩም፡፡ የኢሕአፓንም ሠራዊት (ኢሕአሠን) የመሰረተው ኢሕአፓ ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞችና ታጋዮች ደግሞ ስማቸው ይታወቃልና ለሠራዊቱ መስራች ብለው ማንንም ሊሾሙብን ሊሰይሙብን አይችሉም፡፡ ድርጅት ያስፈልጋል፤ ትግሉን በከፍተኛ ደረጃ ለማስቀጠል የሚለው ሀሳብና ድምዳሜ የተራማጅ ተማሪዎች የአብዛኞቹ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ በተጨባጭ የተነሳነውና በእኔም ቤት፣ በብንያም አዳነም ቤት የመከርነው አራት ነበርን፡፡ ዛሬ እኔ በትግሉ መስክ ስገኝ፤ ሌላው በድርጅትም ባይሆን በፖለቲካው መስክ አሁንም አለ፤ ሶስተኛው ከድርጅቱ ከዓመታ በፊት ወጥቶ ዛሬ ደግሞ የወያኔ ደጋፊ ሆኖ በመቀሌ ከትሟል፤ አራተኛው ብንያም አዳነ ደግሞ በሠራዊት ተከላው ሂደት ተሰውቷል፡፡ በትጥቅ ትግል ሂደት ስላመንን ውጭ ሀገር ሄደን በዚያ ካሉ ተራማጅ ምሁሮች/ተማሪዎች ጋር ተገናኝተን የፖለቲካ ድርጅት መስርተን ትግሉን መጀመር በሚል ስንስማማ የመውጫችን መንገድ ደግሞ ወደ ተማሪውና ህዝብ ትግል ዓለም አቀፋዊ እይታን ይስብ ዘንድ አይሮጵላን ጠለፋ በሚለው ሀሳብ ቀርቦ ተስማማንበት፡፡ ብንያም ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ሀይለየሱስ ወልደ ሰንበትን ስንቀርበውና እሺ ሲል ስንመለምለው እሱ ደግሞ፤ ሽጉጥ ያለው ነው ብሎ ቀጣዩን አቅርቦ ስድስተኛ ሊሆን ቻለ፡፡ እስር የነበረው ብርሃነ መስቀል ሲፈታ ቢደባለቀን ለድርጅት ምስረታው ይጠቅመናል በሚል ስለታመነበትም በዚሁ ተደረገ ፡፡ አብረን እንውጣ ብለናቸው በልዩ ልዩ ምክንያት እምቢ ያሉት (ለምሳሌ ሟቹ መስፍን አርአያ) ሳያጋልጡንም በህዝብ ትግል ቆይተው ዛሬ አልፈዋል ፡፡ የዚያን ጊዜ የመተማመን ልክና ደረጃውንም እስካሁን የሚያስታውሰኝ ነው፡፡ በዚህ ዝግጅት ማንም ሌላ የተካፈለ አልነበረም፡፡ መስራች ነን ባዮች ቶሽ፤ አደብ ግዙ፡፡
ለመቀጠል፤
በርጩማ ተቀማጭ መች ብቅልን ያወርዳል
ከትግል ሜዳ ርቆስ ፋኖ እንዴት ይኮናል?
ውርደት የለመደስ መች ክብርን ይለብሳል
ሞትን የፈራስ ሰው መች ህይወት ያገኛል?
መጎንበስ ሀጢያት ነው ብለው ወላጆችም ሀገርም ስላስተማሩን የፖለቲካ ንቃታችን ዛሬ የታሪክ ላፒሶች እንደሚሉት የመጣው ከሶቪየት ቤተ መጻሃፍት ወይም ከቻይና አልነበረም ፡፡ መሬት ለአራሹ ብለው ተማሪዎች ሲሰለፉና በሥርዓቱ ላይ ሲነሱ አርአያቸው እነ ደጃዝማች ታከለ፤ እነ መንግስቱና ገርማሜ ንዋይ እንጂ ሌሎች አልነበሩም ፡፡ እኔ የፖለቲካ መጽሃፍት ከማንበቤ በፊት ማንነቴን የቀረጹልኝ እናቴና ጸረ ንጉሱ የነበሩት ባህታውያንና ሰባኪዎች ናቸው ፡፡ አባ ጉኒና፤ ባህታዊ ገብረጊዮርጊስ፤ አባ ቸርነት፤ አባ ገብረሥላሴ፡፡ በሂደት ግን ያለው አገዛዝ ለለውጥ መልሱ እምቢ ሲሆንና ዓለም አቀፍ ሁኔታውም የያዘው የትግል አቅጣጫ መሰረታዊ ለውጥን ጠያቂ ሲሆን ዝንባሌው ወደ ግራ መሆኑ አይቀሬ ሆነ፡፡ ኢትዮጵያን በቁጥጥሩ አስገብቶ የወጣቶችን አንጎል ለማጠብ ሲወራጭ የነበረው የምዕራቡ ሀይል በተሰማራው አሸናፊ ቢሆን ኖሮ ወጣቶች ወደ ግራው ባላዘመሙ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ አሜሪካ የፊውዳሉ ስርዓት ደጋፊ ሆነች፡፡ አሜሪካና ምዕራቡ የአፍሪካ ህዝብ ትግል ዘረኛ ጠላቶች ሆኑ፡፡ ማንዴላን ሳይቀር ዘረኛ ብለው አወገዙ፤ አሰሩ፤ በኮንጎ ሉሙምባን ገደሉ አስገደሉ፤ ንክሩማህን ገለበጡ፤ ቪየትናምንና ሌሎችን ወረሩ፤ ወዘተ… የዛሬዎቹ መሃይሞች እንደሚሉት ሳይሆን ስለሀገራችንም ስለ ዓለምም በአያሌው አንበናል፤ ንቃታችን በግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ባላወቁት ተሰማሩ የሚሉን የተደናቆሩት ራሳቸው ናቸው እንጂ በኢትዮጵያ ጭቆና ስለመኖሩና መሰረታዊ ለውጥ ስለማስፈለጉ ማንንም ንገሩን ባይ አልነበርንም፡፡ ለሰፊው ህዝብ የሚበጅ ለውጥንም ፈላጊ ስለነበርን ወደ ጥቂቶች ሰው በላ ስርዓት ቲፎዞነት፣ደጋፊነት የሚወስደን መንገድ ዝግ ነበር ፡፡ ለማወቅ ከሆን ከሀገራችን ሁኔታ ባሻገር የአፍሪካንም፤ የምስራቅ ቲሞርና ካሊማንታን ሁኔታ ወዘተ…በዝርዝር እናውቅ ነበር፡፡ አንድ የዳጎሰ ቀጣፊ የግራ መጽሃፍትን ከውጭ እየላኩልኝ ከሁሉም በፊት የነቃሁ እኔ ብቻ ነበርኩ ሲል ብንታዝበውም፤ በዩኒሸርስቲው በኩባ የሚታተመው ትራይኮንቲንታል መጽሄትና በሚቼል ኮትስ ኩባንያ ሠራተኛ ለዩኒቨርስቲ ቤት መጽሃፍት የተለገስ የማኦ ዘዶንግ መጽሃፍት ነበሩ ፡፡ አንበናል ግን የተመክሮ ትምህርት ያንሰን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አብዮት ለሀገር ማለታችን ትክክል ሆኖ ሳለ ዛሬ የታሪክ በራዦች የጥገና ለውጥ አፈ ቀላጤ ሆነው ሲመጡ መልሳችን ያልደረሰበት ግልግል ያውቃል የሚለው ነው፡፡ ዛሬስ ቢሆን ያን ትውልድ ሊያወግዙ ምላሳቸውን ያሾሉ ክፍሎች ምን የሚበጅ መፍትሄ ሲያቀርቡ ይሰማሉ፤ ያው ብዝበዛ በፈረንጆች ይቀጥልብን ከማለት ሌላ? ወደድነው ስለሚሉት ስርዓት ሆነ ጠላነው ስላሉትም ዕውቀታቸው ውሱንና የተዛባ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ከግሪኮች የመጣ ነው፤ ካፒታሊዝምም በዋሸራና ዋልድባ አልተገኘም የምንላቸውም ለዚህ ነው፡፡ ዴሞክራሲና ሶሽሊዝምን ባለመነጣጠላችንም በተጨባጭ ሶሻሊስት ነን ብለው ግን አምባገነንነትን ያሰፈኑትን ሀገሮች መደገፍ አልተቻለንም ፡፡ የጋዳ ስርዓት ዲሞክራሲያዊ መፍትሄ ነው ሊሉን እየቃጡ ያሉትንም ሆነ መደመር፣ መባዛት ባዮቹን ጥራዝ ነጠቆች አንቀበልም ያልነው ንቃታችን በቦታው በበቂ በመገኘቱ ነው፡፡ ትላንትም ዛሬም፡፡ ለነገሩ የሽግግርን ሂደት ሲቃወሙና የዘረኞችን ምርጫ ሲደግፉ ጭቆና ይቀጥልብን ከማለት ሌላ ምንም ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡
ጥላቻን በፍቅር ገጥመን ሳንረታ
ችግር ኑሮን ችለን በሳቅ ሳንገታ፤
ህይወትን ለሀገር ሳንሰጥ ሳንሰቃይ
ደግ ቀን አይመጣ ነጻነትን አናይ ፡፡
ወደ ሱዳን ለስደትና ትግል ካቀናን በኋላ እንደጠየቅነው ሱዳን በተጽዕኖ የተነሳ ጥገኝነት ሊሰጠን ባለመቻሉና እኛም ወደ ቻይና፤ ሶቭየት ህብረት ወይም ምስራቅ ጀርመን በሚል የቀረበልንን አማራጭ አልቀበል በማለታችን በፖሊስ አጅበው አለምርጫችን ወደ ግብጽና ከዚያም ወደ አልጄሪያ ወደሚባል ሀገር ሰደዱን፡፡ የአልጄሪያ አገዛዝ ያደረሰብንን ስቃይና በደል በሌላ ጊዜ የምንመለስበት ይሁን በሚል ልለፈውና ከዚያ ሆነን ወደ ሀገር ቤትም ወደ አውሮጳና አሜሪካም ግንኙነት መስርተን የድርጅት ምስረታውን ተያያዝነው፡፡ ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ፤ ህግና ደምቡንም፣ ይዘቱንም ገልጸን በቅድሚያም መሰረትን፡፡ የሀሰት የብራዚል ፓስፖርት አውጥተን አቅም ሲኖረን አንድ ጓድ ወደ አውሮጳ ዘልቆ ሊያደራጅና ህዋሳት ሊያቋቁም ሞከረ፡፡ በዚያን ጊዜ የተመለመለ አንዱ ነው ዛሬ መስራች