ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ጥር 13 ቀን 2009 ዓ.ም.): ዓርብ ጥር 12 በየቦታው በቃና ዘገሊላ በዓል ላይ ወጣቶች ወያኔን አወገዙ፤ ፖሊስ የጥቃት እርምጃ ወሰደ – የወያኔ አገዛዝ በሱማሊያ ውስጥ ለፕሬዚዳንት ቦታ በሚደረገው ምርጫ ውስጥ እጁን ለማስገባት እየጣረ ነው – በዚምባብዌ ታግተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሁንም በእስር ላይ እየተሰቃዩ ነው – የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ሥልጣን የሚያስረክቡ መሆኑን ገለጹ፤ ወደሌላ አገር ሄደው ይኖራሉ።
ዓርብ ጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላን በዓል ለማክበር በተለያዩ ቦታዎች፣ ታቦት አጅበው ከሚመለሱ ወጣቶች ጋር የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ግጭት ማድረጋቸው ታውቋል። በባህርዳር እና በጎንደር ከተሞች ወጣቶች የተለያዩ ወያኔን የሚያውግዙ መፈክር አዘል ዜማዎች በማሰማታቸው የተናደዱ የጸጥታ ኃይሎች የተሰበሰቡትን ለመበተንና ገሚሱን ለማሰር ሞክረዋል። በአዲስ አበባም በየካ አካባቢ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲጨፉሩ የነበሩትን ወጣቶች ፖሊሶች የበተኗቸው ሲሆን ዜማ አውራጅ የነበሩትንም አስረው መውሰዳቸውን ታውቋል።
የወያኔ አገዛዝ በሱማሊያ ውስጥ ወታደሮችን በማስገባት ከአሜሪካና ከሌሎች የምዕራብ አገሮች ከፍተኛ ጥቅም ሲያገኝ የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ወደፊት ይካሄዳል በሚባለው በሶማሊያ የፕሬዚዳንት ምርጫ ውስጥ በቀጥታ እጁን ለማስገባት እየጣረ መሆኑ ተነገረ። “የውይይት፤ የምርምርና የትብብር ማዕከል”የተባለውና በወያኔ ባለሥጣኖች ተቋቁሞ ከጸጥታው ክፍል ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው መሆኑ የሚነገርለት ተቋም “በሶማሊያ ሽግግር ላይ ያለው ግርግር”Ύበሚል ርዕስ በቅርቡ ባወጣው ሰነድ፣ በአሁኑ ወቅት በስልጣን ያሉት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሚስተር ሀስን ሼክ መሀመድ እንዲደገፉ ይፋ የሆነ አቋም የወሰደ ሲሆን ተወዳዳሪያቸውን ሚስተር ኦማር አብዱራሺድ ሸርማርኬን ነቅፏል። የአሁኑ ፕሬዚዳንትና ተከታዮቻቸው አክራሪ ከሚባሉት ከእስላማውያን ክፍሎች የመጡ ቢሆንም በወያኔ ባለስልጣኖች ሲደገፉ ቆይተዋል። የወያኔ አገዛዝ ታማኝ አና አሽከር የሆኑት የሱማሌ ባለስልጣኖች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ በተለያየ መንገድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ በውስጥ አዋቂዎች የታወቀ ቢሆንም እንኳ፣ በአሁኑ ወቅት በይፋ ድጋፍ መስጠቱ አስገራሚ ሆኗል ተብሏል። የአሁኑ ፕሬዚዳንት ወያኔ ወታደሮቹን በሱማሊያ ውስጥ ማሰማራቱን እንዲቀጥል አጥብቀው የሚጠይቁ ሲሆኑ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ግን የወያኔን ጣልቃ ገብነትን አጥብቀው ይቃወማሉ ተብሏል።
ባለፈው ታኅሣሥ ወር በዚምባብዌ በአንድ የእርሻ ጣቢያ ውስጥ ተገኝተው በቁጥጥር ስር የዋሉት 34 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሁንም በእስር ቤት የሚማቅቁ ሲሆን በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቢቀርቡም አስተርጓሚ አልተገኘም በሚል ምክንያት ጉዳያቸው ሳይታይ ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል። ስደተኞቹ ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ አራቱ ከ 11 እስከ 12 ዓመት በሆነ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናችው።
የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ሚስተር ያህያ ጃሜህ በትናንትናው ዕለት በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ በተፈጠረው ችግር ምክንያት አንዲት ጠብታ ደም ሲፈስ ማየት የማይፈልጉ መሆኑን ገልጸው ከስልጣን እንደሚወርዱ ተናገረዋል። ሚስተር ጃሜህ ይህንን መግለጫ በቴሌቪዥን የሰጡት ከጊኒ እና ከሞሪታኒያ መሪዎች ጋር ለረዥም ሰዓታት ከተደራደሩና ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው ተብሏል። ፕሬዚዳንቱ በቴለቪዥን ከሰጡት መግለጫ ቀደም ብሎ የሞሪታኒያ ፕሬዚዳንት ስምምነት ላይ ደርሰናል ሚስተር ጃሜህ ከአገር ወጥተው ወደ ሌላ አገር ይሄዳሉ የሚል አጭር መግለጫ ከመስጠታቸው ሌላ የድርድሩ ዝርዝር ይዘት ይፋ አልሆነም። ተወዳዳሪያቸው ሚስተር ባሮ ሴኒጋል በሚገኘው የጋምቢያ ኤምባሲ ቃለ መሃላ መፈጸማቸው የሚታወስ ሲሆን ሚስተር ጃሜህም እስከ አርብ እኩል ቀን ድረስ ከስልጣን እንዲለቁ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑም ይታወቃል።
ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ያዳምጡ