(ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የሻዕቢያው መሪ የወያኔን ክስ አስተባበለ – በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የሕዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት አልተቻለም ተባለ – የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጉዞ የሚያስከፍለውን ተጨማሪ ዋጋ እንዲያነሳ ተጠየቀ።
የሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ከግብጽ ጋር በማበር የአባይን ግድብ ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነው የሚለውን የወያኔን ክስ ያስተባበለ መሆኑ ታውቋል። ቀደም ብሎ የወያኔ አገዛዝ ተቃዋሚዎችን በገንዘብና በማቴሪያል ይረዳል በሚል የግብጽ መንግስትን መወንጀሉና በቅርቡ ደግሞ ግድቡን ለማፍረስ በሻዕቢያ የተላኩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ ቀርበዋል ማለቱ የሚታወቅ ነው። ኢሳያስና ሌሎች የሻዕቢያ ባለስልጣኖች ወደ ግብጽ መሄዳቸውንና መነጋገራቸውን እንዲሁም ዳህላቅ ደሴት ላይ ግብጽ የባህር ኃይል የጦር ሰፈር እንድታቋቋም የተደረገውን ስምምነት በመግለጫው ባይክድም የአባይን ግድብ ለማፍረስ ሻዕቢያና ግብጽ አሲረዋል በሚል የተሰራጨውን ዜና ወያኔ ድጋፍ ለማግኘት የሚያደረገው ፕሮፓጋንዳ ከመሆን ውጭ እውነትነት የሌለው ነው በማለት አስተባብሏል።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሕዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት በማሟላት በኩል ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ዜጎች እየተናገሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በዓለም የጤንነት አገልግሎት መለከያ ከመጨረሻዎቹ ተርታ ያለች መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የጤናው ዘርፍ በመድኃኒትና በህክምና መሳሪዎች እጥረት ከፍተኛ ችግር ውስጥ የገባ መሆኑ እየተነገረ ነው። በአንዳንድ ሆስፒታሎች በማደንዘዣ መድሐኒት እጥረት ምክንያት የቀዶ ጥገና ህክምና ሊሟላ አለመቻሉን የወያኔ ደጋፊ የሆኑ የዜና ምንጮች እንኳ እያጋለጡ ሲሆን በአብዛኛው ሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች በከፍተኛ ደረጃ የመድሐኒት እጥረት መኖሩን ዜጎች እየገለጹ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በናይጄሪያ ዜጎች ላይ የሚያስከፍለውን ተጨማሪ የመጓጓዣ ዋጋ ባስቸኳይ እንዲያነሳ የናይጄሪያ የሲቪል አቢየሽን ባለስልጣን ትዕዛዝ ያስተላለፈ መሆኑን የዜና ምንጮች ገልጸዋል። ከናይጄሪያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚሄዱ መንገደኞች በደቡብ አፍሪካ መንግስት በግዴታ ወደ አገራቸው ሊመለሱ ይችላሉ በሚል ምክንያት አየር መንገዱ እያንዳንዱን መንገደኛ ከ 75 እስከ 150 ዶላር ሲያስከፍል የነበረው ተጨማሪ ገንዘብ ብዙ ናይጄሪያውያን ያስቆጣና ቅሬታ ያሳደረ መሆኑ ተነግሯል። አየር መንገዱ የሚያስከፍለው ከስምምነት ውጭ በማለት የናይጄሪያ የሲቪል አቢየሽን ባለስልጣን ጭማሪው እንዲያነሳ ተጠይቋል። በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ በወያኔ ሹመኞች ቁጥጥርና ባለቤትነት ስር እየገባ በመሆኑ የኢትዮጵያ ለማለት ይከብዳል የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው።