የጎንደር ጎጃም ትዝታ–ከነሐሴ 1961 እስከ ነሐሴ 2008

ኢያሱ ዓለማየሁ

የዛሬ ነሐሴ 5/1961 ዓ. ም. ማለትም  47 ዓመት በፊት ከተማሪ እንቅስቃሴ ወደ ፖለቲካ ድርጅትና ትጥቅ ትግል  መሸጋገር በሚል ከሌሎች ስድስት ጓዶች ጋር በመሆን ከጎንደር ወደ ሱዳን አይሮፕላን ለመጥለፍ  ወስነን ጎንደር ገባን።  በከተማይቷ የሰፈሬ ልጅና አብሮ አደጌ የያኔ ምክትል መቶ አለቃ ብርሃኑ ሰርጹ ሆቴል ውስጥ ያነሳኝን ፎቶ በቅርቡ ልኮልኛል።  በርግጥም ወጣት ነበርኩ።  ልባችን ግን ሙሉ ነበር፤ የአጼው ስርዓት በአጭር ጊዜ (ግፋ ቢል በአራት አምስት ዓመት)ይወድቃል የሚል እምነታችን ጽኑ ነበር።  በተማሪ እንቅስቃሴ ይታወቁ የነበሩ ተማሪዎች በጎንደር መገኘታቸው ጥርጣሬን ያስነሳ ስለመሰለን የተወሰነው ወደ ባሕር ዳር ሄደን ሌሎቹ ጎንደር  ቀርተው የሚሳፈሩትበን አይሮፕላን ባሕር ዳር ላይ ተሳፍረን፣ ከተነሳ ከትንሽ ጊዜ ወዲያ በሀይል አስገድደን ጠለፍነው። ከሰባታችን ሶስቱ ዛሬ በህይወት የሉም። ብንያም አዳነ የኢሕአሠ መስራች ቡድን በበረሃ ወደ ሜዳ ሲያመራ በከባዱ ጉዞ ወቅት ለቡድኑ ሸክም የሆነ መስሎት ራሱን ገደለ። ሌላኛው አንጃ መሪ ሆኖ በደርግ ተገደለ። አንዱ ሌላው የደርግ አጋር ሆኖ የኢሕአፓ የአዲስ አበባ ስኳድ ገደለው። ጎንደር ባሕር ዳርን ለትግል ስል አየኋቸው፤ በትጥቁ ትግል ግዜ ጎጃምና ጎንደርን እንደገና ማየት ዕድል ባገኝም ከተሞቹን ከአዲስ አበባ ጀምሮ ይኽው ሳላያቸው ሳናያቸው ዓመታት ተቆጠሩ።  በ 1966 አጼውም ወደቁ፤ ትግላችን ግን ያው እስካሁን ቀጥሏል።  ጨቋኝ ብለን የታገላንቸው ዛሬ በሀገር ተመልሰው ሲገኙ ታጋዮቹ ግን በወያኔ  ከሀገራችን ተከልክለናል።
ታዲያ ምን ይሁን ያሰኛል መሰል።  በኢሕአፓም ቢሆን የጋራ እንጂ እኔ እኔ አይወደድም።  ነገር ግን የጎንደር ባሕር ዳር ትዝታዬ የትግል እንደመሆኑ አሁንም በነዚህ ቦታዎች በጋለው ትግል ምናልባትም  ለሀገር እንበቃ ይሆን የሚል ስሜት ስለመጣብኝ ይቺን ጽሁፍ ላቀርብ ስለተገፋፋሁ ነው።  ዋናው ምክንያትም ለጎንደርና ጎጃም ሕዝብ ምስጋና ለማቅረብ ና በርቱም ለማለት ነው።  በትግላችሁና በሌሎች ቦታዎችም ባለው የሕዝባችን ትግል ይህ ዘረኛ ቡድን ወድቆ ለሀገሬ  አብቁኝ፤ ለሀገራችን አብቁን ብሎም  ለመጠየቅ ነው።  ከዚያን ድሮ ጊዜ ጀምሮ ግን ኢሕአፓ ተለይቷችሁ አያውቅም፤ ሁሌም በጎናችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ ለማለትም ነው።  