የዘረኛ መንቻካ፤ ቃለ አጋኖ ፖለቲካ፤ አታቱሌ ቡቄ

ከኢያሱ  ዓለማየሁ: በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አማርኛ አስተማሪያችን (ካልረሳሁ አቶ አሻግሬ ይባሉ ነበር ) ሲያስተምሩን በድርሰት/ጽሁፍ ውስጥ ቃለ አጋኖ አታስገቡ አታብዙ ይሉን ነበር።   ሰማይና መሬት ተነጥፈው ብራና ቢሆኑ፤   ውቅያኖሶች ሁሉ ቀለም፤ የዓለም ዛፍ ተቆርጦ መጻፊያ ቀርክሃ/መንጎል ቢሆን፤ የማቱሳላን ዕድሜ እንኳን ቢሰጠኝ ያንቺን ቁንጅና ጽፌ ልጨርሰው ዓይነት ቃለ አጋኖ።  ምስጋና ይድረሳቸው ለአስተማሪዬ! ከቃለ አጋኖ በተጨማሪም በቀላሉ ሊቀርብ የሚችለውን አውቃለሁ ለማለት ተናደደ በማለት ፈንታ ተቆጫበረ ብሎ መጻፍንም ተው ይሉ ነበር።  አንድ የትምህርት ጓደኛዬ በእንግሊዝኛ ጥሩ ከጻፈ በኋላ ቴሳረስ /መዝገበ ቃላት/ ይከፍትና አብዛኛውን ቃል በተመሳሣይ ቀይሮ ስለሚያከብደው ማንበብ ይቸግረን ነበር።   ይህን ሁሉ ያልኩት ቃል አጋኖና ምሁር አዋቂ በሉኝ ወደ ፖለቲካው መስክ ዘው ሲሉ ብዙ ችግርን ያስከትላሉ በሚል ለማቅረብ ነው።  ወር ታስሮ ማንዴላ መሆን፤ ወያኔ መጽሔቶችን ሳያፍን በፊት አንድ መጽሄት አንዱን የተቃዋሚ መሪ ጋንዲ፤ ኢየሱስና ማንዴላ ተዳምረው እነሱን ይመስላል ብሎም ጽፎ ነበር።  ልክ ማጣት፤ በህልም እህል ውቂያ። የዘመኑ ወጣት የሆነ ሲያደናግረኝ አንድ በእንሊዝኛ ችሎታው የሚያደንቀውን አስተማሪ ሲገልጽልኝ “ኤጭ እንኳን ሲል በእንግሊዝኛ ነው” ብሎኝ ለተወሰነ ጊዜ ኤጭ በእንግሊዝኛ ያለ መስሎኝ ቆይቼም ነበር።   ለነገሩ ቃል አጋኖን ለባልስልጣን አወዳሾች መተው ያለብን የጥራዝ ነጠቅነትና ቅጥረኛነት ምልክት ስለሆነም ነው።   ይህን ለምን አሁን ለመጻፍ እንደተነሳሳሁ ለብዙዎች ምስጢር የሚሆን አይደለምና አልፈዋለሁ።   በልክ ወገኖች!

“ሰላም ነው ይሉናል መፍትሔ መንገዱ፣
ይሉናል አይጠቅምም ጠመንጃ ማንሳቱ፣
ሰላማዊ ሆነን አቤት ብንላቸው፣
ለኃይለኛ ቆመው ላይቀር ማፌዛቸው፣”

ተወደደም ተጠላም ከ 40 ዓመታት በላይ በትግል መስክ ቆይተናል።   ወደዱም ጠሉም በሀገራችን የመጀመሪያ ዘመናዊ ፓርቲ ሊባል የሚገባውን ድርጅት መስርተንም፤ ሕዝብ አደራጅተንም  ስርዓት ለዋጭ ትግልን ለማካሄድ ችለናል።  በአቅም ማነስ የተነሳ የታጠ    ቀ የጭቆና ሀይል የሕዝብ ድል ቢነጥቅም ይህንንም በከተሞችም ሆነ በዱር በገደሉ ዓመታት ታግለነዋል። በትምክህት ላይ አተኩረን  ጥበትን ቸል ያልነው ቢመስልም ወያኔን ከተመሰረተ ጀምሮና የግንጠላ ሀይሎችንም ችግር በሰላምና ዴሞክራሲ ተፈቶ ግንጠላ እንዲቀር ስንታገል ግንባር ቀደም ሆነን ቆይተናል።   ወደ ኋላ መለስ ብለን ተመክሮአችንን ስናይና ያለፍነውን ውጣ ውረድ ስናጤን ዛሬ በቀል የፖለቲካ እንክርዳዶች ያን ሁሉ ትግል ሊስያክቸለችሉ ሲነሱና በሰማዕት ላይ ሊሳለቁ ሲቃጡ ለመናደድ ጊዜ ባይኖረንም ከመታዘብ ግን ወደ ኋላ አላልንም።  ወያኔ በከተማው ጭራሽ በሀገሩ/እኛ ስንታገል እነማን ነበሩ?ንም አሰምተናል።   የውጩ ብቻ ሳይሆን የራሳችንም ጠማማ ስለጎዳን ይህንንም አስፍረን ነበር፤

“ያ ቅዱስ  ዓላማ ስንቱን ያሰለፈ፣
ያ ግዙፍ ቤታችን ስንቱን ያስጠለለ፣
እንዳልነበር ሆኖ ዛሬ ተወገዘ፣
የጠላቱስ ይሁን የቤተኛው ባሰ።”

በትግል ስንሰማራ ከምር እንጂ ከቀልድ ስላልነበረም መገደል መግደል ትግላችንን አጅቦታል።   እንደ ዘንድሮቹ ዘመናዊና ስልጡን ፋኖዎች ቦምብ ወርውረን ማንም ሳይጎዳ፤ ውጊያ ገብተን ከጠላትም ከእኛም ሁሌም ማንም ሳይሞት የምንወጣበትን ዘዴ እንኳን ያኔ አሁንም አናውቀውም። በሳይንሳዊ ስልት ተዋግተን ከእኛም ከጠላትም ማን ሳይሞት አሸናፊ ሆንን የሚሉት ትርጉም አልባ ከመሆኑ ባሻገር የሀገር ጉዳይ ባይሆን ኖሮ ያስቀንም ነበር።  ትግል ሞትን መስዋዕትነትን ይጠይቃል።   ድርጅት በተለይም ሠራዊት ጠበቅ ያለ የስነ ስርዓት ህጎች ስላሉትም እነዚህን መጣስ ያስቀጣል።   ጥቂት ቢሆኑም በዚህ መልክ የተቀጡ አሉ።  ጠላትን ተኩሰን ወዘተ ስንገድል እኛም መስዋዕትነትን  ከፍለናል።   መስዋዕትነትን የማይጠይቅ ትግል የእነ የቁጭ ፋኖዎች ቧልት እንጂ ካለው ሁኔታ ጋር የሚገናኝ አይደለም።   ታግለን ስንሰዋ አስጨረሱ አለቁ ንግግር የተሳሳተ ነው፤ ማንም ሳይሰዋ ሚካሄድ ትግል አልታየም በዓለም ደረጃ።  ይህን በተመለከተ በ1992 ዓ.ም ስንተች፤

“ሓኪም ተትረፍርፎ በሽተኛ አልድን አለ፣
ጠንቋይ በህገር ሞልቶ ክታብ ረከሰ፣
ፈላስፋ የትግል ፕሮፌሰር በዝቶ፣
የፋኖን የተኳሽ ድራሹን አጥፍቶ።”

ብለን ነበር።

ኢሕአፓን በዚህም በዚያም ሊተቹ የሚነሱ ክፍሎች ቀደምም ከደርጉ ጋር አብሮ ወንጀለኛ አሁንም ወያኔ ወይም የወያኔ ቡችሎች ካልሆኑ በቀር ነጻ ሊባሉ የሚችሉ ተቺዎች ብዙውን ጊዜ ትችታቸው መሰረት ቢስ የሚሆነው ታሪክን ስለማያውቁ መሆኑ መጠቀስም ያለበት ነው።   ለፈረንጅ ዲፕሎምና ዲግሪ ምርምር ሲያደርጉ የሀገራቸውን ታሪክ በሚመለከት በግልቡ መናገርና መጻፍ እየቀናቸው ችግር ፈጥሯል።  ሀቅ ፍለጋ ጊዜ አያጠፉም።  ውግዘት ለመደርደር ግን ይፈጥናሉ።   ምስጢር ያልነበረውን ታላቅ ግኝት ምስጢር ሊሉንም ይቃጣሉ።   ኢሕአፓ ግራ ክንፍና ሶሻሊስት ነበር ይላሉ።  እንዴታ! ለሰው በላ ሥርዓት ደማችንን አላፈሰስንም።   ምሕረት አልባ ካፒታሊዝም ለፈለጉ ወያኔም አለላቸው።  ቅይጥ ኤኮኖሚ ብለን የያዝነውን አቅዋም ያጤኗል ከትችት በፊት ማለት ነው።   ለሠርቶ አደሩ ሕዝብ ጥቅም በቅድሚያ ታግለናል–አሁንም አቅዋማችን ይህ ነው። ለውጥ ስንልም ለሕዝብ እንጂ ለጥቂት ከበርቴዎች ምቾት አልነበረም፤ አይደለም፤ አይሆንምም። በከተማም ተታኩሰናል – አሁንም ከተመክሮ ተምረን በጥንቃቄ ልንወስደው የሚገባ እርምጃ ነው። ለምናምንበት ታግለን ተሰውተን ለሀገር ቆመናል–እስቲ ተቺዎች ስለ ትግል ወሬውን አቁመው ለሀገር በትግል ሲሰዉላት ለማየት ያብቃን።

“ሞትን ምን አመጣው ከድል ሽንፈት ጋራ፣
ሞቶም ያቸንፋል ያለው ክቡር ዓላማ።”

ትግል የኳስ ጨዋታ አይደለም።  ሽንፈት ድል በገባው ጎል ልክ የሚመዘን የሚወሰን።   ትግል ድልን አከማችቶ የመጨረሻ ድሉን ሊቀዳጅ ዓመታት ሊፈጅበት ይችላል።   በህብረተሰቡ ዘንድ በድርጅት፤ በንቃት ወዘተ የሚታዩ እመርታዎች  የትግል ውጤት ናቸው።  ወያኔ ተፈናጦ ሁሌም ሊገዛ አለመቻሉ የሕዝብ ትግል ውጤት ነው።  ለመጨረሻው ድል የተጀመረም ግብግብ ነው።  ለዚህም ነው በደፈናው ሕዝብ ድርጅት ተሸነፈና አልፎም ለመቸነፍ መሰዋት ምን አስፈለገ የሚል የመሃይምና ቡከኖች ትችት ሳይጥመን የቆየው። ሌላ የሚነሳው የመከፋፈል ጉዳይ ነው።  ድርጅት የሀገር ቅራኔ ነጸብራቅ ነው፤ ያለው ቅራኔ የሚወልደው ነው።   በሌላ በኩል ደግሞ በውስጡ የህብረተሰቡ ቅራኔ ይንጸባረቃል።   ለሠርቶ አደሩ ሕዝብ ጸንተው የቆሙ እንደሚኖሩት ሁሉ ወልመጥ ዘልመጥ ንዑስ ከበርቴያዊ መዋዥቅ የሚያጠቃችውም ይኖራሉ። ቢያሳዝንም ጎጠኞችም ጥልቅ ብለው ከጎጣቸው አልፎ ለሀገር መቆም አቅቷቸው ድርጅቱን ያዳክማሉ። ባለው ቅራኔ የተነሳም ክፍፍል መምጣቱ፤ ግጭት መፈጠሩም መጠበቅ ያለበት ነው። አባላቱ የሚቆሙለት መደብ ጥቅም እርስ በርሱ የተቃረነ ሊሆን ይችላልና። አንዳንዶች ይህን ያልተረዱ ድርጅት ውስጥ ክፍፍል ሲመጣ  ድርጅቱም ማውገዝና መንቀፍ ይቀናቸዋል። ዛሬ ተደራጀን ብለው በጎጥ 17 የሆኑና ክፍፍላቸው መረን ለቆ ሀገር አጥፊን ሻለቃ አስታራቂ ብለው እስከመማጠን የደረሱ ያኔ በየካቲት ኢሕአፓና መኢሶን ሳይሳማሙ ቀሩ ብለው ሲያወግዙ ተደምጠዋል።  ይሉኝታ ማጣት። ሁለቱ ድርጅቶች የተለያዩት በፖለቲካ አቅዋም ልዩነት ሲሆን ምናልባትም በቅራኔ አያያዝ ሊወቀሱ የሚችሉ ቢሆንም ሊስማሙ የሚችሉበት ሁኔታ በተጨባጭ አልነበረም። በኢሕአፓ ውስጥ የመጀመሪያው አንጃ በከተማ የተፈጠረው እንዲሁ ከደርግ ስር ሆነን እንስራ ወይስ ጸረ ደርጉ ትግል ይቀጥል በሚል ልዩነት ሲሆን የብዙሃኑን ውሳኔ የረገጡ ክፍሎች ወደ አንጃነት አምርተው ብዙ ጉዳት በድርጅቱ ላይ ሊደርስ ቻለ። በቅንጅትም በህብረትም በ1997 ና በኋላም የተፈጠረው ልዩነት ለወያኔ ጥቃት ህብረቶቹንና የሕዝብን ትግል ሰለባ ማድረጉ የሚካድ ባይሆንም ለክፍፍሉ ምክንያት ነበረው። ከባለነፍጦችና ገዢዎች ጋር ማበር፤ መጎንበስ፤ ሰላም በሚል ጭንብል እጅ መስጠትን መስበክና የመጣ ቢመጣ አሻፈረኝ ብሎ ለሀገር ለሕዝብ መታገል የሚታረቁ አማራጮች አይደሉም። በጎጥ የሚደራጅ አንጃ ፍጹም በኢሕአፓ ውስጥ ሊተነፍስ የሚፈቀድለት አይሆንም። በህብረተሰቡ ውስጥ አድርባይነትና ጨለምተኝነት– ሽንፈት ጊዜውን እየጠበቀ ማገርሸቱ የማይቀር ነው።   አሁንም የምናየው ነው።   በታሪክ ማጠፊያዎች፤ በተለይም ገዢዎች ሊንኮታኮቱና ሊወድቁ አፋፍ ሲደርሱ የአድርባይነት ከበሮ በሰፊው ይደለቃል።  እንብላ ባዮች የሕዝብን አመጽ በማስቆም ከገዢዎች ሊደራደሩና ሊሞዳሞዱ አንገት ቀና ይላሉ።  በተመክሮአችን ደግመን ደጋግመን ያየነው ቢሆንም ከሾህ ወጥቶ ጋሬጣን የሚመርጡ አሁንም አሉ።   ከባሕር ወጥተው ጤዛ የሚልሱ።

“ሁሉ ሀገር ወዳድ ሁሉ ሀገር ጥሎ፣
ሁሉ አዋጊ ሆኖ ተዋጊ ሟች ጠፍቶ፣
ቃልቻው በዛና ስልቻ ያዥ ጠፍቶ፣
ቆራርጦ ጨረሰን እሬት አልባ ኮሶ።”

ማንው ሀገር ወዳድ? የሀገርስ ትርጉም ምንድነው? ማነው ኢትዮጵያዊ ብሎ በተማሪነቱ ጊዜ የገጠመው ሰው ዛሬ ከሮና በሽቅጦ የሚገኝ የግንጠላ አቀንቃኝ አዛውንት ሆኗል። በኢትዮጵያዊነት ላይ እንደራደር የሚሉና አሁንም እንደ ኦነጉ ፍሬው መዓሾ  (ዳውድ ኢብሳ) ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚሉም አልጠፉም። በኢትዮጵያ ጭቆና ነበርና አብረን ለመኖር ዴሞክራሲን አስፍነን ለመቀጠል እንስማማ ማለት ተገቢና የሚደገፍም ነው።  ግን በታሪክም ኢትዮጵያዊ አልነበርንምና ሀገሪቱን ጥለን ተገንጥለን ሌላ ሀገር (ኢያ፤ ኢያ ወዘተ) እንሁን ማለቱ ግን ስህተትና ሁሉን ጎጂ ግንጠላ ነው።   ግንጠላ ደግሞ ምንም የማይጠቅም የብሔርተኞች፤ የንዑስ ከበርቴዎች ጫጫታ መሆኑን፤ ለባዕድ የሚጠቅም ምርጫ መሆኑን በኤርትራም በደቡብ ሱዳንም ሁኔታ የምናየው ነው።   ወደ ጥፋት ጎዳና አመሩ እንጂ የት ደረሱ? ከመገንጠል በመለስ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለውን ጉዳይ አክርረውና ተገንጥለው ለሕዝባቸው መፈየድ ሳይሆን የባሰ መከራን እንዳመጡ የምናየው ነው።  ይህን ምርጫ ውድቅ የሚያደርገው የነሱም ምሳሌ ነው።  ቁምነገሩ የራስ ባንዲራ መያዝ በነበር ስንቱ ነጻ ወጣ የተባለ የአፍሪካ ሀገር እውነትም ለህዝቡ ጠቃሚና ነጻ ሆኖ በተገኘ ነበር።  ደርግ ለገንጣዮች አመቻችቶን ከፈረጠጠ፤ ከተሸነፈ በኋላ ወያኔ ኢትዮጵያን ሲያጠቃ ለመከላከል አለመቻላችን የታየ ነው።  ቃልቻው በዝቶና ሁሉም እጅ መስጠትን ሰብኮ ሊታገሉ የጣሩትን አጋልጦ ማስጠቃቱ ደግሞ ግልጽ የሆነ ነው።  በአጼው ጊዜ ትጥቅ ትግል ስንል የጊዜው ባንዳዎች ጠመንጃ ነካሽ ይሉን ነበር።   የወያኔ ጀሌዎች ደግሞ ብረት ስናነሳ ደም የጠማቸው፤ መላ ያቃታቸው ሲሉ ተሳልቀውብናል። ከሀያ በላይ ዓመታት ፈጅተው ሁለገብ ትግል ነው መፍትሔው እንዳሉ ስናይ ትጥቅ ትግል ይሉ የነበሩ ደግሞ ተገልብጠው ሰላማዊ ትግል እንጂ ሌላ አይታሰብ ሲሉንም አድምጠናል።  በኢትዮጵያችን፤

