ታዋቂው የታሪክ ምሁር ሪቻርድ ፓንክረስት አረፉ- አቃቤ ህግ በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ያቀረበው መረጃ የይፋ ንግግራቸውን የቪዲዮ ቅጅ ነው – ዚምባብዌ ውስጥ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በረሃብ ምክንያት ፍርድ ቤት ወለል ላይ ወደቁ።
ከህይወት ዘመናቸው ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪካ ላይ ምርምር ያካሄዱና በዚህም ላይ በርካታ የጥናት ጹሁፎችን ያቀረቡ ታዋቂው ሪቻርድ ፓርንከርስት በተወለዱ በ89 ዓመታቸው ሐሙስ የካቲት 9 ቀን 2009 ዓ.ም.ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሪቻርድ ፓንከርስት ሙሶሊኒ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውን ወረራ በመቃወም ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉት የታዋቂዋ የሲልቪያ ፓንከርስት ልጅ ሲሆኑ ከእናታቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በ1949 ዓ.ም. ገና የ28 ጎልማሳ ሆነው ነው። ፓንከርስት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከ20 በላይ መጻሕፍትን የደረሱ ሲሆን በሺ የሚቆጠሩ ድርሰቶችንም አበርክተዋል። ፓንከርስትና ባለቤታቸው ሪታ ፓንከርስት በቴዎድሮስ ላይ የዘመተው የእንግሊዝ ጦር የዘረፈውን የኢትዮጵያን ቅርስና እንዲሁም የሙሶሎኒ ጦር የወሰደውን የአክሱም ሐውልት ለማስመለስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ፓንከርስት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመመህርነት ለረዥም ዓመታት የሰሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምን በመመስረትም ሆነ በዲሬክተርነት በመምራት አገልግለዋል። የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የሆኑት ፓንከርስት ወንድ ልጃቸውን አሉላ ብለው ስይመውታል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ገርባ እና አብረዋቸው የታሰሩት ሌሎች ዜጎች በዛሬው ቀን ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የወያኔ አገዛዝ አቶ በቀለንና ጓደኞቻቸውን ከአንድ ዓመት በላይ አስሮ ሲያሰቃያቸው ከቆየ በኋላ በአቃቤ ህጉ አማካይነት ያቀረበባቸው መረጃ በተለያዩ ቦታዎች ንግግር ሲያደርጉ የተቀረጹት ሁለት ቪዲዮች ብቻ ናቸው። አንደኛው በአምቦ እና በአዳማ ንግግር ሲያደርጉ የተቀረጸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በነሐሴ 2007 ዓም. በኦሮሞ ጥናት ማህበር ስብሰባ ላይ ተገኝተው ያሰሙት ንግግር ነው። በሁለቱም ቪዲዮች ላይ አቶ በቀለ ስለሕዝቡ መበደል ጠቅሰው በሰላማዊ መንገድ መታገል አለብን ከሚል ውጭ የተናገሩት እንደሌለ ግልጽ ሆኖ ሳለ አቃቤ ሕጉ ሕዝቡን በመቀስቀስ ለአመጽ ማነሳሳተቸውና የሽብር ወንጀል ለመፈጸማቸው ማስረጃ ነው ብሎ አቅርቧል። ከቪዲዮዎቹ ሌላ በተጨማሪ የቀረበ የምስክርነት ቃል አልተሰማም። በማስረጃ የቀረቡትን ቪዲዮዎች ለማዘጋጀት የአንድ ሰዓት ጊዜ እንኳ የማይወስድ መሆኑ እየታወቀ የቪዲዮ ማስረጃ በፍርድ ቤት ለማቅረብ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ መውሰዱ የወያኔ አገዛዝ ተቃዋሚዎችን በእስር ላይ ለረጅም ጊዜ ለማሰቃየትና ለማሸት ከሚጠቀምበት ዘዴዎች አንዱ ነው ተብሏል።
ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሰደድ ላይ የነበሩ 56 ኢትዮጵያውያን ባለፈው አርብ ዚምባብዌ ውስጥ የታሰሩ ሲሆን ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ብዙዎቹ በረሃብና በጠኔ ምክንያት ራሳቸውን ስተው በፍርድ ቤቱ ወለል ላይ ወድቀው እንደነበር ክሮኒክል የተባለው የዚምባብዌ ጋዜጣ በአምዱ አስፍሮ አውጥቷል። ኢትዮጵያውኑ በወለል ላይ ከወደቁ በኋላ የምግብ እርዳታ የተደረገላቸው ሲሆን ከመካከላቸው ስምንቱ አካላቸው በመጎዳቱ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ተብሏል። ኢትዮጵያውኑ የተከሰሱት በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል በሚል ክስ ቢሆንም ዳኛው ውሳኔ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ መጀመሪያ በቁጥጥር ስር ወደ አደረጋቸው አካል ወደ ኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት እንዲመለሱ አድርጓል። ስደተኛችን ወደ አገር ውስጥ አስገብቷል የተባለ የከባድ መኪና ሹፌር 500 ዶላር የተቀጣ ሲሆን በኢትዮጵያውያኑ ላይ የሚወስደው እርምጃ ምን እንደሆን አልታወቅም። የወያኔን አስከፊ አገዛዝ በመሸሽ በርካታ ኢትዮጵያን አሁንም አገር ጥለው መሰዳዳቸውና በየቦታውም የሚደርስባቸው ከፍተኛ በደል እየቀጠለ ሲሆን ይህ ሊወገድ የሚችለው አስከፊው አገዛዝ ሲወገድ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው።