ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 11, 2009 ዓ.ም.) – የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ነጋዴዎችን ለመዝረፍ ያደረጉት ሙከራ ከሸፈ – በጎጃምና በጎንደር ወያኔ መሳሪያ ለማስፈታት ያደረገው ጥረት አልተሳካም – የወያኔው አስችኳይ አዋጅ የተለያዩ ችግሮች እየፈጠረ ነው – ኦክላንድ ኢንስቲትውት የወያኔን አገዛዝ አወገዘ – ሂራን በተባለው የሱማሊያ ግዛት በአልሸባብና በወያኔ ወታደሮች መካከል ግጭት ተፈጠረ።
የወያኔ አገዛዝ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በስራ ላይ ካዋለ ጀምሮ በዜጎች ላይ የሚደርሰው በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ሰሞኑን ባስተላለፍነው ዘገባ በርካታ ሰዎች መገደላቸውና በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸው የተዘገበ ሲሆን የንብረት ዝሪያውም ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑ ተነግሯል። ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የወያኔ ፌዴራል ፖሊስ አባላት በየነጋዴዎቹ ቤቶች ገብተው ለመዝረፍ ያደረጉትን ሙከራ ሕዝቡ በቁርጠኛነት በመጋፈጡ ጉዳት ሳያደርሱ ሸሽተው መሄዳቸውን የሚገልጽ መረጃ ደርሶናል ። በአዲስ አበባ በጀሞ፤ አለም ባንክ ሌቡ ቤተል እና የረር አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊቶች የተፈጸሙ መሆናቸውንም የሚገልጹ መረጃዎች አግኝተናል። በተያያዘ ዜና ጥቅምት 10 ቀን 2008 በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ተዋቅረ የነበሩትን የወያኔ ሆድ አደር ግለሰቦች ሰብስቦ በህብረተሰቡ ላይ ስለሚያካሄዱት የስለላ ተግባሮች መመሪያ የተሰጣቸው መሆኑ አወቅ ምንጮች ገልጸዋል። ሕዝባዊ አመጹ እየተቀጣጠለ ባለበት ወቅት ወያኔ አገልጋዮቼ ናቸው የሚላቸው ግለሰቦች ከሕዝብ ጎን እንደሚሰለፉ በጎንደርና በጎጃም እንዲሁም በሌሎች ቦታዎች በነበሩ ሕዝባዊ አመጾች የታዩ በመሆናቸው የማክሰኞ ዕለቱም ሙከራ ከንቱ ልፋት ነው የሚሉ በርካታ ናቸው።
በጎጃም ክፍለ ሀገር ሜጫ ወረዳ አካባቢ በነዋሪው ሕዝብና ወደ አካባቢው ትጥቅ ለማስፈታት በመጡ የወያኔ አግአዚ ወታደሮች መካከል በተፈጠረው ፍልሚያ አራት የአግአዚ ወታደሮች ሲገደሉ አንዱ መቁሰሉ ታውቋል። በዚህም ምክንያት ወደ አካባቢው የመጣው ጦር ሸሽቶ የተመለሰ መሆኑ ከአካባቢው የመጣው ዜና ይገልጻል። በመርአዊ አካባቢም ብረት ለማስፈታት ከመጡ የወያኔ የአግአዚ ቡድን ጋር ሕዝቡ ባደረገው ግጭት የቡድኑ መሪ የሆነች አንዲት ሴት መኮንን መገደሏ ተሰምቷል። በጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በአገው ምድር በሞጣና በቋሪት አካባቢዎች ከፍተኛ ውጥረት ያለ መሆኑ ይነገራል። በጎንደር በላይ አርማጭሆ በገምበራ አካባቢም አርሶ አደሩን መሳሪያ ለማስፈታት የመጣ ጦር ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት በተኩስ የተመለሰ መሆኑ ታውቋል። ስለደረሰው ጉዳት ያገኝነው መረጃ የለም።
የወያኔው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የኢኮኖሚ ውድቀት እያስከተለ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ስራዎችን እያስተጓግለ መሆኑ እየተነገረ ነው። የቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕደን ስራውን ለማስጀመር ከ130 እስከ 140 ሚሊያን ዶላር ካፒታል ያስፈልገዋል የተባለ ቢሆንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የሚጀመርበት ቀን ከ2010 ወደ 2011 የተላለፈ መሆኑ ተገልጿል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያትም የውጭ አገር ኤምባሲዎች እንደልብ የካውንሰለር አገልግሎቶችን ለመስጠት የተቸገሩ መሆናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ኦክላንድ ኢንስቲቲውት የተባለው ተቋም ማክሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የወያኔ አገዛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጣት በዜጎች ላይ ግፍና በደል ለማድረስ በይፋ ማዘዣ አውጥቷል ብሏል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጣላቸው ገደቦች በጣም አሳዛኝና አስከፊ መሆናቸውን ገልጾ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለረጅም ዓመታት በተመሳሳይ ገደብ ውስጥ በመቆየቱ አዋጁ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ አይሰጥም ብሏል። ሕዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች የመብትና የነጻነት ጥያቄዎች በመሆናቸው እነዚህ ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት ይበልጥ በመገደብ ሳይሆን መብትንና ነጻነትን በማሟላት ነው በማለት ተቋሙ ገልጿል። ለአገዛዙ በተለያዩ መንግዶች እርዳታ የሚሰጡና ትብብር የሚያደርጉ አገሮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጠቀም አገዛዙ የሚያካሄደውን የመብት ረገጣ ማውገዝ ግዴታቸው ነው ብሏል።
ሂራን በተባለው የሱማሊያ ግዛት በአልሸባብ ተዋጊዎችና በወያኔ ወታደሮች መካከል ግጭት የተካሄደ መሆኑ ተነግሯል። ግጭቱ የተካሄደው በበለደወይንና በሃልጋን መካከል በምትገኘው ኑር ሊናህ በምትባለው መንደር ውስጥ የአልሸባብ ኃይሎች በአካሂዱት ደፈጣ ሲሆን ስለደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ አልተገኘም።
ባለፈው ወር ለሁለት ቀናት በኮንጎ ኪንሻሳ በነበረ ሕዝባዊ ተቃውሞ 53 ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውና 140 ሰዎች መቁሰላቸው እንዲሁም 299 ሰዎች መያዛቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ዘገባ ገለጸ። ከተገደሉት መካከል አራት የፖሊስ አባላት ይገኙባቸዋል። እስካሁን የኮንጎ መንግስት በዘገባው ላይ የሰጠው ማስተባበያ የለም። የአገሩ ፕሬዚዳንት ሚስተር ካቢላ ሕገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው የጊዜ ገደብ ውጭ በታሰበው ምርጫ ለመወዳደር አቅደዋል የሚለውን አቋም በመቃወም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስልፎችን ማደራጀታችው ይታወቃል። ባለፈው ማክሰኞ የኮንጎ መንግስት ከአንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ንግግር ምርጫን በዚህ ዓመት ሚያዚያ ለማደረግ ስምምነት ላይ ቢደርሱም የአገሪቱ ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲ መቃቀሙ ተነግሯል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ብሩንዲ ከዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ራሷን ያገለለች መሆኗን የገለጸች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ ደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ጉዳዩን በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ውስጥ ያቀረበች መሆኑ ተገልጿል። የብሩንዲና በአሁኑ ወቅትም የደቡብ አፍሪካ ከፍርድ ቤቱ አባላነት ለመገለል የወሰዱት እርምጃ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ይከተሉታል የሚል ስጋት ፈጥሯል። ፍርድ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮችን ብቻ በመመልከት በአፍሪካ አገሮች ላይ አድሎዎ አድርጓል የሚል ክስ በተደጋጋሚ የተሰማ ሲሆን በመጭው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ጉዳዩ በአጀንዳ ቀርቦ ውይይት ሊካሄድበት እንደሚችል እየተነገረ ነው።