ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥቅምት 29፣ 2009 ዓ.ም.) – በጎጃም ጢስ አባይ አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ነበር፤ ተጨማሪ የወያኔ ጦር ወደ ቦታው ሄዷል – በጎንደርም በተለያዩ ቦታዎች ውጥረት ተፈጥሯል – የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የእሳት አደጋ ደረሰበት – ከዘጠኝ ወር በላይ ታስረው የነበሩ ተማሪዎች ፍርድ ቤት ለጥፋታቸው ስድስት ወር ብቻ ፈረዳባቸው።
በጢስ አባይ አካባቢ ለአሰሳ በተሰማራ የወያኔ ጦር እና በአካባቢው በጎብዝ አለቆች ተደራጅተው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ከጎበዝ አለቃዎቹ መካከል አንደኛው መሰዋቱ ይነገራል። ለረጅም ጊዜ በቆየው የተኩስ ልውውጥ የወያኔ አግአዚ ጦር ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰበት ባይታወቅም በ ቁጥር 2000 በላይ የሚሆኑ የ ጦር አባላት ከብር ሸለቆ ወደ ጢስ አባይ የሄዱ መሆናቸውን የአይን እማኞች ይናገራሉ። በምስራቅ ጎጃም የሞጣ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አስተማሪያቸው በወያኔ አፋኝ ኃይሎች ተይዞ መወሰዱን በመቃወም እንቅስቃሴ እያካሄዱ መሆናቸው ታውቋል።
በጎንደርም በተለያዩ ቦታዎች ውጥረቶች ያሉ መሆናቸው ከየካባቢው የሚደርሱ ዜናዎች ይገልጻሉ። በጎንደር ሁመራ መንገድ በተለያዩ አካባቢዎች በታጠቁ ሕዝባዊ ኃይል አባላትና በወያኔ አግአዚ ጦር መካከል ግጭቶች የነበሩ መሆናቸው እንዲሁም በአርማጭሆ አካባቢም ተመሳሳይ ውጥረት መኖሩ እየተነገረ ነው። ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን ብዛት ያለው የወያኔ ጦር ከባህር ዳር ወደ ጎንደር ሲጓጓዝ የታየ መሆኑ የአይን እማኞች ይናገራሉ።
ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የእሳት ቃጥሎ የደረሰብት መሆኑ ታውቋል። በእሳቱ የተጎዱት የአዲስ ተማሪዎች የመኖሪያ ክፍሎች ሲሆኑ ስለቃጠሎው መነሻ የተገኘ መረጃ የለም። በዩኒቨርስቲው የጸጥታ ኃይሎች የዩኒቨርስቲውን ቅጽር ግቢ የተቆጣጠሩት መሆናቸው ታውቋል። በከተማ ውስጥ በርካታ ወጣቶች፤ ነጋዴዎችና ነጋዴዎች እና መምህራን በጅምላ እየታሰሩ በመሆናቸው ከፍተኛ ውጥረት ያለ መሆኑ ይነገራል።
አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ በማድረግ ተቃውሞ አሰምታችኋል ተብለው ተይዘው ላለፉት ዘጠኝ ወራት በእስራት ሲሰቃዩ የነበሩት 11 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2009 ዓ. ም. ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት በስድስት ወራት እንዲቀጡ ብይን የሰጠ መሆኑ ተነግሯል። ተማሪዎቹ ፍርድ ቤቱ ከበየነባችው ጊዜ ሶስት ወራት ተጨማሪ በመታሰራቸው ለደረሰባቸው ጉዳት ማካካሻ የማይሰጣቸው መሆኑ ግልጽ ሲሆን ሁኔታው የወያኔ የፍትህ ይዘት ምን ያህል የዘቀጠ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል በማለት አንዳንድ ዜጎች እየተናገሩ ይገኛሉ።