(የኢሕአፓ መግለጫ) – ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪ ጽንፈኞች በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሱት ጥቃት ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ክልብ ያሳዘነ አረመኒያዊ ድርጊት ነው። ለዚህ አስከፊ ድርጊት በኃላፊነት የሚጠየቀው አገዛዙ መሆኑ ጥርጥር ሊኖር አይገባም። ከወያኔ ባለሥልጣናት ጋር በተቀነባበረ ሴራ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በተገደሉ ወቅት በወታደራዊ ዩኒፎርም ተከሽኖ ሲፎክርና ሲቀጥፍ የነበረው ሹም ቁጥራቸው ከሰማንያ በላይ የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች በወንጀለኞች ያለቁበትን ድርጊት ሲገልጽ በሕዝብ መካከል የተነሳ ግጭት በማለት አድበስብሶ ለማለፍ ከመሞከሩ በላይ ተጠያቂው ማን እንደሆነና ማን በሕግ ፊት ሊቀርብ እንደሚገባ ግልጽ ሳያደርግ አልፎታል። እንደ ቡራዩው ጊዜ አልሰማሁም ባይልም ያው የጭፍሮቹን ግፍ በለሆሳስ ለመሸፋፈን መሞከሩ የሚካድ አልሆነም። ዘረኛው መንጋ በአገዛዙ ፖሊሶችና ባልሥልጣናትም ሙሉ በሙሉ መደገፉ በሕዝብ የታየ ነው። የአገዛዙ ባለሥልጣናት በናዝሬት የቄሮን መንጋ የመለሰውን ወጣት እያፈሱ ወንጀለኞችን አማራን ለመግደል እናስታጥቃችኋለን እያሉ እየፎከሩ ናችው። ሹሞቹ ተደብቀው ባደረጉት ምክክርም ወንጀለኞችን ከመያዝም ሆነ በሕግ ፊት ከማቅረብ ይልቅ ከጽንፈኞቹ ጋር መታረቅን እንደሚሹም ታውቋል። አገዛዙ ከወንጀለኞቹ ጋር ሙሉ ተባባሪና ተጠያቂም ነው የምንለውም ለዚህ ነው።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ሁኔታ በቅድሚያ በመገንዘባችን ነበር ከጠዋቱ ጀምረን የወያኔ ዘረኛ ሥርዓት መቀጠሉ ሀገርን ያጠፋልና ሥርዓቱ ተወግዶ የሽግግር ሂደት ይጀመር ስንል አቅዋም ይዘን የነበረው።፡ የወያኔ ባለሥልጣናት በሹሞቹ መተካት ሳይውል ሳያድር አውሬ ቦዘኔዎችን ሕዝብ ላይ የማሰማራቱ ተከታይ ለመሆኑ ብዙም ነቢይነትን አልጠየቀም። ኦህዴድ/ኦዴፓ ኦሮምኛ ተናጋሪ ህወሓት/ወያኔ ነው ያልነው አለምክንያት አልነበረም። ዛሬ አረመኔያዊ ተግባሮችን በሚሰብከው ጽንፈኛ ግለሰብ ላይ ወንጀሉን ሁሉ ከምሮ የአገዛዙን ባለሥልጣናት ነጻ ማውጣታት አግባብ አለመሆኑ ከእይታችን መራቅ የሌለበት ሲሆን ጽንፈኞቹን ጋብዞ አምጥቶ አይዞህ በማለትና ጥበቃ በመስጠት በያዘው ከፋፋይ ሥራ እንዲሰማራ ያደረገው አገዛዙ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ከሰሞኑ ግድያ በፊትም የክብር እንግዳ ተብለው የተጠሩትና የሹሞቹ አጋር ሆነው የቆዩት ጽንፈኞች በጌዴዎ፥ አፋር፥ ቡራዩ፥ ደምቢዶሎ ወለጋ፥ …ወዘተ ፤ ቤተ ክርስቲያን ያቃጠሉት፤ ሕዝብ ያፈናቀሉት፤ አረመኔ ግድያዎችን ሲያካሂድ የቆዩት ገና ከጠዋቱ መሆኑን የሚታወቅ ነው። በዚህ ድርጊታቸው አገዛዙ ተባባሪ ሆኖ መሳተፉ እንጂ ለማስቆም እርምጃ እንዳልወሰደ ሁሉም የተረዳው ሲሆን