ዘንድሮ ባይታገሉም ከመሃላችሁ ነን ማለት ፈሊጥ ሆኗልና በሳቅ እንደምታልፉት ተስፋ አለኝ።  አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጀግና ነው–የጎንደር ጀግና ደግሞ የጀግና ጀግና ነው።  ስንቱ ብርቅዬ ወጣት ለሀገሩ ሕይወቱን  ሰጥቷል።  ጭልጋ ቋራ፤ በለሳ ጸለምት፤ ወልቃይት ጠገዴ (ከብተና መልስ የተጓዝንበት–የተጠናከርንበት)፤ አርማጨሆ ፤ ጎንደር ከተማ ራሷ ሀገር ስትጣራ መቸም አሳፍረዋት አያውቁምና  ከኢሕአፓ ታሪክ ጋር የተቆራኙ ናቸው።  በኢዲኅም ቢሆን ጎንደር ጸረ ደርግ ሆኖ ተሰልፎ መስዋዕትነትን ከፍሏል። ጎጃም የበላይ ዘለቀ ሀገር ደግሞ መተከል ተባለ አዳኝ ሀገር፤ ዳንግላ አልን ኦሜድላ፤ ቻግኒ በላያ፤ በዚህም በዚያም ጣና ወዘተ ኢሕአፓን አቅፎ ደግፎ ታግሎ መስዋዕትነትን ሲከፍል ባሕር ዳር ደግሞ የድርጅቱ  እንቅስቃሴ ዋና ቦታ ሆና ከርማለች።  ዛሬም ጎንደር ጎጃም ስንል የተለወጠ የለም። በበኩሌ ቅር የሚለኝ በድርጅትና ፖለቲካው የአቅም እየተሰራ ቢሆንም እንደ  በፊቱ በትጥቁ መስክ አለን በማለቱ ድክመት ማሳየታችን ነው። ይህ ቅሬታችን ሌሎች ከተሞችንም ያቅፋል–ሁኔታዎች እስካሁን “አላስኮን” ቢሉም ሚወገዱበትም ጊዜ ሩቅ አይደለም።
የጎንደር ሕዝብ በተለይ መላኩ ተፈራ የሚባል የዲያብሎስ ልጅን የተቋቋመው ነው።  ቅስሙ የተሰበረ የመሰላቸው ነበሩ፣ ግን በሰሞኑ ትግል አሌ ብሏቸዋል።   የጎንደርን ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት ሊክዱና ሊያስክዱም የጣሩ፤ በወያኔ ቦይ ሊፈሱ በጎጠኝነት ሊሰለፉ ትላንትም ዛሬ የጣሩትንም አሳፍሯቸዋል።  በደማቅ ሰልፉ የኢትዮጵያን እውነታና ሰንደቅ እያውለበለበና ኢትዮጵያዊነትን አንግሶ፣ ደማችን አንድ ነው ብሎ እየተመመ ። በባሕር ዳርም እንዲሁ። ጎንደር ጎጃም፤ ናዝሬት/አዳማ፣ ሻሸመኔ፤ ጋምቤላ አፋር የኢትዮጵያዊነትን አቸናፊነት አረጋግጠዋል። ሽንፈትን የተከናነበው ጎጠኝነት ነው። ገንጣዮች ናቸው መንገዳቸው እንደማያዋጣ መረዳት የተገደዱት። ወያኔ ስልጣን ከያዘ በጎንደር የተሞከሩት ትግሎች የደከሙት ሕዝብ ድጋፍ ነስቷቸው ሳይሆን በራሳቸው ችግር ወይም ድካም ነው። አርበኞች ግንባር ተብሎ በተስፋዬ ጌታቸው (ኋላ በሻዕቢያ ግብረ ስየል ተፈጽሞበት ኤርትራ የተገደል) የተመራው ሆነ የኢትዮጵያ አንድነት ግንባር በሚል በኢዴኅቅ የተሞከረው የትጥቅ ትግል (ቋራ አርማጨሆ) በደጀን እጦት በሌሎችም ምክንያት ደከመ እንጂ ሕዝቡ አልደግፍም ስላላቸው አልነበረም። ጊዜ አልፈቅድ ብሎ ሁሉም አልነገር ብሎ አስቸገረ እንጂ ከጎንደር ሕዝብ አብራክ ተወልደውም ሕዝብን የካዱና ሀገርን ያደሙ ዛሬም ህዝብን ሊጎዱ ሲፍጨረጨሩ እንዳሉ ሕዝብ ያውቀዋል። ጥያቄዎች የጎንደር ጎጃም ናቸው፤ ሌላው ምን አገባው ብለው በ1983 ዓ.ም. እሰጥ አገባ የገቡ ዛሬ ሕዝብ   ኢትዮጵያዊነትን እያስተማራቸው እምቢ ብለው መገተራቸውን ስገነዘብ ለጎንደር ጎጃም ሰልፈኛ አድናቆቴ ይጨምራል። ንቃት አግኝቼ ወደ ትግል ከመጣሁ ጀምሮ ለዘረኝነት ቦታ ያልሰጠ ትውልድ አባል ነበርኩና ዛሬ በስተርጅና ዘር ቆጠራ ሊዳዳኝ አይጠበቅም። መቁጠርም ከመጣ  ኢትዮጵያዊነቴን  ማንም ዘረኛ ሊነጥቀኝ የሚችል አይደለም። ገዘፍን ባሉ ሀይሎች ላይ አምጸን ለሚጢጢ  ዘረኛ ዓይጦች እጅ ልንሰጥ የሚጠበቅ ባይሆን ጥሩ ነው ለማለትም ነው። ኢሕአፓ እኮ የብሄረሰቦችና ሀይማኖቶች የግራ መናሀሪያ የነበረና የሆነ ነው!
የጎንደር ጎጃም ወዘተ ሰልፈኞች አመጽ አቀፍ መንፈስ ትግል ብለን ስንነሳ የነበረንን ቁርጠኛነት አሁንም ያስታውሰኛል። ኢትዮጵያዊነትንም። ተማሪ ሳለንና ባለን ዕውቀትና አቅም ፊውዳልና ሉዓላዊነታችንን ደፈሩ ያልናቸውን ነጮች ስንታገል ዘር ቆጠራ የሚባል ነገር አናውቅም ነበር። በኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያ ነው የታገልነው።  የካቲት ሲፈነዳ ወደ ጎጥ ብሄረሰብም የወረዱት ወያኔዎችና ሻዕቢያዎች ናቸው እንጂ ሌላ አልነበረም።  እነ መስፍን ወልደ ማርያም ለወያኔ ሲንበረከኩ እነ ጓድ ገለብ ዳፍላ፤ መሐሪ/አምባዬ፤ ጃብርና ስንቶቹ ወያኔን በጎንደር በጎጃም ታግለው ተሰውተዋል። በወያኔ እጅ ወድቀው አለፍርድ የተገደሉት እነ ይስሓቅ፤ ተክላይ፤ ሓጎስ፤ወዘተ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ።  በአዲስ አበባ ከሌሎች ጋር በስውር የገባው ጋይም/(ገብረ እግዚአብ ሔር) ሌላ ምሳሌ ነው።  ኢትዮጵያዊው ኢሕአፓ ለሀገር ሲል ታግሎ ተሰውቶ ትላንት ከጸረ ሕዝብ አገዛዝ ጋር የነበሩና ወንጀልም የፈጸሙ ተመልሰው ድርጅቱን ሊያወግዙ ሲጥሩ ማድመጡ ይሰቀጥጣል። የጎንደር ጎጃም ሕዝብ ከጥንትም ጀምሮ ለኢትዮጵያ ህይወቱን መስጠቱ ያኮራል እንጂ በግልባጩ የሚፈረጅ አይደለም።  