(ሚያያዚያ 23 ቀን 2011) –
ሚያዝያ 1969 — ኢሕአፓና ደጋፊዎቹ የላባደሩን ቀን በሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ሲያከብሩ በአረመኔው ደርግና ጭፍሮቹ ከሺ በላይ የሆኑት በየቀበሌው ተረሽነው ሲገደሉ ሌሎችንም ከእስር ቤት አውጥተው ረሽነዋል። ሁሌም በዚህ ቀን የምንዘክራቸው ሰማዕታት ናቸው ። ዛሬም ይህን ቀን ስናከብር በሹሞቹ የወያኔ አገዛዝ ቀጥሎ
የኢትዮጵያ ሠርቶ አደር ሕዝብ ከማጡ ወደ ድጡ መስመጡን በማጤን ነው።
ለዓመታት የሠራተኛው ነጻ ማህበር ታግዶ ተለጣፊ ማህበር በምትኩ ተሰይሞ አለ። በደርግ የተጀመረው በወያኔም በሹሞቹም ዛሬም ቀጥሏል ። ለዘመናት ልንል በምንችለው ደረጃም በአሁኑ ወቅት ሠርቶ አደሩ ሕዝብ የኑሮ ዋስትና ተነፍጎ እየተበዘበዘ ይገኛል። መብቱን ለማስከበር ሲነሳም አፈናና ግድያ እየመጣበት ቆይቷል። የሠራተኛ ሕግ የሚባለውን አሁንም በስራ ውሎ ያለው የባርነት ህግ ነው። ባዕዳን በሰርቶ አደሩ ላይ ሙሉ የረገጣና ብዝበዛ መብት ተሰጥቷቸው ላባአደሩን ያሰቃያሉ ። የኑሮ ውድነት ጣራ ጥሶ ወጥቶ ባለበት የሰርቶ አደሩ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ምላሽ ያጣ ከመሆኑ በላይ የአሁኖቹ ሹሞችም ደሞዝ አለመጨመር ኤኮኖሚያዊ ብልህነት ነው ሲሉን እየሰማን ነው ። የየካቲት አብዮት ቁልፍ አንቀሳቃሽ የነበረው የኢትዮጵያ ላባአደር ዛሬ ከዓመታት በኋላ ያኔ ይሻለው ነበር በሚያሰኝ የከፋ ሁኔታ ላይመገኘቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ግንጠላ ከኤርትራ ላባደሮች አለያይቶታል። ዘረኛ ስርዓትም ጎድቶታል። መብቱን ማስከበሪያ የጋራ ማህበር ባለመኖሩ አንድነቱን አጠናክሮ ሊታገል አልቻለም ለሰርቶ አደሩ መብት የተዋደቁትን እነ አበራ ገሙን፤ማርቆስ ሐጎስና ብዙዎቹን ሰመእት ስናስታውስ የላባደሩ ትግል ከግቡ አለመድረሱን መገንዘብ መገደዳችን አልቀረም።
ህገወጥና ተለጣፊው የሠራተኛ ማህበር በአስችኳይ ፈርሶ ላባደሩ በነጻነት የራሱን ማህበራትና የጋራ ተቋም መመስረት መቻል አለበት ። ያለፈውን መቀጠል ጸረ ሰርቶ አደር አቅዋምና እርምጃ ነው። በእስር የሚማቅቁትም የሰርቶ አደሩ ታጋዮች ገና አልተፈቱምና መፈተታታቸው የግድ መሆን አለበት ። የባርነት ህጉ ተሽሮ ሰርቶ አደሩ ሕዝብ በነጻ መክሮና በድምጹ የሚያጸድቀው የሰራተኛ ህግ መደንገግ ይገባዋል። የሰርቶ አደሩ ሕዝብ ከኑሮ ውድነት ተመጣታኝ የሆነ ደሞዝ ሊከፈለው፤ የባርነት የስራ ሁኔታ ሊወገድለትም ያስፈልጋል። ባለው ሁኔታ ሠርቶ አደሩ በይፋም በህቡዕም፤ በሁሉም ፈርጅና መስክ መደራጀቱ ወሳኝ ሆኖ ይገኛል ብንል ትክክል ነው። ቀጥሎ ያለው ዘረኝነትና የግፍ አገዛዝ ጸረ ሰርቶ አደር በመሆኑ ይህ አገዛዝ ተወግዶ በሽግግር መንግሥት መተካቱም ቀነ ቀጠሮ የማይሰጠው ግዳጅ ነው።
የኢትዮጵያ ሠርቶ አደር ሕዝብ መብቶች በትግላችን ይከበሩ !
ዘረኛው ጸረ ላባደር ጸረ ሕዝብ ስርዓት ይውደም !
ኢትዮጵያዊነት ያቸንፋል !!