አሁንም መሰል ወንጀሎችን ለማስቆምና መንጋ ነፍሰ ገዳዮችን ለመቅጣትም ሆነ ለመቆጣጠር ምንም የተጀመረ ሂደት እንደሌለ እያየን ነው። በአርሲና ባሌ፥ በጠቅላላው በመንጋው እየተወሰደ ያለው የጸረ ኦርቶዶክስ እርምጃም ይህን መንጋና መሪዎቹን ከውጭ ሆነው የሚዘውሩ፤ የእርስ በርስ የአረብ ጠባቸውን ያመጡብን፤ የአልሸባብና ሳላፊስቶችንም ጣልቃገብነት የሚያንጸባርቁ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለም። አል ጀዚራ እየተባለ የሚጠራው የካታር መገናኛ ብዙሃን የጽንፈኛውን አላማ አስመልክቶ የሚነዛው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለምን እንደሆነ ስውር አይደለም። የጽንፈኛው ጥቂት የባሌ ተከታይ መንጋዎች ጂሃድ ሊያውጁም መወሰናቸውን ቢያስታውቁንም የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ እነዚህን ጸረእስልምና ሃይማኖት የሆኑ ወሮበላዎችን ተቃውሞ ከወገኑ ከክርስቲያኑ ጋር መቆሙ ደግሞ የዘረኞቹ ዓላማ እንዳልተሳካላቸው ገላጭ ነው። በአንጻሩ የተወሰኑ የኦሮሞ ተወላጅ ልሂቃን የጠቀማቸው መስሏቸው በጸረአማራው ዘረኝነት ሲያጓሩ መታዘቡ አሳዛኝ መሆኑ መጠቀስ ያለበት ነው።
በሹሞቹ የሚደገፈው ጽንፈኛውና ዘረኛው ቡድን የተሰማራው በአማራውና በክርስቲያኑ፣ በጋሞውና ወላይታው፣በአፋሩ ላይ መሆኑ በሚገባ የታየ ነው። የአገዛዙ ባልሥልጣናት በወንጀሉ በቀጥታ ተሳትፈዋል፤ እየተሳተፉም ነው። አኖሌ የሚል ልብ ወለድ ፈጥረው ሲጮሁብን የነበሩት ዘረኞች ዛሬ በአደባባይ ጡትና ብልት ቆራጭ፤ በገጀራ ጨፍጫፊ፤ እርጉዝ ሴት በጦር ገዳይ፤ ቤተክርስቲያን አቃጣይና ቀሳውስት ምዕመናንን ገዳይ፤ ህጻናትን ሳይቀር የቤተሰብ አባላትን በደቦ ዱላ ቀጥቅጦ ገዳይ ሆነዋል። ማን አውሬ እንደሆነም ግልጽ አድርገው የሕዝባችንን ታሪክ ግን አጨቅይተዋል። እኩይ የሆነው የድርጊታቸው ዋና ዓላማ የሚመነጨው ሕዝብ እርስ በርሱ ተባልቶ ኢትዮጵያ ትጠፋለች ከሚል ቅዠት መሆኑ ግልጽ ነው። የቅርብም ሆነ የሩቅ የኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ በተለይ አማራውና ክርስቲያኑን ለማጥቃት ሁሌም ሰምረው ሲሰሩ እንደነበር ነውና ከአሜሪካ እስካ ጄዳ፤ከካይሮ እስከ ካታር በመንጋው ድርጊት ተደስተው እንዲገፉበት እያበረታቱ መሆኑን ግብጽ ጽንፈኞቹን በማድነቅ የምታደርገው እንቅስቃሴ ያጋልጣል። ይህ ጸረ ኢትዮጵያ ከበባ ተግባራዊ እንዲሆን መታቀዱን ሹሞቹን ያጋለጥነው ገና በላያችን ላይ ሲሰየሙ ነው። በአሁኑ ወቅት ሕዝብን ለመከፋፈል ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉት ጽንፈኞች ከወያኔ ጋር ተስማምተው የሚሰሩ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም ፤ መቀሌ ድረስ ሄደው አስሮ ሲያሰቃያቸው ለነበረው ቡድን በይፋ ሲሰግዱ ከመታየታቸውም በላይ በገሀድ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ቅስቀሳ ሲለፍፉ ተደምጠዋል። ወያኔ ቀደም እንደወጥመድ የተጠቀመበት የጎሳ ፌዴሬሽንና ከፋፋይ ፖለቲካ ይሻር፤ ይቀየር፤ ይቁም የሚል ሀሳብ ሲቀርብ የወያኔ ከፋፋይ ሕግማ የደማንለትና የማንነካው ነው በሚል ክፍፍልን ያጸደቀውና የወያኔን የቀድሞ የሴራ አቋም በመደገፍ አቋም የወሰደው የሹሞቹ ቡድን ነው። የወያኔ ባለሥልጣናት የአማራውን የደቡብን የአፋሩን ሆነ የሌላ አካባቢውን ሕዝብ ተለጣፊዎቹን ማለትም የሰገዱለትን በመጠቀም ብጥብጥን አያሰፋ ነው። የሕዝባችንን አመጽ ጠልፋ ሹሞቹን ያመጣችብን አሜሪካ በቅርቡ በኤምባሲዋ በኩል ያሰራጨችው አልባሌ መግለጫ ራሱ ምን ያህል የሹሞቹና የጽንፈኞቹ ጸረ አማራ ጸረ ኢትዮጵያ ወንጀል እንዳላሳሰባት ያጋልጣል። ጥቅማቸውን ለመጠበቅና ኢትዮጵያን መጫወቻቸው ለማድረግ በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጬ ውሽልሽል የፖለቲካ እርምጃቸው መላ ኢትዮጵያን ለከፋ ብጥብጥ መዳረጋቸውና በመላ አፍሪካም ፖለቲካቸውን የሚያቃውስ ሁኔታ ፈጣሪ መሆናቸውን ውሎ አድሮ መረዳታቸው አይቀርም። ቢሆንም ለኢትዮጵያ ጥቅም ብለው የሚጨነቁ አይደሉም። በአካባቢ ፖለቲካ ሰልፋቸው ከኢትዮጵያ ጠላቶች ከእነሳውዲና ኤሚሬትስ ጋር በመሆኑ ነው ቡችላ የሆነላቸውን ሻዕቢያ በሽፋን ከማዕቀብ ካወጡ በኋላ ኢትዮጵያ ጠፋች አልጠፋች ደንታ ቢስ ሆነው ነው ሹሙን በቅርብ እያማከሩ ጽንፈኛውን የሚያስፈነጩብ። ጽንፈኞቹ ሰንደቅ ዓላማችንን እንዲቀድዱ ፤ በእምነት ተቋሞች ላይ እንዲዘምቱ፤ ታሪካችንን እንዲያጎድፉ መከታ የሚሆኑት።
ወያኔ የሚባለው ሙጀሌ ተነቅሎ አልወጣም። ሹሞቹ ቀሪ ሰንኮፍ ናቸው። ሥርዓቱ በሽግግር ሂደት ፈርሶ በሕዝብ በመረጠው መንግሥት አልተተካም። አሁንም የምንለው ላለው የግፍ ሁኔታ ተጠያቂው አገዛዙ ነው። መፌትሄ ቁልፉ የሕዝብ የጋራ ትግል እንጂ ሌላም አይደለም። መጣ የተባለው ለውጥ ምትሃት ሆኖ መቅረቱን ሕዝብ አውቋል። እንደ ወያኔው ሁሉ ጥቂቶችን ጠቀመ እንጂ ለሕዝብ የፈየደው የለም። እንዲያውም ሕዝብ በአረመኔ ጽንፈኞች ድርጊት ተሳቀቀ። ሹሞቹ ብዙሃኑን የኦሮሞ ሕዝብ፤ ባጠቃላይ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ መብት አልባነቱን አጠናክረው ሀገር አልባ ሊያደርጉትም በመጣር ላይ ናቸው። ለውጡ በይስሙላና ለነሱና ለጌቶቻቸው ነው፤ የጓዳ ለውጥ፤ ጎይቶምን በመገርሳ የተካ ብቻ። ሴት ካድሬዎችና የለየላቸውን አድርባዮች መሾም የሴቶችን መብት ማስከበር አይደለም። ጥቂቶችን መፍታትና በሺዎች የፖለቲካ እስረኞች ላይ ሺዎችን መጨመር ፍትሃዊ እርምጃ መውሰድ አይደለም። ሀገር ወዳዶችን እያሳደዱና መብት አልባ እያደረጉ፤ እያፈኑ፤ ጋዜጠኞችን በወያኔ የሽብር አዋጅ መሰረት እያሰሩና እያንገላቱ ለውጥ አመጣን ብሎ መለፈፉ ፋይዳ ቢስ ነው። ጠቀሜታው ለሹሞቹና ለሚያጅቧቸው ባዕዳን ብቻ ነው። ለኢትዮጵያ ግን አሁንም “ሁሌም በገሌ” ያለችው ድመት ሁኔታ ነው፤ የሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ወደ አስከፊ አዘቅት ወድቋል፤ አገዛዙ በመንጋው በኩል ሥርዓትአልበኝነትን አስፍኖ ይገኛል። በመሆኑም በሕዝብና በሀገር ላይ አረመኔያዊ ወንጀልን የፈጸሙትንና እየፈጸሙ ያሉትን ዘረኞች ይህ አገዛዝ ይገታቸዋል፤ ያቆማቸዋል ብሎ መጠበቅና መማጠን ከቶም የሞኝ ሞኝ ሆኖ ሀገርን ማስበላት ነው። ወንጀላቸው፤ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻቸው፣ ጸረ ኦርቶዶክስና ጸረ አማራ ዘመቻቸው ይጠናከራል፤ ይቀጥላል እንጂ የሚቆም አይደለም።
የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ምን ማድረግ አለብን የሚለው ነው። ብዥታና መደናገር ከጠፋ ማድረግ ያለብን ቁልጭ ብሎ ይታየናል፤ ኃይላችንም ሊሆን የሚችለው የኢትዮጵያውያን ህብረትና ተደራጅቶ ለትግል መነሳት ብቻ ነው። ጠላቶቻችን ባለገንዘብና ባለሥልጣንም ናቸው። የመንጋው ጫጫታ ዘላቂ መስሏቸው በባዕድ ተደግፈው ሀገራችንን ሊበታትኑ ተነስተዋል። ይህንን ማስቆም የሚቻለው በሹሞቹ ርህራሄና ከዘረኝነት መራቅ ሳይሆን እነሱም የችግሩ አካልና ዘረኞች በመሆናቸው ተደራጅቶ በሁለገብ ትግል አገዛዙን በመጣልና ወንጀለኛውን መንጋ ከጥቅም ውጪ አድርጎ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የሽግግር ሂደትን ተግባራዊ በማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ይቻላል። ብዙሃኑ የኦሮሞ ሕዝብ የዚህ ትግል አካል ነው። ብዙሃኑም የትግራይ ሕዝብም የወያኔን ሰንሰለት በጥሶ ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር መሰለፊያው ጊዜ ደርሷል። ይህ ዘረኛ አገዛዝ የአፋርን ሕዝብ ትጥቅ እያስፈታ ለጅቡቲና ሶማሊያ ተጠቂ አድርጎ ሀገርን አስደፍሯል። ለሱዳን ስለተሰጠው የሀገራችን መሬት ሆነ ስለ ወልቃይት፥ ጠገዴ፥ ራያ፥ …ወዘተ ትንፍሽም እያለ አይደለም። ለምን መስዋዕትነት ከፈልን ? ግባችን ምን ነበር ? የዚህን መልስ መዘንጋት የለብንም። በሁሉም መስክ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍልና ሕዝብ ለትግል መነሳት አለበት። የትግሉንም ስልት የሚወስነው አገዛዙ ሳይሆን ሕዝብ ነው። ያለፉት በርካታ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ብዙ ሞክረው መክሸፋቸው ግልጽ ሲሆን ዘንድሮ በከሃዲው አገዛዝና መንጋው አማካኝነት አዲስ ዘመቻ ከፍተውብናል። እኛም ክተት ብለን ለአንዴም ለሁሌም ዘረኛውን አገዛዝና መንጋ ማስወገድ አለብን፤ በቆራጥ ትግል፡፡ ጨቋኙን ዘረኛውን ሰልፍ ፍቀድልንና እንጣልህ ማለቱ አይጠበቅም። ዛሬ ደርቶ የሚታየው የዓለም ሕዝብ የተቃውሞ እንቅሳቅሴ
ተፋፍሞ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ማንም የሰልፍ የተቃውሞ ፍቃድ ሲጠይቅ አልታየም። ተቃውሞ ሲታገል እንጂ፤ሲሰለፍ ሲሰዋ እንጂ፤ የሙት ከተማ አድማ ሲያደርግ እንጂ ! ተቃውሞው በሁሉም መስክ ይፋፋም።
ወያኔ ኢሕአዴግ በትግላችን ይውደም !
ኢትዮጵያ ተከብራ ታፍራ ለዘለዓለም ትኑር !!
ክተት ሠራዊት፤ ምታ ነጋሪት !!