ወያኔ አሁንም የሚያዋጣ መስሎት በሰሞኑ ክስ ኢሕአፓ ወጣቶችን አስፈጅቶ ነበር ከሚለው አልፎ ቀይ ሽብር የመጣው በድርጅቱ የትጥቅ እርምጃ ነው በሚል የፋሺስቶችን የሀሰት ውንጀላ እስከመድገሙ ደርሷል።  የኢሕአፓ አባላት ላመኑበት ለሕዝባቸው ለሀገራቸው ታገሉ እንጂ፤ ‘መስዋዕትነታቸው የሚያኮራና አርአያ  የሆነ እንጂ በሌላ የሚገመገም አይደለም።  ፈጂዎቹ ደርጎችና እነመላኩ ተፈራ አይነቶቹ ጭራቆች ናቸው። ወያኔ ሀይለኛ ነኝና አትድፈሩኝ ለማለት ህዝብን ማስፈራራት ሞክሮ ነበር–ግን አልሰራለትም።  ቢደነፋም፤ ቢገድልም ጎንደር ጎጃም የትግል ማዕከል ሆነዋል። ሰማዕት ተዘክረዋል፤ ደማቸው መና አለመቅረቱ ታይቷል። ይህ ነው የሚያኮራኝና የሕዝብ ትግል ለሀገራችን ስርየት ሊያመጣ ነው፤ ለሀገራችን ሊያበቃን ነው ብሎ ተስፋ የሚሰጠኝ፤ የሚሰጠን። የትግልን ውጣ ውረድ በተመለክተ ደግሞ ከኢሕአፓ በላይ ማን አውቆት? ቁም ነገሩ ጸንቶ ትግል መቀጠል ላይ ነው።
የዛሬ 47 ዓመት ከጎንደር ባሕር ዳር አድርገን ወደ ሱዳን ስንሄድ ዛሬ ያለን ተመክሮ ቅንጣቱም አልነበረንም። ያለውን ስርዓት ታግሎ መጣል እንደሚገባ፤ ትግሉ ከፍ ወደአለ ደረጃ ማደግ እንዳለበት፤ ዲሞክራሲያው ሕዝባዊ ስርዓት መመስረት መፍትሔ መሆኑን አምነነ ነበር። ከተግባር የተገኘ ዕውቀታችን ሰፊ ባይሆንም ንቃታችንን ለማሳደግ ያደረግነው ጥረት የሚናቅ አልነበረም። እኛን በተመለከተ ለጠለፋው አለን ስንል አንዳንዶቻችን አይሮፕላን ላይ ስንወጣ የመጀመሪያ ጊዜያችን ነበር። በላቡ የኢትዮጵያ ህዝብ በጨቋኝ ስርዓት ስር ፍዳ መቀበሉን ስናውቅ ና ሊሎች ሕዝቦች ሀገሮች ለውጥ ሲመጣ እኛስ ለምን እንማቅቃለን ብለን ተነሳን።  አቅም አልነበረም። ባዶ እጅ ተማሪ። ያውም በጣት የምንቆጠር። የተማሪው እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ ጠነከረ እንጂ ከመሬት ለአራሹ በፊት ብዙዎችም ስር ነቀል ለውጥ ፈላጊ አልነበሩም። እንቅስቃሴውን ነፍስ የዘሩበትና ለእኛም አርአያ ሆነው ከተገኙት እነ ሀይሉ ገብረ ዮሓንስ (ገሞራው)፤ ዘሩ ክህሸን፤ ብርሃነ መስቀል ረዳና ሌሎችም  ነበሩ። ሁሉም መጨረሻቸው የተለያየ ሆኗል ። ብርሃነ ትግላችንን ከዳና የከንቱ ሞት ሞተ።  ዘሩም ህዝብን ሳይከዳ ሞተ፡፡  ሀይሉ በበኩሉ ለሕዝብ እንደቆመ ህይወቱ በስደት ስቃይ አለፈች።  መሬት ለአራሹ ሰልፍ የትግሉን ይዘት ቀየረው። ወደ ግራ ዘንበል የተባለውም በነበረው ዓለም አቀፋዊ  ሁኔታ መሆኑም ያታወቃል።  በእኛ በኩል ወጣቶች እንደመሆናችን መጠን ከቀደሙንና ቀዝቀዝ ካሉት ታላቆቻችን መለየቱ አልቀረም። በቻይናው መስለውን ትኩስ ሬድ ጋርዶች ይሉን ነበር። ሆነንባቸው ሊሆንም ይችላል። ወጣቶች ካለፈውና ዕድሜው ከገፋው ትውልድ ይበልጥ አማጺና ሸፋች ካልሆኑ የታሪክ ጎማ፤ የለውጥ ተስፋ ቆመ ማለት ነው ባይ ነኝ። እኛ ስናድግ ጂንስ ሱሪ ወይም አጭር ቀሚስ መልበስ ጉድ ያሰኝ ነበር። ትውልድ ሁሉ የየራሱ መለኪያ አለው። የአሁኑ ትውልድ የራሱ ድክመት ቢኖረውም የተላለፈለት የጀግንነት ቅርስም አለው። ወያኔ ለስልጣን ሲበቃ፤ ቡትሮስ ጋሊ ከወያኔ ተባብሮ ኤርትራን ሲያስገነጥል ወዘተ የተቃውሞ ሰልፍ አሳይቷል። በ1997 ምርጫ ተሰልፎ ተሰውቶ አሳይቷል። ዛሬም በጎንደር ጎጃም በመላ ኢትዮጵያ በጸረ ወያኔነት ትግልና መስዋዕትነት አረጋግጧል።  ያውም ተቃዋሚ ነን፤ አርአያ  ነን የሚሉት በአብዛኛው ማፈሪያ እየሆኑ።  መለስ ብዬ ያኔ ትግል ስንል የትግል ምሳሌዎች ሌሎች ቆራጦች ሳይሆኑ የዛሬዎቹ  ስም አይጠሬዎቹ ቢሆኑ ወደ ትግል እመጣ ነበር ወይ ብዬ ስጠይቅ መልሴ ከቶም መቼም አይሆንም ነበር የሚል ነው። ስለዚህ የዛሬው ሰልፈኛ ወጣት በኢትዮጵያ ላይ ያለው ፍቅርና እምነት የሚመሰገን ነው። የጎንደር ወጣት የቋራውን ካሳ አርአያ አደረገ እንጂ የዘንድሮዎቹን ቢከተልማ ለሰልፍ አንዴም አይወጣም ነበር። የበላይ ዘለቀ ወራሾች ቅርሱን ቢረሱ በዛሬዎቹማ ፈለግ መጨረሻው መጎንበስ ነበር። የኢሕአፓ ልጆች እንደ ቴድሮስ ሽጉጣቸውንና ሳያናይድ መርዝ ጠጥተዋል፤ ከፎቅም ተወርውረዋል። እጅ አልሰጡም። እንደ ጭራቁ ፋሺስት የሀገር ገንዘብ ሰርቀው እግሬ አውጪኝ አላሉም። የሚያኮሩ ነበሩ። የጸረ ሕዝቦችንም ዕብሪት በጥይት እየቀጡ ትግሉን አስፋፍተዋል። ወያኔም ቢሆን የሚገባው ቋንቋ ይህ ብቻ በመሆኑ ኢሕአፓ ከወያኔ ጋር ሰላም ሳይሆን ሁለገብ ትግል ሲል ቆይቷል።  አንድ ዜጋ ሲገደል አንድ አግአዚ ወይም ወያኔ አጸፋውን ቢያገኝ ሂደቱ ሌላ መሆኑ ግልጽ ነው። በ 1961 ያመንኩበትን የትጥቅ ትግል አማራጭና የአመጽ ጉዞ የሚተካ ሌላ የረባ አማራጭ እስካሁን አላገኘሁም፤ አልታየንም  ማለትም እችላለሁ።
ማን ያውራ የነበረ ነውና ዛሬ ምስክር የጠፋ ይመስል በነበርን ሽፋን የባጥ የቆጡን ሲቀባጥሩ መታዘብ ማዘንም የማይቀር ሆኗል። ወያኔ ወያኔ ነውና ሀቅ ከሱ ሊጠበቅ ስለማይችል በሬ ወለደ ቢል እኛ የምንገረም አይሆንም። ሌሎች ግን  አመራር ነበርን፤ እናውቃለን ብለው ሲቀባጥሩ ነገሩ ታሪክን ባይመለከት ኖሮ በበኩሌ በሳቅ በተንፈረፈርኩ ነበር።  የልብ ወለድ ጋጋታ። ላይ ታች ብለን ባለን አቅም እንደ ኢትዮጵያዊ ተወያይተን፤ ተደራጅተን የመሰረትነውን ድርጅት ባለቤትነቱን ለሌላ ሲሰጡ ምንኛ የዝቅተኛነት ስሜት እንደ ተጠናወታቸው መታዘቡ ያሳዝናል።  በቅርቡ የውሸት ውሸት የድርጅታችን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበርን የሚሉ ሁለት ሰዎች ወፈር ወፈር ያሉ መፅሃፍት አቅርበዋል ወይም ተጽፎላቸዋል፡፡  እኛ አይሮፕላን ስንጠልፍ ከእናቴ ጋር በአይሮፕላኑ ውስጥ ነበርኩ ያለው ለምሳሌ ተራ ውሸቱን ነው።  በመቶዎች ገጾች እንቆቅልሽ ፈቺ ሊሆን የቃጣውና ክህደት በተደጋጋሚ የተጠናወተው የአባዲና የ 11ኛ ኮርስ ምሩቅም  መቸም ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ያልሆነ መሆኑ ስናውቅ ልብወለዱንም ንቀን አልፈነዋል። መሰል ትረካ በነበረከት ስምኦን ተባባሪነት ሊያቀርቡልን ደፋ ቀና የሚሉ የትላንት ቃል ኪዳናቸውንና ኢትዮጵያዊነታቸውን ክደው ብሔርተኛ የሆኑም አሉ።  ጓዶች ያሏቸውን የገደለውን ወያኔ ያቀፉ።  አተምን ሲሉ እንመለስባቸዋለን።  እኛ ግን ትግል ስንጀምር የዛሬ 40 ዓመት የሚተቹን ይመጣሉና፤ ይህ ያ ስህተት ነው የሚሉን ብቅ ይላሉ ብለን ሰግተንም አስበንም አልነበረም። ሁሉም ቅድመ ሁኔታ ካልተሟላ ትግል መጀመር አንችልም ይሉ ለነበሩትም፤ ትግል ለመጀመር አንድ ሌላ ትውልድ ይፈልጋል ያሉትን፤ ሕዝቡ አልነቃም ያሉትን ጆሮ አልሰጠንም። ዋናው ትኩረታችን ተደራጅቶ በመታገል በማታገል ላይ ነበር። ይህን ደግሞ ችለንበታል፤ አድርግነዋል–የኢሕአፓን ደማቅ ታሪክም ከሕዝብ ጋር ሆነን ጽፈናል። ይህን  የሚክድ ወይም ሊያራክስ የሚችል ማንም የለም። ዛሬ ወያኔ ቢጮህ ቢንጫጫብን ጥሩ እየሰራን ለመሆናችን ምስክር ይሆንልናል። የደርግ ወንጀለኞችም ታሪክን ከልሰውና በተራራ ጸሐይ ክደው በወያኔ ተባባሪነት ጻፍን ቢሉም፤ መድረክ ቢሰጣቸውም ለወንጀላቸው መክፈል ያለባቸውን ዋጋ ከመክፈል መቸም አያመልጡም። የጎንደር ጎጃም ኢትዮጵያዊ ትግል ሊያስደስታቸው ቀርቶ የሚያስፈራቸውም አለምክንያት አይደለም።  በሀሰት የመሰከሩ በሕዝብ የሚጠየቁበት የሚቀጡበት ጊዜ መድረሱ ደስ ይላል። ስንቱን እናትና አባት ያስለቀሱና የገደሉትም ሁሉ የሚጠየቁበት ቀን ደርሷልና ተስፋችን ደምቋል።
ከድርጅት ማንነታችን በፊት የነበረንና ያለው ኢትዮጵያዊነታችን ነው። ድርጅታችንን የምንወደው ኢትዮጵያን ለመታደግ መሳሪያችን ስለሆነ ነው። በትግሉ ሂደት ሀገርን እንዳናስቀድም ብዙ ተጽዕኖ ተደርጎብናል–ሁሉንም አልተቀበልንም። ወያኔ ግን ተቀብሎና የባዕዳንን ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ለስልጣን በቅቷል። መሳሪያ ገንዘብ እንሰጣችኋለን ያሉን ለዚህ የፈለጉት ክፍያ ሀገርን የሚጎዳ በመሆኑ እምቢ ብለናቸዋል። ኢሳያስ በቅርቡ እንዳመነው ከእኛ ዋና ጠቡ ቅኝ ግዛት ነን የሚለውንና ሙሉ ነጻነት ያለውን አልቅበል ስላልነው ነው። ወያኔ ለስልጣን ሲበቃም ኢትዮጵያን ለጥፋት የዳረገው ሄርማን ኮኸን (አሜሪካ) ኢሕአፓን ተለጣፊ ለማድረግ ላደረገው ጥረት የሰጠነው አሉታዊ ምላሽ የሚያኮራን ነው። በሀገር ህልዋና ላይ ድርድርና አጓጉል ጮሌነት ብዙም እንደማያዋጣ በተመክሮ አይተነዋል። ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል። የዚህ ጽሁፌ ዓላማ ግን እየተካሄደ ያለው የህዝብ አመጽ፣ ያኔ ለትግል ስንነሳ የነበረውንና በጎንደር ጎጃም–በመላ ኢትዮጵያ– ያካሄድነውን ትግል ማስታወስ ማንሳት ስላስገደደኝ ነው። ኢሕአፓ የጽናትና የኢትዮጵያዊነት ምሳሌ ሆኖ መቆየቱ የሚያኮራ መሆኑ ግልጽ ነው። ለዚህ ያበቃን ሕዝብ አሁንም በኢትዮጵያዊነቱ እየታገለ መሆን ደግሞ ድካማችን መስዋዕትነታችን ከቶም ከንቱ እንዳልሆነ ያበስረናል። ይህን ስጽፍ ሙስሊሞች በአዲስ አበባ ቀጣይና  ደማቅ የተቃውሞ ሰልፋቸውን አድርገዋል። በጎንደር ጎጃም፤ በምስራቅ በምዕራብ በደቡብ ትግል ተቀጣጥሏል። ወያኔና አጋሮቹም ትግሉን ለማዳፈን መሯሯጥን ይዘዋል፡፡  አቧራው ጤሷል፤ ቀውጢው ብሶበታል። ወሳኝ ቀን መጥቷል ። ህዝብም ለሀገሩ መስዋዕትነት ለመክፈል ቆርጦተነስቷል፤ እየከፈለም ነው። የታገልነው ለዚህ  ነው። ገና እናጫጭሰዋለን ከህዝባችን ጎን ሆነን። ከዚህ የሚበልጥ ምን ደስታ አለ?pdf_print

 

ጸረ ወያኔው ትግል ይፋፋም!  ይቀጥል!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!