(ዴሞ ቅጽ 46 ቁ 3 ሚያዚያ 2013 ዓ.ም.) . . . ዛሬ በሀገራችን ላይ ያንዣበበውን የፖለቲካ ድባብ በጥልቀት ስንመረምር ኢትዮጵያን ለማዳከመና ለመበታተን በየራሳቸው እኩይ የቤት ሥራ የተጠመዱ ዘረኞች የሚርመሰመሱባት ሀገር መሆኗን ማየት ይቻላል። በሀገራችን ሰፍኖ ለሚገኘው የርስበርስ ግጭት፥ ደም መፋሰስ፥ መፈናቀልና አጽያፊ የፖለቲካ መልክዓምድር ክስተት ሀገሪቷን የዳረጋት ከአባቱ ከወያኔ የወረሰውን ሕገአራዊት የሆነውን የዘረኞች ሕገመንግሥትን አስቀጥላላሁ ባዩ የአገዛዙ ሹም ነው። በዚህም የተነሳ አገር እየታመሰችና የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመ ነው። ሹሙ እንደወረደ ከአባቱ ከወያኔ የወረሰውን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይመክርበትና ይሁንታውን ሳይሰጠው የተጫነበትን፣ በእጅጉ ያስመረረውንና እንዲወገድለት የሚፈልገውን የአራዊቶች ሕገመንግሥት እንድንቀበልልት፣ እንድንወድለት፤ እንድናወድስለትና እንድንገዛበት ይመኛል። ከሹሙ የሚወደድ ተግባርም ሆነ አሜን ብሎ ለመቀበል የሚያስችል ፖለቲካዊ፥ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፖሊሲ አላየንበትም። ሹሙ ያለው ችሎታ የሕዝቡን ጥያቄ እየነጠቀ በጣፈጡ ቃላት ህልውናዋን ጠብቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈችውን የሀገራችን ኢትዮጵያን ስም እያንቆለጳጰሰ ማላዘኑ ሲሆን በተግባር ግን ሀገራችንን እያፈረሰብን ነው። በዛሬው ጊዜ ፖለቲካ ማለት የሰውን ልብና አዕምሮ ማሸነፍ ሆኖ ሳለ በጉልበት መተማመንም ሆነ፤ በአፈጮሌነት ተሙለጭልጮ ለማለፍ መሞከር እራስን ያጋልጣል፣ ያዋርዳልም። ሹሙ ሕዝብ የሚያውቀውን የተራራ ግዝፍት ያህል ያለውን ሐቅ አምታትቶና ሸውዶ ለማለፍ የሚያደርጋቸው ሙከራዎች ወደ ገደል የሚውስድ የቁልቁለት ጉዞ ውስጥ አስገብተውታል። “ለዚህ ስንዴ እየለመነና እየሰፈረ ለሚኖር ሕዝብ ዴሞክራሲ ምኑ ነው”፤ እኛ ዘንድ ሰርፕራይዝ (ድንገተኛነት) የለም፤ እናውቀዋልን፤ አሁን የሚደረገውን ጩኸት እናውቀዋለን፤ ብዙ ልምድ ስላለን ቅንጣት ታክል ጫና የሚፈጥርብን አይደለም” በማለት ያሰማቸው ድንፋታዎች ሹሙ ለሕዝብ ያለውን ንቀት በማሳየት በኩል ለናሙና የሚቀርቡ የፖለቲካ ክስረቶቹ ናቸው። ሹሙ ሕዝብን ንቋል። እራሱንም በአደባባይ አጋልጧል። ሊነግሥብን እየተንደረደረብን ለመሆኑ ከዚህ በላይ ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅብንም። ባለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያን ያሉና ለሀገራቸው ሉዓላዊነት የቆሙ፤ ለዚህች አገር ሕዝብ ፍትኅና ዴሞክራሲን የተመኙ ዜጎች ዛሬም ሲጋዙ፥ ሲገደሉና ሰቆቃን ሲቀበሉ እያየን ነው። በዚህም ተባለ በዚያ አሁንም የሹሙ ጥረት አደናግሮም ሆነ ፍጅትን አካሂዶ ከየአቅጣጫው የገነፈለውን የሕዝብ ብሶት/ አመፅ ማፍንና ማስቆም ነው። ለዚህም ሠይጣናዊ ተልኮው የሚተበብሩትን አድርባዮችና እበላ ባዮችን በየአቅጣጫው አሰማርቷል። ሹሙ ተሻጋሪውም፣ አሸጋጋሪውም፥ ገዥውም እሱ ራሱ መሆኑን አስረግጧል። ሹሙ ከስረመሠረቱ ዘረኛ ብቻ ሳይሆን ጸረኢትዮጵያም ጭምር መሆኑን አላምን አልቀበል ብለው ወይም ግራ ተጋብተው ልብና ጆሮ የሰጡትን ሁሉ ያስቆጣና ያስመረረ ወደ ተቃውሞው ጎራ የሰደደ መሆኑ በገሀድ የታየና እየታየም ያለ ሐቅ ነው። ለሹሙ ዴሞክራሲ ማለት ቧልት ማወናበድና ማስመሰል መሆኑን በአንደበቱ ብቻ ሳይሆን በተግባር አረጋግጧል። ትናንት በዘመነ ወያኔ ያየነው ዛሬ በዘመነ ሹሙ እየተደገመብን ነው። በዘመነ ወያኔ ምርጫም ከዴሞክራሲ የተጣላ፤ ወያኔ ራሱን በራሱ መርጦ የሚሰይምበት ሂደት መሆኑን ለ27 ድፍን ዓመታት ታዝበናል፤ ዛሬም እየቀጠለ ያለውና የሚታየው ቲያትር ከዚህ የባሰ እንጂ የተሻለ እንደማይሆን መጽሐፍ ገላጭ መሆን አያስፈልገንም።
አዕምሮ እያላቸው ማሰብ፤ ዐይን እያላቸው ማየት ፤ ጆሮ እያላቸው መስማት አቅቷቸው ለአደጋ የሚጋለጡ ሁሉ ሊወቅሱ የሚችሉት ራሳቸውን ብቻ ነው። ከስህተት ታርሞና ራስን ወቅሶ፤ አገርንና ሕዝብን ለማዳን ከሚደረገው ትግል ጎራ ተሰልፎ ለሀገር መቆሚያ ጊዜው አሁንም አልመሸምና የሚሰማ ጆሮ ያለው አገርን ከሚያፍርሱ ጎጠኞችና አስመሳዮች ራስን ማራቅ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ግዴታ ጭምር መሆኑን እያስገነዘብን ለጋራ ትግል ጥሪያችንን እናስተላለፋለን። ሙሉውን ያንብቡ . . .