እስክ ድል ደጃፍ ድርስ በአላህ ስም ተማምለናል!

EM-logo

እስክ ድል ደጃፍ ድርስ በአላህ ስም ተማምለናል!

ዛሬ በሃገራችን ከእምነት ነፃነት መነፈግ፣ በሕይወት የመኖር ዋስትና እስከ ማጣት ድረስ ጠመንጃ የአነገቡና ሣንጃ የወደሩ የአንድ መንደር ልጆች በተቆጣጠሩት አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር የሕዝቦች መገደል፣ መታሠርና ከአገር መሰደድ እየባሰበት እንጂ የመክሰም ጭላንጭል አይታይበትም። የድብደባውና የማሸማቀቁ ዋና ዓላማ ሕዝብ የፍርሃት ድባብ ሰፍኖበት ፀጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ነው። የወያኔ ሥርዓት በደል ገፈት ቀማሽ የሆነው ሰላማዊው የሙስሊሙ ሕብረተሰብ የፍርሃትን ምሽግ ደርምሶ ታግለው እንዲያታግሉት ለመረጣቸው መሪዎቹ እስከ ድል ደጃፍ ድረስ ከጎናቸው መቆሙን በቃለ መሃላ አረጋግጧል። የዲያስፖራውም ኢትዮጵያዊ ሙስሊም በድምፃችን ይሰማ መሪነት የሚኪያሄደውን ሰላማዊ ትግል በመደገፍ ትግሉን የተቀላቀለው ውዲያው መሆኑ በታሪክ ዓምድ ላይ ሰፍሯል።

ይህ ታሪካዊ ትግል የወለደው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ሕብረት ምሁራንን፣ የሕግና የሚዲያ ባለሙያዎችን፣ የሃይማኖት መሪዎችን እና የታወቁ አክትቪስቶችን ያካተተ ኮንፈረንስ ከጁላይ 15 እስከ ጁላይ 16 2016 ለዋሺንግተን ዲሲ ቅርበት ባላት በላልንሃም ሜሪላንድ በቅርቡ በፕሬዚደንት ኡርዱግዋን በተመርቀው በአዲሱ የቱርክ መስጊድ አዳራሽ ውስጥ አድርጓል። ስብሰባው ላለፍት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያደረጉት የሞትና የሽረት ትግል በጥልቀት የተገመገመበት፣ የወደፊት አቅጣጫውን አመላካች የሆኑ ፅንሰ ሃሳቦች የተሰነዘሩበት ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጋ እምነትና ነፃነት የሚከበርባት የጋራ አገር እንዴት መሆን እንደምትችል የስብሰባው ታዳሚዎችና እንግዳ ተናጋሪዎች ሃሳብ ተለዋውጠውበታል። የስብሰባውም ጠቅላላ ሂደት በዘመናዊ የስርጭት መሳሪያ በቀጥታ ከአዳራሹ ቅፅበት በቅፅበት ይተላለፍ ስለነበረ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ  ያገባኛል ባዮች በኢትዮጵያ ውስጥ ጭምር ተከታትለውታል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ያለ አግባብ ፍርድ የተገመደለባቸው የወንድሞቻችን የፍርድ ሂደት የሕግ ሙያ ባላቸው እንግዳ ተናጋርዎቻችን በሰፊው ሲዳሰስ፣ የሙስሊሙ ሰላማዊ ትግል ለሌላው የሕብረተሰቡ ክፍል ያስተማረው ትምህርት ተወድሷል። የሚዲያ ባለሙያዎች ከሰላማዊ ትግሉ ጋር ተያይዞ የገጠማቸው ፈተናና ትግሉን ለማፋፋም በማድረግ ላይ ያሉት አስተዋጽኦ ለታዳሚው በይበልጥ ግልጽ አድርገውለታል። በዚሁ ስብሰባ ላይ የሚናሶታ እስቴት በመወከል በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ የመጀመሪያ ሙስሊም አባል የሆኑት የኪትዝ ኤሊሶን የቪዲዮ መልእክት ለታዳሚው ሲቀርብ፣ “The Movement” ወይም ‘ንቅናቄው” የተሰኘው ስለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ የተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመልካች ቀርቧል። የታወቀው ገጣሚ ወንድማችን አሊ ሁሴን በውይይቶች መሃል አለፍ አለፍ ብሎ ያቀረባቸው ግጥሞች የታዳሚውን የታመቀ ስሜት ከሚገባ በላይ አገንፍለውት ነበር።

ዲያስፖራ ያለው የኢትዮጵያ ሙስሊም ህብረተሰብ እስካሁን ካዘጋጃቸው ስብሰባዎች ሁሉ በዓይነቱ የተለየ ነው ተብሎ የተመሰከረለት ይህ ስብሰባ የተለያየ እምነትና የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ተናጋሪ እንግዶች ያቀረቧቸው ሃሳቦች በነፃ የተንሸራሸሩበት ከመሆኑም በላይ በመደማመጥ፣ በመተሳሰብ፣ በመከባበርና በመስማማት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነት በመገንባት የጋራ ጠላትን ድል መምታት እንደሚቻል ግንዛቤ የተወሰደበት ውጤታማ ስብሰባ ነበር።

የወያኔ ዘረኛ ሥርአት ሕዝብን በጎሣ እና በሃይማኖት እየነጣጠለ የሚፈፅመውን የጅምላ ጭፍጨፋ ማቆም የሚቻለው ተጠቂው ሕዝብ በጋራ ሲታገል ብቻ መሆኑ በዚህ ስብሰባ ላይ ተሰምሮበታል። በዚህ ወሳኝ የትግል ወቅት በዳይና ገዳይ ሥርዓትን  መቃዎም ፖለቲካ ውስጥ መግባት ነው በሚል ሰንካላ የፈሪዎችና የአድር ባዮች አስተሳሰብ ራስንና ሌላውንም ሕዝብ ከትግል እንዲሸሽ ማድረግ የወያኔን ዓላማ ከማራመድ ተለይቶ መታየት የለበትም በሚለው ሁሉም እንግዳ ተናጋሪዎች ተስማምተውበታል።

ማንም ሕሊና ያለው ግለሰብ፣ ቡድንም ሆነ ድርጅት በደልና ጭፍጨፋ በሕዝብ ላይ ሲፈፀም እያየ ገለልተኛ ነኝ ሊል አይችልም። ዝምታው ከጨፍጫፊው ጋር ከመተባበር ተለይቶ ሊታይም አይችልም። ከተጨፍጫፊው ሕዝብ አብራክ የወጣን ሁሉ እስላማዊ፣ ሞራላዊና ወገናዊ ግዲታ አለብንና።  ኡስታዞቻችንን አህመዲን ጀበል፣ በድሩ ሁሴን፣ ከማል ሸምሱንና ሙሃመድ አባተን ጨምሮ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሎ ስማቸው በወህኒ ቤቶች ሰሌዳ ላይ የተለጠፈው በአጠቃላይ 84 ንፁሃን ወገኖቻችንን ጉዳይ ከትግሉ ጎን ያላቆመን ምን ሊያቆመን ነው? እስከ ዛሬ ድረስ የገለልተኛነትን ጋቢ ተከናንበው የከረሙ ሁሉ ዛሬ የወያኔን አረመኔ ሥርዓት በአደባባይ ወጥተው ከማውገዝ ሌላ አማራጭ የላቸውም። በእርግጥ ማንነታቸው ለሁሉም በበለጠ ፍንትው ብሎና ጠርቶ የሚታይበት ወቅቱ አሁን ነው።

በታሣሪዎች ላይ ሽብር ነዝቶ፣ ሕዝቡም ተሸማቆ ከትግሉ እንዲያፈገፍግ ለማድረግም ሊሆን ይችላል ወያኔ የስም መለጠፉን  የሚጠቀምበት ብሎ ዝም ማለት የዋህነት ሳይሆን ሃላፊነትን መሸሽና ውንድሞቻችንን አሳልፎ መስጠት ነው። ለትግሉ የገባነውን ቃለመሃላም መርሳት ነው። ስለሆነም በዲያስፖራም ሆነ በአገርቤት በየጊዜው የገለልተኛነት አዋጅ በማወጅና በአጥር ላይ በመቀመጥ ትግሉን እንደ አጫዋች የሚመለከቱ ሁሉ ከሰው በላው የወያኔ ዘረኛ ሥርዓት ጋር የሚደረግውን የሞትና የሽረት ትግል ከሕዝብ ጎን በመሆን ነገ ሳይሆን ዛሬ መቀላቀል አለባቸው እንላለን። ማጣፊያ አጠረኝ ከአሁን በኋላ አያዋጣም። የትግሉን አቀበት በአንድነት ወጥተን በድል አምባ ላይ በሕብረት መሰባሰብ አለብን። ትግሉ ሲወጠን እስከድል ደጃፍ ድረስ አብርን ልንጓዝ በአላህ ስም ተማምለናልና!!

ትግላችን በአላህ ፈቃድ እስከድል ደጃፍ ድረስ ይገሰግሳል!
አላሁ አክበር!!!

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊዎች ሕብረት