ነበርኩ ብሎ ሚለፍፈው፡፡ ብንያም አዳነም እህቱ ንግስት አዳነ በሞስኮ ተማሪ ስለነበረች ወደዚያው ዘልቆ እሷንም፤ ክፍሉ ታደሰንም ሲመለምል ያኔ ከነሱ ጋር ይሰሩ የነበሩት እነ ዓለሙ አበበም በሂደቱ ተጠቃለሉ፡፡ ዓለሙ አበበ ለደርግ ደጋፊና አባል ሆኖ በአዲስ አበባ ከንቲባነት በቀይ ሽብር ስንት ጓዶችን ያስጨረሰ ፋሺስት ሲሆን ክፍሉ ታደሰ ራሱን መስራች አድርጎ ወሳጅና ዛሬም ካለው አንጃ ጋር የገጠመ፤ ከወያኔም የሰራ፤ ስለ ድርጅቱም መጽሃፍ ጻፍኩ ባይና በድርጅቱ ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰን ብተና ዛሬም ለሹሞቹ የሰገዱ አንጃዎች ጋር ሆኖ ያካሄደ ነው፡፡ የእሱንም በአጭር ልቅጨውና ለዛሬ አልጄርስ ከተማ መጥተው ከተገናኙን ውስጥ እሱንም፤ ዘሩ ክህሸን፤ መስፍን ሀብቱ፤ ሀይሌ ፊዳንም ቢያንስ መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ከሃይሌ ፊዳ ጋር ያካሄድነው ሁለት ሰፊ ወይይቶች ሁላችንም (ሰባታችን) በተስማማንባቸው ነጥቦች ዙሪያ ሲሆን ከእሱ ጋር በብዙዎቹ ስንስማማ በሌሎች ደግሞ ከቶም ልንሰምር አልቻልንም፡፡ ሀይሌ ፊዳ በትህትና የሚናገርና የበሰለ ሰው በመሆኑም (ለብዙዎቻችን ታላቃችን ነበር) በጥሞና ብናዳምጠውም በአብዮትና አደረጃጀት፤ በትጥቅ ትግል አስፈላጊነት ወዘተ…ላይ ሆነ በዓለም አቀፉ የሶቬየት ቻይና ጠብ ወደ አንድ ወገን መዘንበሉ የአቅዋም ግዴታ ነው ያለውን አልተቀበልነውም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም_ ስለ ህዝብ ንቃትና ለለውጥ ዝግጁነትም ግምገማችን የተለያየ ነበር፡፡ በዋለልኝ የተጻፈው “አዋጅ ለአዋጁ”የሚለው ጽሁፍ ሆነ እኔ፤ ብንያምና አማኑኤል የጻፍነው “እንኳን ለ77ኛው ዓመት የደም ልደትዎ አደረስዎ” የሚሉት ጽሁፎች ጠንካራ ስለሆኑ ህዝብን ያስቆጣሉ በሚል በትግላችን መጽሄታቸው አርመውና ቆራርጠው እንዳተሙም ነግሮን ስለነበር በተጨባጭ ሁኔታው ላይ ግንዛቤያችን የተለያየ ነበር ማለትም ይቻላል፡፡ ምናልባትም አንዳንዶች እንደሚሉት እኛ ወጣቶችና በትኩሱ ከተማሪው ትግልና ከሀገር ቤት የመጣን ስንሆን እነሱ ደግም በእድሜም ገፋ አድርገውና በውጭም በተማሪነት ስለቆዩ ይሆናል፡፡ ቁምነገሩ ግን አልተስማማንም ፡፡ ይህም የሆነው በፖለቲካ አቅዋም ኢትዮጵያን በመሚለከት በተከሰተ ልዩነት እንጂ በጸረ ፊውዳል ጸረ ኢምፔሪያሊስቱ መሰረት ልዩነት አልነበረንም ማለት እችላለሁ ፡፡ ተደራጅቶ በፓርቲ ትጥቅ ትግል ማድረግ ይቻላል ይገባል የሚለውም አቅዋማችን ላይ የነሀይሌ ድጋፍ አልተደመጠም በወቅቱ፡፡ በአሜሪካ እነ እንድርያስም ለፓርቲም፣ ለለውጥም ገና አንድ ትውልድ በኋላ ቢታሰብ ይሻላል ባዮች ነበሩ፡፡ በመሆኑም በራሳችን አነሳሽነት ድርጅት ልንመሰርት ወስነን ወደ ምስረታው ስናቀናም ይህን ውሳኔ ለሀይሌ ፊዳ ነግረነው ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ሁሉ ዛሬ የአንጃ መሪ ሆኖ መስራች፤ ሊቀመንበር፤ ጠንሳሽ ነበርኩ የሚለውን ግለሰብ እኔ አላውቀውም ነበር፡፡ ትጥቅ ትግል ማክሄድ አለብን በሚል በየት ለሚለው የመጀመሪያ መልስ በባሌ ስለነበር በሶማሊያና በአቶ ዋቆ ጉቱ በኩል እንቅስቃሴ በማስፈለጉ ብርሃነ መስቀል ከዚህ ሰው ጋር እውቅና ስለነበረው ሊጻጻፈው ጀመረ፡፡ በዚያን ጊዜ የዛሬው አንጃ መስራች ግንኙነቱ ከነሀይሌ ፊዳ ጋር እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
