ከደብተራው ዝግጅት ክፍል ማስታወሻ: ይህ ጽሁፍ አቶ ነብዩ ያሬድ እ/ኤ/አ በጁላይ ወር 2015 ልከውልን አትመነው ነበር። አሁንም አዲስ የተተከለውን የኦነግ/ኦዴፓ ዘረኛ ቡድን አለዚያም ህወሓትን በጭፍን ለሚደግፉትም ሆነ፣ የኦሮምኛ ተናጋሪ ወይም የትግራይን ህዝብ ከነኝህ ዘረኛ ቡድኖች ጋር አንድ አድርገው በመመልከት ለሚሳሳቱ ቢያነቡት ትምህርታዊ ይሆናቸዋል ብለን ስላሰብን በድጋሚ ይኸው በድረገፃችን ላይ አወጣነው።
ከነብዩ ያሬድ – (መግቢያ) – የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ዓላማ የትግራይ ሕዝብና የተሓህት/ህወሓትን የግኑኝነት ታሪክና ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ በጣም በአጭሩ መግለጽ ነው። የዚህ ፅሁፍ ፀሓፊ የተቃዋሚው ጐራ ውስጥ ወዳጅና ጠላትን የመለየት ብዥታ ሰፍኖ ይገኛል ብሎ ያምናል። ይህንን ብዥታ ማጥራት ደግሞ የአገራዊው ዴሞክራሲያዊ የአንድነት ትግሉ ሀሁ ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ ይህ ጽሁፍ የትግራይ ሕዝብና የተሓህት/ህወሓትን ታሪካዊና ወቅታዊ ግኑኝነት እጅግ አጭር በሆነ መንገድ በመግለጽ ወዳጅና ጠላትን በመለየት ረገድ አስተዋፅዖ ለማድረግ ታስቦ የቀረበ ነው። ይህ ጉዳይ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ጦማሮች ሊወጣው የሚችል በመሆኑ በዚህ አጭር፣ አጠቃላይና ቀላል አቀራረብ ይሸፈናል የሚል ግምት በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዘንድ የለም።