ማስታወሻ ከደብተራው ድረ-ገጽ ዝግጅት ክፍል፡ ታላቁ የጥበብ ሰው ገሞራው በ1999 ዓ. ም ’’የቅዱሳንን ዐጽመ-ርስት ርኩሣን አይወስዱትም! (የማስጠንቀቂያ ጦማር!)’’ በሚል ርዕስ የፃፈውን በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ልኮልን በድረ-ገፃችን ላይ አትመነው ነበር። ’’… የታላቅና ክቡር ውድ አባት ዐጽመ-ርስት የሆነውንና በይዞታው ንብረትነት ለዘመናት የቆየውን ቦታ ኢሕጋዊ በሆነ መንገድ በዘረፋ ወስደዋል። … ’’ በማለት ጀምሮ ’’… አሁን ይህን ቦታ በዳረጎትነት ተሰጠኝ ብሎ የሚጨፍረውና ጮቤ የሚረግጠው ሰው በቀጣዩ የፍትሕ ወቅት የደም እንባ ከሚያለቅስ ዛሬውኑ አስረክቦ ዞር ቢል ይመረጣል። … ’’ ብሎ ያጠቃለለውን ጽሑፍ የደመደመበትን ግጥም (ቀጥሎ በቀይ ቀለም የተቀመጠው) ያልሆነ ትርጉም እየሰጡ፣ ጥቂት ሰዎች የዚህን ክቡር የኢትዮጵያ ልጅ አስክሬን ከወያኔ ጋር ለመሞዳሞድ ሲያውሉት ታዝበናል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ በ እኛ በኩል በሰፊው እንመለሥበታለን። ለዛሬው የቅርብ ወዳጃቸው አቶ ዘነበ በቀለ የላኩልንን ጽሑፍ ከዚህ በታች አቅርበናል። ጽሑፉን ያንብቡ …