ሶማሌዎች ሲተርቱ ዋሾ ሰው ምስክር ሊሆኑበት የሚችሉትን ያርቃል ይላሉ ፡፡ የእኛዎቹ ቀዳዳዎች ደግሞ እስከ ስድስት መቶ ገጽ ጽፈው ያውም ምስክሮች ሊሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ይገድላሉ፡፡ ተስፋዬ ደበሳይን ሾፈርነው፤ እንዲህ ተባባልን፤ ዕውቀቴን አደነቀልኝ፤ መደበቂያውን አሳየኝ፤ ከሱራፌል ካባ ጋር ኦፐሬሽን በከተማ አካሄድን፤ በጊዜው ለግርማቸው ለማ ይህን ያን መክሬው ነበር፤ ሻምበል አምሀ በተሰዋበት ተኩስ ልውውጥ ነበርኩ፤ ዘሩ እንዲህ ብሎኝ ነበር ወዘተ…የሚሉትን ዓይን አውጣ ዋሾዎች፤ በምስክር እንዳንረታቸው የጠቀሷቸው ሁሉ ተሰውተዋል፡፡ አንድ ሌላ ቀጣፊ ለምሳሌ ከጓድ ጋይም ጋር በግል ግንኙነት በምስጢር አዲስ አበባ እሰራ ነበር ያለውን በቀላሉ አውቀንበት ወያኔን አገልጋይ መሆኑን በጊዜውም አጋልጠነዋል ፡፡ አሁንም ግን ስለ ኢሕአፓ እንደ አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አንሶላ ይቀደዳል ፡፡ ሀሰታቸውን መጽሃፍ ያደርጉና ውሸታም ከውሸታም እየተደጋጋፈ ይተረተራል፡፡ እንቆቅልሽ ወዘተ…ብሎ ከሰባት መቶ ገጽ በላይ የጻፈ ወሽካታም እንዲሁ እኔን ጠቅሶ ሳያፍር የዋሸውን፤ ሌላው ደግሞ አዲስ አበባ ሆኜ ፋሺስቱ ኮለኔል ላይ የሞት ፍርድ ፈረደ ብሎ የከተበውንም ከዚህ በፊት ማጋለጤን መጥቀስም እፈልጋለሁ፡፡ ውሸቶቹን አጋልጦ ሀቁን ማስፈር ለሰማዕትም ዝክር ነው በሚል እንጂ ይህ ስምሪት ለመጪው ትውልድ አስተማሪነቱ ያን ያህል ነው፡፡ ታዲያ ምን ይጠበስ ብሎም ሊታለፍ የሚችል ነው፡፡ ግን ሀቁን ክደው ሲዋሹ በዝምታ ማለፉ ከታሪክ አንጻር ትክክል ባለመሆኑ በየጊዜው ጊዜ ያስጠፉናል፡፡ ዘረኞች ዛሬ የሀገራችንን ታሪክ ሲበርዙ ዝም ካልናቸው ጉዳቱ ግልጽ ነውና ምኒሊክን ለቀቅ የምንላቸውም ለዚህ ነው፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት፤ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም ወዘተን ለሰኮንድም አንቀበልም ያልነው ውሸት ሀቅ እንዳይሆን ብለን ነው፡፡ ለወሰድነው አቅዋም ዋጋ ከፍለንበታል። በተለይም ከኤርትራ ግንባሮች በኩልና ከረዳቶቻቸውም አንጻር፡፡ ሀሰት የተጋቱ ኋላቀርና መሃይም ወጣቶች ቄሮ ነን ብለው የሚያጓሩት ጥላቻ ሊጠቀስ ይገባዋል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ተምረዋል፤ አወቀዋል፤ ኢትዮጵያዊነታቸውንም ተቀብለዋል ያልናቸው ምሁር በሉን ባዮች የጥላቻና የሀሰት ዘመቻው ግንባር ቀደም መሆናቸው ነው፡፡ ለማንኛውም ከተነሳንበት አንጻር ዋናው ቁም ነገሩ ይቻላል ብለን ሳንፈራ ቆርጠን ተነስተንና ብዙ ችግርና መከራን ችለን ማደራጀት መደራጀት፤ ታሪክ ሰሪ ድርጅት መመስረት መቻላችን ነው፡፡ ሌላው ትርፍ የታሪክ አጋጣሚ ውሳኔ ይሆናል፡፡ ዛሬም መንጋው ቢያጓራም፤ ልዩ ሀይሎች መሰረትኩ ብሎ ቢውገረገርም ተደራጅተን ከታገልነው ወደ መቀመቅ ልንሰደው እንደምንችል ትውልድ ሊያምንበት ይገባል፡፡
በድርጅቶ መሃል ልዩነት ሲከሰት ድንግጥግጣቸው የሚወጣባቸው አሉ፡፡ የህብረተሰብን ዕድገት፤ ይዘትና አካሄድ መረዳት የተሳናቸው ናቸው፡፡ አሊያም ለሥልጣን ሲሉ ተጋጩ ብለው ያማርራሉ፡፡ ትግላችን የማንንም ጎፈሬ ለማበጠር ሳይሆን የፖለቲካ ሥልጣንን የህዝብ ለማድረግ ነው፡፡ ድርጅትና የድርጅት አባላት የህብረተሰቡ አካልና የቅራኔውም ነጸብራቅ ናችው፡፡ ለአንድ ግብ ቢሰለፉም፤ በአንድ ርዕዮት ስር ቢሰባሰቡም ሁሉም አንድ አስተሳሰብና እውነትም ግለኝነትን አሸንፈው ለህዝብ ዓላማ ቆሙ ማለት አይደለም ፡፡ የጸኑት ይጸናሉ፤ ሸብረክ ባዮችና ግለኞች ደግሞ ይለያሉ፡፡ እኔ ያልኩት ይሁን ባዮች ተነው አዩጠፉም፤ በጋራው ሰልፍ ይህ ስሜታቸው አይወገድም፡፡ የግል ሥልጣንና ዝና ፍላጎት ያሸንፋቸዋል፡፡ ተከለሰውነት ይጠናወታቸዋል፡፡ የኮሪያው ኪም ኢል ሱንጎች በሽታ ያጠቃቸዋል፡፡ በትግል ጊዜም አምባገነኖች ሊሆኑ በድርጅታቸውና በህዝብ ላይ ይመኛሉ፡፡ ይህ በኢሕአፓም ተመክሮ የታየ፤ የኖርነውና ጉዳት ያደረሰብንም ነው፡፡ ሁሉም አንድ ናቸው ደርግም ወያኔም፤ ኢህአፓም መኢሶንም ብለው ያኔ የለፈፉት ፕሮፌሰር (በቅርቡ ደግሞ ለሹሙ ቅኔ ሊዘርፉ የጣሩት) በጊዜው በሚገባ መልሰንላቸው ነበር፡፡ አንድ አልነበርንም፤ አንድ አይደለንም ብለን፡፡ ኢሕአፓና አንጃ የሃሳብ ልዩነት የላቸውም ሲልም አንድ ወሽካታ በቅርቡ ተደምጧል፡፡ አንጃ ነበርና ለምን ወግድ እንዳልነው ዛሬም አልገባውም ማለት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመጀመሪያዎቹን አንጃ አጠቃ በሚል በድርጅቱ ላይ ሊዘምቱ የሚከጅሉ አሉ፡፡ ብርሃነ መስቀልና ጌታቸው ማሩ የመጀመሪያዎቹ አንጃ አፈንጋጭና ሌላ ቡድን ፈጣሪ መሆናቸውን_ ብርሃነ መስቀል ራሱ ለፖሊስ በሰጠው ኑዛዜ አምኗል፡፡ የሁለተኛው ፍቅረኛ፤ የፍቅረኛዋን ድርሳን ብትጽፍልንም ብዙ ቦታ ከሀቅ የራቀ መሆኑን እናውቃለን ፡፡ ከደርግ ጋር አብረን እንስራ ብለው ያቀረቡት አቅዋም ድጋፍ ሲያጣ አፈነገጡና የብዙሃኑን ውሳኔ ረገጡ በሚል አንጃ ተባሉ እንጂ ለምንስ ሀሳቡ ቀረበ ብሎ ማንም የከሰሳቸው አልነበረም፡፡ ከድርጅቱ ህግና ደምብ ውጪ በምስጢር ከተፈሪ በንቲ ረዳት/ኤዲሲ ከሆነው ከጊታቸው ማሩ ወንድም መለስ ማሩ ጋር ሆነ ከአዲስ ዘመኑ ብርሃኑ ዘርይሁን ጋር ያደረጉት ግንኙነትና የወሰዱት እርምጃ ተጠያቂ አድርጓቸዋል። ጌታቸው ማሩን ገደሉትና በአሲድ አቃጠሉት ብለው የሚያሰሙትም ክስ የሚመለከተውን ግለሰብ መጠየቅ ትተውና ይባስ ብለው በአንጃነት አሁንም አቅፈው፤ እኛን ኢሕአፓዎችን ባያደርቁን ይመረጣል፡፡ በተጨማሪ ድርጅቱ በሞት የሚያስቀጣ ጥፋትን በሞት መቅጣት መብቱ ነው፤ ልሰናበት ያለውን ሁሉ ሲረሽኑ የቆዩት ጠባቦች በተለይ ድርጅታችንን ሊከሱ የሞራል ብቃት የላቸውም፡፡ እንደሚሉት ፈንገጥ ያለውን ሁሉ ብረሽንማ ኖሮ ዛሬ በህይወት ተርፈው አፋቸውን ባልከፈቱብን ባልጻፉብን ነበር፡፡ በሀሰት ሲናገር 15 ያህሉን ረሸኑ ያለውም ቡከን ተይዞ የተለቀቀው ወጣት ነህ ተብሎ ሳይሆን፤ እነ እገሌ በአንጃነት ተሰማርተው አመራሩንም ሊገድሉ አሲረዋል ብሎ 21 ገጽ ሉክ ወረቀት ኑዛዜ በማድረጉ መሆኑን የምናውቅ እናውቃለን እንጂ፤ አንድ የአመራር ግለሰብ አይዞህ ብሎ ለቀቀኝ የሚለው ውሸት ነው፡፡ ደግሞስ ተለቀቅኩና ሱዳን ገባሁ ብሎ ከጻፈ በኋላ አምልጫቸው ሱዳን ገባሁ ብሎ መቀባጠር እርስ በርስ ከራሱ አይቃረንም? በዚህም የጋራ አመራር ጉዳይ ቢነሳ ደግ ይሆናል፡፡ ኢሕአፓ በጋራ አመራር ያምናል፤ በውስጡ አንድ አምባገነን ማንገስን አላመነበትም፡፡ ማንምግለሰብ ለብቻው ወሳኝ፤ አሳሪም ለቃቂም ሊሆን አይችልም፡፡ ከመጀመሪያው ብርሃነ መስቀል የተባለው መስራች አባል የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ተብሎ እንደተመደበ እስታሊን በነፍሱ ሊሆን ሞክሮ ጓዶች ስለከሰሱትና ስላወገዙት በድርጅቱ የአዲስ አበባ የምስጢር ስብሰባ የዋና ጸፊው ቦታ ተሰርዞና የጋራ አሰራርም ተጠናክሮ እንዲሰፍን ተደርጓል፡፡ በኢሕአፓ ውስጥ ዋና መሪና ሊቀመንበር እንዳይኖርም ተደርጎ በጋራ አመራር እንዲሰራ ተወሰነ፡፡ እኔም ውጭ ሀገር ስለነበርኩ ከድርጅት ፖሊት ቢሮ ወይም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ተነሳሁ አንጂ፤ አንድ ቀባጣሪ እንደጻፈው በድርጅቱ አስር ዓመት የውጭ ጉዳይ ሀላፊና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆኜ አልሰራሁም፡፡ ያኔ በ1967፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በድርጅቱ ላይ ሊወዘፉ የፈለጉ ግለሰቦች ሁሉ አንጃ ይሆኗታል እንጂ እንዲፈነጩ አልፈቀድንላቸውም፡፡ የምትሃት ሊቀመንበር ዘንድሮ መጣብን እንጂ ኢሕአፓ ሊቀመንበር ኖሮት አያውቅም፤ አሁንም የለውም፤ የግለሰቦችም ንብረት አልነበረም፤ አሁንም አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃም አምባገነን መሪዎች መሰየማቸውን ትላንትም ዛሬም ተቃዋሚ ነን ፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ከዚያ ሁሉ ዓመታትና ተመክሮ በኋላ ነቃሁ መጠቅኩ ብሎ ማርክሲዝምን ሊተች የሚዳዳው ግለሰብ ባለፈው ሰሞን የጋራ አመራርን መርህ ወቅሶ ባህላችን ያለውን የጎበዝ አለቃነት (ያንድ መሪ የበላይነት) ሲመኝና ለዚህም በይፋ ሲቆም መስማቱ መቸም ያልታደለች ሀገር እንድንል ገፋፍቶናል፡፡ ሊቀጡ ሲገባቸውና ማፈሪያ ታሪክ የነበራቸውን በነጻ ለቀናቸው ዛሬ ተመልሰው ክስ በድርጅቱ ላይ ከመንዛታቸው በፊት ቆም ብለው ቢያስቡበትና አደብ ቢገዙ የተሻለ ይሆናል ብለን መምከር እንሻለን፡፡ ለጻፉት የሀሰት ስንክሳር እጥፍ የሀቅ መልስ ልንሰጣቸው ሀቁም ችሎታውም አለን ልንላቸውም እንፈልጋለን፡፡
ሀቅን ልናሰፍን ስንጥር ሀቅን እየካድን አይደለም፡፡ ጠባቦች በአጼ ምኒሊክና በታሪክም ላይ ጸያፍ ዘመቻ ስላደረጉ ሀቁን መካድ ከቶም አይገባም፡፡ በሀገራችን የብሄረሰብ ጭቆና ነበር፤ በሀይማኖት በኩልም እኩልነት አልነበረም፡፡ በሀገራችን ባርነትም ነበር፡፡ ሙሶሊኒ የባርያን ሽያጭ ላጠፋ ወረርኩ ያለው ውሸት ቢሆንም፤ አጼ ምኒሊክ ራሳቸውም ለአባ ጅፋር ሰው መሸጥ እንዲያቆም ማስጠንቀቂያ መላካቸውን ታሪክ ዘግቧል፡፡ ቤት ጸሊምም አፈ ታሪክ አልነበረም፡፡ አጼ ምኒሊክ በሰላም እጅ የሰጣቸውንና የበላይነታቸውን የተቀበለውን አልወጉም፤ ያልገበረውን ግን በሀይል ማስገበራቸው ሀቅ ነው፡፡ እነ ጋቢሳ በዚህ ዙሪያ አኖሌያዊ ጥላቻና ሀሰትን አጠነጠኑ እንጂ፤ አጼ ዮሃንስም ብዙ ትግሬና አማራ በተለይ በሀይማኖት/ክታብ ጉዳይም ገድለዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ሥልጣናቸውን ሊያሰፍኑ የጣሩት በዚያው በሰሜኑና ምዕራብ ክፍሉ በውጊያ በግድያ ነው፡፡ ይህን መደበቅ ፋይዳ የለውም፡፡ ሀገር ማቅናት የሚባለው ወይም በአንድ ንጉስና ማዕከላዊ ስልጣን ስር አንድ ማድረግ በሁሉም ሀገር ሀይልን መሰረት ያደረገ ሂደት ነበር፡፡ ቢስማርክ አልን ጋሪባልዲ፤ ትልቁ ፒተር አልን ካተሪን፤ ጄንጂስ ካን አልን ቄሳር፤ ወዘተ…በጊዜያቸው የነበረ ነውና መንገዳቸው ሀይልን መሰረት ቢያደርግ አያስደንቅም፡፡ የሚያገርመውና የሚያስወግዘው ግን በ20ኛው ክፍል ዘመን በደኖ አርባጉጉን፤ ቡራዩ አሶሳን፤ አጣዬ፣ ደምቢዶሎ፣ ሻሸመኔና አዋሳን የፍጅት ማዕከል ማድረግ ነው፤ በዚህ በኛ ዘመን የሜንጫ ፖለቲካ አካሂዶ ህጻናትን አዛውንትን፤ ቄሶችን ሼኮችን መጨፍጨፍና የእምነት ቦታዎችን ማቃጠል ነው፡፡ የህዝብን እርስ በርስ ፍጅት መጠንሰስና በስራ ለማዋል መወራጨት ነው መወገዝ ያለበት፡፡ ሁሉም የጊዜውና የዘመኑን አሻራ ይዞ የሚነሳ ነውና፤ በዲሞክራሲ ዘመን እንበልና ፋሺዝምን፤ ዘረኝነትን፤ ፍጅትን፤ ዘር ማጽዳትን ለማስፈን መጣሩ ነው ውጉዝ ሀራም ሊባል የሚገባው፡፡ የነገይቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ልትመሰረት የምትችለው በሀሰት ላይ በተራገበ ጥላቻና የጭቆናና የብልግና ስርዓት ላይ ሊሆን አይችልም፡፡ በቄሮና ዘረኞች ስር ሆነ በትምክህተኞችና አምባገነኖች ስር ስርየት ለኢትዮጵያ አይመጣም፡፡
ያገር ጆሮ ሁሉ በጋራ ተደፍኖ
መናገር ፋይዳ ቢስ ቃልን ማርከስ ከቶ
በግፍ የገደለ በገፍ የመተረ
በንጹሃንም ደም ራሱን ያጠበ
ዛሬም ይከረፋል
ነገም ይጠየቃል
ፍትህ ካላገኘ የሰው ደም ይጮሃል፡፡
ሟቹ ዶክተር ዘውዴ ገብረ ሥላሴ መለያ ወረቀታቻውን ወይም የጉብኝት ካርድ የሚባለውን ሲሰጡኝ ዶክተር ደጃዝማችና በኦክስፎርድ መመረቃቸውን አስፍረውበት በማየቴ በፊታቸው ሳቅ አምልጦኝ ነበር፡፡ የእሱ ቅጣት ነው መሰል ዶክተር ኮለኔል፤ ኢንጂኔር ፖለቲከኛ፤ ፕሮፌሰር ዘረኛ፤ መምህር መሳቂያ፣ ፈልተውብናል፡፡ በወያኔ የቀበሌ ምርጫ ጊዜ ተወዳዳሪዎች ታፔላቸውን ዘረዝረውና ለጥፈው መሳቂያ ሆነውም ነበር፡፡ ሀቁ ሲነገር ምንም ትምህርት የማያስፈልገው ተብለው የተወሰዱት፤ ጋዜጠኛነትና ፖለቲካኛ መሆን ናቸው ብንል ስህተት አይሆንም፡፡ እንደነዶክተር፤ ኢንጂነር፤ ፕሮፌሰር የሚለውን ታፔላ ሁሉ ባሁኑ ጊዜ ተጠቃሚዎቹ አፍረው ቢተዉት ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ የእኔ እኔ ዓይነቶቹ ሹመትና ዲግሪ ቢደረደር፤ ወይ ፍንክች ለሆነው አያስፈራራንምና ጥቅም የለውም፡፡ ኢሕአፓ በሚባል ዩኒቨርስቲ ገብቼ የተመክሮ ባለጸጋ ነኝና (ምንም እንኳን ለዲግሪ ሳልደርስ ከዩኒቨርስቲ አገዛዙ ቢያባርረኝም ) የተመክሮ ዲግሪ ደርድሪያለሁ፡፡ ሹሙ የደረደራቸው ዘረኛ ጄኔራሎች ማንን ያስፈራሉ? የተማረ ማለት ምንድነውና ነው ባስተማራቸው ህዝብ ላይ የሚጀነኑትና እናውቅልሃለን የሚሉት? ከዚህ በፊት በዶክተሮቹ ላይ ቀናህ ሊሉኝ ለከጀሉት የናንተ ትችት፦
ይቅርብኝ፤ ልደንቁር ይቅር ባልማረው፤
ተማረ የተባለው ሰው መሆን ካቃተው።
ብዬ በግጥም መልሼላቸው ነበር፡፡ በሹሙና በአሜሪካኖቹ የማደናገር ዘመቻ ተባባሪ ሆነው፤ ግንባር ቀደም ሆነው ኢትዮጵያን ለጥፋት የዳረጓት በአብዛኛው ራሳቸውን ዶክተር ፕሮፌሰር ያሉት መሆናቸውን መታዘባችን አልቀረም፡፡ በርዋንዳው ፍጅት ሁቱው በቱትሲው ላይ ፍጅት እንዲያካሄድ የቀሰቀሱት ምሁሮች ናቸው፡፡ የአልጄሪያ አክራሪ ሙስሊሞች፤ የሶማሌ ጎጠኞችና ፍጅት ጋባዦች፤ ወዘተ ምሁሮች ናቸው፡፡ በደቡብ ሱዳን ህዝብን ሚያጫርሱትና በሙስና ሀገሪቷን ያራቆቱት ሁለቱም፤ ሪያክ ማሻርም ሆነ ሳልቫ ኪር ዶክተር በሉን ባዮች ናቸው፡፡ ባለሜንጫው የካታሩ ቅጥረኛ እንኳን ተምሮ የጨረሰው ትምህርትና ያገኘውም ታፔላ ባይኖርም የሹሞቹ አጃቢ ዘረኞች በብዛት ታፔላቸውን መለጣጠፍ ልምዳቸው ሆኗል፡፡ በተለይም ወያኔ ዲግሪ እየገዛ ዶክተር በመባል መሳቂያ መሳለቂያ ሆነው ስናይ ቆይተን ዛሬም ኢንጂነር ዶክተር በሉን ባዮቹ መሃይም ዘረኞች በምኒሊክ ጊዜ የደነቆረ ዛሬም ቢነግሩት አይሰማም እየተባለባቸው ነው፡፡ ያልነበረ አንጎል በሌለበት ቀረ እንበል?