“የሥልጣን ባለቤት የዙፋን ተቀማጭ፣
የሰው ሥጋ በይ በሰው ደም ተጉመጥማጭ፣”

ነውና እባብን በእንጭጩ ብንል ብዙ ሰሚ አላገኘንም።  ወያኔም ጊዜ አግኝቶ ተደላደለብን።  የተከሰተውን፤ የኖርነውን መከራ፤ ስቃይና ውርደት ሁሉም ያውቀዋል።

“ለገዛ ሀገሩ ሙቱልኝ የሚለው፣
ከትግል ርቆ ጦር የሚሰብቀው፣
የዘንድሮ ሀበሻ ሁሉን አበላሸው፣
ለጊዜ ለራሱ ጊዜን እየሰጠው።”

ጊዜ እንስጥ ፖለቲካ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሲያደነቁረን የቆየ ነው።  በአጼው ጊዜ ዶክተር ፕሮፌሰር የተባሉ ሕዝብ ገና አልነቃም፤ ግዜ እንስጥ፤ ለእንዳልካቸው መኮንንም ጊዜ እንስጠው ብለው ሲለፍፉ ስንሰማ ቆይተናል።   ትግሉ የተካሄደው እነዚህን ለጨቋኝ ጊዜ እንስጥ ባዮችን ወግዱ በማለት ነው።  የታሪክ በራዦች–ያውም በትግሉ ያልነበሩ- ዛሬ ተገልብጠው እንዳልካቸውን ጊዜ ብንሰጥ ኖሮ ደርግ ባልመጣብንም ብለው ኢታሪካዊ ምኞትን ያስደምጡናል። ለመሆኑ ያኔ የት ነበሩ? ደርግ ባይመጣም ግን ጭቆናው ይቀጥል እንደነበር ማስታወስ ተስኗቸዋል።  ለደርግ ለራሱ ጊዜ ይሰጠው፤ ለመቃወም አንቸኩል ያሉን ሐሳዊዎች አሁንም ተመሳሳይ እየሰበኩ አሉ።  የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው –አውቁትም አላወቁትም።  ወያኔ ስልጣን ሲይዝም ይህንኑ “ጊዜ ይሰጣቸው ለልጆቹ” የሰበኩና ከወያኔ ጋር የተቃቀፉት ጥቂቶች አልነበሩም። ጊዜ የሚሰጠው ሲመረመር ለጭቆና መቀጠል፤ ለጨቋኞች መተንፈስና በያዙት መቆየትና መግፋት ነው።  እኛ በዚህ ሁሉ ሳንታለል ታግለናል።   ለሥልጣን የበቁትን ሀይሎች መሠረታዊ ይዘትና ጠባይ ስለማናውቅ–መቸም ቢሆን መቸ ስላልተደናገርን– ሳይደላደሉ መታገል–መጣል፤ ሁሌም መሰረት አሳጥቶ ማስወገድ በሚለው አምነን ታግለናል።  ይህ ያኮራናል–ለሆድ አልተቸነፍንም፤ መደንቆርን አላስተናገድንም።  ግባችን የሕዝብ በመሆኑና ሕዝባዊ መንግሥት ምስረታ በመሆኑም በሸንካላ ግማሽ ግብ ወይም ጥገና በማመን አልተጠቃንም።  ከጠዋቱ የተናገርነው ሀቅ ሆኖ ቆይቶ አሁንም ሀቅ ነው።

“ማዳመጥ ያልቻለ ጆሮው ላይ የተኛ፣
ዓይኑን ሆዱ ከቶ እውር ነኝ ያለማ፣
በዝቶ ተበራክቶ ሀገር ስለሞላ፣
ጊዜው አመቸለት ሀገር ለሚያጠፋ”።

በአሁኑ ጊዜ ለወያኔ አመችቶት የሕዝብንም አመጽ ሊያቀዘቅዝ የተነሳው ከታሪክ መማር ያቃተው፤ የታወረ በመብዛቱ መሆኑ ክርክርን የሚጋብዝ አይደለም። ወያኔ ሕዝብን ማደናገሪያ ክፍሎችና መምሪያዎች እንዳሉት ይታወቃል።  ለባድሜ ብሎ ስንቱን አታሎ እንዳስጨረሰው ነው።  ተዉ ገንጣይ ከጠባብ ይፋጅ እርስ በርስም ይዳከሙ ሲባል ለወያኔ ጫጫታ ጆሮ ተስጥቶ ስንቱ ተሰልፎ ውድ ሕይወቱን ገበረ? መላ ኤርትራን አስገንጥሎ እያለ ለባድሜ ሙቱልኝ ሲል ሰሚ አገኘ ማለት ነው።  በጦርነቱ በተፈጠረው አመቺ ሁኔታ ተጠቅሞ ወያኔን ማዳከምና ማስወገድ መሞከር ሲገባው አልተደረገም።  ከባዕድ ሀገር ተጫጭነው የተጓዙት ተላላዎች ሁሉ አንድም እንኳን የፖለቲካ እስረኛ ሊያስፈቱ ካለመቻላቸው ሌላ አቅዋማቸው ከሀቀኛ ሀገር ወዳድነት ጋር የተጻረረ መሆኑም ቢነገራቸው አልሰማም ብለው ነበር።   ማዳመጥ ያልቻሉ፤ የተደናገሩ፤ ወያኔ  የተጫወተባቸው።   ለሳሞራ ዩኒስ ሽልማት ሲሰጡ፤ ከወያኔ ጦር ጋር ሲተቃቀፉ ያየነውን አንረሳውም።  በዚህ ዝቅጠት ገብተው ወደዱም ጠሉም የወያኔ ሰሎጎች የሆኑት ጥፋታቸውን-ስህተታቸውን ግን አምነው አጠፋን ሲሉ አልሰማንም። ዛሬም ያን ስህተታቸውን አድሰውና አጅበው ብቅ ብለዋል እንጂ።  ወያኔን ይህን ተንኮሉን በየጊዜው ደጋግሞ፤ ጊዜን ገዝቶ ዕድሜውን ሊያራዝምብንም ችሏል።  በቅርቡ ያካሄደውና እያካሄደ ያለው ቲያትር ወይም አስቂኝ ድራማ ተመሳሳይ ነው።የሕዝብ ትግል ወያኔ ይውረድ፤ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት እውን ይሁን፤ ዘረኛው አገዛዝ ያክትም የሚል በመሆኑ ለውጥ ያደረገ አስመስሎ ሊቀርብ ባደረገው ጥናት ከነበሩት የሀይለማርያም ተኪዎች የተሻለና የሚያዋጣው አሁን ጠቅላይ ሚኒስቴር የተባለው ግለሰብ በመሆኑ ይህን ሰው በተመለከተ የሚያሻሽጡ ሀሰተኛ ክስተቶች ሀቅ ሆኑ ተብለው ተሰራጩ።  ይህን እጩ ወያኔዎች ጠልተውታል፤ ለውጥ ፈላጊ ነው፤ የሕዝብ ወገን ነው፤ አማራም ኦሮሞም፤ እስላምም ክርስቲያንም ነው ወዘተ ተባለና ልፈፋው ጦፈ።  ያመኑ ብዙዎች ነበሩ።  ሰውየው 27 ዓመት በትንሹ በወያኔ ጉያ ስር የቆየ፤ ሌፍተናንት ኮለኔል የሆነ፤ በአፋኝ የመረጃ ተቋሞች የሰራ፤ ስንቱ ኦሮሞ ሲገደል፤ ስንቱ ንጹህ ዜጋ ሲፈጅ ድምጹ ያልተሰማ ነው ቢባልም ጆሮአቸው ላይ ተኝተው መስማት የተሳናቸው ጥቂቶች አልነበሩም፤ አይደሉምም።   የጊዜ እንስጥ አባወራዎችም እንደገና ቀና ብለው ግዜ ይሰጠው እንጂ ብለው ሊወርዱብን ተጋበዙ።  ንቁ ፖለቲከኞች ነን ባዮች የባዕድ ሀገር ነዋሪ ዶክተሮችና የቀድሞ የደርግ ሰማያዊ ለባሽ የፓርቲ መሪዎችም አሁን ዋናው ጉዳይ ለግለሰቡ ስልጣን እንዲያገኝ/እንዲሰጠው ማድረግ ነው ብለውም መከሩ።  ግለሰቡ ለዚህ ቦታው የበቃው ምንም ስልጣን ሳይኖረውና ወያኔን ሳይጎረብጥ በታዘዘው የሚሰራ መሆኑ ተረጋግጦ መሆኑንም ስተዋል።

“በህዋ ብልጭታ በአጉል ሕልም አባዜ፣
የሰው ነፍስ ይለካል ባልተገራ ጊዜ።”