ባለው አገዛዝና፤ በይዘቱና አቅጣጫው ላይ ምንም ብዥታ አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያን ማፈራረስና ህዝቧንም በጎሳ በሃይማኖት ማጨራረስ ነው ግባቸው፡፡ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ለማድብዘዝ ባዕዳን ያላቸውን ዕቅድ ሊያሟሉ የመጡ ናቸው፡፡ በደከምንበት ተባብረውና ተድራጅተው የመጡብን ናቸውና አደገኛነታቸውን አቅልሎ መውሰድ ከባድ ስህተት ይሆናል፡፡የቀደሞ ስንኞችን በአዲስ ለመድገም በበኩላችን አቅዋማችን ያው ነው፤
ደምቢዶሎ እናቴ አባቴ ከሸዋ
አጎቴ ከወሎ አያቴ ከአድዋ
ነፍሴ ኢትዮጵያ ሆነች ቅርጫ መሆን ትታ
ተጣልታ ከሹሞች ከቄሮ ከመንጋ፡፡
ኢትዮጵያውያን ነን እና ትላንትም ዛሬም ነገም ፡፡ ሰንደቃችን ምንም ልጣፊ የሌለበት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ፡፡ እነ ዘርዓይ ደረስም እነ አብዲሳ አጋም፤ እነ መንግስቱና ገርማሜ ንዋይ፤ እነ ገርሱና በላይ ዘለቀ፤ አሞራው ውብነህ ፤ ፊታውራሪ ወርቁ፤ እነ ጥላሁንና ዋለልኝ እነ ጣይቱና ጽጌ፤ ቆንጂትና ድላይ ሁሉ የተቀበሉት የተሰዉለት፡፡ ዛሬ ክቡር ሰንደቅ አላማችን ላይ የተጀመረው እኩይ የቂመኞች ዘመቻ ከወያኔ የተወረሰ ነው፡፡ እነ መለስ ዜናዊ የጫማችን ማዘቢያ እናደርገዋለን፤ ሰንደቅ ዓላማ ተራ ጨርቅ ነው ብለው በዚያውም የሰይጣን ምልክታቸውን ለጥፈውበታል፡፡ የዘንድሮዎቹ ደግሞ ያንድ ድርጅትን ባንዲራ ሊተኩ መሃይሞችን አሰማርተው እስከ ግድያ ደርሰዋል፡፡ አገዛዛቸው ጸረ ኢትዮጵያ ነው፤ በዝምታ ካየነው ሁሉም ኬኛ ኬኛ ስግብግቦች ሀገር ሊነጥቁን ነው ዕቅዳቸው፡፡ ሹሙ ኢትዮጵያን ይወዳል ወይም ኢትዮጵያዊነት ሱሳቸው ነው የሚሉትንም ሆኑ በምርጫ ሊያጅቧቸው የተነሱትም ኢትዮጵያን ለከፋ አደጋ አጋላጮች ናቸው፡፡ ታሪክና መጪውም ትውልድ የሚጠይቃቸው ከሀዲዎች፤ ባንዳዎችና ማፈሪያ አንጃዎች ናቸው፡፡ ይህን መቀበልና ማመን አስፈለጊ ነው፡፡ ጠላትን ወዳጅ ብሎ አቅፎ ከመደናገር ጠላትን አውቆ ሀገርን ከውደቀት ለማዳን መደራጀትና መታገል ነው መፍትሄው፡፡ መንቃትና ፍርሃትን በድፍረት ማቸነፍ ይጠበቅብናል፡፡ በአፍ ተኩሶ ገዳይ የዘንድሮ ፋኖ ያልነው ባይኖር ይመረጣል፡፡ ሀገር አጥፍፊዎቹ ተደራጃተው እየታጠቁ እየተኮሱም ናቸውና እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው ማለቱ ቆሞ፤ የመጣውን በተሰጠን አቅምና ብልሃት ለመመከትና አርበኞች ደም አፍሰው ያስረከቡንን አንድ ሀገር ለመጠበቅ ሳንታክት ዛሬውኑ መነሳት ይኖርብናል፡፡ አቅዋማችንን ስለሚያውቁት፤ አንዴም በታሪካችን ኢትዮጵያን አሳልፈን ለግል ጥቅም፤ ለፍርፋሪና ለበርጩማ አንዳልሸጥን ስለሚያውቁ ባላቸው አቅምና በመገናኛቸው (ራዲዮ፤ ወዘተ) ዘምተውብናል፤ ከሀዲዎችን አሰማርተውብናል፤ ሊቀመንበሮች ስም ነጣቂዎችንም ደግፈው ለቀውብናል፡፡ የሚጠሉን ኢትዮጵያን ስለምንወድ ነው፤ የማይወዱን ሀገራችንን ስለሚጠሉ ነው፡፡ ነውናም፤ ይህንን ሁኔታ ዓይናችንን ጨፍነን አናይም አንልምና፤ ለሁለ ገብ ትግል እንነሳ፤ ባንዳን ማሽሞንሞን ያብቃ፤ ከሃዲ ተለይ ነጋሪት ይጎሰም፤ ለሀገራችን እንድማላት፤ እንለቅላት ወይም ተልካሾቹ እንድሚሉት አዎን እንፈጅላት፡፡ አስፈጁ ተፈጁ አይደል ያሉን ፋሺስቶችን ስለታገልን ?
ላሉትና ለመጪዎቹ የሚኖረን መልዕክት ይህ ነው፡፡ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፤ ክብቶቼን ምኒሊክ ወረሰብኝ፤ ሁሉን አዋቂ ነበርኩ ፉከራና መልዕእክት ምንም ጠቅሜታ የለውም፡፡ ይህን አደረግኩ ፈጸምኩ ለማለትማ ከሆነ የሞት አይፈሬ ጀግና ኢሕአፓዎች ታሪክ ገና በቅጡም አልተጻፈ፡፡ የግል ኩራት መመንጨት ያለበት ለሀገራችን ከሰጠነው ጥቅምና ግልጋሎት፤ መስዋዕትነትና በጽናት ከተቀበልንላት መከራ ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡
የተወለድንባት ያደግንባት ምድር
ክብር እሷ ለኛ ህይወታችን ሳይቀር
ክቶ ማትደፈር ሞተን ሳንቀበር
የእናት እናት አኩሪ ህልው ለዘለዓለም
ሌላ ሀገር የለን ከኢትዮጵያ በቀር፡፡
ለኢትዮጵያ እንታገል !
ውድቀት ለዘረኞች መንጋ!!
ይቀጥላል