ባልተገራ ጊዜ ማለትም በዘመነ ወያኔ ሆድ ቀደመና፤ መደንቆር ተመረጠና ለወያኔ ሰለባ መሆኑ ተደጋገመ።  ተፋፍሞ የነበረውና ወያኔን ያንገዳገደው ትግል እነሆ ቀዝቀዝ ያለበት ሁኔታ እየታየ ነው።   አዋቂ ነን ባዮች ምሁሮች ተወናበዱና ተደናቆሩ እንጂ የትግል ዋናው ግብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ለመሆን ነው።   ሥልጣን ለማን፤ ሥልጣን ምን አይነት ነው የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ። በኢትዮጵያ አሁን ፍጹም ሥልጣንን ይዞ ያለው ወያኔ ነው። ተለጣፊዎች ትንፋሻቸው ሚፈቀደው ተለጣፊ ሆነው ተዋርደውና እዝ ተቀብለው እስከቆዩ ብቻ ነው። ይህ ሀቅ ያልመሰላቸው አሳዛኝ ሀቁን መረዳት ያቃታቸው ጉዶች ግን አሉ። ሀቅ ግን ሀዘን አዘል፤ ሞት አዘልና ቀዝቃዛ መርዶ መሆንም ትችላለች። ተስፋ አዘል ምኞትንም ትገድላለች። ምሁር ተብዬዎቹ ፤ በየድረገጹ እናስተምራችሁ ባዮቹ ሁሉ አንድም ሳይቀርና ማፈሪያ አንጃዎችና ባንዳዎች ለአዲሱ ተሿሚ ምክር ሊለግሱ፤ ክጀርባህ ቆመናል ሊሉና፤ ሥልጣን ያግኝ ሲሉና ወያኔ ነው ሰውየው ያልናቸውን ሁሉ ሊያወግዙ ተሽቀዳድመው ነበር። ሙባሸራው ፖለቲከኛም ከአዲሱ ሹም ጋር መገናኘትን የሚፈልጉትን ለመመዝገብም ተነስቶ ነበር –ጉድ አይሰማ ጆሮ። ወያኔ ግን የራሱ መሰሪ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነና ለሰውየው ትንሽም የማወናበጃ ጊዜ ሊሰጠው አልቻለም። መሰረቴ ያለው ትግራይ የወያኔ ልፈፋ ስላስደነገጠው የበላይነታችንን የሚያናጋ፤ የሚያጠቃን እንዴትስ ይሾማል ብሎ ማጉረምረም በመጀመሩ ውሎ ሳያድር ለማደናገር የታጨውን ያው የወያኔ ሎሌ መሆኑን ማጋለጥ ተገደዱና ከጀርባው ደብረጽዮን ቆሞ ተሿሚው የተሰናዳለትን ንግግር በትግርኛ አንቦ የትግራይን ሕዝብ ወርቅነት፤ የመለስን ታላቅነት፤ የወልቃይትን ችግር በውጭ ነዋሪዎች መቀሰቀስና ችግሩ የውሃና መብራት እጥረት መሆኑን፤ ወያኔ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ለትግራይ የተሰዉትን ለኢትዮጵያ ተሰዉ በሚል ቀጥፎ (እነ ተስፋዬና ኢሕአፓዎችን፤ የኢዲኅ አባላትን ሳይጠቀልል ሳይጠቅስ ማለት ነው ) ወዘተ ማቅረብ ተገደደ።  ሳይውል ሳያድር ተለጣፊና ጭምብላቸው መሆኑን አጋለጡት። ብዙዎች ራሳቸውን ሳያዋርዱ በፊት መሆኑ አሳዝኖኛል።   የተዋረዱት ደግሞ ያው ትቢያነታቸውን አስረግጠዋልና ዋጋቸውን ቢያገኙ በሕዝብ ዘንድ ተገቢ ይሆናል።  ለነሱ ያለን መልእክት፤

“መሬት ያራሰውን ያንን ደም የጀግና፣
መሬት ያቀላውን የእሱዋን ደም የጀግና፣
ጠቅጥቆ ያለፈ ምራቁን የተፋ፣
ታሪክን አዋራጅ ሀገር የሚያጠፋ”

የሚለው ነው።   አበራሽ በርታና የታገቱ ሴት ጀግናዎች ይፈቱ በማለት ፈንታ ለአላሙዲ መፈታት ጩሁለት የሚሉን የከንቱ ከንቱዎች ህሊና ቢሶች አሉ። ምሁሩ በጣም አሰቃቂና አሳፋሪ ፍጥረቶችን ይዞብናል። አውቅን ባዮች የነበሩት በእርያ ጭቃ መገላበጥ የለመደባቸው የወያኔው አዲስ ተብዬ ሰው ሲሾም የሕይወታችን የመጀመሪያ የደስታ ቀን ነው ሲሉንም ውርደት ቅሌት እያልን ሰምተናል።  ሰውየው በአምቦ አልፎ ቢያጓራም አንድም ተቃዋሚ ጋር በዚያ ሊገናኝ አልተፈቀደለትም። ከወያኔ ዕዝ ወጥቶ የሚሰራው፤ ከተጻፈለትም ውጪ የሚያነበው ወረቀት አይኖርም። የፖለቲካ ሰዎች በሚናገሩት ሳይሆን በድርጊታቸው መገመት እንዳለባቸው የኛ የፍየል ጭራ ምሁሮች ባይገባቸውም መለኪያው ድርጊት ነው። ሁለት ሳምንት ሳይሞላው ደግሞ ወያኔ የሾመውን ተለጣፊ አደባባይ አውጥቶ መጋዣችን ነው ብሎ ነግሮናል፤ ላላመኑትም አርድቷቸዋል። ስህተት የፈጸሙት ግን ከዚህ ቀደም ከታዘብነው ከሆነ ስህተት ፈጸምን ሳይሉ በዚያው ይቀጥላሉ። የዘንድሮ ምሁርና አጠፋሁ ላይገናኙ ተማምለዋል ማለትም ይቻላል።

“ታሪኩን የረሳ ቅርሱን የዘነጋ
የሞተለትንም  ያልሰጠ ምስጋና
ጠላት ይገዛዋል ባሪያ አርጎ ቀጥቅጦ
ማን ሊያዝንለት ይሆን እሱ ራሱን ጥሎ።”

ነጋ ጠባ ለወያኔ ቅጥፈት ሰለባ ሆነን ለመገዛት ዝግጁ ከሆንን ጥፋቱ በቅድሚያ የራሳችን ነው። የወያኔን ውጥረት ያመጣው አንድ ግለሰብ–ያውም ራሱ ወያኔ– ሳይሆን የሕዝብ ትግል ነው። ክንቱ ምሁሮች አንድን ግለሰብ–ያውም ወያኔ ወያኔ ለ27 ዓመት የሸተተን ሰው– ስርየት አምጪ ብለው ሊያቀርቡ የተነሱት በሕዝብ ከሃሊነት ላይ እምነት አጥተው የምርጦች ፖለቲካ አቀንቃኝ ስለሆኑ ነው። የረጩት ሽቶና ያጠኑት ከርቤ የወያኔ ወያኔ ጠረኑን አልሸፈነለትም።  በሀገራችን ኢትዮጵያ ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ ሰጪ ሕዝብ ነው።  አንድ መሪ፤ አንድ ደጃዝማች፤ አንድ ዶክተር፤ አንድ ምሁር አይደለም፤ሊሆንም አይችልም። ይህ የግለሰብ ወሳኝነት የማይሰፍንበትን ስርዓት እውን ለማድረግም ነው ትግላችን። ሀይልና ሥልጣን የሕዝብ ብቻ ነው። ሕዝብ ነው በትግሉ ስርዓቱን አስጨንቆ ከዚህ ያደረሰው። ተዋጋን መራን የሚሉት አስመሳይ ፋኖዎች ከምቾት ፎቴያቸው ተነስተው ጠመንጃ ያላነገቡ መሆናቸውን እናውቃለን። የሚታገለውና የሚደማው ማን እንደሆነም ለሕዝብ ምስጢር አይደለም። መፍትሔም የሚመጣው በህዝብ ትግል፤ በወያኔ መውደቅና በዴሞክራሲ እንጂ ወያኔ በሚሾምልን ቡችላ አማካይነት ሊሆን አለመቻሉን መገንዘብም የግድ ነው።   ቡችላማ ሁሌም የሚጮኸው ለጌታው እኮ ነው።  የፖለቲካ ሥልጣን አሁንም በወያኔ እጅ ነውና ይህን ሥልጣን ከወያኔ መቀማት ነው ዋናው ግዳጃችን። ነውናም በወያኔ ቅጥረኞች ልንዘናጋም ሆነ ትግላችንን ልናቀዘቅዝ ከቶምና መቸም መፍቀድ የለብንም።

ችግራችን ስናጤንና ስንገመግም የራስችንን ጥፋት ቁልጭ ብሎ የምናየው ነው። የሰጎን ፖለቲካና ግምገማ አይጠቅመንም። ጥፋታችን አንድም የቃለ አጋኖ ፖለቲካ ሲሆን በሌላው በኩልም የሐረር ሰዎች እንደሚሉት አታቱሌ ቡቄ ነው።  ቢሆንም ቅሉ።

“ስንቱን የገደሉ ስንቱን ሰው የፈጁ፣
ዛሬ ተዘክረው ባገር ሲቀበሩ፣
ለፍትህ ለሀገር የሞቱት ተረስተው፣
ዛሬም እንደትላንት በዝምታ ታልፈው፣
ስለትግል ወሬ ስለ ጦርም ወሬ፣
ስለ ህብረት ወሬ ስለ ወኔም ወሬ፣
ስለትግል ወሬ ስለ ሀገር ወሬ፣
ወሬ በወሬ ላይ ሁሉ ሁሌም ወሬ፣
ሚስራ ጠፋና ቀረን አለፍሬ።”

ዜጎች ባንዳና አርበኛው ያለውን ልዩነት ስተው ድብልቅልቅ ካለባችው የሚከተለው ጉዳት በጣም ከፍተኛና ሀገርን አጥፊ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።  ጸረ ወያኔ ትግላችን ለረጅም ዓመታት ደብዝዞ የቆየው አንድም ወያኔ ሕዝብን ከፋፍሎና ምሁሩንም በዚሁ ቃኝቶ ስላዳከመው ከመሆኑ በላይ ትግሉ የሚጠይቀውን እንቅስቃሴና ህብረት እውን ለማድረግ እንቅፋት የሆኑ ክፍሎች በዝተው ስለ ትግል ወሬ ከትግሉ ግን ሁዳዴ/ረመዳን ስለሰፈነ ነው። ዓይኑን ከፍቶ የታወረው የበዛ ይመስል ወያኔን ራሱን ሳይቀር ጊዜ ለመስጠትና ለማለፍ የተዘጋጁ በዝተው ነበር።  እነ እንድርያስና ፕሮፌሰር መስፍንን አጅበውም ስለ መለስ ብልህነት አድምጡን ያሉ ጥቂቶች አልነበሩም።   ወያኔ እነ ኢሕአፓን ከሱዳንና ሻዕቢያ ጋር ጠቅጥቆና ገድሎ ለስልጣን ሲበቃም፤ ሀገር ወዳድ ሀይሎች በየትኛውም ሀገርን በሚመለከት ጉባኤ እንዳይገኙ ሲያግድ፤ የራሱን ጦር የሽግግሩ ጦር ሲያደርግና በነሌንጮ ሲደገፍ፤ ኤርትራን ሲያስገነጥል ተንፈሽ ብለው መቃወም የደፈሩት ፕሮፌሰር አሥራት ብቻ እንደነበሩ ታሪክ መዝግቧል።  ከየጎራው የጎጥ ድርጅቶችና ስብስብ ነን ባዮች ፈልተው ወያኔን በክፍፍል ተልዕኮውና በጸረ አማራ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻው አጀቡት። ዛሬ ተቃዋሚ በሉን የሚሉት ያኔ ከወያኔ ጎን ሆነው ሲያረጠርጡም ታዝበናል።  የመቀሌ ምልምሎችም ተገልብጠው አክራሪ አማር በሉን እያሉን ክፍፍልን በስልት ሊያሰፍኑ እየጣሩ ናቸው።

“ማዳመጥ ያልቻለ ጆሮው ላይ የተኛ፣
ዓይኑን ሆዱ ከቶ እውር ነኝ ያለማ፣
በዝቶ ተበራክቶ ሀገር ስለሞላ፣
ጊዜው አመቸለት ሀገር ለሚያጠፋ።”

በሚል በበኩላችን የተቸነው ከያኔው መሆኑ ይታወሳል።

ምሁሩን ምን ነካው በሚያሰኝም ደረጃ ለወያኔ የክፍፍልና ዘረኛ ፖለቲካ ምሁሩ ሰለባ ሆነ። የትግራይ ምሁሮች በተለይ ተጠቃለው ወደ ወያኔ ገቡ ሊያሰኝም የሚችል ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር የሚታወስ ነው። የትግራይን ሕዝብ በጥቅሉ ወያኔ  ማለቱ በየፈርጁ ሲታይ ስህተት ነው ብለን ልንመክር የሞከርነውም ራሳችሁ ትግሬም-ሐማሴንም ናችሁ የሚል ትችት ከመቀበል በቀር የፈየድነው የለም። የትግራይ ምሁሮችም በብዛት ወይነው የሕዝብ ቅሬታ አተረፉ። የብሄር ድርጅቶች–በተለይም ጸረ አማራና ግንጠላ የሚሉት– ግባቸውን በወያኔ የሚያገኙ መስሏቸው በሰጡት ድጋፍም ወያኔ ጊዜ አግኝቶ ተጠናከረ።  የኦነግ መሪዎች በለንደን ጉባኤ ወያኔን እንዳያጅቡ ብናማክራቸውም (ጉዳዩ በወያኔ ሻዕቢያና ኮኸን መሃል አልቆ ነበርና) ሱዳን ተጭኖናል በሚል ለንደን ሄደው ሌንጮ ራሱ እንዳመነው የግድግዳ ዝንብ ሆነው ተመለሱ።  ለአዲስ አበባው ጉባኤ ሲሰናዱም ኢዴኅቅ-ኢሕአፓ በጉባኤው እንዲገኙ ጠይቁ ቢባል ድምጽን ሳያሰሙ(አንዱ መሪ እንደነገረኝ ከሆነ ወያኔና ሻዕቢያን ፈርተው) ያው የበላይነቱን ለወያኔ ለግሰው ፋይዳ ቢስ ሚናቸውን ታቅፈው ብዙም ሳይፈጅ የመውጫ ቪዛ ተሰጥቷቸው በጊዜው የኤርትራ አምባሰደር በሀይሌ መርቆሪዎስ አቅራቢነት ሌንጮና ዲማ ነገዎ መለስ ዜናዊን ተሰናብተው ወደ ስደት አቀኑ። ወያኔ ብዙ ሺ ኦነጎችን አስሮ እያለ። የተቃውሞ ማዕክል ሆኖ ታሪክ የጻፈው ዩኒቨርስቲ ሁሉ በዘረኞች ተከፋፍሎ እርስ በርስ በጎሪጥ እየተያየ ተለያይቶና በድን ሆኖ ከረመ።

“በዘር ዘርዝሮናል፣
በክልል ሸንሽኖ በጎጥ በትንኖናል፣
በቁም ሰንጥቆናል፣
ተሰንጥቀን አይተን ህብረት ተስኖናል፣
ጎጠኛው መርዞን እሱኑ መስለናል፣
መስፋቱ አቅቶን ጭራሹን ጠበናል።”

ለዚህ ጆሮ የሰጡ ባለመኖራቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወያኔ ከፋፍሎና በድን አድርጎ ጨፍሮብናል፤ ደም አስተፍቶ ገዝቶናል። ይህ የማንክደው ሀቅ ነው።  ኢአግ ብለን በሱዳን በኩል ትጥቅ ትግል ስንጀመር ትጥቅ ትግል ይጀመር እንጂ ቤታችንን ሸጠን እንረዳለን ያሉት ሁሉም መረጃ የለም ብለው ተሰወሩ።  ትግል አፍራሾች ደግሞ ትግሉ የእኛ ነው ብለው ማደናገርን ጀመሩ-ዛሬም የሕዝብ ትግል የእኛ ማለቱ ወልፋቸው አለ።  የሚያሳዝነው ዛሬም በከሸፈ ቅዠታቸው እየቀጠሉ፤ ክፍፍልን የሚሰብኩ አሶሳ በደኖን ቀፍቃፊ መኖራቸው ነው።  ከሕዝብ ቁጥር አንጻር አማራና ኦሮሞ ብዙ ናቸው ይባላል።ከዚህም ከዚያም ተደባልቀው የተወለዱ ዜጎችን ቁጥር የሚናገር ጠፍቷል። ኢትዮጵያ የሚለውን ማጥፋት ስለሆነ የወያኔ ተልዕኮ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰጠው ትርጉም ጎጥና ብሄር ነው። የድብልቆች ኢትዮጵያውያን ቀን መች ይመጣ ይሆን? በይፋ

“ደምቢዶሎ እናቴ አባቴ ከሸዋ፣
አጎቴ ከወሎ አያቴ ከአድዋ፣
ነፍሴ ኢትዮጵያ ሆነች ቅርጫ መሆን ትታ፣
ተጣልታ ከመለስ ከነ ሌንጮ ለታ”

ባልነው መንፈስ ማለት ነው። ሕብረ ብሄር ይዘታችን ጸጋችን መሆኑን ወያኔ ክዶ ሊያሳምነን የጣረው ሙሉ በሙሉ  ውድቅ ነበር ማለት አንችልም። ወያኔ የክፍፍል ፖለቲካው ከሽፎ ሕዝብ እያበረና እያመጸበት ሲመጣ ከዚህ ከዚያ  ከትቢያው ከጭቃው ቆሻሻዎችን ሰብስቦ ማሰማራቱ ደግሞ ምስጢር አይደለም። የሚደንቀው በሬ ወለደ ብቻ ሳይሆን፤ ወልዶም ወተት ሰጠ የሚሉ ቅጥረኞቹን ማሰማራቱ ነው። ቀደም ጽፌ እንደነበረው ኢሕአፓ ለሕዝብ መብት ቆርጦ ሲታገልና ሲያታግል የብሔር ነን ያሉት ቡድኖች ደርግ መጣልን ብለው ደርግንም፤ ወያኔን መጣልን ብለው ወያኔንም ደግፈዋል። ስለዚህ ድርጅቱን ለመተቸት የሞራል ብቃት ከቶም የላቸውም።  እነ አቦ እገሌ በየፊናቸው የቀይ ሽብር አራማጆች መሆናቸውን የምናውቀው ነው።  ደርግ ወጣቱን–የጎንደርን ወጣት ለምሳሌ–ሲጨፈጭፍ ከመላኩ ተፈራ ጎን ቆሞ በወንጀል ሲካፈል የነበር ዛሬ የሆነ አማራ ቡድን መሪ ነኝ ብሎ ኢሕአፓን በጸረ አማራነት ሊከስ ደጋግሞ ሞክሯል።   የደርግ ታዛዥ ሆነው ያገለገሉትም ስደት ለወሬ ያመቻል ነውና ሳያፍሩ ሁሉን ክደው ለሕዝብ ስንቆም ድርጅቱ ግን ኢትዮጵያን ሊጎዳ ተነሳ ሲሉም ሰምተናል።   ክርክራቸው ያው ሀሰትን መሰረት ያደረገ ሲሆን አዲስነት ደግሞ ባዳ ሆኖበት ደርጉ ያለውን፤ ወያኔ የደገመውን መድገም ዕጣ ክፍላቸው ሆኗል።  ኤርትራን አስገነጠለ፤ የብሄር ጥያቄ ያነሳው እርሱ ነው፤  ዚያድ ባሬን ደገፈ፤ ወዘተ ብሎ ያን የሀገር ጀግና – -ወሬ መፍተል ሳይሆን ለአመነበት ሕይወቱን የሰጠውን ዋለልኝ መኮንንና እሱን የመሰሉትን– ማውገዙን ቀጥለውብታል።  ታሪክ አበላሾችቹ ጭንቀታቸው የኢሕአፓ ሰማዕት ያሳዩትን ቆራጥነት ዛሬ ማሳየት ተስኗቸው ስለሚጋለጡ ነው።   የድርጅት ምስጢርን ላለማውጣት መርዝ ውጠው፤ ከፎቅ ተወርውረው፤ ግብረ ስየልን ችለው፤ ሌሎችን ለማዳን ሲሉ ተሰውተው ምሳሌ የሚሆኑ ዛሬ ተፈልገው በስፋት የሚገኙ አልሆኑም ። ያኔ ጀግኞቹ ታሪክ ጽፈው ሲያልፉ፣ ዛሬ ተቺዎቻቸው:

“በሀገር ሁሉ ብዞር ዝምታው ጮኸብኝ፤
ሁሉ አንገት ደፍቶ ሁሉ አቆዝሞብኝ፣
የሚያሰኙ ሆነዋል። አሊያም ደግሞ፤
“ተስፋን ለመቃብር መዳረግ ተለምዶ፣
የጸሓይ ብርሃን ሳይሆን ጨለማ ተመርጦ፣
ለዓላማ መቆምም ከጅል አስፈርጆ፣
ይመረት ገባልን ሬት ከንብ ቀፎ።”

የኢሕአፓ ጠላቶች የበረከቱት ከላይ አንዳስቀመጥነው የወያኔ ቅጥረኞችና ወንጀለኞች ስለተነሱበት ብቻ ሳይሆን አቅዋሙም ጠላትን ስላበረከተበት ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ብሎ በመጽናቱ፤ ለአንድነት በመቆሙ፤ ለጨቋኝ ድለላ ተገዢ አለመሆኑ ሁሌም ጥቃትን አምጥቶበታል። ኢትዮጵያን አሳልፎ ቢሰጥ ገዢዎችም ሆኑ የውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ወዳጅ ብለው ይደግፉት ነበር። ደጋግመን ያልነው ነው። ኢሕአፓ ሆነን ስንታገል ስለ ጨቋኝ አገዛዞች፤ ስለ ቃላት ድርደራና አሳሳች ፕሮፕጋንዳ ብዙ ትምህርት ቀስመናል። በስደት ትንሽ ዓመታት የነበርንበት አልጄሪያ የሚባል ሀገር ራሱን ሶሻሊስት ብሎ ያቀረበ የአረብ ዘረኛ በመፈንቅለ መንግሥት የመጣ የወታደር አገዛዝ ነበር። ይህን ግን ከጋዜጦቹና ከመሪዎቹ ዲስኩር ማወቅ የሚቻል አልነበረም። አስከፊ የሴቶች ጭቆና ሰፍኖ በማርች 8 የዓለም ሴቶች ቀን አልጄርስ ከተማ ስለ ሴቶች ነጻነትና እኩልነት በሚያቀርቡ የግራ መፈክሮች አሸብርቃ ትገኝ ነበር።  ከሩቅ ስትታይና አልጄሪያ ሲኖርባት ሰማይና መሬት የተቃረነች ሀገር ነበረች። የኬንያ የቀድሞ መሪ አፍ አውጥቶ ጉቦ ስጡኝ ባይ እንደነበረው ሁሉ በአልጄርስ ስደት የማውቀው የደቡብ አፍሪካ መሪ የነበረው ጃኮብ ዙማ ከመውረዱ በፊት ያሳየው ጠባይ ለእኔ አዲስ አልነበረም። ደርግ ወደ አምባገነንነት ማምራቱ ብዙም ምስጢር ስላልነበር በጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ይተካ ስንል ፕሮፌርሰር መስፍን ግን ለሲቪል ሥልጣን እንዳትለቁ ብለው ይመክሯቸው ነበር።  ወያኔም ዴሞክራሲ ስላለ የምናውቀው እባብ ርግብ ሊወልድ ነው ብለን ራሳችንንም ሕዝብንም አላሞኘንም– ሳይጠነክር ጊዜ ሳይገዛ እንምታው ነበር ያልነው። ዛሬ የወያኔ የረጅም ጊዜ ተለጣፊ ድንገት የለውጥ ሀዋርያ ሆነን መቀበል ማመን ቢያዳግተን ልንወቀስ አይገባም። በትግሉ ወቅትማ በበኩሌ ላገኛቸው የቻልኳቸው የሀገር መሪዎችም ከሩቁ በጋዜጣ የሚባልላቸው ጋር ግንኙነታቸው ተፈልጎም የሚገኝ ሳይሆን ራሳቸውን ለትዝብት የሚዳርጉ ነበሩ። የቻይናን ብሄርተኛነት ያወቅነው ገና ከነሱ ጋር ግንኙነት ሲኖረን ነው።
በዚህ መልክ አቅርቤውም ነበርን፤

“ቻይናም ሄጄ ነበር የክብር እንግዳ፣
ቀድሞን አገኘሁት ያን የአኛኑ በሽታ
ሁሉን ሰው በክሎ መሆን ብሔርተኛ።”

ጭፍን የማኦ-ቻይና አምላኪ የነበሩት አሜሪካ የነበሩ አባሎቻችን ሊያወግዙኝ፤ ድርጅቱንም ቀጥለው ሊኮንኑ ብዙም ጊዜ አልጠበቁም።  የሰሜን ኮሪያ መሪዎች አሰቃቂ ተክለ ሰውነትማ መሳቂያችን ነበር። የፖለቲከኞችን ዲስኩር የማመን ልምድ የለኝም። በሕግ ፋኩልቲ ወይም ት/ቤት ስማር አሜሪካኖቹ የአጼው ህገ መንግስት እንዴት ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ ሊሽነግሉን ይሞክሩ ነበር–በተጨባጭ መብት ተነፍጎና ተሰጠ የተባለውም መብት በህጉ መሰረት በሚል አጉል ማሰሪያ ተሸብቦ። የተጻፈና የሚነገርን በጭፍኑ መቀበል ንቃት አልባ መሆን እንጂ የዛሬ የፖለቲካ አለሌዎች እንደሚሉት መሰልጠን ማወቅ አይደለም።  አንድ ወያኔ ተነስቶ ኢትዮጵያ ስላለ እውነትም ለሀገራችን ቆመ እንድል ከኔም ከኢሕአፓዎችም መጠበቅ የለበትም።  በተግባር መፈተን፤ ታሪኩን መመርመር የግድ ነው። አፉ ቅቤ ልቡ ጩቤ የተባለውን ሁሌም ማስታወስ ተገቢ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ባለኝ የትግል ተመክሮ ብዙ ሰው ከስህተቱ ይማራል፤ ለደግ ይለወጣል ብሎ ማመኑ ይከብደኛል። በተጨባጭ በብዛት ስላለየሁም ይሆናል። በውጊያ ማርከን የለቀቅናቸው ወታደሮች ተመልሰው ሊወጉን ሲመጡ ታዝበናል–ምክንያቱ የሆድ የደሞዝ ሊሆንም ይችላል። የጎዱንን በሂስ እናስተካክላለን ብለን፤ ብተና ያካሄዱብንን ይቅር ብለን እንደገና በድርጅት  ስናስገባቸውም (እኔና የተወሰንን አይገቡም ብንልም  ብዙሃኑ ይግቡ ስላሉ) ውለው አድረው አንጃነትን አቀንቅነው ሊጎዱን ከመነሳት አልፈው ይኸው በአሁኑ ጊዜ ወያኔን ደግፈው፣ እቀፈን በወንድ ልጅ አምላክ እያሉ ወያኔን በመማጠን ላይ ናቸው።  ሰውን ማመን በቀላሉ የሚሆን ከአለመሆኑ ሌላ 27 ዓመት በላይ ወያኔ የሆኑትንማ በአንድ ቀን አስመሳይ ዲስኩር የደማ ልባችንን ልንሰጣቸው መጠበቅ የለበትም።   ይሁን እንበል፤ ተሳስተናል እንበል፤ ሰውየው ከልቡም ከወያኔ ርቆና ተቃርኖ ለውጥ ይፈልጋል እንበል።  የሕዝብ አመጽ መቀጠሉ ሊጎዳው ሳይሆን ሊጠቅመው የሚችል ነው ማለት እንችላለን። በወያኔያዊ ኮረኮንች ከመጓዝ በሌላ መንገድ መጓዝ፤ የወርቅ ዜጋን ፖለቲካ መተውና የሕዝብን ፍቃድና ይሁንታ መሻት ይገባዋል ልንል እንችላለን። ጉዳዩ ግን ስለተሾመው ሳይሆን አሁንም ስለሿሚዎቹ፤ ስለ ወያኔ፤ ስለነሱ ቀጣይ ጸረ ሕዝብ፤ ጸረ ኢትዮጵያ መሆን፤ ስልጣኑን ጠቅልሎ መያዝ ነው።  ከማንም በላይ የያዝነው አቅዋም የተሳሳተ ሆኖ በሀገራችን ዴሞክራሲ ሰፍኖ እንዲገኝ የምንመኝ ነን። በስደት ያለነውም ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሀቀኛ ምስረታ ተካፋይ ታዛቢ ለመሆን ማንም የሚቀድመን ባልኖረ ነበር።

“በህልም የተጠጣ ያ የድሃ ቅቤ፣
አራሰኝ ያለ ሰው አጣሁኝ ፈልጌ።”  ሆኖብን እንጂ ተጨባጩ ሁኔታ።

“ያልቀበረ ያርዳ የተባለ ይመስል፣
ያልነበረ ያውራ የተባለ ይመስል፣
የነነበርን ወሬ ሀገሪቷን ሞላት፣
የነበረው ሳይሆን ያልነበረው በላት።”

በካምፓላ ዩጋንዳ ሳለሁ አንድ በወያኔ ማተሚያ ቤት ይሰራ የነበር የትግራይ ተወላጅ እንዴት እሱና ሌሎች ኢሕአፓን እንደመሰረቱ አስረድቶኝ ስም ዝርዝሮችንም ነግሮኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።  እሱን ጨምሮ አንዳቸውም ግን መሥራች አልነበሩም።  መስራች ነበርን ብለው ሚዋሹም በዝተዋል።  በዘመነ ወያኔ ኢሕአፓ ላይ የሚጻፉትን ውድቅ የምላቸው ሰናፍጭ እውነትን ይዘው ደጀን -ተራራ ውሸትን የሚገነቡ በመሆናቸው ነው። በትግሉ ነበርን፤ የተማሪ እንቅስቃሴ መሪ ነበርን፤ የኢሕአፓ ኮሚሳር ኮማንደር መሪ ነበርን፤ በየካቲት አብዮት ይህ ያ ሚና ነበረን— ቅጥፈት በኩንታል። ከዚህ በፊት ጽፌው ከሆነ አላውቅም ግን በመንግሥቱ ግድያ ሙከራ ላይ ነበርን ብለው በአሜሪካ የነገሩኝ ወደ ሰባት ደርሰዋል–አንዳቸውም ግን አልነበሩም።  በሙከራው የነበሩ፤ የተካፈሉና በህይወት ያሉት ግን ለሰኮንድም አፋቸውን ሲከፍቱ በበኩሌ አዳምጪ አላውቅም።  ይህን ሁሉ ያነሳሁት አንዳንዶች ውሸታቸው አልታመን ሲላቸው እኔው ራሴ በዚያ አልነበርኩም እንዴ ብለው መዋሸትን ስለተያያዙት ነው።  ከማፈሪያዎች አንዱ (ዛሬም ሹመኛውን ደግፎ ወንድሜ ከጀርባህ ነኝ ብሏል) ለምሳሌ ወደ ፖለቲካ ዘው ያልኩት በ1997ኡ ምርጫ ሰሞን ነው ከማለቱ ሳይውል ሳይድር በማያውቀው ኢሕአፓን መተቸት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል አያውቁም ብሎ ጽፎ ነበር።  ንቃቱና ፖለቲካው መቸ እንደጀመረ መናገሩ ምናልባትም ላያስወቅሰው ይችላል–ሌሎቹ ግን ሚናቸውን ደብቀው ሀሰት ታሪክ ያወሳሉ።  ለመሆኑ ዛሬ ከ17 በላይ አማራ የሚሉ ቡድኖች መስራቾችና አባሎች (ካሉ) እስካዛሬ የት ነበሩ? ብዙዎች የዛሬ አውራ ዶሮዎች በደርግ ጊዜስ ጫጩት ነበሩ ወይስ ምን? የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበረውና የሞተው ሳይቶቲ ምስክር ሁንልን ብለው ሲጠሩት የራሴን መስቀል ልሸከምበት አታስቸግሩኝ ብሎ እንደነበረው ሁሉ ኢሕአፓ በሰራው ሊወቀስም ዝግጁ ነውና ባልነበረበት ሀሰት ባይደረደርበት ይመረጣል። እኔንም ባልነበርኩበትም እየዶሉ ከመቀጥቀጥ ይልቅ በሰራሁበትና በተሰማራሁበት (በኢሕአፓነቴ የምኮራ ስለሆንኩ የምክደውም ስለሌለ) ብወቀስ ይሻላል ባይ ነኝ።   ከ40 ዓመት በላይ በጽናት ለእናት ሀገሩ ስለታገለ ድርጅቱ ሊመሰገን ሊደነቅ ሲገባ በዝሆን የቀኑ ዕንቁራሪቶች የያዙት የስም ማጥፋትና ውንጀላ ዘመቻ መወገዝ ያለበት ነው።   አሉባልታውን ሁሉ በተመለከተ ግን ያልነው የሚከተለውን ነው:

“የአሉባልታ ቡና አቦሉ ገዳይ ነው፣
በረካው ያ ስጋ ሶስተኛውም ደም ነው።”

በጥቅሉ የሰፈነው ሁኔታ ግን በዚህ መልክ ቀርቦ ነበር።

“ከባድ መስሎኝ እኔ ትግል የሚሉቱ፣
መስሎኝ የሚያስፈራ ዱር ጫካ መግባቱ፣
ወኔ ጠይቅ መስሎኝ ማመጽ መሸፈቱ፣
ሳይዋጉ ጀግና ሳይሸፍቱ ፋኖ የሚሆኑበቱ፣
መሆን ሚቻልበት ጠፍቶኝ ብልሃቱ፣
ስጨነቅ ከርሜ በራሴ አፍሬ፣
ምላሴም ታጥፎብኝ መናገርም ትቼ፣
ዶክተር-ፕሮፌሰር መጣና ፈወሰኝ፣
በባዶ መለፍለፍ ታጋዩን ማብጠልጠል መድሃኒቱ አለኝ።”

የለውጥ መንገድ ህብረትን ጠያቂ መሆኑ ይታወቃል።  ተደጋግሞም የተነገረ ነው። ኢሕአፓ እንደተመሰረተ የምዕራብ ሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ውስጥ የነበሩ የአርሲና ባሌ ተወላጆች በሼክ ሁሴን በመመራት ራሳቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኢብነአግ) ባሉበት ጊዜ የትብብርና ህብረትን ጉዳይ ድርጅቱ ከሼኩ ጋርና ኋላም በካይሮ ከነበሩት ተወካዮቻቸው ጋር ተነጋግሮ ነበር።   በሌሎች ጣልቃ ገብነት ሊሳካ አልቻለም።   ኋላም እንዲሁ ተቃርኖ ከነበረው ኢዲኅ ጋር ህብረትን በየጊዜው መስርቷል፤ ችግሮች ቢከሰቱም ጥረቶቹ ለትግል ጠቅመዋል ማለትም የሚቻል ነው። ደርግ ከመውደቁ በፊትም የተመሰረተው ኢዴኅቅ ሌላ ምሳሌ ነው።  ለሀገር ሲባል የግል ልዩነቶችና ቅራኔዎችን ወደ ጎን ማድረግ በሚለው መርህ መሰረት ጠላት ሆነውን ከቆዩት ከነመኢሶን፤ የመለስ ተቃዋሚ ነን ካሉ ወያኔን መስራቾች፤ ከደርጉ አንድ ኮለኒል  ጋር ግንባር መስርተናል። ይህ ግንባር በጊዜ ተመስርቶ ወያኔን እንዳይቁቋም የሕዝብ ወገን መስለው ግን ብቅጥረኛነት ያደናቀፉት እነ ኤፍሬም ይስሓቅና ሌሎችንም ጠቅሼ ማለፍ እውዳለሁ። ዛሬ ግን ሀገርን አስቀድሙና የወያኔን ሹም ደግፉ የሚለን ካለ ወይም የሚል ካለ ይሄ የሀገርን ጥቅም አስቀዳሚ ሳይሆን የሀገርን ምጸት አስቀጣይ ብቻ ነው። በ1997 በህብረት ተጠቃለንም በምርጫው ሂደት ባናምንም የብዙሃኑን ውሳኔ ተቀብለን፤ ቢያንስ ከ13 ድርጅቶች ጋር አብረን ታግለናል።  በየህብረቱ ስብስብ ኢሕአፓ የነበረው ድምጽ አንድ ቢሆንም ድርጅቱ ግንባሮቹን ተቆጣጠረ የሚል መሰረተ ቢስ ክስ ሲሰነዝርብንም ከርሟል። ህብረቱን ያፈረሱት መሪዎች የነበሩትና ዛሬ ከወያኔ ጉያ የሚገኙት መሆናቸውንም አልረሳንም።  ክሱ ሲበዛ ይሁንላችሁ በሚል ከግንባር ጥረቱም ስንሸሽ ይኸው እስከዛሬ ይህ ነው የሚባል፤ ጥርስ ያለው፤የሚፈይድ  ህብረት ሊቋቋም አልቻለም።  የህብረት ጥረት ራሱ የነ ኢሳያስና የኢምንቶች መጫወቻ መስክ ሆኖ ቀርቷል።ዛሬም ይህ ድክመት ካልተወገደና ለሀገር የሚበጅ ህብረት ካልተቋቋመ ድል የሚገኝ አይሆንም። ህብረት ስንል በሀገር ወዳድና ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶ መሀል የሚኖረውን ትብብር ሲጠቅስ በሌላ በኩል ደማችሁ ደማችን ነው የሚለውን የሕዝብ ተጨባጭ ሕብረት ያመላክታል። ወያኔ ህብረት እውን እንዳይሆን አሁንም ሕዝብን ለመከፋፈል ሰፊ ተንኮልን እያካሄደ ሲሆን በዚህም በዚያም የወያኔን እኩይ ዕላማ ከግቡ ለማድረስ ሰበር ሰካ የሚሉትን ደግሞ በትዝብት እያየናቸው ነው።

“የሀገር ጦር ይሉታል የጎጠኛን መንጋ፣
ሀገሬ ለሚላት ክልል አንድ በደማ፣
ያገር ጦር ይሉታል ዘረኛ የሆነውን፣
ስንቱን ያገር ጀግና  ደም ያፈሰሰውን፣
ኢትዮጵያ ልብወለድ የለችም ያለውን፣
የሀገር ጦር ይሉታል ህገር የካደውን።”

የፖለቲካ ሥልጣን የሀይል ጉዳይ ነው። በማንኛውም ጊዜ ሕዝባዊ ከሆነ በሕዝብ ምርጫ በስልጣን ይሰየማል። አምባገነናዊ ከሆነ ደግሞ በጉልበቱ በሀይል በሕዝብ ላይ ይወዘፋል። የስልጣኑ ምንጭ ሀይሉ ነው። ማለትም ጦሩ፤ አፋኝ ተቋሞቹ፤ኤኮኖሚውን ጨምድዶ መያዙ፤ ወዘተ። በአፍሪካ ምሳሌዎች ብዙ ናቸው፤ ይባስ ብለው የራሳቸውን ህግም እየጣሱና እያፈረሱ ከስልጣን አንወርድም በሚል ተጨማሪ ደም እያፈሰሱ ናቸው። መለስ ዜናዊም ደም እያፈሰስንና የምርጫ ቧልት የሚለውን በመቀጠል 50 ዓመት በላይ እንቆይባችኋለን ብሎ ነበር –የተለየ እያደረጉ አይደለም ዘረኞቹ። በመከላከያ ሚኒስቴር ስም ፈርጌሳ ተባለ ሌላ ቢሾም 95 በመቶ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የትግራይ ተወላጅ ወያኔዎች ናቸው። የጸጥታና ፖሊስ ተቋሞችም ዋና አዛዦች አሁንም የትግራይ ተወላጆች ወይም ትግሬዎች ናቸው። የሀገሪቷን ኢኮኖሚ የሚበዘብዙትና የከበሩት የትግራይ ተወላጆችና የወያኔ የንግድ ተቋም (ኤፈርት ) እነ ሜቴክ ናቸው። ሙስና ከተባለም የሀገራችንን ቢሊዮን ዘርፈው በባዕድ ባንክ ከታቾቹ ዋናዎቹ እነ አዜብ ጎላ ወያኔዎች ናቸው። ለዚህ ነው ወያኔና ኢትዮጵያ የተቃረኑ ናቸውና የሀገር ጦር፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ፤ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ወዘተ የሚባል ነገር ሊኖር ልንቀበለው አይገባም የምንለው። ተቃዋሚ ነን ባዮች ወያኔን የኢትዮጵያ መንግሥትና አንቱ ማለቱን ተዉ የምንላቸው። የወያኔ ጦር ሌላውም ሕዝብን ጨቁኖ የመግዣ የወያኔ መሳሪያ ነው። ሀገራዊ ይዘት ቅንጣትም የለውም። ወያኔ ኢትዮጵያዊ ሀይል አይደለምና መወለድ ቋንቋ ነው የተባለው እዚህ ላይ ቦታ አለው።

“ወያኔ የነበረው ኢሕአዴግ ስላለ፣
ሀገር አስገንጣዩ በሀገር ስለማለ፣
ልጨፈን ልሞኝ ባይ ስንቱ ተታለለ፣
አውቆ የተኛ ሰው ባርነት ገጠመው፣
ወያኔ ሀገር ወዳድ ጎመን ጮማ የለው።”

ከዚህ ሌላ የ27 ዓመት መከራ ምን አስተማረን?

ዘረኞቹ መንቻካ ናቸው።  ጫካ ሳሉ የምናውቃቸው የምናረጋግጠው ሀቅ ነው።  ኢትዮጵያ ላይ የነበራቸውና ያላቸው ጥላቻ ሁሌም ቤንዚናቸው ነበር።  ወያኔ መጥፎ አገዛዝ ብቻ አይደለም– ይሁነኝ ብሎ ጸረ ኢትዮጵያ ነው–ጠባብ ዘረኛ የትግራይ አገዛዝ ነው።  መለያው ይህ ሆኖ ቆይቷል።   27 ዓመት ኢትዮጵያን ቢገዛም ጎጠኘነት-ዘረኝነቱ አለቀቀውም።  ስብሃት ተባለ አባይ በረከት ሁሉም ጸረ ኢትዮጵያ ናቸው።  ልጆች ችኮ መንቻኬ የሚሉት ይገልጣቸዋል –ችኮ ዘረኞች።  በበኩላችን በሕዝብ ደረጃም ቃለ አጋኖ ፖለቲካ ልለው የሞከርኩት–ከንቱዎችን የማሞገስና ነጋ ጠባ የመታለል ዝንባሌ ሀገራችንን ትግላችንን ጎድቷል።   ሀቁን የመረዳት ጉድለት ድክመት።  የሀገራችንን የነገ ዕጣ ወሳኝ ሕዝብ መሆኑን በመዘንጋት ዕጣ ክፍላችንን ለግለሰቦች መስጠትም አቁስሎናል።  ሀገር ማዳኑ ግዳጅ በአንድ ግለሰብ ወይም አዋቂ የፈረንጅ ምሁሮች ነን በሚሉ እጅ የገባ ወይም መግባት ያለበት አድርጎ መውሰድ።  በአጭሩ ጥፋት።  በሌላ በኩል ይህም አታቱሌ ቡቄ ነው። ማለትም ቢሆንም ቅሉ መንፈስ።  ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ እንዳሳየን ሰውየው ከሀዲና የፖለቲካ ደላላ ነው ሲባል አታቱሌ ቡቄን ማሰማት። ቢሆንም ቅሉ ብሎ በድላላው መደናገር። እንደገና እንደገና።  ቢሆንም ቅሉ መወገድ ያለበትና ነው አይደለም መስፈን የሚገባው ነው። ይመስልሃል አይመስልህም ተብሎ ሲጠየቅ አይመስለኛል ይላል የሚለውን ቀደም አንስቼው ነበር።  እንጀግን እስቲ እንዳለፉት ዕንቁዎች።

ጀግና እናንሳ ካልን ደግሞ በበኩሌ የሚከተለውን ማቅረብ እመርጣለሁ:

”ጀግናስ እኒያ እናቶች ልጅ አጥተው የጸኑ፣
ሥቃይ ሳይሰብራቸው አርአያ የሆኑ፣
ጀግናስ እኒያ እናቶች እንባን ያሸነፉ፣
ታሪክን ለዋጮች ቀንን እየገፉ፣
ጀግናስ የጀግና እናት የጀግንነት ምንጯ፣
ፋኖ አልነው አርበኛ ያው የእሷ ቁራጯ።”

የታላቄ ታላቅ ታላቅ ወንድሜና ጓድ ሳሙኤል የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ኮልነል አስናቀ እንግዳ ሙሉ የሀገራችንን ነጭ ልብስ ለብሰው መጥተው ለእናቴ ሲናገሩ  ዛሬ የሀዘን ቀን ሳይሆን ደስታ ነው “አንቺንም፤ ሀገሩንም፣ ሕዝቡንም፣ ድርጅቱንም ሳያሳፍርና ቃል ኪዳኑን ሳያፈርስ ስለአረፈ መኩራት መደሰት አለብሽ ” ያሉት ሁሌም ይታወሰኛል።  የኢሕአፓ ሀቀኛ ልጆች–ዛሬም በድርጅቱና በትግል ያሉ –ሕዝብን፤ ሀገርን ወላጅንም አላሳፈሩም።

ጀግኖች እናቶችን፤ የሰማዕት እናቶችን አናሳፍራቸው!
ባልተገራ ጊዜ በቆርፋዳ ዘረኞች አንሸነፍ!!
ለሕዝብና ለኢትዮጵያ ትግላችን ጠንክሮ ይቀጥል!!

pdf_print